በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የልግስና መንፈስ አዳብሩ

የልግስና መንፈስ አዳብሩ

የልግስና መንፈስ አዳብሩ

ማናችንም ብንሆን የልግስና መንፈስ ይዘን አልተወለድንም። አንድ ጨቅላ ሕፃን ተፈጥሯዊ ዝንባሌው የራሱን ፍላጎት ማርካት ብቻ ነው። ሕፃኑ ስለሚንከባከቡት ሰዎች ፍላጎት እንኳ አያስብም። በጊዜ ሂደት ግን ልጁ ትኩረት የሚያሻው እርሱ ብቻ እንዳልሆነ ይገነዘባል። የሌሎችን ፍላጎት ግምት ውስጥ ማስገባትን እንዲሁም መቀበልን ብቻ ሳይሆን መስጠትንና ማካፈልንም መማር ይኖርበታል። በሌላ አባባል የልግስና መንፈስ ማዳበር አለበት።

አንዳንድ ሰዎች እርዳታ የሚሰጡት ምንም ሳይሰስቱ ቢሆንም እንኳ እርዳታ የሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ የልግስና መንፈስ አላቸው ሊባል አይችልም። አንዳንዶች ለአንድ ተቋም የገንዘብ እርዳታ የሚሰጡት የራሳቸውን ፍላጎት ለማራመድ ብለው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ መዋጮ የሚያደርጉት ከሰዎች ክብር ለማግኘት ሊሆን ይችላል። እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያሳዩት ልግስና ግን ከዚህ የተለየ ነው። ታዲያ የአምላክ ቃል የሚያበረታታው ምን ዓይነት ልግስናን ነው? በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ያደርጉ የነበረውን ልግስና በአጭሩ በመመርመር የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት እንችላለን።

ክርስቲያኖች ልግስና ያሳዩባቸው መንገዶች

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ክርስቲያናዊ ልግስና ሲባል በእርግጥ ችግረኛ ለሆኑ ‘ማካፈል’ ማለት ነው። (ዕብራውያን 13:16፤ ሮሜ 15:26) ይህ የሚደረገው በግዴታ መሆን የለበትም። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 9:7) ልግስና ለታይታ ተብሎ መደረግም የለበትም። ሐናንያና ሰጲራ እንዲህ ማድረጋቸው ከባድ መዘዝ አስከትሎባቸዋል።—ሥራ 5:1-10

አይሁዶችና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ በርካታ ሰዎች በ33 እዘአ የጰንጠቆስጤን በዓል ለማክበር ከሩቅ ቦታ ወደ ኢየሩሳሌም በመጡበት ወቅት እርዳታ ማድረግ የሚያስፈልግበት ሁኔታ ተከስቶ ነበር። እዚያም የኢየሱስ ተከታዮች ‘መንፈስም ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው በሌላ ልሳኖች መናገር ጀመሩ።’ በዚህ ጊዜ ብዙ ሰዎች ወደ እነርሱ የተሰበሰቡ ሲሆን ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ያቀረበውን ቀስቃሽ ንግግርም አዳምጠዋል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ሕዝቡ ጴጥሮስና ዮሐንስ ቤተ መቅደሱ ደጃፍ ላይ የነበረን አንካሳ ሲፈውሱ የተመለከቱ ከመሆኑም በላይ ጴጥሮስ ንስሐ የመግባትን አስፈላጊነትና ኢየሱስን በተመለከተ በድጋሚ ንግግር ሲሰጥ ሰምተዋል። ከዚያም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ንስሐ ገብተው የክርስቶስ ተከታይ በመሆን ተጠመቁ።—ሥራ ምዕራፍ 2 እና 3

ክርስትናን የተቀበሉት አዳዲስ አማኞች በኢየሩሳሌም ቆይተው ከኢየሱስ ሐዋርያት ተጨማሪ ትምህርት ለማግኘት ፈለጉ። ሆኖም ሐዋርያት ለእነዚህ ሁሉ እንግዶች የሚያስፈልጉትን ነገሮች ማሟላት የሚችሉት እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “መሬት ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፣ በሐዋርያትም እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ ያካፍሉት ነበር።” (ሥራ 4:33-35) በእርግጥም፣ በቅርቡ የተቋቋመው የኢየሩሳሌም ጉባኤ የልግስና መንፈስ ነበረው!

ከጊዜ በኋላ ሌሎች ጉባኤዎችም ተመሳሳይ የልግስና መንፈስ አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በመቄዶንያ የሚኖሩት ክርስቲያኖች እነርሱ ራሳቸው ድሆች ቢሆኑም በይሁዳ ለነበሩ ችግረኛ ወንድሞቻቸው ከአቅማቸው በላይ መዋጮ አድርገዋል። (ሮሜ 15:26፤ 2 ቆሮንቶስ 8:1-7) የፊልጵስዩስ ጉባኤ ጳውሎስ ለሚያከናውነው አገልግሎት ድጋፍ በመስጠት ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል። (ፊልጵስዩስ 4:15, 16) በኢየሩሳሌም የነበረው ጉባኤም ችግረኛ ለነበሩ መበለቶች በየዕለቱ ምግብ ያከፋፍል የነበረ ከመሆኑም ሌላ እርዳታ ማግኘት ያለባቸው መበለቶች ችላ እንዳይባሉ ሐዋርያት ብቃት ያላቸው ሰባት ወንዶችን ሾመዋል።—ሥራ 6:1-6

የቀድሞዎቹ ጉባኤዎች አስቸጋሪ ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል ሲያውቁ ምላሽ ለመስጠት ፈጣኖች ነበሩ። ለአብነት ያህል፣ ነቢዩ አጋቦስ ታላቅ ረሃብ እንደሚመጣ ትንቢት በተናገረ ጊዜ በሶርያ አንጾኪያ በሚገኘው ጉባኤ የነበሩ ደቀ መዛሙርት “እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ።” (ሥራ 11:28, 29) ሌሎች ክርስቲያኖች ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር አስቀድመው በማሰብና የእርዳታ ዝግጅት በማድረግ ረገድ እጅግ የሚደነቅ መንፈስ አሳይተዋል!

የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ይህን የመሰለ ልግስናና ፍቅር እንዲያሳዩ የገፋፋቸው ምንድን ነው? ደግሞስ አንድ ሰው የልግስና መንፈስ ማዳበር የሚችለው እንዴት ነው? ንጉሥ ዳዊት የተወውን ምሳሌ በአጭሩ በመመርመር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

ዳዊት እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ ያደረገው ልግስና

ይሖዋ በእስራኤላውያን መካከል እንደሚገኝ የሚያመለክተው ቅዱስ ሣጥን ማለትም የቃል ኪዳኑ ታቦት ለ500 ዓመታት ያህል ቋሚ ቤት አልነበረውም። ታቦቱ በድንኳን ውስጥ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን እስራኤላውያን በምድረ በዳ በተጓዙበት ወቅትና ከዚያም ተስፋይቱ ምድር ከገቡ በኋላ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀስ ነበር። ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ አምልኮ ተስማሚ የሆነ ቤት ለመገንባትና ቅዱሱን ታቦት ከድንኳኑ ውስጥ አውጥቶ በዚያ ለማስቀመጥ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። ዳዊት ለነቢዩ ናታን “እነሆ፣ እኔ ከዝግባ በተሠራ ቤት ተቀምጫለሁ፤ የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት በመጋረጃዎች ውስጥ ተቀምጦአል” ብሎት ነበር።—1 ዜና መዋዕል 17:1

ሆኖም ዳዊት ብዙ ውጊያዎችን ያካሄደ ሰው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ የዳዊት ልጅ የሆነው ሰሎሞን ሰላም በሰፈነበት የንግሥና ዘመኑ የቃል ኪዳኑ ታቦት የሚቀመጥበትን ቤተ መቅደስ እንደሚገነባ አሳወቀ። (1 ዜና መዋዕል 22:7-10) ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ዳዊት የልግስና መንፈሱን እንዲያጣ አላደረገውም። ከፍተኛ ግብረ ኃይል በማሰባሰብ ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁስ አዘጋጀ። ከጊዜ በኋላ ሰሎሞንን እንዲህ ብሎታል:- “ለእግዚአብሔር ቤት መቶ ሺህ መክሊት ወርቅና አንድ ሚሊዮን መክሊት ብር፣ ሚዛንም የሌላቸው ብዙ ናስና ብረት አዘጋጀሁ፤ ደግሞም እንጨትና ድንጋዮች አዘጋጀሁ።” (1 ዜና መዋዕል 22:14) ዳዊት በዚህ ሳይረካ ከግል ሀብቱ በዛሬው የዋጋ ተመን መሠረት 1,200,000,000 የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ብር አበርክቷል። ከዚህ በተጨማሪ አለቆችም በልግስና አስተዋጽኦ አድርገዋል። (1 ዜና መዋዕል 29:3-9) ዳዊት ከፍተኛ የልግስና መንፈስ እንዳሳየ ምንም ጥያቄ የለውም!

ዳዊት ይህን የመሰለ ልግስና እንዲያሳይ የገፋፋው ምንድን ነው? ያፈራው ሀብትም ሆነ ያከናወናቸው ነገሮች በሙሉ ከይሖዋ ያገኘው በረከት መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ባቀረበው ጸሎት ላይ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “አቤቱ አምላካችን ሆይ፣ ለቅዱስ ስምህ ቤት እንሠራ ዘንድ ይህ ያዘጋጀነው ባለጠግነት ሁሉ ከእጅህ የመጣ ነው፣ ሁሉም የአንተ ነው። አምላኬ ሆይ፣ ልብን እንድትመረምር፣ ቅንነትንም እንድትወድድ አውቃለሁ፤ እኔም በልቤ ቅንነትና በፈቃዴ ይህን ሁሉ አቅርቤአለሁ፤ አሁንም በዚህ ያለው ሕዝብህ በፈቃዱ እንዳቀረበልህ በደስታ አይቻለሁ።” (1 ዜና መዋዕል 29:16, 17) ዳዊት ከይሖዋ ጋር ላለው ዝምድና ከፍተኛ ግምት ሰጥቷል። አምላክን ‘በፍጹም ልብና በፈቃደኛ ነፍስ’ ማገልገል አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቧል፤ እንዲህ በማድረጉም ደስታ አግኝቷል። (1 ዜና መዋዕል 28:9) የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖችም የልግስና መንፈስ እንዲያሳዩ ያደረጓቸው እነዚሁ ባሕርያት ነበሩ።

ይሖዋ—በልግስናው አቻ የለውም

ልግስና በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌያችን ይሖዋ ነው። ይሖዋ እጅግ አፍቃሪና አሳቢ ከመሆኑ የተነሳ ‘በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣል፣ በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባል።’ (ማቴዎስ 5:44, 45) ለሰው ዘር በሙሉ “ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም [ነገር]” ይሰጣል። (ሥራ 17:25) በእርግጥም፣ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንደተናገረው “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው፣ . . . ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ።”—ያዕቆብ 1:17

ይሖዋ የሰጠን ከሁሉ የላቀው ስጦታ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን’ ለእኛ መላኩ ነው። (ዮሐንስ 3:16) ‘ሁላችንም ኃጢአት የሠራንና የእግዚአብሔር ክብር የጎደለን’ በመሆናችን ይህን ስጦታ ማግኘት ይገባኛል ማለት የሚችል ሰው የለም። (ሮሜ 3:23, 24፤ 1 ዮሐንስ 4:9, 10) የክርስቶስ ቤዛ ‘የማይነገረውን የእግዚአብሔር ስጦታ’ ማለትም የአምላክን “ጸጋ” እንድናገኝ የሚያስችለን መሠረትና መንገድ ነው። (2 ቆሮንቶስ 9:14, 15) ጳውሎስ ለአምላክ ስጦታ ያደረበት የአመስጋኝነት ስሜት “የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን መመስከር” በሕይወቱ ውስጥ ተቀዳሚ ሥራው እንዲሆን አነሳስቶት ነበር። (ሥራ 20:24) የአምላክ ፈቃድ ‘ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ መሆኑን ተገንዝቧል።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

በዛሬው ጊዜ በምድር ዙሪያ በ234 አገሮች ውስጥ በሚከናወን ከፍተኛ የስብከትና የማስተማር እንቅስቃሴ አማካኝነት ይህ የአምላክ ፈቃድ እየተፈጸመ ነው። ይህን በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተንብዮ ነበር:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) አዎን፣ “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል።” (ማርቆስ 13:10) ባለፈው ዓመት ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የምስራቹ አዋጅ ነጋሪዎች በዚህ ሥራ ላይ 1,202,381,302 ሰዓት ያሳለፉ ሲሆን ከ5,300,000 በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም መርተዋል። የሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ስለሚገኝ ምስራቹን መስማታቸው በጣም አስፈላጊ ነው።—ሮሜ 10:13-15፤ 1 ቆሮንቶስ 1:21

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተራቡ ሰዎችን ለመርዳት መጽሐፍ ቅዱሶችን፣ መጻሕፍትንና ብሮሹሮችን ጨምሮ በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ጽሑፎች ይታተማሉ። ከዚህ በተጨማሪ ከአንድ ቢሊዮን በላይ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች ይታተማሉ። ሰዎች ለምስራቹ ምላሽ በሰጡ መጠን የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ ማዕከል ሆነው የሚያገለግሉ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችና የትልልቅ ስብሰባ አዳራሾች ይገነባሉ። በየዓመቱ የወረዳ፣ የልዩና የአውራጃ ስብሰባዎች ይዘጋጃሉ። ለሚስዮናውያን፣ ለተጓዥ የበላይ ተመልካቾች፣ ለሽማግሌዎችና ለጉባኤ አገልጋዮች ቀጣይነት ያለው ሥልጠና ይሰጣል። ይሖዋ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት እነዚህን ሁሉ ዝግጅቶች ስላደረገልን አመስጋኞች ነን። (ማቴዎስ 24:45-47) ለእርሱ ያለንን አመስጋኝነት መግለጽ እንደምንፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም!

ለይሖዋ አመስጋኝነታችንን መግለጽ

ለቤተ መቅደሱ ግንባታም ሆነ በቀድሞዎቹ የክርስቲያን ጉባኤዎች ውስጥ የነበሩ ችግረኞችን ለመርዳት እንደተደረገው ሁሉ በአሁኑ ጊዜም ለሚከናወኑት ሥራዎች የሚያስፈልገው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ የሚገኘው በፈቃደኝነት ከሚሰጥ መዋጮ ነው። ይሁን እንጂ የሁሉም ነገር ባለቤት የሆነውን ይሖዋን ማንም ሰው በስጦታው ሊያበለጽገው እንደማይችል መዘንጋት የለብንም። (1 ዜና መዋዕል 29:14፤ ሐጌ 2:8) በመሆኑም መዋጮ የምናደርገው ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና እውነተኛው አምልኮ እንዲስፋፋ ያለንን ምኞት ለመግለጽ ነው። ጳውሎስ በዚህ መንገድ ልግስና ማሳየታችን “ለእግዚአብሔር የምስጋና ምክንያት” እንደሚሆን ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 9:8-13) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት ልግስና እንድናሳይ የሚያበረታታን ትክክለኛ የመስጠት መንፈስና እርሱን የሚወድድ ልብ እንዳለን የምናሳይበት መንገድ በመሆኑ ነው። ልግስና የሚያሳዩና በይሖዋ የሚታመኑ ሰዎች የእርሱን በረከት የሚያገኙ ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ይበለጽጋሉ። (ዘዳግም 11:13-15፤ ምሳሌ 3:9, 10፤ 11:25) ኢየሱስ እንዲህ በማድረጋችን ደስታ እንደምናገኝ ሲገልጽ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሏል።—ሥራ 20:35

የልግስና መንፈስ ያላቸው ክርስቲያኖች የችግር ጊዜ እስኪመጣ ድረስ አይጠብቁም። ከዚህ ይልቅ “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም” ማድረግ የሚችሉበትን አጋጣሚ ይፈልጋሉ። (ገላትያ 6:10) ጳውሎስ አምላካዊ የልግስና ባሕርይ እንድናሳይ ሲያበረታታ “መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:16) ያለንን ሀብት ይኸውም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ገንዘባችንን ሌሎችን ለመርዳትና እውነተኛውን አምልኮ ለማስፋፋት ማዋላችን ይሖዋ አምላክን በጣም ያስደስተዋል። በእርግጥም ይሖዋ የልግስናን መንፈስ ይወድዳል።

[በገጽ 28, 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

አንዳንዶች መዋጮ የሚያደርጉባቸው መንገዶች

ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረጉ መዋጮዎች

ብዙዎች “ለዓለም አቀፉ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ የተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚጨምሩት የተወሰነ ገንዘብ ያስቀምጣሉ ወይም ይመድባሉ።

ጉባኤዎች የተዋጣውን ገንዘብ በአገራቸው ሥራውን ለሚቆጣጠረው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በየወሩ ይልካሉ። ከዚህ በተጨማሪ በፈቃደኝነት የሚደረጉ የገንዘብ መዋጮዎችን በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, c/o Office of the Secretary and Treasurer, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201-2483 በሚለው አድራሻ ወይም በአገራችሁ ለሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ መላክ ይቻላል። ቼኮች “ለይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈሉ መሆናቸው መገለጽ አለበት። ከውድ ማዕድናት የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችንም መስጠት ይቻላል። የተላከው ዕቃ ሙሉ በሙሉ ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤ ተያይዞ መላክ ይኖርበታል።

ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ የሚሰጥበት ዝግጅት

አንድ ሰው የሰጠው ገንዘብ እንዲመለስለት ከፈለገ መልሶ ሊያገኝ የሚችልበትን ልዩ ዝግጅት በማድረግ መስጠት ይችላል። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ከላይ በተገለጸው አድራሻ መጠየቅ ይቻላል።

በእቅድ የሚደረግ ስጦታ

ገንዘብ በስጦታ ከመለገስና ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ከመስጠት በተጨማሪ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ መደገፍ የሚቻልባቸው ሌሎች መንገዶችም አሉ። ይህም የሚከተሉትን ያጠቃልላል:-

ኢንሹራንስ:- የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል።

የባንክ ሒሳብ:- የአገሩ ባንክ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምሥክር ወረቀት ወይም የግል ጡረታ ሒሳቦች በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል።

አክሲዮኖችና ቦንዶች:- አክሲዮኖችንና ቦንዶችን በስጦታ መልክ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መስጠት ይቻላል።

የማይንቀሳቀስ ንብረት:- ሊሸጥ ሊለወጥ የሚችል ቋሚ ንብረት በስጦታ መስጠት ወይም መኖሪያ ቤት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ባለ ንብረቱ በሕይወት እስካለ ድረስ ተጠቅሞበት ከዚያ በኋላ ማውረስ ይቻላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ባለቤትነት ከማዛወሩ በፊት በአገሩ ከሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር መነጋገር ይኖርበታል።

የስጦታ አበል:- የስጦታ አበል አንድ ሰው ገንዘቡን ወይም የባለቤትነት መብትን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ለማዛወር የሚያደርገውን ዝግጅት ያመለክታል። በምላሹም ለጋሹ ወይም እርሱ የወከለው ግለሰብ በሕይወት እስካለበት ጊዜ ድረስ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየዓመቱ በአበል መልክ ይከፈለዋል። ለጋሹ የስጦታ አበሉን ለማስተላለፍ ከተስማማበት ጊዜ አንስቶ የገቢ ግብር ቅናሽ ያገኛል።

ኑዛዜዎችና አደራዎች:- ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተቀባይነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በውርሻ ሊሰጥ ወይም ማኅበሩ በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ ተደርጎ ስሙ ሊዘዋወር ይችላል። አንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች አሉ።

“በእቅድ የሚደረግ ስጦታ” የሚለው ሐረግ እንደሚያመለክተው እነዚህን የመሳሰሉ መዋጮዎች በሰጪው በኩል እቅድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያሳያሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ ሥራ በእቅድ በሚደረግ ስጦታ ለመደገፍ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ጉዳዩን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ዓለም አቀፉን የመንግሥት ሥራ ለመደገፍ በእቅድ የሚደረግ ስጦታ የሚል ብሮሹር በእንግሊዝኛና በስፓንኛ ተዘጋጅቷል። ይህ ብሮሹር የተዘጋጀው ስጦታዎችን፣ ኑዛዜዎችንና አደራዎችን በተመለከተ ለቀረቡት በርካታ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ታስቦ ነው። በተጨማሪም ብሮሹሩ ከማይንቀሳቀስ ንብረት፣ ከገንዘብና ከቀረጥ ክፍያ ጋር በተያያዘ እቅድ ማውጣትን አስመልክቶ ጠቃሚ የሆኑ ተጨማሪ መረጃዎችን የያዘ ነው። ከዚህም ሌላ ብሮሹሩ ሰዎች ስጦታ ለመስጠት ወይም በሚሞቱበት ጊዜ በኑዛዜ ውርስ ለመተው የሚችሉባቸውን መንገዶች ይጠቁማል። ይህን ብሮሹር ካነበቡ በኋላ ከራሳቸው የሕግ ወይም የባጀት አማካሪዎችና በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ ከሚከታተለው ቢሮ ጋር በመማከር ብዙዎች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመርዳት ከመቻላቸውም በላይ እንዲህ ማድረጋቸው ከቀረጥ ጋር በተያያዘ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል። ይህን ብሮሹር ለማግኘት በእቅድ የሚደረግ ስጦታን ጉዳይ የሚከታተለውን ቢሮ በቀጥታ መጠየቅ ይቻላል።

ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከታች ያለውን አድራሻ ተጠቅመህ ወይም በአገርህ ለሥራው አመራር ለሚሰጠው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ በመጻፍ ወይም በመደወል መጠየቅ ትችላለህ።

Charitable Planning Office

Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania

100 Watchtower Drive,

Patterson, New York 12563-9204

ስልክ:- (845) 306-0707

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ለጋስ እንዲሆኑ ያነሳሳቸው ምንድን ነው?