በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

አንድ ክርስቲያን ከተወለደበት ወር ጋር ይያያዛል ተብሎ የሚታሰብ የከበረ ድንጋይ ያለበት ቀለበት ወይም ጌጣጌጥ ማድረጉ ተገቢ ነው?

በአንዳንድ አገሮች የከበሩ ድንጋዮች አንድ ሰው ከተወለደበት ወር ጋር ይያያዛሉ ተብሎ ይታመናል። አንድ ክርስቲያን የከበረ ድንጋይ ያለበት ቀለበት ማድረግ አለማድረጉ ለግሉ የተተወ ውሳኔ ነው። (ገላትያ 6:5) ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ ግን አንዳንድ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል።

ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ከልደት ወር ጋር የሚያያዝ የከበረ ድንጋይ ማድረግ “መልካም እድል ወይም ጥሩ ጤንነት ያመጣል ተብሎ በሰፊው ይታመናል” ይላል። ይህ የማመሳከሪያ ጽሑፍ አክሎ እንዲህ ብሏል:- “ከረጅም ጊዜ አንስቶ ኮከብ ቆጣሪዎች አንዳንድ የከበሩ ድንጋዮች ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ኃይል አላቸው ብለው ያምኑ ነበር።”

በተለይ ደግሞ በጥንት ዘመናት ብዙ ሰዎች ከልደት ወር ጋር የሚያያዝ የከበረ ድንጋይ ማድረግ መልካም እድል ያስገኛል የሚል እምነት ነበራቸው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን እንዲህ ብሎ ማመን ይኖርበታል? በፍጹም። ይሖዋ እርሱን ትተው ‘እድል በተባለ ጣዖት’ የታመኑትን እንዳወገዛቸው ስለሚያውቅ እንዲህ ብሎ ማመን አይኖርበትም።​—⁠ኢሳይያስ 65:11

በመካከለኛው ዘመን ጠንቋዮች ለእያንዳንዱ ወር አንድ የከበረ ድንጋይ መርጠው ነበር። ከዚህም በላይ ሰዎች ከክፉ ነገር እንዲጠብቃቸው በሚል ከተወለዱበት ወር ጋር የሚዛመደውን የከበረ ድንጋይ እንዲያደርጉ ያበረታቱ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ጠንቋዮችን ስለሚያወግዝ ክርስቲያኖች በእነርሱ መመራታቸው ከቅዱስ ጽሑፉ አንጻር ተገቢ አይደለም።​—⁠ዘዳግም 18:9-12

በተጨማሪም ክርስቲያኖች አንድ ቀለበት ከተወለዱበት ወር ጋር የሚያያዝ የከበረ ድንጋይ ስላለው ብቻ ልዩ ትርጉም አለው ብለው ማሰባቸው ተገቢ አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች የልደት ቀናቸውን አያከብሩም። ይህ የሆነበት ምክንያት የልደት በዓላት ለግለሰቡ ከልክ ያለፈ ትኩረት እንዲሰጠው ስለሚያደርጉና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የልደት በዓላቸውን እንዳከበሩ የተጠቀሱት ሰዎች አምላክን የማያመልኩ ገዢዎች ስለሆኑ ነው።​—⁠ዘፍጥረት 40:20፤ ማቴዎስ 14:6-10

አንዳንድ ሰዎች ከልደት ወር ጋር የተያያዘ የከበረ ድንጋይ ያለበትን ቀለበት ማድረግ በባሕርይ ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ። እውነተኛ ክርስቲያኖች ግን ‘አዲሱን ሰውነት’ መልበስ የሚቻለው በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ እንደሆነ ስለሚያውቁ እንዲህ ዓይነት አመለካከት የላቸውም።​—⁠ኤፌሶን 4:22-24

ሌላው ሊታሰብበት የሚገባው ትልቁ ጉዳይ እንዲህ ዓይነቱን ቀለበት ለማድረግ የፈለግንበት ምክንያት ነው። አንድ ክርስቲያን ከተወለደበት ወር ጋር የሚያያዝ የከበረ ድንጋይ ያለበት ቀለበት ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ሲወስን እንዲህ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል:- ‘ከተወለድኩበት ወር ጋር ይያያዛል ተብሎ የሚታሰብ የከበረ ድንጋይ ያለበት ቀለበት ለማድረግ የፈለግኩት ድንጋዩን ስለወደድኩት ብቻ ነው? ወይስ አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ዓይነት የከበሩ ድንጋዮችን በሚመለከት ያላቸው አጉል እምነት ተጽዕኖ አሳድሮብኝ?’

አንድ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ቀለበት ለማድረግ የፈለገበትን ምክንያት ለማወቅ ልቡን መመርመር ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስ “አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፣ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና” ይላል። (ምሳሌ 4:23) እያንዳንዱ ክርስቲያን እንዲህ ዓይነቱን ቀለበት ለማድረግ የፈለገበትን ምክንያትና ቀለበቱን ማድረጉ በእርሱም ሆነ በሌሎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ውጤት በጥሞና ማሰቡ ተገቢ ነው።​—⁠ሮሜ 14:13