በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፊትና አሁን—የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት መማሩ ለውጥ እንዲያደርግ ረዳው

በፊትና አሁን—የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት መማሩ ለውጥ እንዲያደርግ ረዳው

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል”

በፊትና አሁን—የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት መማሩ ለውጥ እንዲያደርግ ረዳው

አድሪያን ወጣት ሳለ ግልፍተኛና በቁጣ መደንፋት የሚቀናው ሰው ነበር። ከዚህም በላይ ይሰክር፣ ያጨስና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ሕይወት ይመራ ነበር። አድሪያን በሰዎች ዘንድ የሚታወቀው በዱርዬነቱ ሲሆን ሥርዓተ አልበኝነትን እንደሚደግፍ የሚያሳይ ንቅሳት ነበረው። በዚህ ዓይነት ሕይወት ስላሳለፋቸው ዓመታት ሲናገር እንዲህ ይላል:- “ፀጉሬን ፓንክ የሚባለውን ስታይል ከተቆረጥኩ በኋላ ተንጨፍሮ እንዲቆም ለማድረግ ኬሚካል እቀባለሁ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በቀይ ወይም በሌላ ዓይነት ቀለም አቀልመው ነበር።” አድሪያን አፍንጫውንም ተበስቶ ነበር።

አድሪያን ከጥቂት ዱርዬ ወጣቶች ጋር አንድ ያረጀ ቤት ውስጥ መኖር ጀመረ። እዚያም መጠጥ ይጠጡና አደገኛ ዕፅ ይወስዱ ነበር። “ስፒድ የተባለውን አደገኛ ዕፅ ቫሊየም ከሚባል መድኃኒትና ከሌላ ማንኛውም ዓይነት ዕፅ ጋር ቀላቅዬ ራሴን እወጋ ነበር” በማለት ይናገራል። “አደንዛዥ ዕፅ ወይም የማሸትተው ሙጫ ካጣሁ ከቆሙ መኪናዎች ላይ ቤንዚን በጎማ እስብና ያንን እያሸተትኩ እሰክር ነበር።” አድሪያን በሰዎች የሚፈራ ኃይለኛ የጎዳና ላይ ወንጀለኛ ሆነ። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በሩቁ ይሸሹት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህን ዝናውን የወደዱለት መጥፎ ሰዎች ይቀርቡት ጀመር።

ውሎ አድሮ አድሪያን “ጓደኞቹ” ከእሱ ጋር የተወዳጁት ለራሳቸው ጥቅም ብለው መሆኑን ተገነዘበ። ከዚህም በላይ “የግልፍተኝነት ባሕርዩና ዓመጸኝነቱ ምንም እንዳልፈየደለት” ተረዳ። የባዶነት ስሜት ተሰምቶትና ተበሳጭቶ ጓደኞቹን ተዋቸው። በአንድ የሕንፃ ግንባታ ቦታ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት አግኝቶ ሲያነብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው መልእክቱ ማረከውና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። አድሪያን “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” ለሚለው ግብዣ በደስታ ምላሽ ሰጠ። (ያዕቆብ 4:​8) ብዙም ሳይቆይ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል መጀመር እንዳለበት ተገነዘበ።

አድሪያን በየጊዜው የሚያገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቱ በሕሊናው ላይ በጎ ተጽዕኖ በማሳደር ሕይወቱን አዲስ አቅጣጫ አስያዘለት። ይህም ግልፍተኝነቱን እንዲቆጣጠርና ራሱን እንዲገዛ ረዳው። የአምላክ ቃል ላለው ኃይል ምስጋና ይግባውና የአድሪያን ባሕርይ በጣም ተለወጠ።​—ዕብራውያን 4:​12

ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ያህል ኃይል ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት ‘አዲሱን ሰው እንድንለብስ’ ይረዳናል። (ኤፌሶን 4:​24) አዎን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ትክክለኛ እውቀት በሥራ ላይ ስናውል ባሕርያችን ይለወጣል። ይሁንና እንዲህ ያለው እውቀት ሰዎችን የሚለውጠው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ልናስወግዳቸው የሚገባንን የማይፈለጉ ባሕርያት ለይቶ ይናገራል። (ምሳሌ 6:​16-19) ሁለተኛ፣ ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የሚያፈራቸውን ተፈላጊ ባሕርያት እንድናሳይ ያሳስቡናል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ይገኙበታል።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

አድሪያን አምላክ ያወጣቸውን መስፈርቶች በጥልቅ መረዳቱ ራሱን እንዲመረምርና ሊያዳብራቸው የሚያስፈልጉትንና ሊያስወግዳቸው የሚገቡትን ባሕርያት ለይቶ እንዲያውቅ ረድቶታል። (ያዕቆብ 1:​22-25) ይህ ግን የመጀመሪያ እርምጃ ብቻ ነበር። አድሪያን ከእውቀት በተጨማሪ ሕይወቱን እንዲለውጥ የሚገፋፋው ነገር ያስፈልገው ነበር።

አድሪያን ተፈላጊው አዲስ ባሕርይ “የፈጣሪውን መልክ እንዲመስል” ሆኖ የተቀረጸ መሆኑን ተረዳ። (ቆላስይስ 3:​10 አ.መ.ት ) የአንድ ክርስቲያን ባሕርይ ከአምላክ ባሕርይ ጋር መመሳሰል እንዳለበት ተገነዘበ። (ኤፌሶን 5:​1) አድሪያን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ አማካኝነት ይሖዋ ሰዎችን ስለሚይዝበት መንገድ የተማረ ሲሆን እንደ ፍቅር፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ምሕረትና ጽድቅ ያሉትን የአምላክን ጥሩ ጥሩ ባሕርያት አስተዋለ። እንዲህ ያለው እውቀት ለአምላክ ፍቅር እንዲያድርበትና ይሖዋ የሚወደው ዓይነት ሰው ለመሆን እንዲጣጣር አነሳሳው።​—ማቴዎስ 22:​37

አድሪያን ውሎ አድሮ በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ የግልፍተኝነት ባሕርይውን ለመቆጣጠር ቻለ። በአሁኑ ወቅት እሱና ሚስቱ ሌሎች ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት አማካኝነት ሕይወታቸውን እንዲለውጡ እየረዱ ነው። አድሪያን እንዲህ ይላል:- “በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ከሌሉት ከአብዛኞቹ የቀድሞ ጓደኞቼ በተቃራኒ እኔ በሕይወት ከመኖሬም በላይ አስደሳች የቤተሰብ ሕይወት መምራት ችያለሁ።” አድሪያን መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው የሚያሳይ ሕያው ማስረጃ ነው።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

‘የግልፍተኝነት ባሕርይና ዓመጸኝነት ምንም አልፈየዱለትም’

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያላቸው ኃይል

ቁጡና ዓመጸኛ የነበሩ ብዙ ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ ከረዷቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል:-

“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፣ ራሳችሁ አትበቀሉ፣ ለቁጣው ፈንታ ስጡ እንጂ።” (ሮሜ 12:​18, 19) በማን ላይና መቼ የበቀል እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ለአምላክ ተዉለት። አምላክ የሚበቀለው ስለ ሁኔታው ባለው የተሟላ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ስለሆነ ከእሱ የሚመጣ ቅጣት ሁሉ ፍጹም ፍትሑን የሚያን​ፀባርቅ ነው።

“ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፣ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት።” (ኤፌሶን 4:​26, 27) አንድ ሰው አልፎ አልፎ የሚያስቆጣ ጉዳይ ያጋጥመው ይሆናል። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ለረዥም ጊዜ ተቆጥቶ መቆየት የለበትም። ለምን? ምክንያቱም ቁጣው ለረዥም ጊዜ ከቆየ ‘ለዲያብሎስ ቦታ ስለሚሰጠው’ ክፉ ነገር ለማድረግ ሊነሳሳና በይሖዋ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል።

“ከንዴት ተቆጠብ፤ ቁጣንም ተወው፤ ወደ እኩይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ።” (መዝሙር 37:​8 አ.መ.ት ) ልጓም ያልተበጀለት ኃይለኛ ስሜት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ድርጊት ወደ መፈጸም ይመራል። አንድ ሰው ቁጣውን መቆጣጠር ካቃተው ሌሎችን የሚጎዳ ነገር መናገሩ ወይም ማድረጉ አይቀርም።