በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘በአምላክ ቃል በትክክል ተጠቀሙ’

‘በአምላክ ቃል በትክክል ተጠቀሙ’

‘በአምላክ ቃል በትክክል ተጠቀሙ’

“የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር [“በትክክል የሚጠቀም፣” NW ] የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።”​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:15

1, 2. (ሀ) የእጅ ባለሙያዎች መሣሪያዎች የሚያስፈልጓቸው ለምንድን ነው? (ለ) ክርስቲያኖች ምን ሥራ ተሰጥቷቸዋል? መንግሥቱን ማስቀደማቸውን የሚያሳዩትስ እንዴት ነው?

 የእጅ ባለሙያዎች ሥራቸውን ለማከናወን የተለያዩ መሣሪያዎች ያስፈልጓቸዋል። ሆኖም የመሣሪያው መኖር ብቻውን በቂ አይደለም። ባለሙያው ትክ​ክለኛው ዓይነት መሣሪያ የሚያስፈልገው ከመሆኑም በላይ በተገቢው መንገድ ሊጠቀምበት ይገባል። ለምሳሌ ያህል አንድ ትንሽ መጠለያ እየሠራህ ነው እንበል። ሁለት እንጨቶችን አንድ ላይ ለማያያዝ ብትፈልግ መዶሻና ምስማር መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም። ምስማሩን ሳታጣምም እንጨቱ ላይ የመምታት ችሎታ ሊኖርህ ይገባል። መዶሻውን እንዴት መጠቀም እንደምትችል ካላወቅህ ምስማሩን እንጨት ላይ መምታት ሊያስቸግርህ ብሎም ተስፋ አስቆራጭ ሊሆንብህ ይችላል። መሣሪያዎችን በትክክል መጠቀም መቻል አርኪና ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ያስ​ችላል።

2 እኛ ክርስቲያኖችም እንድናከናውነው የተሰጠን ሥራ አለን። ይህ ሥራ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ‘መንግሥቱን እንዲያስቀድሙ’ አሳስቧል። (ማቴዎስ 6:33) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛ በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ነው። በአገልግሎታችን ላይ የአምላክን ቃል መጠቀም ሁለተኛው መንገድ ሲሆን ሦስተኛው መልካም ምግባር ማሳየት ነው። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ የሐዋርያት ሥራ 8:25፤ 1 ጴጥሮስ 2:12) በዚህ ክርስቲያናዊ ሥራ ውጤታማና ደስተኛ ለመሆን አስፈላጊ የሆኑ መሣሪያዎችን መያዝና እንዴት እንደምንጠቀምባቸው ማወቅ ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ የተወልን ሲሆን የእምነት ባልንጀሮቹ አርዓያውን እንዲከተሉ አበረታቷል። (1 ቆሮንቶስ 11:1፤ 15:10) ታዲያ ከአገልግሎት ባልደረባችን ከጳውሎስ ምን ልንማር እንችላለን?

ጳውሎስ ቀናተኛ የመንግሥቱ ሰባኪ ነበር

3. ሐዋርያው ጳውሎስ የመንግሥቱን ምሥራች በቅንዓት ሰብኳል ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

3 ጳውሎስ ምን ዓይነት ሠራተኛ ነበር? “ቀናተኛ” ሰባኪ እንደነበረ አያጠራጥርም። ጳውሎስ በሜዲትራኒያን አካባቢ ምሥራቹን በብዙ ቦታዎች ለማሰራጨት ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርጓል። ደከመኝ የማያውቀው ይህ ሐዋርያ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በግለት የሚያውጅበትን ምክንያት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ወንጌልን ብሰብክ እንኳ የምመካበት የለኝም፤ ግድ ደርሶብኝ ነውና፤ ወንጌልንም ባልሰብክ ወዮልኝ።” (1 ቆሮንቶስ 9:16) ጳውሎስ ምሥራቹን ይሰብክ የነበረው የራሱን ሕይወት ለማዳን ሲል ብቻ ነበር? በፍጹም። ራስ ወዳድ ሰው አልነበረም። ሌሎችም ምሥራቹን ሰምተው እንዲጠቀሙ ይፈልግ ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ይህን ሁሉ የማደርገው፣ ከወንጌል በረከት [ከሌሎች ጋር] እካፈል ዘንድ፣ ስለ ወንጌል ብዬ ነው።”​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:23 አ.መ.ት 

4. ክርስቲያኖች በአገልግሎታቸው በዋነኝነት የሚጠቀሙበት መሣሪያ ምንድን ነው?

4 ሐዋርያው ጳውሎስ አቅሙን የሚያውቅ ሰው ስለነበር በራሱ ችሎታ ብቻ መመካት እንደሌለበት ተገንዝቧል። አንድ አናጢ መዶሻ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጳውሎስም የአምላክን እውነት በአድማጮቹ ልብ ለመትከል ትክክለኛው መሣሪያ ያስፈልገው ነበር። በዋነኝነት የተጠቀመበት መሣሪያ ምንድን ነው? የአምላክ ቃል ነው። እኛም በተመሳሳይ ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የምንጠቀምበት ዋነኛው መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።

5. በአገልግሎታችን ውጤታማ ለመሆን ጥቅስ ከመጥቀስ በተጨማሪ ምን ማድረግ ያስፈልገናል?

5 ጳውሎስ በአምላክ ቃል በሚገባ መጠቀም ጥቅስ ከመጥቀስ የበለጠ ነገርን እንደሚጨምር ያውቅ ነበር። በአገልግሎቱ ላይ ሰዎችን ‘ያስረዳቸው’ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 28:23) እንዴት? ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን እውነት እንዲቀበሉ ለማሳመን በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ቃል በጥሩ ሁኔታ ተጠቅሟል። አሳማኝ ነጥቦችን እየጠቀሰ ያስረዳቸው ነበር። በኤፌሶን በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ “ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እየተነጋገረና እያስረዳቸው” ለሦስት ወራት ያህል ቆይቷል። አንዳንዶች ‘እልከኞች ሆነው ባያምኑም’ ሌሎች ግን አዳምጠውታል። ጳውሎስ በኤፌሶን ባከናወነው አገልግሎት የተነሳ “የጌታ ቃል በኃይል ያድግና ያሸንፍ ነበር።”​—⁠የሐዋርያት ሥራ 19:8, 9, 20

6, 7. ጳውሎስ አገልግሎቱን ያከበረው እንዴት ነው? እኛስ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

6 ጳውሎስ ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን ‘አገልግሎቱን አክብሯል።’ (ሮሜ 11:13) እንዴት? የራሱን ስም የማስጠራት ፍላጎት አልነበረውም፤ እንዲሁም ከአምላክ ጋር አብረው ከሚሠሩት መካከል እንደ አንዱ ሆኖ መቆጠሩ በሰው ፊት አላሳፈረውም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎቱን እንደ ታላቅ ክብር ተመልክቶታል። ጳውሎስ የአምላክን ቃል በዘዴና ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅሞበታል። በአገልግሎቱ ያገኘው ፍሬ ሌሎች አገልግሎታቸውን ይበልጥ በተሟላ መልኩ እንዲያከናውኑ አነሳስቷቸዋል። በዚህም መንገድ አገልግሎቱን አክብሯል።

7 እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ አዘውትረን በመጠቀም አገልግሎታችንን ልናከብር እንችላለን። በሁሉም የመስክ አገልግሎት ዘርፎች ስንካፈል በተቻለ መጠን ለበርካታ ሰዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች ላይ አንድ ቁም ነገር የማካፈል ግብ ሊኖረን ይገባል። በዚህ መንገድ ሰዎችን ማሳመን የምንችለው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እንመልከት:- (1) ሰዎች ለአምላክ ቃል አክብሮት እንዲያድርባቸው በሚያደርግ መንገድ በቃሉ መጠቀም። (2) ጥቅሱን ሊገባ በሚችል መንገድ ማብራራትና ከነጥቡ ጋር ማገናዘብ። (3) አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት።

8. በዛሬው ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት ለመስበክ በየትኞቹ መሣሪያዎች እንጠቀማለን? በእነዚህ መሣሪያዎች ምን ያህል ተጠቅመህባቸዋል?

8 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ጳውሎስ አገልግሎቱን በሚያከናውንበት ወቅት ያልነበሩት በርካታ መሣሪያዎች አሏቸው። ከእነዚህ መካከል መጻሕፍት፣ መጽሔቶች፣ ብሮሹሮች፣ የስብሰባ መጋበዣ ወረቀቶች፣ ትራክቶች እንዲሁም የቴፕና የቪዲዮ ክሮች ይገኙበታል። ባለፈው ክፍለ ዘመን መመሥከሪያ ካርዶች፣ የሸክላ ማጫወቻዎች፣ ድምፅ ማጉያ የተገጠመላቸው መኪናዎችና የሬዲዮ ስርጭቶች ጥቅም ላይ ውለው ነበር። እርግጥ ነው፣ ከሁሉም የላቀው መሣሪያችን መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ ይህን ወደር የማይገኝለት መሣሪያ በተገቢው መንገድ ጥሩ አድርገን ልንጠቀምበት ይገባናል።

አገልግሎታችን በአምላክ ቃል ላይ መመሥረት አለበት

9, 10. የአምላክን ቃል የምንጠቀምበትን መንገድ በተመለከተ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ከሰጠው ምክር ምን እንማራለን?

9 በአምላክ ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለአገልግሎት ባልደረባው ለጢሞቴዎስ “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር [“በትክክል የሚጠቀም፣” NW ] የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ” በማለት የሰጠውን ምክር በሥራ ላይ በማዋል ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ‘የእውነትን ቃል በትክክል መጠቀም’ ሲባል ምን ማለት ነው?

10 ‘በትክክል መጠቀም’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ፍቺው “ቀጥ አድርጎ መቁረጥ” ወይም “ቀጥ ያለ መስመር ማውጣት” የሚል ነው። ይህ ቃል በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ደብዳቤ ውስጥ ብቻ ነው። ይኸው ቃል በእርሻ ላይ ቀጥ ያለ ፈር እያወጡ ማረስን ለማመልከት ሊሠራበት ይችላል። አንድ ልምድ ያለው ገበሬ የተወለጋገደ ፈር እያወጣ ቢያርስ በሥራው ማፈሩ አይቀርም። ጢሞቴዎስ “የማያሳፍር ሠራተኛ” እንዲሆን በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኘው እውነተኛ ትምህርት ውልፍት ማለት እንደሌለበት ማሳሰቢያ ተሰጥቶት ነበር። የግል አመለካከቶቹ በትምህርቱ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ መፍቀድ አይኖርበትም። ስብከቱም ሆነ ትምህርቱ ሙሉ በሙሉ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ መሆን ነበረበት። (2 ጢሞቴዎስ 4:2-4) በዚህ መንገድ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች በዓለማዊ ፍልስፍና ፋንታ የይሖዋን አስተሳሰብ እንዲያዳብሩ መርዳት ይቻላል። (ቆላስይስ 2:4, 8) እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል።

መልካም ጠባይ ማሳየት አለብን

11, 12. የአምላክን ቃል በትክክል እንደምንጠቀም በጠባያችን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

11 የአምላክን ቃል በትክክል የምንጠቀመው በውስጡ የያዘውን እውነት በማወጅ ብቻ አይደለም። ጠባያችን ከቃሉ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። “[ከአምላክ] ጋር አብረን የምንሠራ” ስለሆንን ግብዝ ሠራተኞች መሆን አይኖርብንም። (1 ቆሮንቶስ 3:9) የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል:- “እንግዲህ አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን? ጣዖትን የምትጸየፍ ቤተ መቅደስን ትዘርፋለህን?” (ሮሜ 2:21, 22) እኛም የአምላክ የሥራ ባልደረቦች እንደመሆናችን መጠን “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” የሚለውን ማሳሰቢያ በሥራ ላይ በማዋል የአምላክን ቃል በትክክል መጠቀም እንችላለን።​—⁠ምሳሌ 3:5, 6

12 የአምላክን ቃል በትክክል መጠቀማችን ምን ውጤት ያስገኝልናል? በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እንዴት ሊለውጥ እንደሚችል እንመልከት።

የአምላክ ቃል ሰዎችን የመለወጥ ኃይል አለው

13. አንድ ሰው የአምላክን ቃል ተግባራዊ ማድረጉ በሕይወቱ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?

13 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት ሰዎች በሕይወታቸው ላይ አስደናቂ ለውጥ እንዲያደርጉ የሚረዳ ከፍተኛ ኃይል አለው። ይህ የሚሆነው ግን ሰዎች እምነት ሲጥሉበት ነው። ጳውሎስ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል የተመለከተ ሲሆን በጥንቷ ተሰሎንቄ ወደ ክርስትና እምነት በተለወጡ ሰዎች ላይ ያስከተለውን መልካም ውጤትም አይቷል። በመሆኑም እንዲህ ብሏቸዋል:- “የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፣ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፣ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን።” (1 ተሰሎንቄ 2:13) እነዚህ ክርስቲያኖችም ሆኑ ሌሎች እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች እዚህ ግባ የማይባለው የሰው እውቀት ወደር ከማይገኝለት የአምላክ ጥበብ ጋር ሊነጻጸር እንደማይችል ያውቃሉ። (ኢሳይያስ 55:9) የተሰሎንቄ ሰዎች “ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ ደስታ ጋር” የተቀበሉ ሲሆን ለሌሎች አማኞችም ምሳሌዎች ሆነዋል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 1:5-7

14, 15. በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው መልእክት ምን ያህል ኃይል አለው? ለምንስ?

14 የአምላክ ቃል ልክ እንደ ምንጩ እንደ ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል አለው። ያስጻፈው በቃሉ ‘ሰማያትን ያጸናው’ ‘ሕያው አምላክ’ ሲሆን ይህ ቃል ምንጊዜም ‘የተላከበትን ይፈጽማል።’ (ዕብራውያን 3:12፤ መዝሙር 33:6፤ ኢሳይያስ 55:11) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንዲህ ብለዋል:- “አምላክ ራሱን ከቃሉ አይነጥልም። ቃሉ የእርሱ ያልሆነ ይመስል ከእርሱ ጋር ያለውን ግንኙነት አያቋርጥም። . . . ስለሆነም ሕያው ከሆነው አምላክ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ምንም ነገር ቢፈጠር ያለቀለት ጉዳይ ነው በሚል ስሜት አምላክ እርግፍ አድርጎ አይተወውም።”

15 የአምላክ ቃል የያዘው መልእክት ምን ያህል ኃይል ያለው ነው? በጣም ከፍተኛ ኃይል አለው። በመሆኑም ጳውሎስ እንዲህ ሊል ችሏል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል።”​—⁠ዕብራውያን 4:12

16. የአምላክ ቃል አንድን ሰው ምን ያህል ሊለውጠው ይችላል?

16 በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል የያዘው መልእክት “ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው።” ስለሆነም ከማንኛውም ሰብዓዊ መሣሪያ የበለጠ ልብን ዘልቆ የመንካት ኃይል አለው። የአምላክ ቃል አንድን ሰው ውስጥ ድረስ ዘልቆ የመውጋት ኃይል ስላለው በአስተሳሰቡና በሚወደው ነገር ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ውስጣዊ ለውጥ እንዲያደርግ ሊገፋፋውና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቀናተኛ ሠራተኛ ሊያደርገው ይችላል። በእርግጥም ኃይለኛ መሣሪያ ነው!

17. የአምላክ ቃል ያለውን የመለወጥ ኃይል ግለጽ።

17 የአምላክ ቃል አንድ ሰው ስለ ራሱ ከሚያስበው ወይም ሌሎች ስለ እርሱ ከሚያውቁት በተለየ መልኩ ውስጣዊ ማንነቱ በግልጽ እንዲታይ ያደርጋል። (1 ሳ⁠ሙ​ኤል 16:7) አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሰው እንኳን መልካም ነገሮች በማድረግ ወይም ሃይማኖተኛ መስሎ በመታየት ውስጣዊ ማንነቱን ሊሸፍን ይችላል። መጥፎ ሰዎች የክፋት ዓላማቸውን ለማሳካት የማስመሰያ ጭምብል አድርገው ሊቀርቡ ይችላሉ። ትዕቢተኛ ሰዎች የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍ እየፈለጉም ትሑት መስለው ለመታየት ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ትሑት የሆነን ግለሰብ ውስጣዊ ማንነት በመግለጥ አሮጌውን ሰውነት እንዲያወልቅና “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” እንዲለብስ ይገፋፋዋል። (ኤፌሶን 4:22-24) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው ትምህርት ፍርሃት ያለባቸውን ሰዎች ደፋር የይሖዋ ምሥክርና ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሊያደርጋቸው ይችላል።​—⁠ኤርምያስ 1:6-9

18, 19. በአንቀጾቹ ውስጥ ከተጠቀሰው ወይም በመስክ አገልግሎት ካገኘኸው ተሞክሮ በመነሳት በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘው እውነት የአንድን ሰው አመለካከት እንዴት እንደሚለውጥ ተናገር።

18 የአምላክ ቃል ያለው የመለወጥ ኃይል በየትኛውም ሥፍራ በሚኖሩ ሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። ለምሳሌ ያህል፣ በፕኖም ፔን፣ ካምቦዲያ የሚገኙ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በወር ሁለት ጊዜ ወደ ካምፓን ቻም አውራጃ በመሄድ ያገለግሉ ነበር። አንዲት የአካባቢው ፓስተር ሌሎች ቀሳውስት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ክፉ ሲናገሩ ሰማችና ምሥክሮቹ በሚቀጥለው ጉብኝታቸው ሲመጡ ልታነጋግራቸው ሁኔታዎችን አመቻቸች። በዓላትን ማክበርን በሚመለከት በርካታ ጥያቄዎች ያቀረበችላቸው ሲሆን ከቅዱሳን ጽሑፎች ሲያስረዷት በጥሞና አዳመጠቻቸው። ከዚያም እንዲህ አለቻቸው:- “ሌሎቹ ቄሶች ስለ እናንተ የተናገሩት ሁሉ እውነት እንዳልሆነ አሁን ገባኝ! መጽሐፍ ቅዱስን አይጠቀሙም ብለውኝ ነበር፤ እናንተ ግን መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ነበር የተጠቀማችሁት!”

19 ይህቺ ሴት ከፓስተርነት እንደሚያወርዷት ማስፈራሪያ ቢሰነዝሩባትም በዚህ ሳትበገር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የምታደርገውን የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ገፋችበት። ለአንዲት ጓደኛዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንደጀመረች ስትገልጽላት እርሷም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ጓደኛዋ በምትማረው ነገር በጣም ከመነካቷ የተነሳ በምትሰበሰብበት ቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ላይ “ኑና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥኑ!” እስከ ማለት ደርሳ ነበር። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፓስተር የነበረችው ሴትና ሌሎች ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ።

20. በጋና የምትኖር የአንዲት ሴት ታሪክ የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል የሚያሳየው እንዴት ነው?

20 ፓውሊና የምትባል የአንዲት ጋናዊት ሴት ታሪክም የአምላክ ቃል ያለውን ኃይል በጉልህ ያሳያል። አንዲት የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ ሰባኪ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ፓውሊናን መጽሐፍ ቅዱስ ታስጠናት ነበር። a ባሏ ከእርሷ ሌላ ሚስት ስለነበረው ፓውሊና በትዳሯ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ እንዳለባት ተገነዘበች። ሆኖም ባሏና ዘመዶቿ በሙሉ አጥብቀው ተቃወሟት። የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የነበሩት አያቷ ማቴዎስ 19:4-6ን አጣምመው በመጥቀስ ሐሳቧን እንድትቀይር ሊያግባቧት ሞከሩ። አነጋገራቸው ትክክል ቢመስልም ፓውሊና ጥረታቸው ሰይጣን ኢየሱስ ክርስቶስን ለማሳሳት ቅዱሳን ጽሑፎችን እያጣመመ ይጠቅስ ከነበረበት ሁኔታ ጋር እንደሚመሳሰል ተገነዘበች። (ማቴዎስ 4:5-7) ኢየሱስ ትዳርን በሚመለከት የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ማለትም አምላክ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንጂ አንድ ወንድና ሁለት ሴቶች አድርጎ እንዳልፈጠራቸውና አንድ ሥጋ የሚሆኑት ሁለቱ እንጂ ሦስቱ እንዳልሆኑ አስታወሰች። በውሳኔዋ የጸናች ሲሆን በመጨረሻም በአካባቢው ልማድ መሠረት ከባሏ ተፋታች። ብዙም ሳይቆይ ተጠምቃ ደስተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ሆናለች።

ምንጊዜም በአምላክ ቃል በትክክል ተጠቀሙ

21, 22. (ሀ) የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች እንደመሆናችን ምን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን ይብራራል?

21 በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል ሌሎች ወደ ይሖዋ መቅረብ ይችሉ ዘንድ በሕይወታቸው ላይ ለውጥ እንዲያደርጉ ለመርዳት የምንጠቀምበት ከፍተኛ ኃይል ያለው መሣሪያ ነው። (ያዕቆብ 4:8) ጥሩ ችሎታ ያላቸው የእጅ ባለሙያዎች የተዋጣለት ሥራ ለመሥራት የተለያዩ መሣሪያዎች እንደሚጠቀሙ ሁሉ እኛም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እንድንሆን የተሰጠንን ተልእኮ ስንወጣ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ ለመጠቀም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

22 ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራችን ላይ ቅዱሳን ጽሑፎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የማሳመን ችሎታችንን በማዳበር ነው። የሚቀጥለው ርዕስ ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ማስተማርና መርዳት የሚቻልባቸውን መንገዶች ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ።

ታስታውሳለህ?

• የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

• ጳውሎስ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

• የአምላክን ቃል በትክክል መጠቀም ምን ነገሮችን ይጨምራል?

• በጽሑፍ የሰፈረው የይሖዋ ቃል ምን ያህል ኃይል አለው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች መንግሥቱን በማወጁ ሥራ ላይ ከሚጠቀሙባቸው መሣሪያዎች መካከል ጥቂቶቹ