በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ”

“ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ”

“ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ”

“ለገዦችና ለባለ ሥልጣኖች የሚገዙና የሚታዘዙ፣ ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ፣ . . . እንዲሆኑ አሳስባቸው።” (ቲቶ 3:1) ሐዋርያው ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ለእምነት ባልረደቦቹ ሲጽፍ በአእምሮው ይዞት የነበረው በጎ ሥራ ምንድን ነው? ኧርነስት ስኮት የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንደሚከተለው ሲሉ አንዱን ዓይነት የበጎ ሥራ ዘርፍ አመልክተዋል:- “ክርስቲያኖች ለሥልጣን መታዘዝ ብቻ ሳይሆን ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ መሆን ነበረባቸው። . . . አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲከሰቱ ክርስቲያኖች ለኅብረተሰቡ አሳቢነት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ መሆን ይጠበቅባቸዋል። መልካም ዜጎች በሙሉ ጎረቤቶቻቸውን ለመርዳት እንዲረባረቡ የሚያስገድድ እሳት አደጋ፣ ወረርሽኝና የተለያዩ አደጋዎች በየጊዜው ይከታተላሉ።”

ክርስቲያኖች ከአምላክ ሕግ ጋር የሚጋጭ እስካልሆነ ድረስ ኅብረተሰቡን በሚጠቅሙ በአንዳንድ ሥራዎች ይካፈላሉ። (የሐዋርያት ሥራ 5:29) ለምሳሌ ያህል በጃፓን፣ ኤቢና የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የአካባቢው የእሳት አደጋ መከላከያ ብርጌድ የሚያወጣውን መመሪያ በመከተል ዓመታዊ የሆነ የእሳት አደጋ መከላከል ልምምድ ያደርጋል። እንዲህ ባሉት ወቅቶች ሁሉም የቤቴል ቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ተሰብስበው ከእሳት አደጋ መከላከያ ቢሮ የተላከው ተወካይ የሚሰጠውን ትምህርት ያዳምጣሉ።

በተጨማሪም ከአሥር ዓመታት በላይ ቅርንጫፍ ቢሮው የእሳት አደጋ መከላከል ግንዛቤን ለማስፋት በሚዘጋጀው ኤግዚብሽን ላይ ከከተማው ባለ ሥልጣናት ጋር ተባብሮ ሲሠራ ቆይቷል። በኤግዚብሽኑ ላይ በከተማው ያሉ ኩባንያዎችና የንግድ ድርጅቶች የእሳት አደጋን ለመከላከልና ለማጥፋት ምን ዝግጅት እንዳደረጉ ያሳያሉ። ቅርንጫፍ ቢሮው ሠራተኞቹ ባላቸው ችሎታና በሚያሳዩት ተባባሪነት ብዙ ጊዜ ለመሸለም በቅቷል። በ2001 ቢሮው በኤግዚብሽኑ ላይ አንደኛ በመውጣት ተሸልሟል። የእሳት አደጋ ቢነሳ ሕይወት አድን የሆነ በጎ ሥራ ለማከናወን ዝግጁ ናቸው።

ጠቃሚ አገልግሎት

ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ሕይወት አድን ሥራ መሥራት ያስደስታቸዋል። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለጎረቤቶቻቸው ለማካፈል አዘውትረው ከቤት ወደ ቤት ይሄዳሉ። (ማቴዎስ 24:14) ምሥክሮቹ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ አኗኗራቸው እንዲሻሻልና ወደፊት ደግሞ እውነተኛ ሰላምና ደህንነት በሚሰፍንበት ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓት እንዲማሩና በሕይወታቸው በሥራ እንዲያውሉ ያበረታታሉ።

አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት አገልግሎት ያለውን ጠቀሜታ ባለመገንዘብ ሰላም የሚነሱ አድርገው ይቆጥሯቸዋል። ይሁንና በካናዳ የኩቤክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ የሆኑት ዣን ክራፖ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለየ አመለካከት አላቸው። በዚያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በኩቤክ ግዛት በብላንቪል ከተማ ከቤት ወደ ቤት ለሚያከናውኑት አገልግሎት ፈቃድ እንዲያቀርቡ የሚጠይቀውን የከተማውን መተዳደሪያ ደንብ አልተቀበሉም። ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ ዳኛ ክራፖ እንዲህ ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ስብከት ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት ክርስቲያናዊ አገልግሎት ሲሆን . . . ምሥክሮቹ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች የሚያበረክቷቸው ጽሑፎች ሃይማኖትን፣ መጽሐፍ ቅዱስን፣ አደገኛ ዕፆችን፣ የአልኮል ሱሰኝነትን፣ ወጣቶችን ማስተማርን፣ የትዳር ችግሮችንና ፍቺን የሚመለከቱ ከፍተኛ ቁም ነገር ያላቸውን ርዕሶች የያዙ ናቸው።” ብያኔው በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ከጽሑፍ አዟሪዎች ተለይተው አይታዩም ማለት ከመሳደብ፣ የሌላውን ክብርና ስሜት ከመንካት እንዲሁም ስም ከማጥፋት እንደማይተናነስ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።”

የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ማሸነፍ እንዲችሉ በመርዳትና ከፊታችን ያለውን ተስፋ በመንገር ለኅብረተሰቡ ደህንነት አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሥራ ማከናወን እንዲችሉ ያስታጥቃቸዋል። “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

የይሖዋ ምሥክሮች “ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጁ” የሚሆኑት እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ማወቅ እንድትችል የሚሰጡህን እርዳታ እንድትቀበልና በአገርህም ሆነ በመላው ዓለም ከሚካሄደው ከዚህ ኅብረተሰቡን ከሚጠቅም አገልግሎት ተጠቃሚ እንድትሆን እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ከዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ጋር ተባብረው መሥራት ይፈልጋሉ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች ጎረቤቶቻቸውን በመርዳት የታወቁ ናቸው