ደስተኛ ሕይወት ለመምራት መተማመን አስፈላጊ ነው
ደስተኛ ሕይወት ለመምራት መተማመን አስፈላጊ ነው
በምግብ መመረዝ የተነሳ የሚፈጠር ሕመም በጣም ያሰቃያል። የምግብ መመረዝ በተደጋጋሚ ያጋጠመው ሰው በአመጋገቡ ረገድ ይበልጥ ጠንቃቃ መሆን ያስፈልገዋል። ሆኖም የምግብ መመረዝን ለማስወገድ ሲባል ጨርሶ ምግብ አለመብላት የሚያዋጣ ምርጫ አይደለም። አንድ ሰው መብላት ቢያቆም ችግሩን ከማቃለል ይልቅ ያባብሰዋል። ማንም ሰው ምግብ ሳይበላ መኖር አይችልም።
በተመሳሳይም የተማመኑበት ሰው በቃሉ ሳይገኝ ሲቀር ያሳዝናል። በተደጋጋሚ የዚህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመን ስለ ባልንጀራ ምርጫችን በጥንቃቄ እንድናስብ ያደርገን ይሆናል። ሆኖም በተማመንባቸው ሰዎች መከዳትን ለማስቀረት ሲባል ጨርሶ ከሰዎች መራቅም መፍትሔ አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ተጠራጣሪ መሆን ደስታችንን ስለሚነጥቀን ነው። እርካታ ያለበት ሕይወት ለመምራት በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ዝምድና ሊኖረን ይገባል።
ዩገንት 2002 የተባለው መጽሐፍ “መተማመን ከሌሎች ጋር ነፃ የሆነ ዕለታዊ ግንኙነት ለማድረግ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱ ነው” ይላል። ኖይ ጹኧርከር ጻይቱንግ የተባለ አንድ የጀርመን ጋዜጣ ደግሞ “ማንኛውም ግለሰብ የሚተማመንበት ሰው ለማግኘት ይፈልጋል” በማለት ዘግቧል። “መተማመን የተሻለ ሕይወት ለመምራት” ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ በመሆኑ “በሕይወት ለመቀጠል በጣም አስፈላጊ ነው።” በእርግጥም ጋዜጣው በመቀጠል እንደገለጸው መተማመን ሳይኖር “አንድ ሰው ኑሮን መቋቋም አይችልም።”
ሁላችንም በሌሎች ላይ እምነት የማሳደር መሠረታዊ ፍላጎት አለን። ታዲያ እንደማይከዳን እርግጠኛ ሆነን መተማመን የምንችለው በማን ነው?
በፍጹም ልብህ በይሖዋ ታመን
መጽሐፍ ቅዱስ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን” ይለናል። (ምሳሌ 3:5) በእርግጥም፣ የአምላክ ቃል በፈጣሪያችን በይሖዋ አምላክ እንድንተማመን በተደጋጋሚ ያበረታታናል።
በአምላክ መተማመን የምንችለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ይሖዋ አምላክ ቅዱስ ስለሆነ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” በማለት ጽፏል። (ኢሳይያስ 6:3) ስለቅድስና የሚናገረው ሐሳብ አይማርክህ ይሆን? ሊማርክህ ይገባል፣ ምክንያቱም ይሖዋ ቅዱስ ነው ሲባል ንጹሕ፣ ከማንኛውም ዓይነት ክፋት የጠራና ፍጹም እምነት ሊጣልበት የሚችል ነው ማለት ነው። እርሱ በፍጹም ምግባረ ብልሹ ሊሆን የማይችልና በሥልጣኑ ያለአግባብ የማይጠቀም በመሆኑ የጣልንበትን እምነት ሊያጎድል አይቻለውም።
ከዚህም በላይ አምላክ የሚያገለግሉትን ሰዎች ለመደገፍ ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ ስላለው በእርሱ መተማመን እንችላለን። ለአብነት ያህል፣ ታላቅ ኃይሉ አንድ ነገር እንዲያከናውን ያስችለዋል። አንድን ጉዳይ ለማከናወን ፍትሑን እና ጥበቡን ይጠቀማል። አቻ የማይገኝለት ፍቅሩ ደግሞ አንድ ዓይነት እርምጃ እንዲወስድ ይገፋፋዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:8) አምላክ ሁሉን ነገር የሚያደርገው በፍቅሩ ተገፋፍቶ ነው። የይሖዋ ቅድስናና ሌሎች የላቁ ባሕርያቱ ሙሉ እምነት ልንጥልበት የምንችል ጥሩ አባት ያደርጉታል። ከይሖዋ በላይ ልንተማመንበት የምንችል ማንም ወይም ምንም ነገር የለም።
በይሖዋ በመተማመን ደስተኛ ሁን
በይሖዋ ለመታመን የሚገፋፋን ሌላው ጠንካራ ምክንያት ከማንም ሰው በላይ የሚያውቀን መሆኑ ነው። ይሖዋ፣ እያንዳንዱ ሰው ከፈጣሪው ጋር አስተማማኝ የሆነ፣ ዘላቂና መተማመን ያለበት ዝምድና የመመሥረት መሠረታዊ ፍላጎት እንዳለው ያውቃል። ከፈጣሪ ጋር እንደዚህ ዓይነት ዝምድና ያላቸው ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ ሕይወታቸው አስተማማኝ እንደሆነ ይሰማቸዋል። መዝሙራዊው ዳዊት “እግዚአብሔርን የታመነ . . . ሰው ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW] ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝሙር 40:4) በዛሬው ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዳዊትን ሐሳብ ከልባቸው ያስተጋባሉ።
አንዳንድ ምሳሌዎች ተመልከት። ዶሪስ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ፣ በጀርመን፣ በግሪክና በዩናይትድ ስቴትስ ኖራለች። እንዲህ ትላለች:- “በይሖዋ በመታመኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። እርሱ አካላዊ፣ መንፈሳዊና ስሜታዊ እንክብካቤ እንዴት እንደሚያደርግልኝ ያውቃል። ማንም ሰው ሊኖሩት ከሚችሉት ወዳጆች ሁሉ የላቀ ወዳጅ ነው።” የሕግ አማካሪ የሆነው ዉልፍጋንግ “ስለ ደህንነታችሁ ከልብ በሚያስብላችሁ ማለትም ለእናንተ ከሁሉ የተሻለውን ሊያደርግላችሁ በሚችልና ደግሞም በሚያደርግላችሁ አካል መተማመን መቻል ድንቅ ነገር ነው!” ብሏል። በእስያ ቢወለድም አሁን ግን በአውሮፓ የሚኖረው ሃም ደግሞ “ይሖዋ ሁሉ ነገር በእጁ እንደሆነና እንደማይሳሳት እርግጠኛ ስለሆንኩ በእርሱ በመታመኔ ደስተኛ ነኝ” በማለት ተናግሯል።
እርግጥ ነው፣ ሁላችንም ብንሆን በፈጣሪያችን ላይ ብቻ ሳይሆን በሰዎችም ላይ እምነት መጣል ያስፈልገናል። ስለሆነም እንደ አንድ ጥበበኛና ተሞክሮ ያካበተ ወዳጅ ይሖዋም ልንተማመንባቸው የሚገቡ ሰዎች ምን ዓይነት መሆን እንዳለባቸው ይመክረናል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ በማጥናት በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠንን ምክር መመልከት እንችላለን።
ልንተማመንባቸው የምንችላቸው ሰዎች
መዝሙራዊው “ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች አትታመኑ” በማለት ጽፏል። (መዝሙር 146:3) ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር አብዛኞቹ ሰዎች ልንተማመንባቸው የሚገቡ እንዳልሆኑ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ሌላው ቀርቶ ሰዎች በአንድ ዓይነት የእውቀት ወይም የሥራ መስክ ጠበብት መሆናቸውና በዓለም ላይ እንደ “አለቆች” ከፍ ተደርገው መታየታቸው በራሱ እምነት እንድንጥልባቸው ሊያደርገን አይገባም። ብዙውን ጊዜ የሚሰጡት አመራር አሳሳች ስለሆነ እንዲህ ባሉት “አለቆች” መታመን ለብስጭት ይዳርጋል።
እርግጥ፣ ይህ ሁሉንም ሰው እንድንጠራጠር ሊያደርገን አይገባም። ይሁን እንጂ ልንተማመንባቸው የሚገቡ ሰዎች ዘጸአት 18:21) እኛ ከዚህ ምን ልንማር እንችላለን?
በምንፈልግበት ጊዜ መራጮች መሆን እንደሚያስፈልገን ግልጽ ነው። ምን ዓይነት መሥፈርት መጠቀም ይኖርብናል? በጥንቱ የእስራኤል ብሔር የተፈጸመ አንድ ሁኔታ ምሳሌ ሊሆነን ይችላል። በእስራኤል ውስጥ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶችን የሚሸከሙ ግለሰቦችን መሾም ባስፈለገ ጊዜ ሙሴ “ከሕዝቡ ሁሉ አዋቂዎችን፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ” የሚል ምክር ተሰጥቶታል። (እነዚህ ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው እንዲሆኑ የሚጠይቁ ኃላፊነቶችን ከመቀበላቸው በፊት አንዳንድ አምላካዊ ባሕርያትን ያሳዩ ሰዎች ናቸው። አምላክን የሚፈሩ ማለትም ለፈጣሪ ጤናማ የሆነ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸውና እርሱን ላለማሳዘን የሚጠነቀቁ ሰዎች መሆናቸውን ቀደም ሲል ያረጋገጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የአምላክን መሥፈርቶች ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ እንዳደረጉ በግልጽ የሚታይ ነበር። የግፍን ረብ የጠሉ ሲሆን ይህም ሥልጣናቸውን አለአግባብ ከመጠቀም የሚያግዳቸው የሥነ ምግባር ጥንካሬ እንዳላቸው ያመለክታል። የግል ጥቅማቸውን ወይም የዘመዶቻቸውን አሊያም የወዳጆቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የተጣለባቸውን አደራ የማይበሉ ሰዎች ነበሩ።
እኛም ዛሬ ልንተማመንባቸው የሚገቡ ሰዎች በምንመርጥበት ጊዜ ተመሳሳይ መመዘኛ መጠቀማችን ጥበብ አይሆንም? በጠባያቸው አምላክን እንደሚፈሩ የሚያሳዩ ግለሰቦች እናውቃለን? የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመጠበቅ የቆረጡ ናቸው? ትክክል ያልሆኑ ነገሮችን ከማድረግ ለመቆጠብ የሚያስችል የአቋም ጽናት አላቸው? ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ ወይም የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት ሲሉ ነገሮችን ባለማምታታት ሐቀኞች መሆናቸውን ያሳያሉ? እንዲህ ያሉ ባሕርያትን በሚያንፀባርቁ ወንዶችና ሴቶች ልንተማመን እንደምንችል ጥርጥር የለውም።
አልፎ አልፎ እምነት ማጉደል ቢያጋጥምህ ተስፋ አትቁረጥ
በሰዎች መተማመን የሚመጣው በጊዜ ሂደት በመሆኑ በእነማን ላይ እምነት ልንጥል እንደሚገባን ለመወሰን መቸኮል የለብንም። በዚህ ረገድ ጥበብ የሚሆነው በአንድ ሰው ላይ እምነት የምንጥለው ቀስ በቀስና ደረጃ በደረጃ ቢሆን ነው። እንዴት? በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር የሚወስደውን እርምጃ ልብ በማለት የአንድን ሰው አካሄድ በጊዜ ሂደት መመልከት እንችላለን። ግለሰቡ በጥቃቅን ነገሮች እምነት የሚጣልበት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ የተዋሰውን ነገር ቃል በገባው ጊዜ ይመልሳል? ቀጠሮስ ያከብራል? ከሆነ ይህን ሰው ከበድ ባሉ ጉዳዮችም ልንተማመንበት እንደምንችል ሊሰማን ይችላል። ይህም “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር ይስማማል። (ሉቃስ 16:10) መራጭና ታጋሽ መሆናችን ከፍተኛ ብስጭትን ለማስቀረት ይረዳል።
እንዲህም ሆኖ አንድ ሰው እንደጠበቅነው ሆኖ ባይገኝስ? ኢየሱስ በተያዘበት ምሽት ሐዋርያቱ እንደሚጠበቅባቸው ሳይሆኑ በመቅረታቸው እንዳሳዘኑት መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብቡ ሰዎች ያስታውሳሉ። የአስቆሮቱ ይሁዳ አሳልፎ ሲሰጠው ሌሎቹ ደግሞ በፍርሃት ጥለውት ሸሹ። እንዲያውም ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ካደው። ቢሆንም ኢየሱስ ሆን ብሎ የክህደት እርምጃ የወሰደው ይሁዳ ብቻ እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ባለው የቁርጥ ቀን እንደሚጠበቅባቸው ሆነው አለመገኘታቸው ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በአሥራ አንዱ ሐዋርያት ላይ እንደሚተማመንባቸው በድጋሚ ከመናገር አላገደውም። (ማቴዎስ 26:45-47, 56, 69-75፤ 28:16-20) በተመሳሳይም የምናምነው ሰው እንደከዳን ሆኖ ቢሰማን፣ ክህደት የመሰለን ነገር ግለሰቡ እምነት የማይጣልበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው ወይስ የሥጋ ድካም ያስከተለው ድንገተኛ ስሕተት የሚለውን ብናስብበት የተሻለ ነው።
እኔስ እምነት የሚጣልብኝ ነኝ?
ማንን ማመን እንደሚችል ለመወሰን መራጭ የሆነ ሰው ለራሱ ሳያደላ ‘እኔስ እምነት የሚጣልብኝ ሰው ነኝ? እምነት የሚጣልበት ስለመሆን ከራሴም ሆነ ከሌሎች የምጠብቃቸው ምክንያታዊ የሆኑ መሥፈርቶች ምንድን ናቸው?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ አለበት።
እምነት የሚጣልበት ሰው ምንጊዜም እውነት እንደሚናገር ጥርጥር የለውም። (ኤፌሶን 4:25) የግል ጥቅም ለማግኘት ሲል የሚሰሙትን ሰዎች ለማስደሰት በልቡ የሌለ ነገር በመናገር ሰዎችን አይሸነግልም። እምነት የሚጣልበት ሰው አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከገባ ቃሉን ለመጠበቅ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። (ማቴዎስ 5:37) እምነት የሚጣልበት ግለሰብ የተነገረውን ምስጢር ይጠብቃል እንጂ ለሌላ ሰው አያወራም። እምነት የሚጣልበት ሰው ለትዳር ጓደኛውም ታማኝ ነው። የብልግና ሥዕሎችን አይመለከትም፤ እንዲሁም ትኩረቱ በሥጋ ፍትወት ቅዠቶች ላይ እንዲያርፍ የማይፈቅድ ከመሆኑም በላይ ማንንም አያሽኮረምምም። (ማቴዎስ 5:27, 28) እምነት የሚጣልበት ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ መተዳደሪያ ለማግኘት ተግቶ ይሠራል እንጂ በሌሎች ኪሳራ ለራሱ ትርፍ ማጋበስ አይሻም። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) እንዲህ ያሉትን ምክንያታዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሥፈርቶች ማስታወሳችን ልንተማመንባቸው የሚገቡ ሰዎችን ለይተን ለማወቅ ይረዳናል። ከዚህም በላይ እያንዳንዳችን እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን ሌሎች የሚተማመኑብን ዓይነት ሰዎች እንድንሆን ይረዳናል።
ሁሉም ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው በሚሆኑበትና በምናምነው ሰው በመከዳታችን ምክንያት በማናዝንበት ዓለም መኖር በጣም ያስደስታል! ይህ እንዲያው ሕልም ብቻ ነው? የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋዎች በቁም ነገር ለሚመለከቱ ሰዎች ይህ ሕልም ብቻ ሆኖ የሚቀር አይደለም። ምክንያቱም የአምላክ ቃል ከማንኛውም ዓይነት ማታለል፣ ውሸትና ብዝበዛ እንዲሁም ከሐዘን፣ ከበሽታና ከሞትም እንኳን ሳይቀር ነፃ የሆነ ውብ “አዲስ ምድር” እንደሚመጣ ይተነብያል! (2 ጴጥሮስ 3:13፤ መዝሙር 37:11, 29፤ ራእይ 21:3-5) ስለዚህ ተስፋ ተጨማሪ እውቀት ለማግኘት ጥረት ማድረግ ጠቃሚ አይመስልህም? የይሖዋ ምሥክሮች በዚህና በሌሎችም ዓቢይ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ መረጃ ሊሰጡህ ፈቃደኞች ናቸው።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተጠራጣሪ መሆን ደስታችንን ይነጥቀናል
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ከማንም በላይ ልንተማመንበት የሚገባ አምላክ ነው
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሁላችንም በጋራ መተማመን ላይ የተመሠረተ ዝምድና እንፈልጋለን