በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ለይሖዋ ምንን እመልሳለሁ?”

“ለይሖዋ ምንን እመልሳለሁ?”

የሕይወት ታሪክ

“ለይሖዋ ምንን እመልሳለሁ?”

ማሪያ ከራሲኒስ እንደተናገረችው

የ18 ዓመት ልጅ እያለሁ ወላጆቼ አዝነውብኝ፣ ዘመዶቼ አግልለውኝ፣ የመንደራችን ነዋሪዎች ደግሞ መሳለቂያ አድርገውኝ ነበር። አምላክን በታማኝነት ማገልገሌን ለማስቆም አንዳንድ ጊዜ ይለማመጡኝ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኃይልና ማስፈራሪያ ይጠቀሙ ነበር። ይሁን እንጂ ሊሳካላቸው አልቻለም። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በጥብቅ መከተል መንፈሳዊ በረከት እንደሚያስገኝልኝ እርግጠኛ ነበርኩ። ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸውን ከ50 የሚበልጡ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ “ስላደረገልኝ ሁሉ [ለይሖዋ] ምንን እመልሳለሁ?” በማለት መዝሙራዊው የገለጸው ዓይነት ስሜት ይሰማኛል።—መዝሙር 116:12

የተወለድኩት በ1930 አንጌሎካስትሮ በምትባል መንደር ነበር። ይህ ቦታ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የእውነተኛ ክርስቲያኖች ጉባኤ ተቋቁሞ ከነበረባት ከቆሮንቶስ ልሳነ ምድር በስተ ምሥራቅ ከምትገኘው የክንክራኦስ ወደብ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል።—የሐዋርያት ሥራ 18:18፤ ሮሜ 16:1

የቤተሰባችን ሕይወት ሰላም የሰፈነበት ነበር። አባቴ የመንደሩ አለቃ ከመሆኑም ሌላ የተከበረ ሰው ነበር። ከአምስት ልጆች መካከል ሦስተኛ ስሆን ወላጆቼ ያሳደጉን የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አጥባቂ ተከታዮች እንድንሆን አድርገው ነው። እሁድ እሁድ ምንጊዜም ቤተ ክርስቲያን ሄጄ አስቀድሳለሁ። በምስሎች ፊት ኃጢአቴን እናዘዝ፣ ቤተ ክርስቲያን እየሄድኩ ሻማ አበራ እንዲሁም እጾም ነበር። ሳድግ ደግሞ የመመንኮስ ፍላጎት ነበረኝ። ከጊዜ በኋላ ግን ወላጆቼ ያዘኑብኝ የመጀመሪያዋ ልጅ ሆንኩ።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስሰማ ተደሰትኩ

አሥራ ስምንት ዓመት ገደማ ሲሆነኝ በአቅራቢያችን በሚገኝ መንደር የምትኖረው የእህቴ ባል እህት የሆነችው ካቲና የይሖዋ ምሥክሮችን ጽሑፍ እንደምታነብብና ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እንዳቆመች ሰማሁ። ጉዳዩ በጣም ስላሳሰበኝ ትክክለኛ መንገድ ነው ብዬ ወደማስበው አቅጣጫ እንድትመለስ እርሷን ለመርዳት ወሰንኩ። ስለዚህ እኛን ለመጠየቅ በመጣችበት ወቅት ወጣ ብለን ለመንሸራሸር ተቀጣጠርን፤ ይህንንም ያደረግሁት ቄሱ ቤት ስንደርስ ጎራ እንድንል ስላሰብኩ ነበር። ቄሱ ገና ከመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክሮች መናፍቃን እንደሆኑና ካቲናን እንዳሳሳቷት በመናገር የስድብ ቃላት አዥጎደጎደ። ውይይቱ ለሦስት ተከታታይ ምሽቶች ቀጠለ። ካቲና መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ማስረጃ በሚገባ ተዘጋጅታ እየመጣች ቄሱ የሚሰነዝረውን ነቀፋ በሙሉ ውድቅ አደረገችበት። መጨረሻ ላይ ቄሱ፣ መልከ ቀናና አስተዋይ ወጣት ስለሆነች በዚህ ዕድሜዋ መደሰት እንዳለባትና ስለ አምላክ ማሰብ ያለባት ስታረጅ እንደሆነ ነገራት።

ይህን ነገር ለወላጆቼ አልነገርኳቸውም፤ በሚቀጥለው እሁድ ግን ከቤተ ክርስቲያን ቀረሁ። እኩለ ቀን ላይ ቄሱ በቀጥታ ወደ ሱቃችን መጣ። ከቤተ ክርስቲያን የቀረሁት አባቴን ለመርዳት ሱቅ ውስጥ መሆን ስለነበረብኝ ነው ብዬ ሰበብ አቀረብኩ።

“በእርግጥ ምክንያቱ ይህ ነው ወይስ ያቺ ልጅ ሰበከችሽ?” ሲል ጠየቀኝ።

“የእነርሱ እምነት ከእኛ ይሻላል” ብዬ ፊት ለፊት መለስኩለት።

ቄሱ ወደ አባቴ ዞር ብሎ “አቶ ኢኮኖሞስ፣ ቤትህ ውስጥ ከባድ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ያቺ ዘመድህን አሁኑኑ አባርራት” አለው።

ቤተሰቦቼ ተነሱብኝ

ይህ የተከሰተው ግሪክ ከባድ በሆነ የእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ባለበት በ1940ዎቹ ማብቂያ ላይ ነበር። አባዬ ሽምቅ ተዋጊዎቹ አፍነው እንዳይወስዱኝ ስጋት ስላደረበት አካባቢውን ለቅቄ ካቲና በምትኖርበት መንደር ውስጥ ታላቅ እህቴ ጋር እንድቀመጥ ሁኔታዎችን አመቻቸ። እዚያ በቆየሁባቸው ሁለት ወራት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተማርኩ። የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምራቸው አብዛኞቹ መሠረተ ትምህርቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ እንደሌላቸው ሳውቅ አዘንኩ። አምላክ በምስሎች አማካኝነት የሚቀርብለትን አምልኮ እንደማይቀበል፣ መስቀልን እንደ ማምለክ የመሳሰሉ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ልማዶች ክርስቲያናዊ አመጣጥ እንደሌላቸውና አንድ ሰው አምላክን ማስደሰት ከፈለገ እርሱን ማምለክ ያለበት “በመንፈስና በእውነት” እንደሆነ ተማርኩ። (ዮሐንስ 4:23፤ ዘጸአት 20:4, 5) ከሁሉም በላይ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ብሩህ ተስፋ እንደሚሰጥ አወቅሁ! እነዚህን የመሳሰሉ ውድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ከይሖዋ ካገኘኋቸው ጥቅሞች መካከል የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

በዚህ መሃል እህቴና ባሏ ለምግብ ስቀርብ ማማተብ እንደተውኩና በሃይማኖታዊ ምስሎች ፊት መጸለይ እንዳቆምኩም አስተዋሉ። አንድ ቀን ማታ ተጋግዘው ስለደበደቡኝ በሚቀጥለው ቀን ከእነርሱ ቤት ወጥቼ ወደ አክስቴ ቤት ሄድኩ። የእህቴ ባል ጉዳዩን ለአባቴ የነገረው ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ አባቴ መጥቶ አስተሳሰቤን እንድለውጥ እያለቀሰ ለመነኝ። የእህቴ ባልም እግሬ ላይ ወድቆ ይቅርታ ጠየቀኝ፤ እኔም ይቅር አልኩት። ጉዳዩ በዚህ እንዲያበቃ ወደ ቀድሞ እምነቴ እንድመለስ ጠየቁኝ፤ ሆኖም በአቋሜ ጸናሁ።

ቤተሰቦቼ ወደሚኖሩበት መንደር ከተመለስኩ በኋላም የሚደርስብኝ ተጽዕኖ አላባራም። ከካቲና ጋር የተጠፋፋን ከመሆኑም በላይ መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌላ የማነብበው ጽሑፍ አልነበረኝም። የአክስቴ ልጅ እኔን ለመርዳት ያደረገችው ጥረት በጣም አስደሰተኝ። ወደ ቆሮንቶስ በሄደችበት ወቅት ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር ጋር ተገናኝታ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለውን መጽሐፍና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ አመጣችልኝ። እነዚህን መጻሕፍት ተደብቄ ማንበብ ጀመርኩ።

ሕይወቴ ባልታሰበ መንገድ ተለወጠ

የሚደርስብኝ ኃይለኛ ተቃውሞ ለሦስት ዓመታት ያህል ዘለቀ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የምገናኝበትም ሆነ ጽሑፍ ማግኘት የምችልበት መንገድ አልነበረም። ይሁን እንጂ እኔ የማውቀው ነገር ባይኖርም በሕይወቴ ከፍተኛ ለውጥ የሚከሰትበት ጊዜ እየተቃረበ ነበር።

አባዬ ተሰሎንቄ የሚኖረው አጎቴ ጋር እንድሄድ ነገረኝ። ወደ ተሰሎንቄ ከመሄዴ በፊት ኮት ለማሰፋት ቆሮንቶስ ውስጥ ወደሚገኝ ልብስ ሰፊ ሄድኩ። ካቲና እዚያ እንደምትሠራ ሳውቅ በደስታ ፈነደቅሁ! ከረጅም ጊዜ በኋላ በመገናኘታችን በጣም ተደሰትን። ከሱቁ እየወጣን ሳለ ከሥራ ወደ ቤቱ በቢስክሌት ይሄድ ከነበረ በጣም ደስ የሚል ወጣት ጋር ተገናኘን። ስሙ ካራላምበስ ይባላል። በደንብ ከተዋወቅን በኋላ ለመጋባት ተስማማን። በዚሁ ጊዜ ጥር 9, 1952 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በጥምቀት አሳየሁ።

ካራላምበስ ቀደም ሲል ተጠምቆ የነበረ ሲሆን እንደ እኔ የቤተሰብ ተቃውሞ ይደርስበት ነበር። ረዳት የጉባኤ አገልጋይ ከመሆኑም በላይ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች የሚመራ ቀናተኛ ክርስቲያን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ወንድሞቹ እውነትን የተቀበሉ ሲሆን በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ የቤተሰባቸው አባላት ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

አባዬ ካራላምበስን በጣም ስለወደደው በጋብቻው ተስማማ፤ እማዬ ግን በቀላሉ እሺ አላለችም። ያም ሆነ ይህ እኔና ካራላምበስ መጋቢት 29, 1952 ተጋባን። የጋብቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት ታላቅ ወንድሜና አንድ የአጎቴ ልጅ ብቻ ነበሩ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ካራላምበስ ልዩ በረከት ማለትም ከይሖዋ ያገኘሁት ውድ ስጦታ መሆኑን ተገነዘብኩ! ከእርሱ ጋር ስኖር ሕይወቴ በይሖዋ አገልግሎት እንዲጠመድ ማድረግ ችያለሁ።

ወንድሞቻችንን ማበረታታት

በ1953 እኔና ካራላምበስ ወደ አቴንስ ለመዛወር ወሰንን። ካራላምበስ በስብከቱ ሥራ የበለጠ ተሳትፎ ለማድረግ ስለፈለገ በቤተሰቡ ድርጅት ውስጥ መሥራቱን አቁሞ የግማሽ ቀን ሥራ ተቀጠረ። ሁልጊዜ ከሰዓት በኋላ አብረን እናገለግል እንዲሁም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንመራ ነበር።

የስብከት ሥራችን በመንግሥት ታግዶ ስለነበር ዘዴኞች መሆን ነበረብን። ለምሳሌ ያህል፣ አቴንስ መሃል በሚገኘው ባለቤቴ በሚሠራበት ሱቅ መስኮት ላይ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ለማስቀመጥ ወሰንን። ከፍተኛ ሥልጣን ያለው አንድ የፖሊስ መኮንን መጽሔቱ የታገደ መሆኑን ነገረን። ሆኖም አንድ ቅጂ ወስዶ ወደ ደህንነት ቢሮ በመሄድ ጉዳዩን ለማጣራት ፈለገ። መጽሔቱ ሕጋዊ መሆኑን ከገለጹለት በኋላ ተመልሶ መጥቶ ነገረን። ሱቅ ያላቸው ወንድሞች ይህን ሲሰሙ እነርሱም የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን የሱቃቸው መስኮት ላይ ማስቀመጥ ጀመሩ። ከሱቃችን መጠበቂያ ግንብ የወሰደ አንድ ሰው ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል።

ከዚህም በላይ ታናሽ ወንድሜ እውነትን ማወቁ አስደስቶናል። በንግድ መርከብ ኮሌጅ ለመማር አቴንስ መጥቶ እያለ ወደ አውራጃ ስብሰባ ይዘነው ሄድን። የአውራጃ ስብሰባ የምናደርገው ጫካ ውስጥ በድብቅ ነበር። በስብሰባው ላይ የቀረበውን ትምህርት የወደደው ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ በመርከብ መጓዝ ጀመረ። በአንድ ወቅት አርጀንቲና በሚገኝ ወደብ ላይ ቆመው እያሉ አንድ ሚስዮናዊ ምሥራቹን ለመስበክ መርከቡ ላይ ወጣ። ወንድሜም መጽሔቶች እንዲሰጠው ጠየቀው። በጻፈልን ደብዳቤ ላይ “እውነትን አግኝቻለሁ። የመጽሔት ኮንትራት መግባት እፈልጋለሁ” በማለቱ በጣም ተደሰትን። በዛሬው ጊዜ እርሱና ቤተሰቡ ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ናቸው።

በ1958 ባለቤቴ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ። ሥራችን በእገዳ ሥር በመሆኑና ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ ስለነበሩ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ከቦታ ቦታ ሲጓዙ አብዛኛውን ጊዜ ሚስቶቻቸውን ይዘው አይሄዱም። ጥቅምት 1959 በቅርንጫፍ ቢሮው የሚሠሩትን ኃላፊነት ያላቸውን ወንድሞች አብሬው መጓዝ እችል እንደሆነ ጠየቅናቸው፤ እነርሱም ፈቀዱልን። በማዕከላዊና በሰሜናዊ ግሪክ የሚገኙትን ጉባኤዎች እንድንጎበኝና እንድናበረታታ ተመደብን።

የምናደርገው ጉዞ በጣም አድካሚ ሲሆን ያን ያህል ጥርጊያ መንገድም አልነበረም። መኪና ስላልነበረን አብዛኛውን ጊዜ የምንጓዘው በሕዝብ ትራንስፖርት ወይም በጭነት መኪና ላይ ከዶሮና ከሌሎች ሸቀጦች ጋር ተጭነን ነበር። ጭቃማ መንገዶችን አቋርጠን መሄድ እንድንችል ቦት ጫማ እናደርጋለን። በእያንዳንዱ መንደር ሲቪል ሚሊሻ ስላለ እንዳንያዝ በሚል ወደ መንደሮች የምንገባው ከጨላለመ በኋላ ነበር።

ወንድሞች ለጉብኝቱ ከፍተኛ አድናቆት ነበራቸው። አብዛኞቹ በእርሻቸው ላይ ሲደክሙ ቢውሉም ማታ በተለያዩ ቤቶች በምናደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የቻሉትን ሁሉ ያደርጉ ነበር። ከዚህም በላይ ጥሩ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ነበራቸው፤ ኑሯቸው ዝቅተኛ ቢሆንም እንኳ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ አድርገውልናል። አንዳንድ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር በአጠቃላይ አንድ ክፍል ውስጥ እናድር ነበር። ከዚህ ሌላ ወንድሞች የሚያሳዩት እምነት፣ ጽናትና ቅንዓት በጣም ጠቅሞናል።

አገልግሎታችንን ማስፋት

የካቲት 1961 አቴንስ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ እየጎበኘን ሳለ በቤቴል ለማገልገል ፈቃደኛ እንደሆንን ተጠየቅን። እንደ ኢሳይያስ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” የሚል መልስ ሰጠን። (ኢሳይያስ 6:8) ከሁለት ወራት በኋላ ወዲያውኑ ወደ ቤቴል እንድንመጣ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን። ከዚያም ግንቦት 27, 1961 የቤቴል አገልግሎት ጀመርን።

አዲሱ የአገልግሎት ምድባችንን በጣም ወደድነው፤ እዚያ ካሉት ጋር ለመላመድም ጊዜ አልወሰደብንም። ባለቤቴ በአገልግሎትና በመጽሔት ኮንትራት ክፍል የተመደበ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ደግሞ የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ ለተወሰነ ጊዜ አገልግሏል። እኔ በቤቴል ቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን አከናውን ነበር። በወቅቱ የቤቴል ቤተሰብ አባላት 18 ቢሆኑም ለአምስት ዓመታት ያህል በቤቴል ለሽማግሌዎች ሥልጠና ይሰጥ ስለነበር ብዛታችን ወደ 40 ገደማ ነበር። በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ዕቃ አጥባለሁ፣ ወጥ ቤቱን እረዳለሁ፣ 12 አልጋዎች አነጥፋለሁ እንዲሁም የገበታ ጠረጴዛዎቹን ለምሳ አሰናዳለሁ። ከሰዓት በኋላ ልብስ እተኩሳለሁ እንዲሁም መጸዳጃ ቤቶቹንና መኖሪያ ክፍሎቹን አጸዳለሁ። በሳምንት አንድ ቀን ደግሞ በልብስ ማጠቢያ ክፍሉ ውስጥ እሠራለሁ። ሥራ ይበዛብኝ የነበረ ቢሆንም አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ ደስተኛ ነበርኩ።

ጊዜያችን በሙሉ በቤቴል ሥራችንና በመስክ አገልግሎት ተይዞ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ እስከ ሰባት የሚደርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንመራለን። ቅዳሜና እሁድ ካራላምበስ በተለያዩ ጉባኤዎች ንግግር ሲሰጥ አብሬው እሄዳለሁ፤ መቼም ቢሆን ተለያይተን አናውቅም።

ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበራቸውንና የቤተ ክርስቲያኑ የፀረ ኑፋቄ ቢሮ ኃላፊ ከሆኑት ቄስ ጋር የቅርብ ወዳጅነት የነበራቸውን አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠና ነበር። ቤታቸው ውስጥ ብዙ ምስሎች ያሉበት፣ ሁልጊዜ ዕጣን የሚጤስበትና ቀኑን ሙሉ በቴፕ መዝሙር የሚዘመርበት አንድ ክፍል ነበራቸው። ለተወሰነ ጊዜ እኛ ሐሙስ ሐሙስ ቤታቸው እየሄድን መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናቸው የነበረ ሲሆን ወዳጃቸው የሆኑት ቄስ ደግሞ ሁልጊዜ አርብ ይጠይቋቸው ነበር። አንድ ቀን አስገራሚ ጉዳይ ስለሚያሳዩን መምጣት እንዳለብን ነገሩን። ቤታቸው እንደደረስን በቀጥታ ወደዚያ ክፍል ወሰዱን። ምስሎቹን በሙሉ አስወግደው ክፍሉ ታድሶ አገኘነው። እነዚህ ባልና ሚስት ቀጣይ እድገት አድርገው በኋላም ተጠመቁ። በድምሩ ወደ 50 ገደማ የሚሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናናቸው ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው ሲጠመቁ በማየታችን ተደስተናል።

በመንፈስ ከተቀቡ ወንድሞች ጋር በቅርብ የመገናኘት አጋጣሚ በማግኘቴ እጅግ ተጠቅሜያለሁ። ወንድም ኖር፣ ፍራንዝና ሄንሸልን የመሳሰሉ የአስተዳደር አካል አባላት ካደረጉልን ጉብኝት ከፍተኛ ማበረታቻ አግኝተናል። ከ40 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላም በቤቴል ማገልገል ትልቅ ክብርና መብት እንደሆነ ይሰማኛል።

ባለቤቴን ማስታመምና የደረሰብኝን ሐዘን መቋቋም

በ1982 ባለቤቴ ኦልዛይመር በተባለ የማሰብ ችሎታን በሚያዳክም በሽታ መያዙን የሚያሳዩ ምልክቶች ይታዩበት ጀመር። በ1990 ጤንነቱ ከማሽቆልቆሉ የተነሳ ምንጊዜም አጠገቡ የሚሆን ሰው ያስፈልግ ነበር። በሕይወት በቆየባቸው የመጨረሻዎቹ ስምንት ዓመታት ፈጽሞ ከቤቴል ወጥተን መሄድ አልቻልንም። በቤቴል ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ብዙ አፍቃሪ ወንድሞች እንዲሁም ኃላፊነት ያላቸው የበላይ ተመልካቾች እኛን ለመርዳት የተለያዩ ዝግጅቶች አድርገውልናል። ደግነት የተሞላበት ድጋፍ ቢያደርጉልንም እንኳ እርሱን በመንከባከብ ቀንም ሆነ ማታ ብዙ ሰዓት አሳልፍ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች በጣም አስቸጋሪ ይሆናሉ፤ ሳልተኛ ያደርኩባቸው ብዙ ቀናት አሉ።

ሐምሌ 1998 ውዱ ባለቤቴ በሞት አንቀላፋ። እርሱን በማጣቴ በጣም ያዘንኩ ቢሆንም ይሖዋ እንደሚያስበው ማወቄ ያጽናናኛል። እንዲሁም ይሖዋ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ከሌሎች ሰዎች ጋር በትንሣኤ እንደሚያስነሣው አውቃለሁ።—ዮሐንስ 5:28, 29

ከይሖዋ ላገኘኋቸው በረከቶች አመስጋኝ ነኝ

ባለቤቴን በሞት ያጣሁ ቢሆንም እንኳ ብቻዬን አልቀረሁም። አሁንም በቤቴል እያገለገልኩ ሲሆን መላው የቤቴል ቤተሰብ ፍቅርና አሳቢነት ያሳየኛል። ከዚህም በላይ በመላው ግሪክ ያሉ መንፈሳዊ ወንድሞቼና እህቶቼ ቤተሰቦቼ ናቸው። ምንም እንኳ በአሁኑ ጊዜ ዕድሜዬ ከ70 ዓመት በላይ ቢሆንም በወጥ ቤቱና በመመገቢያ አዳራሹ ውስጥ ሙሉ ቀን እሠራለሁ።

በ1999 በኒው ዮርክ የሚገኘውን ዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት መጎብኘት በመቻሌ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ስመኘው የነበረው ነገር ተፈጽሞልኛል። የተሰማኝን ደስታ የምገልጽበት ቃል የለኝም፤ የሚያንጽና የማይረሳ ወቅት ነበር።

ያሳለፍኩትን ጊዜ መለስ ብዬ ሳስብ በሕይወቴ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዳደረግሁ ከልብ ይሰማኛል። አንድ ሰው ሊያከናውነው ከሚችለው ሥራ ሁሉ የላቀው ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ማገልገል ነው። ጎደለኝ የምለው አንድም ነገር የለም ብዬ በትምክህት መናገር እችላለሁ። ይሖዋ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ እኔና ባለቤቴን በፍቅር ተንከባክቦናል። ከራሴ ተሞክሮ በመነሳት “ስላደረገልኝ ሁሉ [ለይሖዋ] ምንን እመልሳለሁ?” በማለት መዝሙራዊው የጠየቀው ለምን እንደሆነ ይገባኛል።—መዝሙር 116:12

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ካራላምበስ የትም ቦታ የምንሄደው አብረን ነበር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ባለቤቴ በቤቴል ቢሮው ውስጥ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤቴል ማገልገል መቻሌን እንደ ታላቅ ክብር እቆጥረዋለሁ