በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ከልጅነቴ ጀምሮ አስተምሮኛል

ይሖዋ ከልጅነቴ ጀምሮ አስተምሮኛል

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ከልጅነቴ ጀምሮ አስተምሮኛል

ሪቻርድ አብረሃምሰን እንደተናገረው

“አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ እኔም እስከ ዛሬ ድረስ ድንቅ ሥራህን ዐውጃለሁ።” (መዝሙር 71:17 አ.መ.ት) እነዚህ ቃላት ለእኔ ልዩ ትርጉም ያላቸው ለምን እንደሆነ ልንገራችሁ።

እናቴ ፋኒ አብረሃምሰን በ1924 ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው ከሚጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ተገናኘች። ያን ጊዜ ገና የአንድ ዓመት ልጅ ነበርኩ። እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተመለከተ አዲስ ነገር ባወቀች ቁጥር ወዲያውኑ ጎረቤቶቿ ጋር ሄዳ የሰማችውን ትነግራቸው ነበር፤ እኔን፣ ታላቅ ወንድሜንና እህቴንም ታስተምረን ነበር። ማንበብ ከመቻሌ በፊት ስለ አምላክ መንግሥት በረከቶች የሚገልጹ ብዙ ጥቅሶችን በቃሌ አስጠንታኛለች።

በ1920ዎቹ መጨረሻ ላይ፣ ተወልጄ ባደግኩበት በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኦሪገን ግዛት ላ ግራንድ ከተማ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ቡድን ጥቂት ሴቶችንና ልጆችን ያቀፈ ነበር። በገለልተኛ ሥፍራ የምንኖር ቢሆንም በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ይጎበኙን ነበር። እነዚህ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች አበረታች ንግግሮች ያቀርቡልን፣ አብረውን ከቤት ወደ ቤት ያገለግሉና ልጆች ለሆንነውም ትኩረት ይሰጡን ነበር። ከእነዚያ ውድ ወንድሞች መካከል ሺልድ ቱትጂአን፣ ጂን ኦረል እና ጆን ቡዝ ይገኙበታል።

በ1931 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም ባገኙበት በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ በተካሄደው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከቡድናችን የተገኘ ሰው አልነበረም። ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ ተወካዮች መላክ ያልቻሉ ጉባኤዎች እና ገለልተኛ ቡድኖች የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም መቀበላቸውን የሚያሳውቅ የአቋም መግለጫ ለማሳለፍ በነሐሴ ወር በየጉባኤያቸው ስብሰባ አደረጉ (በዚያ ወቅት ጉባኤዎች በእንግሊዝኛ ካምፓኒ ይባሉ ነበር)። በላ ግራንድ የሚገኘው ትንሹ ቡድናችንም ስብሰባ አድርጎ ነበር። ከዚያም በ1933 ዘ ክራይስስ የተሰኘውን አነስተኛ መጽሐፍ ለማሠራጨት በተደረገ ዘመቻ ላይ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አቀራረብ ተዘጋጅቼ ለመጀመሪያ ጊዜ ከቤት ወደ ቤት ብቻዬን አገለገልኩ።

በ1930ዎቹ በስብከቱ ሥራችን ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የሚሄድ ተቃውሞ ያጋጥመን ጀመር። ይህን ለመቋቋም የተወሰኑ ጉባኤዎች አንድ ላይ በመቀናጀት በዓመት አንዴ ወይም ሁለቴ ትልቅ ስብሰባ ያደርጉ የነበረ ከመሆኑም በላይ የስብከት ዘመቻም ያካሂዱ ነበር። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ መስበክ የምንችልባቸውን መንገዶች እንማር የነበረ ሲሆን ፖሊሶች ሥራችንን ለማስቆም ጣልቃ ሲገቡ እንዴት አድርገን በአክብሮት መልስ እንደምንሰጥ ሥልጠና ይሰጠንም ነበር። ምሥክሮቹ የፖሊስ ዳኛ አሊያም መደበኛ ችሎት ፊት በተደጋጋሚ ይቀርቡ ስለነበር የፍርድ ቤት ሥርዓት በሚባል ሰነድ ላይ የቀረበውን መመሪያ እያነበብን እንለማመድ ነበር። ይህም ተቃውሞ ሲገጥመን ምን ማድረግ እንዳለብን አዘጋጅቶናል።

ከልጅነት ጀምሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር

ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለተመሠረተው በአምላክ መንግሥት ሥር በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ የነበረኝ አድናቆት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጣ። በዚያን ጊዜ፣ በሰማይ ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋ የሌላቸው ሰዎች እንዲጠመቁ ብዙም ትኩረት አይሰጥም ነበር። (ራእይ 5:10፤ 14:1, 3) የሆነ ሆኖ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ በልቤ ከወሰንኩ መጠመቄ ተገቢ እንደሚሆን ተነገረኝ። በመሆኑም ነሐሴ 1933 ተጠመቅሁ።

የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ መምህሬ ንግግር የማቅረብ ጥሩ ችሎታ እንዳለኝ ስለተሰማት ተጨማሪ ሥልጠና የማገኝበት ዝግጅት እንድታደርግልኝ ለእናቴ ነገረቻት። እናቴም ሥልጠናው ይሖዋን በተሻለ መንገድ ለማገልገል ሊረዳኝ እንደሚችል ስለተሰማት ለአንድ ዓመት ያህል የንግግር ባሕርይ ትምህርቱን እንድከታተል የአስተማሪዬን ልብስ በማጠብ ወጪውን ሸፈነችልኝ። ይህ ሥልጠና ለአገልግሎቴ ጠቅሞኛል። 14 ዓመት ሲሆነኝ የቁርጥማት በሽታ የሚያስከትል ትኩሳት ያዘኝና ለአንድ ዓመት ያህል ትምህርቴን አቋረጥሁ።

በ1939 ዋረን ሄንሸል የተባለ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወደ አካባቢያችን መጣ። a እሱም ቀኑን ሙሉ ወደ መስክ አገልግሎት ይዞኝ ይወጣ ስለነበር በመንፈሳዊ ሁኔታ እንደ ታላቅ ወንድሜ ነበር። ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከጊዜያዊ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አንዱ በሆነው የበጋ የአቅኚነት አገልግሎት እንድካፈል አበረታታኝ። በዚያ የበጋ ወቅት ቡድናችን አድጎ ጉባኤ ሆነ። ዋረን የጉባኤው አገልጋይ ሆኖ የተሾመ ሲሆን እኔ ደግሞ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት መሪ ሆንሁ። ዋረን በቤቴል፣ ማለትም በብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ዋና መሥሪያ ቤት ለማገልገል ሲሄድ እኔ የጉባኤው አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ

የጉባኤ አገልጋይ በመሆን የተሰጠኝ ተጨማሪ ኃላፊነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር የነበረኝን ምኞት ይበልጥ ስላጠናከረልኝ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ3ኛ ዓመት ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ በ17 ዓመቴ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። አባቴ ሃይማኖታዊ እምነታችንን ባይቀበልም የቤተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት ተግቶ የሚሠራና ሥርዓታማ ሰው ነበር። ኮሌጅ እንድገባ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ለቤትና ለምግብ እንዲከፍልልኝ እስካልጠየቅሁት ድረስ የፈለግሁትን ማድረግ እንደምችል ነገረኝ። ስለዚህ መስከረም 1, 1940 የአቅኚነት አገልግሎት ጀመርኩ።

ከቤት በወጣሁበት ዕለት እናቴ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን ምሳሌ 3:5, 6ን አስነበበችኝ። ሁልጊዜ በይሖዋ መታመኔ በእርግጥ ትልቅ እርዳታ ሆኖልኛል።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በሰሜን ማዕከላዊ ዋሽንግተን ክፍለ ሀገር በማገልገል ላይ ከነበሩት ጆ እና ማርጋሬት ሃርት ከተባሉ ባልና ሚስት ጋር አብሬ ማገልገል ጀመርኩ። የአገልግሎት ክልላችን የከብትና የበግ ማርቢያ ቦታዎች፣ ለአሜሪካ ሕንዶች የተከለለ መሬት እንዲሁም በርካታ ትናንሽ ከተሞችና መንደሮች ያሉበት የተለያየ ገጽታ ያለው ክልል ነበር። በ1941 የጸደይ ወራት በዋሽንግተን፣ ወናቺ በሚገኝ ጉባኤ አገልጋይ ሆኜ ተመደብኩ።

በዋላ ዋላ፣ ዋሽንግተን ካደረግናቸው ትልልቅ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ለሚገቡት አቀባበል እንዳደርግ በአስተናጋጅነት እንድሠራ ተመድቤ ነበር። አንድ ወጣት ወንድም የድምፅ ማጉያ መሣሪያውን ማሠራት አቅቶት ሲታገል አየሁና እሱ የእኔን ቦታ እንዲሸፍን፣ እኔ ደግሞ በእሱ ቦታ እንድሠራ ሐሳብ አቀረብኩለት። የአውራጃ የበላይ ተመልካች የሆነው አልበርት ሆፍማን ምድብ ቦታዬ ላይ ሲያጣኝ አንድ ሰው ሳይታዘዝ ከተመደበበት ቦታ መንቀሳቀስ እንደሌለበት በደግነት ነገረኝ። የሰጠኝን ምክር እስከ አሁን ድረስ አልረሳሁትም።

ነሐሴ 1941 የይሖዋ ምሥክሮች በሴይንት ሉዊ፣ ሚዙሪ ትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ለማድረግ ዝግጅት አደረጉ። ጆ እና ማርጋሬት ሃርት በመኪናቸው እቃ መጫኛ ላይ አግዳሚ ወንበሮች ገጥመው ሸራ አለበሱት። ዘጠኝ የምንሆን አቅኚዎች ከኋላ ተሳፍረን ወደ ሴይንት ሉዊ 2,400 ኪሎ ሜትር የሚፈጅ ጉዞ ያደረግን ሲሆን ደርሶ መልስ ጉዞው ወደ ሁለት ሳምንት ገደማ ይፈጃል። ፖሊስ በአውራጃ ስብሰባው ላይ የተገኙት ሰዎች 115,000 እንደሚያህሉ ገምቶ ነበር። ሆኖም የተሰብሳቢዎች ቁጥር ያን ያህል እንደማይደርስ የታወቀ ቢሆንም በወቅቱ በዩናይትድ ስቴትስ ከነበሩት 65,000 የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚበልጥ እርግጠኞች ነበርን። ስብሰባው በእርግጥ በመንፈሳዊ አነቃቅቶናል።

በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል

ወደ ወናቺ ከተመለስኩ በኋላ በብሩክሊን ቤቴል እንዳገለግል መጠራቴን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። ጥቅምት 27, 1941 ብሩክሊን ቤቴል ስደርስ የማተሚያ ክፍሉ የበላይ ተመልካች ወደሆነው ወደ ናታን ኤች ኖር ቢሮ ወሰዱኝ። እሱም የቤቴል ኑሮ ምን እንደሚመስል ጥሩ አድርጎ ካብራራልኝ በኋላ በቤቴል ሕይወት ስኬታማ ለመሆን ከይሖዋ ጋር ተጣብቆ መኖር አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ገለጸልኝ። ከዚያም ወደ ጽሑፍ መላኪያ ክፍል ተወሰድኩና ካርቶኖች የማሸግ ሥራ ተሰጠኝ።

ጥር 8, 1942 በዓለም ዙሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አመራር ይሰጥ የነበረው ጆሴፍ ራዘርፎርድ አረፈ። ከአምስት ቀናት በኋላ የማኅበሩ ዲሬክተሮች የእሱን ቦታ ወንድም ኖር እንዲይዝ ወሰኑ። ለረዥም ጊዜ የማኅበሩ ገንዘብ ያዥ የነበረው ዊልያም ቫን አምበርግ ወንድም ኖር መመረጡን ለቤቴል ቤተሰብ ሲያሳውቅ እንዲህ አለ:- “በ1916 ወንድም ራስል ሞቶ ወንድም ራዘርፎርድ የተተካበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። ጌታ ሥራውን መምራቱንና መባረኩን ቀጥሏል። ሥራው የሰው ሳይሆን የጌታ በመሆኑ ናታን ኖር ፕሬዚዳንት ሆኖ በሚያገለግልበት ጊዜ ሥራው ወደፊት እንደሚገሰግስ እርግጠኛ ነኝ።”

በየካቲት 1942 “በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ልዩ ሥልጠና” እንደሚሰጥ ማስታወቂያ ተነገረ። ዓላማው በቤቴል ያሉት ወንድሞች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሶች ላይ ምርምር የማድረግ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ፣ የሚያቀርቡትን ንግግር በተገቢው መንገድ እንዲያዋቅሩና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲያስተምሩ ለማሰልጠን ታስቦ የተዘጋጀ ነበር። ቀደም ሲል ያገኘሁት ንግግር የማቅረብ ሥልጠና እገዛ ስላደረገልኝ በፕሮግራሙ ፈጣን መሻሻል ማድረግ ቻልኩ።

ብዙም ሳይቆይ በዩናይትድ ስቴትስ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች የአገልግሎት እንቅስቃሴ በሚከታተለው የአገልግሎት ክፍል እንድሠራ ተመደብኩ። በዚያው ዓመት ቆየት ብሎ አገልጋይ የሆኑ ወንድሞች የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች የሚጎበኙበት ዝግጅት በድጋሚ እንዲቋቋም ተወሰነ። ከጊዜ በኋላ የወንድሞች አገልጋዮች ተብለው ይጠሩ የነበሩት እነዚህ ተጓዥ አገልጋዮች የወረዳ የበላይ ተመልካች የሚል ስያሜ ተሰጣቸው። በ1942 የበጋ ወራት ወንድሞች ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት የሚሠለጥኑበት ኮርስ በቤቴል የተዘጋጀ ሲሆን እኔም በሥልጠናው ከሚካፈሉት መካከል የመሆን መብት አገኘሁ። ከአስተማሪዎቻችን አንዱ የሆነው ወንድም ኖር ጠበቅ አድርጎ የገለጸልንን የሚከተለውን ነጥብ ፈጽሞ አልረሳውም:- “ጥረታችሁ ሰዎችን ማስደሰት መሆን የለበትም። ይህ ከሆነ በመጨረሻ ማንንም ሳታስደስቱ ትቀራላችሁ። ይሖዋን የምታስደስቱ ከሆነ ግን እሱን የሚወዱትን ሁሉ ማስደሰት ትችላላችሁ።”

ጉባኤዎችን የመጎብኘቱ ዝግጅት ጥቅምት 1942 ላይ ተግባራዊ ሆነ። በቤቴል ከነበርነው አንዳንዶቻችን በተወሰኑ የሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ከኒው ዮርክ ከተማ በ400 ኪሎ ሜትር ክልል ውስጥ የሚገኙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት በሥራው ተካፈልን። በጉብኝቱ ወቅት ከምናከናውናቸው ሥራዎች መካከል የጉባኤዎችን የስብከት እንቅስቃሴና የተሰብሳቢዎችን ቁጥር ሪፖርት መመርመር፣ በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ካላቸው ወንድሞች ጋር ስብሰባ ማድረግ፣ አንድ ወይም ሁለት ንግግር ማቅረብ እንዲሁም ከጉባኤው አስፋፊዎች ጋር አብሮ ማገልገል ይገኙበታል።

በ1944፣ በአገልግሎት ቢሮ ከምንሠራው ወንድሞች ውስጥ በዴለዋር፣ ሜሪላንድ፣ ፔንሲልቫኒያና ቨርጂኒያ ለስድስት ወራት በተጓዥነት ሥራ እንዲያገለግሉ ከተላኩት ወንድሞች መካከል አንዱ ነበርኩ። በኋላም ለጥቂት ወራት በከኔቲከት፣ በማሳቹሴትስና በሮድ ደሴት ጉባኤዎችን በመጎብኘት አገለገልኩ። ወደ ቤቴል ከተመለስኩ በኋላ በቀን ውስጥ የተወሰነ ሰዓት ከወንድም ኖርና ከጸሐፊው ሚልተን ሄንሸል ጋር እሠራ የነበረ ሲሆን ይህም ስለ ዓለም አቀፉ ሥራችን ግንዛቤ እንዳገኝ አስችሎኛል። በተጨማሪም በቀን ለተወሰነ ሰዓት ከዊልያም ቫን አምበርግና ከረዳቱ ከግራንት ሱተር ጋር በሒሳብ ክፍል እሠራ ነበር። ከዚያም በ1946 ቤቴል ውስጥ የተወሰኑ ቢሮዎች የበላይ ተመልካች ሆንኩ።

በሕይወቴ የተከሰቱ ከፍተኛ ለውጦች

በ1945 ጉባኤዎችን በምጎበኝበት ጊዜ በፕሮቪደንስ ከተማ፣ ሮድ ደሴት ከጁሊያ ቻርኖስከስ ጋር ተዋወቅሁ። ከዚያም በ1947 አጋማሽ ላይ ለመጋባት ተስማማን። የቤቴልን አገልግሎት በጣም እወደው ነበር፤ ሆኖም ከጋብቻ በኋላ አንድ ላይ በቤቴል ማገልገል የሚቻልበት ዝግጅት አልነበረም። ስለዚህ ጥር 1948 ከቤቴል ወጥቼ ከጁልያ (ጁሊ) ጋር ተጋባን። በፕሮቪደንስ ከተማ የግማሽ ቀን ሥራ አገኘሁና ሁለታችንም አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን።

መስከረም 1949 በሰሜን ምዕራብ ዊስኮንሲን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። በአብዛኛው በትንንሽ ከተሞችና የወተት ውጤቶች በሚመረቱበት ገጠራማ አካባቢዎች መስበክ ለእኔና ለጁሊ ትልቅ ለውጥ ነበር። የክረምቱ ወራት ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅና በጣም የሚበርድ ከመሆኑም በላይ ለበርካታ ሳምንታት ቅዝቃዜው ከዜሮ በታች የሚወርድ ሲሆን አካባቢውም በበረዶ ይሸፈናል። በወቅቱ መኪና አልነበረንም፤ ሆኖም ወንድሞች ከአንዱ ጉባኤ ወደሚቀጥለው በመኪና ያደርሱን ነበር።

በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል ከጀመርኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የወረዳ ስብሰባ አደረግን። ሁሉም ነገር በትክክል እየተሠራ መሆኑን በጥብቅ እከታተል እንደነበረና ይህም ወንድሞችን እንዳስጨነቃቸው አስታውሳለሁ። በመሆኑም የአውራጃ የበላይ ተመልካቹ ኒኮላስ ኮቨላክ ወንድሞች የለመዱት አሠራር እንዳላቸውና ይህን ያህል ነገሮችን ለመቆጣጠር መሞከር እንደሌለብኝ በደግነት አስረዳኝ። ወንድም የሰጠኝ ምክር ከዚያ በኋላ ተመድቤ በሠራሁባቸው ቦታዎች ሁሉ ጠቅሞኛል።

በ1950 በኒው ዮርክ ከተማ ያንኪ ስታዲየም ካደረግናቸው በርካታ ትላልቅ ስብሰባዎች የመጀመሪያ በሆነው ላይ ለስብሰባው ለመጡት ልዑካን ማረፊያ የሚያዘጋጀው ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኜ እንድሠራ ተመደብኩ። የአውራጃ ስብሰባው ተጀምሮ እስኪያልቅ አስደሳች የነበረ ሲሆን ከ67 አገሮች የመጡ ልዑካንና 123,707 ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ነበረ! ከስብሰባው በኋላ እኔና ጁሊ ጉባኤዎችን መጎብኘታችንን የቀጠልን ሲሆን ሥራው በጣም አስደስቶን ነበር። ይሁን እንጂ በማንኛውም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ራሳችንን ማቅረብ እንዳለብን ይሰማን ስለነበር ለቤቴልና ለሚስዮናዊነት አገልግሎት በየዓመቱ እናመለክት ነበር። በ1952 በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በሚስዮናዊነት ለማገልገል የሚሰጠውን ሥልጠና ለመከታተል በ20ኛው ክፍል እንድንገኝ ስንጋበዝ በጣም ተደሰትን።

በውጭ አገር ማገልገል

በ1953 ከትምህርት ቤቱ ስንመረቅ የአገልግሎት ምድባችን ብሪታንያ መሆኑ ተነገረን። በደቡባዊ እንግሊዝ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገለገልኩ። እኔና ጁሊ በዚህ የአገልግሎት መስክ በጣም ተደስተን የነበረ ቢሆንም ዓመት ሳይሞላን ወደ ዴንማርክ እንድንዛወር ሲነገረን ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ሆነብን። ዴንማርክ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አዲስ የበላይ ተመልካች ያስፈልግ ነበር። ከዚያ ብዙም በማትርቀው በእንግሊዝ ስለነበርኩና ብሩክሊን ሳለሁ ለዚህ ዓይነቱ ሥራ ሥልጠና አግኝቼ ስለነበር እርዳታ እንዳበረክት ወደ ዴንማርክ ተላክሁ። በመጀመሪያ ወደ ኔዘርላንድስ በጀልባ የሄድን ሲሆን ከዚያም ወደ ኮፐንሃገን፣ ዴንማርክ በባቡር ተጉዘን ነሐሴ 9, 1954 ደረስን።

በወቅቱ ከነበሩት መፍትሔ የሚያስፈልጋቸው ችግሮች አንዱ በኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ጥቂት ወንድሞች በብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት የሚላክላቸውን መመሪያ መቀበል አሻፈረን ማለታቸው ነበር። በተጨማሪም ጽሑፎቻችንን ወደ ዳኒሽ ቋንቋ ከሚተረጉሙት አራት ወንድሞች መካከል ሦስቱ ከቤቴል የወጡ ሲሆን በኋላም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ። ሆኖም ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ በመስጠት በትርፍ ጊዜያቸው ጽሑፎች ይተረጉሙ የነበሩት ዮረንና አና ላርሰን የሚባሉ ባልና ሚስት አቅኚዎች በሙሉ ጊዜያቸው የትርጉም ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን አቀረቡ። በመሆኑም ወደ ዳኒሽ ቋንቋ የሚተረጎሙት መጽሔቶቻችን አንድም እትም አላመለጠንም። ዮረንና አና ላርሰን እስከ አሁን ድረስ በዴንማርክ ቤቴል እያገለገሉ ሲሆን ዮረን የቅርንጫፍ ኮሚቴው አስተባባሪ ሆኖ ይሠራል።

በዚያን ጊዜ ወንድም ኖር በየጊዜው ከሚያደርግልን ጉብኝት ከፍተኛ ማበረታቻ እናገኝ ነበር። ጊዜ ወስዶ እያንዳንዳችንን በማነጋገር ችግሮችን መፍታት የምንችልበትን ማስተዋል እንድናገኝ ልምድ ያካፍለን ነበር። በ1955 ባደረገልን ጉብኝት በዳኒሽ ቋንቋ መጽሔቶችን ማተም እንችል ዘንድ ሕትመት የምናካሂድበት አዲስ የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ እንዲገነባ ተወሰነ። ከኮፐንሃገን በስተ ሰሜን ከከተማ ወጣ ብሎ መሬት ተገዝቶ ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ በ1957 በጋ ላይ ወደ አዲሱ ቤቴል ተዛወርን። ሃሪ ጆንሰን ከባለቤቱ ከካሪን ጋር ከጊልያድ 26ኛ ክፍል ተመርቀው ከጥቂት ጊዜ በፊት ወደ ዴንማርክ መጥተው ስለነበር የማተሚያ መሣሪያውን ገጣጥመው የሕትመት ሥራው እንዲጀመር አደረጉ።

በዴንማርክ ትላልቅ ስብሰባ ለማድረግ የሚከናወነውን ሥራ አደረጃጀት አሻሽለነው የነበረ ሲሆን በዚህ ረገድ ዩናይትድ ስቴትስ እያለሁ በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ስሠራ ያገኘሁት ተሞክሮ በጣም ጠቅሞኛል። በ1961 በኮፐንሃገን ባደረግነው ትልቅ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከ30 አገሮች የመጡ ልዑካን ተገኝተው የነበረ ሲሆን ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር 33,513 ነበር። በ1969 በስካንዲኔቪያን አገሮች ከተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ሁሉ በትልቅነቱ ተወዳዳሪ የሌለው 42,073 ሰዎች የተገኙበት ስብሰባ አድርገን ነበር!

በ1963 በጊልያድ 38ኛ ክፍል እንድሰለጥን ተጋበዝኩ። ይህ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላትን ለማሠልጠን ተብሎ የተዘጋጀ የአሥር ወር ትምህርት ነበር። በብሩክሊን ካለው የቤቴል ቤተሰብ ጋር እንደገና አብሮ መሆንና በዋና መሥሪያ ቤቱ ከሚሠሩ የብዙ ዓመታት ልምድ ካላቸው ወንድሞች ሥልጠና ማግኘት በጣም አስደሳች ነበር።

ሥልጠናውን ከጨረስኩ በኋላ ወደ ዴንማርክ ተመልሼ የቤቴል አገልግሎቴን ቀጠልኩ። በተጨማሪም በምዕራብና ሰሜን አውሮፓ ያሉ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን በመጎብኘት ለቤቴላውያን ማበረታቻ በመስጠትና ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዲችሉ በመርዳት የዞን የበላይ ተመልካች ሆኜ የማገልገል መብት አገኘሁ። በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ አፍሪካና በካሪቢያን አገሮች በዞን የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ።

በ1970ዎቹ መጨረሻ ላይ፣ በዴንማርክ የነበሩ ወንድሞች የትርጉምና የሕትመት ሥራውን ማስፋት እንዲቻል ከበፊቱ የበለጠ ሕንፃ የሚሠራበት ቦታ መፈለግ ጀመሩ። ከኮፐንሃገን በስተ ምዕራብ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተስማሚ ቦታ ተገኘ። የዚህን አዲስ ሕንፃ የግንባታ ሥራ ዕቅድና ንድፍ በማውጣት ከሌሎች ወንድሞች ጋር የሠራሁ ሲሆን እኔና ጁሊ በዚህ አዲስ የቤቴል ቤት ውስጥ ለመኖር ጓጉተን ነበር። ይሁን እንጂ ምኞታችን ሳይፈጸም ቀረ።

ወደ ብሩክሊን ተመለስን

ኅዳር 1980 ጁሊና እኔ በብሩክሊን ቤቴል እንድናገለግል የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰንና በ1981 ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ወደ ብሩክሊን ሄድን። በዚያን ጊዜ በ50ዎቹ መጨረሻ ላይ የነበርን ሲሆን ከዕድሜያችን ግማሽ ያህሉን ያሳለፍነው በዴንማርክ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር በማገልገል ስለነበር ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ ከበደን። ሆኖም ስለ ራሳችን ምርጫ ከማሰብ ይልቅ በአዲሱ ምድባችንና ከዚያ ጋር ተያይዘው በሚመጡት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ላይ ትኩረት ለማድረግ ጥረት አደረግን።

ወደ ብሩክሊን መጥተን የቤቴል አገልግሎታችንን ቀጠልን። ጁሊ ዴንማርክ እያለች ትሠራው እንደነበረው የሒሳብ ሥራ ላይ ተመደበች። እኔ ደግሞ ጽሑፎቻችን የሚታተሙበትን ፕሮግራም በማዘጋጀት እንድረዳ በጽሑፍ ክፍሉ ተመደብኩ። የ1980ዎቹ መጀመሪያ ከጽሕፈት መኪና እና ኋላ ቀር ከሆነ የሕትመት ሥራ ወደ ኮምፒውተርና ዘመናዊ የማተሚያ መሣሪያዎች የተሸጋገርንበት ጊዜ ስለነበር በብሩክሊን በነበረው የሥራ ሂደት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ተደርጓል። ስለ ኮምፒውተር የማውቀው ነገር ባይኖርም ድርጅታዊ አሠራሮችንና ከሌሎች ጋር አብሮ መሥራትን በተመለከተ መጠነኛ እውቀት ነበረኝ።

ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ባለ ሙሉ ቀለም ዘመናዊ ማተሚያና ባለ ቀለም ሥዕሎችንና ፎቶግራፎችን መጠቀም በመጀመራችን ይህ ሥራ የሚከናወንበትን ክፍል (Art Department) አደረጃጀት ማጠናከር አስፈልጎ ነበር። ከሥዕልና ፎቶግራፍ ሥራ ጋር በተያያዘ ምንም ልምድ ያልነበረኝ ቢሆንም የሥራውን አደረጃጀት በተመለከተ ግን እገዛ አደርግ ነበር። በመሆኑም ለዘጠኝ ዓመታት የዚህ ክፍል የበላይ ተመልካች ሆኖ የማገልገል መብት አግኝቻለሁ።

በ1992 የአስተዳደር አካሉን የሕትመት ኮሚቴ እንድረዳ ተመደብኩ፤ ከዚያም ወደ ገንዘብ ያዥ ቢሮ ተዛወርኩ። የይሖዋ ምሥክሮችን ገንዘብ ነክ ጉዳዮች በሚከታተለው በዚህ ቢሮ እስከ አሁን እየሠራሁ ነው።

ከልጅነቴ ጀምሮ ያከናወንኩት አገልግሎት

ከልጅነቴ ጀምሮ እንዲሁም አምላክን በማገልገል ባሳለፍኳቸው 70 ዓመታት ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስና ድንቅ በሆነው ድርጅቱ ውስጥ ባሉ ወንድሞች አማካኝነት በትዕግሥት አስተምሮኛል። ከ63 ዓመታት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተካፈልኩ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከ55 ዓመት በላይ የሚሆነውን ያሳለፍኩት ታማኝ ከሆነችው ባለቤቴ ከጁሊ ጋር ነው። ይሖዋ አብዝቶ እንደባረከኝ ከልብ አምናለሁ።

በ1940 የአቅኚነት አገልግሎት ለመጀመር ከቤት ስወጣ አባቴ “ለዚህ ብለህ ሄደህ ችግር ቢያጋጥምህ ወደ ቤት እመለሳለሁ ብለህ አታስብ” በማለት ባደረግሁት ውሳኔ አፊዞብኝ ነበር። በእነዚያ ዓመታት ሁሉ እርዳታ ለማግኘት እሱ ጋር መሄድ አስፈልጎኝ አያውቅም። ይሖዋ፣ አብዛኛውን ጊዜ አሳቢ በሆኑ ክርስቲያን ባልንጀሮቼ አማካኝነት የሚያስፈልገኝን ሁሉ በሚገባ አሟልቶልኛል። ከጊዜ በኋላ አባቴ ሥራችንን በአክብሮት መመልከት የጀመረ ከመሆኑም በላይ በ1972 ከመሞቱ በፊት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተምሮ የተወሰነ እድገት አድርጎ ነበር። በሰማይ የመኖር ተስፋ የነበራት እናቴ በ1985 በ102 ዓመቷ እስከሞተችበት ዕለት ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግላለች።

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ችግሮች ማጋጠማቸው የማይቀር ቢሆንም እኔና ጁሊ አገልግሎታችንን ስለማቆም አስበን አናውቅም። ይሖዋም በዚህ ውሳኔያችን እንድንጸና ረድቶናል። ወላጆቼ አርጅተው እርዳታ ባስፈለጋቸው ወቅት እንኳ እህቴ፣ ቪክቶሪያ ማርሊን በደግነት ተንከባክባቸዋለች። እሷ ያበረከተችው እርዳታ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድንቀጥል ስላስቻለን በፍቅር ተነሳስታ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ከልብ እናመሰግናታለን።

ጁሊ በተመደብንበት የአገልግሎት መስክ ሁሉ ለእኔ ድጋፍ መስጠት ራሷን ለይሖዋ የወሰነችበት አንዱ ክፍል እንደሆነ በመቁጠር በታማኝነት ደግፋኛለች። አሁን 80 ዓመት የሞላኝና መጠነኛ የጤና ችግር ያለብኝ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ አብዝቶ እንደባረከኝ ይሰማኛል። መዝሙራዊው፣ አምላክ ከልጅነቱ ጀምሮ እንዳስተማረው ከተናገረ በኋላ ‘እስካረጅም ድረስ፣ ለሚመጣ ትውልድም ሁሉ ክንድህን ኃይልህንም ጽድቅህንም እስክነግር ድረስ፣ አቤቱ፣ አትተወኝ’ ብሎ የተናገረው ቃል ያበረታታኛል።—መዝሙር 71:17, 18

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዋረን፣ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ ለብዙ ዓመታት ያገለገለው የሚልተን ሄንሸል ታላቅ ወንድም ነው።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አቅኚነት በጀመርኩበት በ1940 ከእናቴ ጋር

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአቅኚነት አብረን ካገለገልነው ከጆ እና ማርጋሬት ሃርት ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥር 1948 በሠርጋችን ቀን

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1953 በጊልያድ አብረውኝ ከተማሩት ጋር። ከግራ ወደ ቀኝ:- ዶን እና ቨርጂኒያ ዋርድ፣ ሃርቱዳ ስቴሄንጋ፣ ጁሊ እና እኔ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1961 ከፍሬድሪክ ዊልያም ፍራንዝ እና ከናታን ኖር ጋር በኮፐንሃገን፣ ዴንማርክ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአሁኑ ጊዜ ከጁሊ ጋር