የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ኤልሳዕ የኤልያስ መንፈስ “ሁለት እጥፍ” ሆኖ እንዲሰጠው የጠየቀው ለምን ነበር?
ኤልያስ በእስራኤል ያከናወነው የነቢይነት አገልግሎት የሚጠናቀቅበት ጊዜ ሲቃረብ ከእርሱ በዕድሜ የሚያንሰው ነቢዩ ኤልሳዕ “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ” ሲል ጠየቀው። (2 ነገሥት 2:9) ጉዳዩን በመንፈሳዊ ዓይን ስናየው ኤልሳዕ ለበኩር ልጅ እንደሚደረገው ሁለት እጥፍ ድርሻ እንዲሰጠው መጠየቁ እንደነበር ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። (ዘዳግም 21:17) ታሪኩን በአጭሩ መመርመራችን ይህን ጉዳይ ግልጽ የሚያደርግልን ከመሆኑም ሌላ በወቅቱ ከተፈጸመው ሁኔታ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
ነቢዩ ኤልያስ ይሖዋ በሰጠው መመሪያ መሠረት ኤልሳዕን ተተኪው አድርጎ ቀብቶታል። (1 ነገሥት 19:19-21) ኤልሳዕ ለስድስት ዓመታት ያህል ኤልያስን በታማኝነት ያገለገለው ሲሆን እስከ መጨረሻው ድረስ በዚሁ ለመቀጠል ቆርጦ ነበር። ኤልያስ በእስራኤል በነቢይነት ባሳለፈው በመጨረሻው ቀን እንኳ ኤልሳዕ ከአጠገቡ አልተለየውም። ኤልያስ ከእርሱ እንዲለይ ኤልሳዕን ደጋግሞ ቢጎተጉተውም ይህ ነቢይ “አልለይህም” በማለት ሦስት ጊዜ መልሶለታል። (2 ነገሥት 2:2, 4, 6፤ 3:11) በእርግጥም ኤልሳዕ በዕድሜ የሚበልጠውን ነቢይ እንደ መንፈሳዊ አባቱ ተመልክቶታል።—2 ነገሥት 2:12
ይሁን እንጂ የኤልያስ መንፈሳዊ ልጅ ኤልሳዕ ብቻ አልነበረም። ኤልያስና ኤልሳዕ “የነቢያት ልጆች” ተብለው ከተጠሩ ሰዎች ጋር ግንኙነት ነበራቸው። (2 ነገሥት 2:3) በሁለተኛ ነገሥት ላይ የሚገኘው ዘገባ እንደሚያሳየው እነዚህም “ልጆች” ከመንፈሳዊ አባታቸው ከኤልያስ ጋር በጣም ይቀራረቡ ነበር። (2 ነገሥት 2:3, 5, 7, 15-17) ሆኖም በኤልያስ እግር እንዲተካ የተቀባው ኤልሳዕ በመሆኑ ከኤልያስ መንፈሳዊ ልጆች መካከል የመጀመሪያው ማለትም በኩሩ እርሱ ነበር ማለት ይቻላል። በጥንቷ እስራኤል አንድ የበኩር ልጅ ከአባቱ ውርስ ሁለት እጥፍ የሚደርሰው ሲሆን የተቀሩት ወንዶች ልጆች ግን እያንዳንዳቸው አንድ እጅ ይሰጣቸው ነበር። ኤልሳዕ ከኤልያስ መንፈሳዊ ውርስ ሁለት እጥፍ እንዲሰጠው የጠየቀው በዚህ ምክንያት ነው።
ኤልሳዕ ይህን ጥያቄ በዚያ ወቅት ያቀረበው ለምን ነበር? ኤልያስን ተክቶ በእስራኤል ነቢይ የመሆን ከባድ ኃላፊነት የሚረከብበት ጊዜ ተቃርቦ ስለነበር ነው። ኤልሳዕ ከተጣለበት ከባድ ኃላፊነት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ሥራዎችን በሚገባ ለማከናወን ከራሱ ችሎታ እጅግ የላቀ ኃይል ማለትም ይሖዋ ብቻ ሊሰጠው የሚችል መንፈሳዊ ኃይል እንደሚያስፈልገው ተገንዝቦ ነበር። እርሱም እንደ ኤልያስ ደፋር መሆን ነበረበት። (2 ነገሥት 1:3, 4, 15, 16) በመሆኑም ኤልያስ ያንጸባረቀው የድፍረትና ‘ለይሖዋ እጅግ የመቅናት’ መንፈስ ሁለት እጥፍ ሆኖ እንዲሰጠው ጠየቀ። ድፍረትና ቅንዓት የአምላክ መንፈስ የሚያፈራቸው ግሩም ባሕርያት ናቸው። (1 ነገሥት 19:10, 14) ኤልያስ ምን ምላሽ ሰጠ?
ኤልያስ፣ ኤልሳዕ የጠየቀው ነገር ከእርሱ አቅም በላይ እንደሆነና ይህን ሊያደርግለት የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ አሳምሮ ያውቃል። በመሆኑም ኤልያስ “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል” በማለት ትሕትና የተሞላበት መልስ ሰጥቶታል። (2 ነገሥት 2:10) በእርግጥም ይሖዋ፣ ኤልያስ በዐውሎ ነፋስ ወደ ላይ ሲወጣ ኤልሳዕ እንዲያይ ፈቅዶለታል። (2 ነገሥት 2:11, 12) ኤልሳዕ የጠየቀውን ነገር አግኝቷል። የተሰጠውን ሥራ ለመጀመርና ከፊቱ የሚጠብቁትን ፈታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ የሚያስፈልገውን መንፈስ ይሖዋ ሰጥቶታል።
በዛሬው ጊዜ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች (አንዳንድ ጊዜ የኤልያስ ክፍል ተብለው ይጠራሉ) እና የአምላክ አገልጋዮች በአጠቃላይ ከዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ከፍተኛ ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ አዲስ ኃላፊነት ሲሰጠን ፍርሃት ሊያድርብንና ብቁ እንዳልሆንን ሊሰማን ይችላል፤ ወይም ደግሞ በአገልግሎት ክልላችን ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ የሰዎች ግዴለሽነት አሊያም ተቃውሞ ሲያጋጥመን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ በድፍረት እንዳንቀጥል ሊያደርገን ይችላል። ሆኖም ይሖዋ እንዲረዳን ከለመንነው ፈተናዎችንና የሁኔታዎችን መለዋወጥ ለመቋቋም እንድንችል በሚያስፈልገን መጠን መንፈስ ቅዱሱን ይሰጠናል። (ሉቃስ 11:13፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ፊልጵስዩስ 4:13) አዎን፣ ይሖዋ ከባድ የሆኑ ኃላፊነቶቹን መወጣት እንዲችል ለኤልሳዕ ኃይል እንደሰጠው ሁሉ ወጣትም ሆንን አረጋዊ አገልግሎታችንን መፈጸም እንድንችል ሁላችንንም ይረዳናል።—2 ጢሞቴዎስ 4:5