በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አምላክን እንድታከብር አደረጋት

አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አምላክን እንድታከብር አደረጋት

የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት

አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አምላክን እንድታከብር አደረጋት

ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዳንዶች ከቅንዓትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 1:15) አንዳንድ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ስም ለማጉደፍ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ሳያውቁት ልበ ቅን የሆኑ ግለሰቦች ወደ እውነት እንዲመጡ አድርገዋል።

ኅዳር 1998፣ የቤቴልን ማለትም በሉቪዬ፣ ፈረንሳይ የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያሳይ ፊልም በፈረንሳይ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ቀርቦ ነበር። ፕሮግራሙን የተከታተሉ ሰዎች የተለያየ ምላሽ የሰጡ ቢሆንም ያልተጠበቁ መልካም ውጤቶች ተገኝተዋል።

ፕሮግራሙን ከተከታተሉት መካከል ከቤቴል 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትኖረው አና ፓውላ አንዷ ነች። ከባሏ ጋር ተፋትታ ከሁለት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ይህች ሴት ሥራ ፈላጊ ነበረች። ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ወደ ቤቴል ደውላ ሥራ ይቀጥሯት እንደሆነ ጠየቀች። “ቤቴል ጥሩ ቦታ እንደሆነና እዚያ የሚከናወነው ሥራ ጠቃሚ እንደሆነ ተሰማኝ” አለች። በቤቴል የሚሠሩት ሁሉ በነፃ የሚያገለግሉ ሰዎች መሆናቸውን ስታውቅ በጣም ተገረመች! ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በመጠኑ ከተወያዩ በኋላ አንዲት የይሖዋ ምሥክር መጥታ እንድታነጋግራት ተስማማች።

በአካባቢው በሚገኝ ጉባኤ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከሆነችው ከሊና ጋር ሰፊ ውይይት ያደረጉ ከመሆኑም በላይ አና ፓውላ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ወሰደች። a በሚቀጥለው ቀጠሯቸው ሲገናኙ አና ፓውላ መጽሐፉን ከዳር እስከ ዳር አንብባ ጨርሳ ነበር፤ በርካታ ጥያቄዎችም ነበሯት። መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናትም በደስታ ተስማማች። “መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴ የአምላክን ቃል የማወቅ አጋጣሚ ሰጥቶኛል። ከዚህ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ኖሮኝ አያውቅም” ብላለች።

አና ፓውላ በጥር ወር ቤቴልን ጎበኘች፤ በሚቀጥለው ሳምንት ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በክርስቲያናዊ ስብሰባ ላይ ተገኘች። ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናትና ለጓደኞቿ መመስከር ጀመረች። “የተማርኩትን ነገር ይዤ ዝም ማለት አልቻልኩም። የተማርኩትን እውነት ለሌሎች የማካፈልና እነርሱን የማጽናናት ፍላጎት ነበረኝ” ብላለች። የነበሩባትን በርካታ ችግሮች ታግላ ካሸነፈች በኋላ አዘውትራ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረች። ከዚያ በኋላ እድገት ማድረጓን በመቀጠል ግንቦት 5, 2002 ተጠመቀች።

ከዚህ በተጨማሪ አና ፓውላ ባሳየችው ግሩም ምሳሌና ቅንዓት የታከለበት ስብከት የተነሳ እናቷ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የጀመሩ ከመሆኑም በላይ በቅርቡ ተጠምቀዋል። አና ፓውላ እንዲህ ትላለች፦ “የሚሰማኝን ደስታ የምገልጽበት ቃላት ያጥረኛል። ይሖዋ እርሱን እንዳውቀውና እንዳገለግለው ስላስቻለኝ እንዲሁም ለሰጠኝ ስጦታዎች ሁሉ በየዕለቱ አመሰግነዋለሁ።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከላይ፦ አና ፓውላ

ከታች፦ በፈረንሳይ የሚገኘው የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃ መግቢያ