በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የምታመሰግኑ ሁኑ”

“የምታመሰግኑ ሁኑ”

“የምታመሰግኑ ሁኑ”

“የክርስቶስ ሰላም በልባችሁ ይግዛ፤ የምታመሰግኑም ሁኑ።”ቆላስይስ 3:15

1. በክርስቲያን ጉባኤና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም መካከል ምን ዓይነት ልዩነት ይታያል?

 በዓለም ዙሪያ በሚገኙት 94,600 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የአመስጋኝነት መንፈስ ይታያል። እያንዳንዱ ስብሰባ የሚጀመረውም ሆነ የሚደመደመው ይሖዋን በጸሎት በማመስገን ነው። ወጣቶችና ጎልማሶች እንዲሁም አዲሶችና ለረጅም ጊዜ የቆዩ ምሥክሮች ለአምልኮም ሆነ አንድ ላይ ለመጫወት በሚገናኙበት ጊዜ “አመሰግናለሁ፣” “ምንም አይደለም” ወይም ተመሳሳይ አባባሎችን ሲናገሩ መስማት የተለመደ ነገር ነው። (መዝሙር 133:1) ይህ ‘ይሖዋን የማያውቁና ለወንጌል የማይታዘዙ’ ብዙ ሰዎች ከሚያሳዩት ራስ ወዳድነት ምንኛ የተለየ ነው! (2 ተሰሎንቄ 1:8) የምንኖረው ምስጋና ቢስ በሆነ ዓለም ውስጥ ነው። የዚህ ዓለም አምላክ ማን መሆኑን ስለምናውቅ ሁኔታው እንዲህ መሆኑ ብዙም አይደንቀንም። አዎን፣ ከማንም በላይ ራስ ወዳድነትን የሚያስፋፋው እንዲሁም የኩራትና የዓመፀኝነት ዝንባሌው በሰው ልጆች ኅብረተሰብ ላይ የሚንጸባረቀው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው!—ዮሐንስ 8:44፤ 2 ቆሮንቶስ 4:4፤ 1 ዮሐንስ 5:19

2. ለየትኛው ማስጠንቀቂያ ትኩረት መስጠት አለብን? የትኞቹን ጥያቄዎችስ እንመረምራለን?

2 በሰይጣን ዓለም የተከበብን በመሆናችን በዓለም ዝንባሌ ላለመበከል መጠንቀቅ ይኖርብናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል አሳስቧቸዋል:- “በዚህ ዓለም እንዳለው ኑሮ፣ በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደ ሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ፣ በፊት ተመላለሳችሁባቸው። በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፣ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፣ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቊጣ ልጆች ነበርን።” (ኤፌሶን 2:1-3) በዛሬው ጊዜም ብዙዎች እንዲህ ዓይነት መንፈስ ያንጸባርቃሉ። ታዲያ የአመስጋኝነት መንፈስ ይዘን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ምን ዓይነት እርዳታ ያደርግልናል? ከልብ አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?

አመስጋኝ እንድንሆን የሚገፋፉ ምክንያቶች

3. ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያደርጉን ነገሮች ምንድን ናቸው?

3 ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችንና ሕይወት ሰጪያችን በመሆኑ ልናመሰግነው ይገባል፤ በተለይ ደግሞ አትረፍርፎ ከሰጠን በርካታ ስጦታዎች አንዳንዶቹን ስናስብ እንደዚህ ለማድረግ እንገፋፋለን። (ያዕቆብ 1:17) በሕይወት መኖራችን ራሱ በየዕለቱ ይሖዋን እንድናመሰግነው ያደርገናል። (መዝሙር 36:9) እንደ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብትን የመሳሰሉ የይሖዋ እጅ ሥራ የሆኑ በርካታ ማስረጃዎችን በዙሪያችን እናያለን። በፕላኔታችን ላይ የሚገኙ ለሕይወት ጠቃሚ የሆኑ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ማዕድናት፣ በከባቢ አየር ውስጥ በተመጣጠነ ሁኔታ የሚገኙት አስፈላጊ ጋዞችና በግዑዙ ጽንፈ ዓለም ላይ የሚታዩት ውስብስብ ዑደቶች በሙሉ በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አምላካችን ባለዕዳ መሆናችንን ያሳያሉ። ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 40:5

4. በጉባኤያችን ውስጥ ላለው አስደሳች ወዳጅነት ይሖዋን ማመስገን ያለብን ለምንድን ነው?

4 የይሖዋ አገልጋዮች የሚኖሩት በምድራዊ ገነት ውስጥ ባይሆንም በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ በመሆናቸው ይደሰታሉ። በመንግሥት አዳራሽና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ የእምነት ባልደረቦቻችን የአምላክን መንፈስ ፍሬዎች ሲያንጸባርቁ እናያለን። በእርግጥም አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ሃይማኖት አናሳ ወይም ምንም ግንዛቤ ለሌላቸው ሰዎች በሚሰብኩበት ጊዜ ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ የተናገረውን ሐሳብ ይጠቅሳሉ። በመጀመሪያ “የሥጋ ሥራ” ተብለው የተዘረዘሩትን ነገሮች ካነበቡላቸው በኋላ ስለዚህ ጉዳይ ምን ያስተዋሉት ነገር እንዳለ ይጠይቋቸዋል። (ገላትያ 5:19-23) አብዛኞቹ ሰዎች የሥጋ ሥራ የተባሉት ነገሮች በዛሬው ጊዜ በኅብረተሰቡ መካከል በሰፊው የሚታዩ መሆናቸውን ለመናገር ማሰብ እንኳ አይጠይቅባቸውም። የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች የትኞቹ እንደሆኑ ሲነገራቸውና በአካባቢያቸው ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች መሰብሰቢያ አዳራሽ ሄደው ይህን በተጨባጭ እንዲመለከቱ ሲጋበዙ ብዙዎች “እግዚአብሔር በእርግጥ በመካከላችሁ ነው” በማለት ይናገራሉ። (1 ቆሮንቶስ 14:25 አ.መ.ት) ደግሞም ይህ በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ብቻ የሚታይ ነገር አይደለም። የትም ቦታ ሄዳችሁ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ከሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ከአንዱ ጋር ብትገናኙ ተመሳሳይ የሆነ ደስተኛ መንፈስ ታዩበታላችሁ። በእርግጥም እንዲህ የመሰለ የሚያንጽ ወዳጅነት ሊገኝ የቻለው በይሖዋ መንፈስ አማካኝነት ስለሆነ ይህ እርሱን ለማመስገን የሚገፋፋ ምክንያት ነው።—ሶፎንያስ 3:9፤ ኤፌሶን 3:20, 21

5, 6. ከሁሉ ለላቀው የአምላክ ስጦታ ማለትም ለቤዛው አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?

5 ይሖዋ የሰጠን ከሁሉ የላቀው ስጦታና ፍጹም በረከት ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበልን ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:11) አዎን፣ ለቤዛው ያለንን አመስጋኝነት የምንገልጸው ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አመስጋኝነት በመግለጽ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ፍቅር እንዳለን በሚያሳይ መንገድ በመኖርም ነው።—ማቴዎስ 22:37-39

6 ይሖዋ በጥንት ዘመን ለነበሩት እስራኤላውያን ያደረገላቸውን በመመርመር አመስጋኝ ስለመሆን ብዙ መማር እንችላለን። ይሖዋ በሙሴ በኩል ለብሔሩ በሰጠው ሕግ አማካኝነት ሕዝቡን ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል። ‘በሕጉም ካገኘነው እውቀትና እውነት የተነሳ’ ጳውሎስ “የምታመሰግኑ ሁኑ” ሲል የሰጠንን ምክር ለመከተል የሚረዳን ከፍተኛ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።—ሮሜ 2:19, 20፤ ቆላስይስ 3:15

ከሙሴ ሕግ የምንማራቸው ሦስት ነገሮች

7. አሥራት የማውጣት ዝግጅት እስራኤላውያን ለይሖዋ ያላቸውን አመስጋኝነት እንዲገልጹ አጋጣሚ የሰጣቸው እንዴት ነበር?

7 ይሖዋ፣ እስራኤላውያን እርሱ ላሳያቸው ደግነት ልባዊ አመስጋኝነት ማሳየት የሚችሉባቸውን ሦስት መንገዶች በሙሴ ሕግ ውስጥ አስፍሮላቸው ነበር። የመጀመሪያው አሥራት ማውጣት ሲሆን ምድሪቱ ከምታፈራው አንድ አሥረኛ እንዲሁም ‘ከበሬ፣ ከበግና ከፍየል ሁሉ ከአሥር አንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ’ መሆን ነበረበት። (ዘሌዋውያን 27:30-32) እስራኤላውያን ሕጉን ሲታዘዙ ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። “በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ፤ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፣ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈስስላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፣ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር።”—ሚልክያስ 3:10

8. ቁርባን ከአሥራት የሚለየው በምንድን ነው?

8 በሁለተኛ ደረጃ አሥራት ከማውጣት ግዴታ በተጨማሪ እስራኤላውያን ቁርባን (በፈቃደኝነት የሚደረግ መዋጮ) እንዲሰጡ ይሖዋ ዝግጅት አድርጎ ነበር። ለእስራኤላውያን እንዲህ ብሎ እንዲነግራቸው ሙሴን አዝዞታል:- “ወደማመጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ፣ እናንተ የምድሪቱን እንጀራ በበላችሁ ጊዜ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቁርባን ታደርጋላችሁ።” እስራኤላውያን መጀመሪያ ከሚያደርጉት “ሊጥ አንድ እንጐቻ” ‘ለእግዚአብሔር ቁርባን’ መስጠት ነበረባቸው። ከዚህ መጀመሪያ ከሚያስገቡት እህል ውስጥ የፈለጉትን ያህል ይዘው ይመጣሉ እንጂ የተወሰነ መጠን እንዲሰጡ አይጠበቅባቸውም ነበር። (ዘኍልቁ 15:18-21) ሆኖም እስራኤላውያን በምስጋና መልክ ቁርባን በሚያቀርቡበት ጊዜ ከይሖዋ በረከት እንደሚያገኙ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል። ሕዝቅኤል በራእይ ካየው ቤተ መቅደስ ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ዝግጅት ተጠቅሷል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “የበኩራቱ ሁሉ መጀመሪያ ከየዓይነቱ ከቁርባናችሁም ሁሉ የማንሣት ቁርባን ሁሉ ለካህናት ይሆናል፤ በቤታችሁም ውስጥ በረከት ያድር ዘንድ የዱቄታችሁን በኩራት ለካህናቱ ትሰጣላችሁ።”—ሕዝቅኤል 44:30

9. ይሖዋ ቃርሚያ የመተው ዝግጅት በማድረግ ምን ትምህርት ሰጥቷል?

9 በሦስተኛ ደረጃ ይሖዋ ቃርሚያ እንዲተዉ ዝግጅት አድርጓል። “የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ፣ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ። የወይንህንም ቃርሚያ አትቃርም፣ የወደቀውንም የወይንህን ፍሬ አትሰብስብ፤ ለድሆችና ለእንግዶች ተወው፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ” የሚል መመሪያ ሰጥቷቸዋል። (ዘሌዋውያን 19:9, 10) በዚህ ጊዜም ቢሆን የተወሰነ መጠን እንዲሰጡ አይጠበቅባቸውም ነበር። ለችግረኞች ምን ያህል እንደሚያስቀር የመወሰኑ ጉዳይ ለእያንዳንዱ እስራኤላዊ የተተወ ነበር። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ለድሀ ቸርነትን የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፣ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል” ሲል ሁኔታውን በትክክል ገልጿል። (ምሳሌ 19:17) በመሆኑም ይሖዋ ችግረኛ ለሆኑ ሰዎች ርኅራኄና አሳቢነት እንዲያሳዩ አስተምሯቸዋል።

10. እስራኤላውያን አመስጋኝ ሳይሆኑ መቅረታቸው ምን አስከትሎባቸዋል?

10 ይሖዋ እስራኤላውያን በታዛዥነት አሥራት በማውጣታቸው፣ ቁርባን በመስጠታቸውና ለድሆች እርዳታ በመለገሳቸው ባርኳቸዋል። ሆኖም እስራኤላውያን አመስጋኝ ሳይሆኑ በቀሩበት ጊዜ የይሖዋን ሞገስ አጥተዋል። ይህም ለውድቀትና በመጨረሻም ለስደት ዳርጓቸዋል። (2 ዜና መዋዕል 36:17-21) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው?

አመስጋኝነታችንን የምንገልጽባቸው መንገዶች

11. ለይሖዋ አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ ምንድን ነው?

11 እኛም በተመሳሳይ ለይሖዋ ውዳሴ የምናቀርብበትና አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት ዋናው መንገድ “መሥዋዕት” ማቅረብ ነው። እርግጥ፣ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን በሙሴ ሕግ ሥር አይደለንም። በመሆኑም የእንስሳትና የእህል መሥዋዕት የማቅረብ ግዴታ የለብንም። (ቆላስይስ 2:14) ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ የዕብራውያን ክርስቲያኖችን “ዘወትር ለእግዚአብሔር የምሥጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት” ሲል አሳስቧቸዋል። (ዕብራውያን 13:15) ለሕዝብ በምንሰጠው አገልግሎትም ሆነ ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር “በማኅበር” ችሎታችንንና ሀብታችንን ተጠቅመን በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ለይሖዋ አምላክ ልባዊ የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብ እንችላለን። (መዝሙር 26:12) በዚህ ረገድ እስራኤላውያን አመስጋኝነታቸውን ለይሖዋ ይገልጹባቸው ከነበሩት መንገዶች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

12. ክርስቲያናዊ ኃላፊነታችንን በተመለከተ አሥራት ከማውጣት ዝግጅት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

12 በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቀደም ሲል እንዳየነው አሥራት የማውጣት ዝግጅት ለምርጫ የተተወ አልነበረም። በዚህ ረገድ እያንዳንዱ እስራኤላዊ ግዴታ ተጥሎበት ነበር። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን በአገልግሎት የመሳተፍና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት ኃላፊነት አለብን። እነዚህ የአምልኮ ዘርፎች ለምርጫ የተተዉ አይደሉም። ኢየሱስ የፍጻሜውን ዘመን በተመለከተ በተናገረው ታላቅ ትንቢት ላይ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል በግልጽ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ለፍቅርና ለመልካምም ሥራ እንድንነቃቃ እርስ በርሳችን እንተያይ፤ በአንዳንዶችም ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው፣ መሰብሰባችንን አንተው እርስ በርሳችን እንመካከር እንጂ፤ ይልቁንም ቀኑ ሲቀርብ እያያችሁ አብልጣችሁ ይህን አድርጉ።” (ዕብራውያን 10:24, 25) እንድንሰብክና እንድናስተምር እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከወንድሞቻችን ጋር አዘውትረን እንድንሰበሰብ የተሰጠንን ኃላፊነት እንደ መብትና ክብር ቆጥረን በደስታ ስንወጣው ለይሖዋ ያለንን አመስጋኝነት እናሳያለን።

13. ከቁርባንና ከቃርሚያ ምን ትምህርት እናገኛለን?

13 ከዚህ በተጨማሪ ለእስራኤላውያን የአድናቆታቸው መግለጫ የነበሩትን ቁርባንንና ቃርሚያን በመመርመር ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እንደ ግዴታ ከሚታየውና የተወሰነ መጠን ካለው የአሥራት ክፍያ በተለየ ቁርባንና ቃርሚያ የተወሰነ መጠን መስጠትን አያስገድዱም። ከዚህ ይልቅ እነዚህ ዝግጅቶች አንድ የይሖዋ አገልጋይ በልቡ ያለው ጥልቅ አድናቆት እንዳነሳሳው እንዲለግስ አጋጣሚ ይሰጡታል። በተመሳሳይ መንገድ በአገልግሎት መሳተፍና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እያንዳንዱ የይሖዋ አገልጋይ ያለበት መሠረታዊ ግዴታ እንደሆነ እንገነዘባለን። ሆኖም በዚህ ረገድ የምናደርገው ተሳትፎ በሙሉ ልብና በፈቃደኝነት መንፈስ የሚደረግ ነው? ይሖዋ ላደረገልን ነገር ሁሉ የተሰማንን ልባዊ አድናቆት ለመግለጽ እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን እንመለከታቸዋለን? ሁኔታችን በሚፈቅድልን መጠን በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ እናደርጋለን? ወይስ ልንወጣው የሚገባ ግዴታ እንደሆነ አድርገን ብቻ ነው የምንመለከተው? እነዚህ ጥያቄዎች በግላችን መልስ ልንሰጥባቸው የሚገቡ እንደሆነ የታወቀ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሁኔታውን እንዲህ ሲል ገልጿል:- “እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፣ ከዚያም በኋላ ስለ ሌላው ሰው ያልሆነ ስለ ራሱ ብቻ የሚመካበትን ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

14. ይሖዋ ለእርሱ የምናቀርበውን አገልግሎት በተመለከተ ምን ይጠብቅብናል?

14 ይሖዋ አምላክ ሁኔታችንን በሚገባ ያውቃል። ያሉብንን የአቅም ገደቦች ይገነዘባል። ትልቅም ሆነ ትንሽ አገልጋዮቹ በፈቃደኝነት የሚያቀርቧቸውን መሥዋዕቶች ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ሁላችንም ተመሳሳይ መጠን እንድንሰጥ አይጠብቅብንም፤ እኛም እንደዚያ ማድረግ አንችልም። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ገንዘብ መዋጮ በተናገረበት ጊዜ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም” ብሏቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 8:12) ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት በተመለከተም የዚያኑ ያህል ተፈጻሚነት አለው። አገልግሎታችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችለው መጠኑ ሳይሆን የምናከናውንበት መንገድ ነው። በደስታና በሙሉ ነፍስ መከናወን ይኖርበታል።—መዝሙር 100:1-5፤ ቆላስይስ 3:23

የአቅኚነት መንፈስ ይኑራችሁ

15, 16. (ሀ) በአቅኚነት አገልግሎትና አመስጋኝ በመሆን መካከል ምን ዝምድና አለ? (ለ) አቅኚ መሆን የማይችሉ አስፋፊዎች የአቅኚነት መንፈስ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ለይሖዋ አመስጋኝነታችንን መግለጽ የምንችልበት መንገድ ከመሆኑም ሌላ ከፍተኛ ደስታና እርካታ ያስገኝልናል። ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ በርካታ አገልጋዮች ይሖዋ ባሳያቸው ፍቅር በመነሳሳትና ይገባናል ለማንለው ደግነቱ ባደረባቸው አመስጋኝነት የተነሳ ይሖዋን ከበፊቱ የበለጠ ለማገልገል በሕይወታቸው ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አድርገዋል። አንዳንዶች ምሥራቹን በመስበክና ለሰዎች እውነትን በማስተማር በየወሩ በአማካይ 70 ሰዓት በማሳለፍ የዘወትር አቅኚ ሆነው ማገልገል ችለዋል። ሁኔታቸው የማይፈቅድላቸው ደግሞ አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ በመሆን በስብከቱ ሥራ በወር 50 ሰዓት ለማሳለፍ ሁኔታቸውን ያመቻቻሉ።

16 ይሁንና የዘወትርም ሆነ ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል ስለማይችሉ በርካታ የይሖዋ አገልጋዮችስ ምን ማለት ይቻላል? የአቅኚነት መንፈስ በማዳበርና ይህንን መንፈስ ይዘው በመቀጠል አመስጋኝነታቸውን ማሳየት ይችላሉ። እንዴት? አቅኚ ሆነው የሚያገለግሉትን በማበረታታት፣ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ግብ በመቅረጽ እንዲሁም ሁኔታቸው በሚፈቅድላቸው መጠን በስብከቱ ሥራ በትጋት በመካፈል ነው። በአገልግሎት የምናደርገው ተሳትፎ በአብዛኛው የሚመካው ይሖዋ ላደረገልን፣ እያደረገልን ላለውና ወደፊት ለሚያደርግልን ነገር ባለን የአድናቆት ጥልቀት ላይ ነው።

‘በሀብታችን’ አመስጋኝነታችንን ማሳየት

17, 18. (ሀ) ‘በሀብታችን’ አመስጋኝነታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ መበለቲቱ የሰጠችውን መዋጮ በተመለከተ ምን ብሏል? ለምንስ?

17 ምሳሌ 3:9 “እግዚአብሔርን ከሀብትህ አክብር፣ ከፍሬህም ሁሉ በኩራት” ይላል። በአሁኑ ጊዜ ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች አሥራት እንዲያወጡ አይጠበቅባቸውም። ከዚህ ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔር በደስታ የሚሰጠውን ይወዳልና እያንዳንዱ በልቡ እንዳሰበ ይስጥ፣ በኀዘን ወይም በግድ አይደለም።” (2 ቆሮንቶስ 9:7) ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለመደገፍ መዋጮ መስጠትም አመስጋኝነታችንን ያሳያል። ልባችን በአድናቆት ከተሞላ ይህን አዘውትረን እንድናደርግ ያነሳሳናል። የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ያደርጉ እንደነበረው በየሳምንቱ የተወሰነ ገንዘብ በማስቀመጥ መዋጮ መስጠት እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 16:1, 2

18 ለይሖዋ ያለን አመስጋኝነት የሚታየው በምንሰጠው መዋጮ መጠን ሳይሆን እንድንሰጥ ባነሳሳን መንፈስ ነው። ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚገኙት የመዋጮ ሣጥኖች ሰዎች ገንዘብ ሲከቱ በተመለከተበት ወቅት ይህን አስተውሏል። ኢየሱስ አንዲት ድሀ መበለት “ሁለት ሳንቲም” ስትጥል አያትና እንዲህ አለ:- “እውነት እላችኋለሁ፣ ይህች ድሀ መበለት ከሁሉ ይልቅ አብልጣ ጣለች፤ እነዚህ ሁሉ ከትርፋቸው ወደ እግዚአብሔር መዝገብ ጥለዋልና፤ ይህች ግን ከጒድለትዋ የነበራትን ትዳርዋን ሁሉ ጣለች።”—ሉቃስ 21:1-4

19. አመስጋኝነታችንን የምናሳይባቸውን መንገዶች በድጋሚ ማጤናችን ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

19 አመስጋኝነታችንን እንዴት መግለጽ እንደምንችል የተመለከትንበት ይህ ጥናት በዚህ ረገድ የምናደርገውን ተሳትፎ በድጋሚ እንድናጤን የሚያነሳሳን ይሁን። ለይሖዋ የምናቀርበውን የምስጋና መሥዋዕትም ሆነ ለዓለም አቀፉ ሥራ የምንሰጠውን ቁሳዊ ድጋፍ መጨመር እንችል ይሆን? እንዲህ ባደረግን መጠን ለጋስ የሆነው አፍቃሪ አባታችን ይሖዋ አመስጋኞች በመሆናችን ምክንያት በጣም እንደሚደሰት እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ታስታውሳለህ?

• ይሖዋን እንድናመሰግን የሚያነሳሱን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

• ከአሥራት፣ ከቁርባንና ከቃርሚያ የምናገኛቸው ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

• የአቅኚነት መንፈስ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?

• ‘ሀብታችንን’ ይሖዋን ለማመስገን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው”

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዚህ ጥናት ላይ የተጠቀሱት ከሕጉ የምንማራቸው ሦስት ነገሮች ምንድን ናቸው?

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምን ዓይነት መሥዋዕቶች ማቅረብ እንችላለን?