በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ለምንድን ነው?

ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ለምንድን ነው?

ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት ለምንድን ነው?

“በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኮሪያ የሚገኙት የፕሪስባይቴሪያን ሃይማኖት ተከታዮች በአሜሪካ ካሉት በአራት እጥፍ ያህል ይበልጣሉ።” ብዙ ሰዎች በኮሪያ ዋነኞቹ ሃይማኖቶች ኮንፊሽየስና ቡድሂዝም እንደሆኑ ስለሚያስቡ በኒውስዊክ መጽሔት ላይ የወጣው ይህ ዘገባ በርካታ አንባቢዎችን ያስገርም ይሆናል። ዛሬ፣ ኮሪያን የሚጎበኝ ሰው በአብዛኛው ቀይ መብራት ባላቸው መስቀሎቻቸው ተለይተው የሚታወቁ በጣም ብዙ “የክርስቲያን” አብያተ ክርስቲያናት ይመለከታል። እሁድ እሁድ ሰዎች ሁለት ወይም ሦስት ሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በእጃቸው ይዘው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ማየት የተለመደ ነው። በ1998 የተካሄደ ጥናት እንዳሳየው ወደ 30 በመቶ የሚሆኑ ኮሪያውያን ወይ የካቶሊክ አሊያም የፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያን አባል ናቸው። ይህም የክርስትና እምነት ተከታዮች ብዛት ቡድሂስት ነን ከሚሉት ሰዎች እንደሚበልጥ ያሳያል።

በዛሬው ጊዜ በየትኛውም ቦታ ቢሆን ይህን ያህል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አዘውትረው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ መመልከት ያልተለመደ ነገር ነው። ሆኖም በኮሪያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የእስያ አገሮች እንዲሁም በአፍሪካና በላቲን አሜሪካም ብዙዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። ለሃይማኖት ግዴለሽነትና ቸልተኝነት በጣም በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ብዙዎች አሁንም ቢሆን በአምላክ እንደሚያምኑ የሚናገሩት ለምንድን ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱትስ ለምንድን ነው?

በተወሰኑ ሰዎች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በኮሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከሚሄዱት ሰዎች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት እንደዚህ የሚያደርጉት የአእምሮ ሰላም ለማግኘት፣ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ከሞቱ በኋላ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት እንዲሁም አንድ አሥረኛ የሚሆኑት ጥሩ ጤንነት፣ ሀብትና ስኬት ለማግኘት ብለው ነው።

ቻይና ውስጥ ብዙዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት የኮሚኒስት አስተሳሰብ በካፒታሊዝም ላይ በተመሠረቱ ግቦች ቀስ በቀስ መተካቱ ያስከተለባቸውን መንፈሳዊ ባዶነት የሚያስወግድ ነገር ካገኘን ብለው ነው። በቻይና በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች ታትመው የሚሰራጩ ሲሆን ሰዎች የማኦን ቀይ መጽሐፍ ያነብቡ የነበረውን ያህል መጽሐፍ ቅዱስን ያነብባሉ።

በብራዚል የሚኖሩ አንዳንድ ካቶሊኮች በተለይም ወጣቱ ትውልድ ወደፊት አስደሳች ሕይወት ይመጣል የሚለው ተስፋ አያረካቸውም፤ ይህ ተስፋ አሁኑኑ እንዲፈጸምላቸው ይፈልጋሉ። ቱዱ የተባለው የዜና መጽሔት “በ1970ዎቹ ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሄዱ ይገፋፋቸው የነበረው ቤተ ክርስቲያን የምታራምደው የነፃነት መርሕ ከነበረ ዛሬ ደግሞ ብልጽግና የማግኘት ፍላጎት ነው” ብሏል። በብሪታንያ በተካሄደ አንድ ጥናት ላይ ምዕመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የሚያስደስታቸው ለምን እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። አብዛኞቹ ወዳጆች ስለሚያገኙ እንደሆነ ተናግረዋል።

እነዚህ ሐሳቦች እንደሚያሳዩት ዛሬም እንኳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በአምላክ የሚያምኑ ቢሆንም ብዙዎቹ ይበልጥ የሚያሳስባቸው የወደፊቱ ተስፋ ወይም ስለ አምላክ ማወቃቸው ሳይሆን አሁን የሚያገኙት ጥቅም ነው። በአምላክ ለማመን ሊያነሳሳን የሚገባው ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው ትላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? የሚቀጥለው ርዕስ መልሱን ይዟል።