በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሩሳሌም በተከበበችበትና በጠፋችበት ወቅት ሕዝቅኤል “ዲዳ” ሆኖ የነበረው በምን መልኩ ነው?

ቀደም ሲል ባስተላለፈው የይሖዋ ትንቢታዊ መልእክት ላይ የሚጨምረው ነገር ስላልነበረው እንደ ዲዳ ሆኖ ነበር ማለት ይቻላል።

ነቢዩ ሕዝቅኤል በባቢሎን በግዞት ለነበሩት እስራኤላውያን ታማኝ ጉበኛ ሆኖ ማገልገል የጀመረው “ንጉሡ ዮአኪን በተማረከ በአምስተኛው ዓመት” ማለትም በ613 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። (ሕዝቅኤል 1:2, 3) በ609 ከክርስቶስ ልደት በፊት በአሥረኛው የጨረቃ ወር፣ ከወሩም በአሥረኛው ቀን ባቢሎናውያን በኢየሩሳሌም ላይ ከበባ እንደጀመሩ አምላክ በመንፈስ ለሕዝቅኤል ነገረው። (ሕዝቅኤል 24:1, 2) ከበባው ምን ያስከትል ይሆን? ኢየሩሳሌምና እምነት የለሾቹ ነዋሪዎቿ ከጥፋት ይተርፉ ይሆን? ጉበኛው ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ የነገረውንና ያለጥርጥር የሚፈጸመውን የጥፋት መልእክት አስቀድሞ ተናግሯል፤ በመሆኑም መልእክቱ ይበልጥ አሳማኝ እንዲሆን ለማድረግ ተጨማሪ ነገር መናገር አያስፈልገውም። ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን ከበባ በተመለከተ ምንም የሚያክለው ነገር ስላልነበረ እንደ ዲዳ ሆኖ ነበር።—ሕዝቅኤል 24:25-27

ኢየሩሳሌም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከጠፋች ከስድስት ወራት በኋላ ከዚያ አምልጦ የመጣ ሰው ቅድስቲቱ ከተማ ባድማ እንደሆነች በባቢሎን ለነበረው ለሕዝቅኤል ነገረው። ይህ ሰው ከመምጣቱ በፊት በነበረው ምሽት ይሖዋ ‘የሕዝቅኤልን አፍ ከፈተው፤ ከዚያም በኋላ ዲዳ አልሆነም።’ (ሕዝቅኤል 33:22) ሕዝቅኤል ዲዳ መሆኑ በዚያን ጊዜ አበቃ።

ሕዝቅኤል ዲዳ የሆነው ቃል በቃል ነበር? ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው አልነበረም፤ ምክንያቱም “ዲዳ” ከሆነም በኋላ እንኳ በኢየሩሳሌም መውደቅ በተደሰቱት በአካባቢው በነበሩት መንግሥታት ላይ ትንቢት ተናግሯል። (ሕዝቅኤል ምዕራፍ 25-32) ሕዝቅኤል ነቢይና ጉበኛ ሆኖ ቀደም ሲል ባከናወነው አገልግሎት ወቅት ይሖዋ እንዲህ ብሎት ነበር:- “እኔም ምላስህን ከትናጋህ ጋር አጣብቃታለሁ አንተም ዲዳ ትሆናለህ፣ እነርሱም ዓመፀኛ ቤት ናቸውና የሚዘልፍ ሰው አትሆንባቸውም። ነገር ግን በተናገርሁህ ጊዜ አፍህን እከፍታለሁ።” (ሕዝቅኤል 3:26, 27) ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሚልከው ተጨማሪ መልእክት ባለመኖሩ ሕዝቅኤል ለዚህ ብሔር የሚናገረው ነገር አልነበረም። የሕዝቅኤል ተልእኮ ይሖዋ እንዲናገር የሰጠውን መልእክት ይሖዋ በፈለገው ጊዜ መናገር ነበር። ሕዝቅኤል ዲዳ መሆኑ ለእስራኤላውያን ትንቢታዊ መልእክት በማስተላለፍ ረገድ ምንም የሚናገረው ነገር እንደሌለ ያመለክታል።

ዘመናዊው የጉበኛ ክፍል ማለትም በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች የኢየሩሳሌም አምሳያ የሆነችው ሕዝበ ክርስትና እንደምትጠፋ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ‘ታላቁ መከራ’ ሲጀምርና የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችውን ‘ታላቂቱ ባቢሎንን’ ድምጥማጧን ሲያጠፋት የሕዝቅኤል ክፍል የሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሐሰት ሃይማኖት ዋና ክፍል ስለሆነችው ስለ ሕዝበ ክርስትና ውድቀት ምንም ተጨማሪ ነገር መናገር አያስፈልጋቸውም።—ማቴዎስ 24:21፤ ራእይ 17:1, 2, 5

አዎን፣ በመንፈስ የተቀቡት ቀሪዎችና ተባባሪዎቻቸው ለሕዝበ ክርስትና የሚናገሩት ተጨማሪ ነገር ስለማይኖር ዲዳ የሚሆኑበት ጊዜ ይመጣል። ይህም የሚሆነው ‘አሥሩ ቀንዶች’ እና “አውሬው” ታላቂቱ ባቢሎንን በሚያጠፏትና ራቁቷን በሚያደርጓት ጊዜ ነው። (ራእይ 17:16) እርግጥ ነው፣ ይህ ማለት ክርስቲያኖች ቃል በቃል ዲዳ ይሆናሉ ማለት አይደለም። አሁንም እያደረጉ እንዳሉት ያን ጊዜም ይሖዋን ያወድሳሉ እንዲሁም ስለ እርሱ በየዕለቱና “ለልጅ ልጅ ሁሉ” ይናገራሉ።—መዝሙር 45:17፤ 145:2