በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅታችሁ ኑሩ

ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅታችሁ ኑሩ

ለይሖዋ ቀን ተዘጋጅታችሁ ኑሩ

“ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፣ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና።”—⁠ማቴዎስ 24:44

1. የይሖዋን ቀን በትኩረት ልንጠባበቀው የሚገባን ለምንድን ነው?

 አስፈሪው የይሖዋ ቀን የጦርነትና የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የጨለማና የመጥፋት ቀን ይሆናል። በኖኅ ዘመን የነበረው ክፉ ዓለም በጥፋት ውኃ ተጠራርጎ እንደጠፋ ሁሉ “ታላቁና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን” ይህን ክፉ ሥርዓት ለማጥፋት መምጣቱ አይቀርም። አዎን፣ እንደሚመጣ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም “የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW ] ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል።” (ኢዩኤል 2:30-32፤ አሞጽ 5:18-20) አምላክ ጠላቶቹን አጥፍቶ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል። የጊዜውን አጣዳፊነት የተገነዘበው ነቢዩ ሶፎንያስ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል።” (ሶፎንያስ 1:14) ታዲያ ይህ መለኮታዊ ፍርድ የሚፈጸመው መቼ ነው?

2, 3. የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:36) የይሖዋ ቀን የሚመጣበትን ትክክለኛ ሰዓት ስለማናውቅ “ንቁ . . . ተዘጋጅታችሁ ኑሩ” የሚለው የ2004 የዓመት ጥቅሳችን የያዘውን ምክር ተግባራዊ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:42, 44

3 ኢየሱስ ዝግጁ ሆነው የጠበቁት እንደሚወሰዱ ማለትም እንደሚድኑ ሌሎች ግን እንደሚጠፉ ሲጠቁም እንዲህ ብሏል:- “በዚያን ጊዜ ሁለት ሰዎች በእርሻ ይሆናሉ፤ አንዱ ይወሰዳል አንዱም ይቀራል፤ ሁለት ሴቶች በወፍጮ ይፈጫሉ አንዲቱ ትወሰዳለች አንዲቱም ትቀራለች።” (ማቴዎስ 24:40, 41) ወሳኝ የሆነው ያ ጊዜ ሲመጣ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንገኝ ይሆን? ተዘጋጅተን እንጠብቃለን ወይስ ሳናስበው ድንገት ይደርስብናል? ይህ በአብዛኛው የተመካው አሁን በምንወስደው እርምጃ ላይ ነው። የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን ለመጠበቅ በዚህ ዘመን በብዙዎች ዘንድ የተለመደን አንድ ዓይነት ዝንባሌ ማስወገድ፣ መንፈሳዊ ድብታ እንዳይዘን መታገል እንዲሁም አንዳንድ የአኗኗር ዘይቤዎችን መተው ያስፈልገናል።

የቸልተኝነትን ዝንባሌ አስወግዱ

4. በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ምን ዓይነት ዝንባሌ ነበራቸው?

4 እስቲ በኖኅ ዘመን የነበረውን ሁኔታ ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት አዘጋጀ” ይላል። (ዕብራውያን 11:7) መርከቡ ከዚያ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ በቀላሉ ትኩረት የሚስብ ነበር። በተጨማሪም ኖኅ ‘ጽድቅን ይሰብክ’ ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:5) በጊዜው የነበሩት ሰዎች ግን መርከቡን ማየታቸውም ሆነ የኖኅን ስብከት መስማታቸው እርምጃ እንዲወስዱ አልገፋፋቸውም። ለምን? ምክንያቱም “ሲበሉና ሲጠጡ ሲያገቡና ሲጋቡም” ነበር። ኖኅ ይሰብክላቸው የነበሩት ሰዎች በግል ጉዳዮቻቸውና ተድላን በማሳደድ ከልክ በላይ ተጠምደው ስለነበር ‘የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉን እስከ ወሰደ ድረስ አላወቁም።’​—⁠ማቴዎስ 24:38, 39

5. በሎጥ ዘመን የሰዶም ነዋሪዎች የነበራቸው ዝንባሌ ምን ይመስላል?

5 በሎጥ ዘመንም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “ይበሉ ይጠጡም ይገዙም ይሸጡም ይተ​ክሉም ቤትም ይሠሩ ነበር፤ ሎጥ ከሰዶም በወጣበት ቀን ግን ከሰማይ እሳትና ዲን ዘነበ ሁሉንም አጠፋ።” (ሉቃስ 17:28, 29) መላእክት ጥፋት መቅረቡን ለሎጥ ሲነግሩት እርሱ ደግሞ ልጆቹን ለሚያገቡት ለአማቾቹ ስለ ሁኔታው ነገራቸው። እነርሱ ግን “የሚያፌዝባቸው መሰላቸው።”​—⁠ዘፍጥረት 19:14

6. የትኛውን ዝንባሌ ማስወገድ ይገባናል?

6 ኢየሱስ “የሰው ልጅ መምጣት” በኖኅና በሎጥ ዘመን ከነበረው ሁኔታ ጋር እንደሚመሳሰል ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:39፤ ሉቃስ 17:30) በእርግጥም በዛሬው ጊዜ የቸልተኝነት ዝንባሌ ተስፋፍቷል። እኛም እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ጥሩ ምግብ መብላትና የአልኮል መጠጥ በልክ መጠጣት ምንም ችግር የለውም። ጋብቻም ቢሆን የአምላክ ዝግጅት ነው። ይሁን እንጂ በሕይወታችን ውስጥ ለእነዚህ ነገሮች ከልክ ያለፈ ቦታ ሰጥተን መንፈሳዊ ጉዳዮችን ቸል የምንል ከሆነ አስፈሪውን የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን እየጠበቅን ነው ለማለት እንችላለን?

7. ማንኛውንም ግብ ከማውጣታችን በፊት ራሳችንን ምን እያልን መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ?

7 ሐዋርያው ጳውሎስ “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 7:29-31) አምላክ የሰጠንን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ከግብ ለማድረስ የቀረን ጊዜ በጣም አጭር ነው። (ማቴዎስ 24:14) ጳውሎስ ያገቡት እንኳን ለትዳር ጓደኛቸው ከልክ ያለፈ ትኩረት በመስጠት ለመንግሥቱ ጉዳዮች በሕይወታቸው ውስጥ ሁለተኛ ቦታ እንዳይሰጡ መክሯል። ጳውሎስ ቸልተኞች እንዳይሆኑ ማበረታታቱ እንደነበር ግልጽ ነው። ኢየሱስ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድ​ቁንም ፈልጉ” ብሏል። (ማቴዎስ 6:33) ማንኛውንም ውሳኔ ከማድረጋችን ወይም ግብ ከማውጣታችን በፊት ራሳችንን ‘ይህ በሕይወቴ ውስጥ መንግሥቱን ለማስቀደም የማደርገውን ጥረት የሚነካው እንዴት ነው?’ እያልን መጠየቅ ይኖርብናል።

8. በዋነኝነት የሚያሳስቡን የዕለት ተዕለት የኑሮ ጉዳዮች ከሆኑ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

8 መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ችላ እስክንል ድረስ ለዕለት ተዕለት ጉዳዮች ከፍተኛ ቦታ እንደሰጠን ብንገነዘብስ? የአኗኗር ዘይቤን በሚመለከት በእኛና ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በሌላቸው እንዲሁም የመንግሥቱ ሰባኪዎች ባልሆኑት ጎረቤቶቻችን መካከል እምብዛም ልዩነት የማይታይ ቢሆንስ? ሁኔታው እንደዚህ ከሆነ ጉዳዩን በጸሎት ልናስብበት ይገባል። ይሖዋ ትክክለኛው ዝንባሌ እንዲኖረን ሊረዳን ይችላል። (ሮሜ 15:5፤ ፊልጵስዩስ 3:15) ለመንግሥቱ ጉዳዮች ቅድሚያ እንድንሰጥ፣ ትክክል የሆነውን እንድናደርግና ለእርሱ ያለብንን ግዴታ እንድንወጣ ሊረዳን ይችላል።​—⁠ሮሜ 12:2፤ 2 ቆሮንቶስ 13:7

መንፈሳዊ ድብታ እንዳይዛችሁ ተጠንቀቁ

9. በራእይ 16:14-16 መሠረት መንፈሳዊ ድብታ እንዳይዘን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

9 “በታላቁም ሁሉን በሚገዛ በእግዚአብሔር ቀን” በአርማጌዶን ስለሚደረገው ጦርነት የሚናገረው ትንቢት አንዳንዶች ነቅተው እንደማይጠብቁ ይጠቁማል። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እነሆ፣ እንደ ሌባ ሆኜ እመጣለሁ፤ ራቁቱን እንዳይሄድ እፍረቱንም እንዳያዩ ነቅቶ ልብሱን የሚጠብቅ ብፁዕ ነው” በማለት ተናግሯል። (ራእይ 16:14-16) እዚህ ላይ የተጠቀሰው ልብስ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክር መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቅ ምልክት ነው። ይህም የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሆነን የምናከናውነውን ሥራና ክርስቲያናዊ ባሕርያችንን ይጨምራል። በመንፈሳዊ ብናሸልብና እንቅስቃሴያችን ቢዳከም ክርስቲያናዊ መለያችንን ልናጣ እንችላለን። ይህ አሳፋሪ ብሎም አደገኛ ነው። መንፈሳዊ ድብታ እንዳይዘን መታገል ይኖርብናል። እንዲህ ያለውን ሁኔታ መታገል የምንችለው እንዴት ነው?

10. በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን እንድንጠብቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ነቅቶ የመኖርንና የማስተዋል ስሜታችንን የመጠበቅን አስፈላጊነት በተደጋጋሚ ያጎላል። ለምሳሌ ያህል የወንጌል ዘገባዎች እንደሚከተለው በማለት ያሳስቡናል:- “ንቁ፤” (ማቴዎስ 24:​42፤ 25:13፤ ማርቆስ 13:35, 37) “ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤” (ማቴዎስ 24:44፤ ሉቃስ 12:40) “ተጠንቀቁ፤ ትጉ።” (ማርቆስ 13:33) ሐዋርያው ጳውሎስ የይሖዋ ቀን በዚህ ዓለም ላይ ባልተጠበቀ ሰዓት በድንገት እንደሚመጣ ካስጠነቀቀ በኋላ “እንግዲያስ እንንቃ በመጠንም እንኑር እንጂ እንደ ሌሎች አናንቀላፋ” በማለት የእምነት ባልንጀሮቹን አሳስቧቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:6) ታላቅ ክብር የተቀዳጀው ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ “በቶሎ እመጣለሁ” በማለት በድንገት እንደሚመጣ ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። (ራእይ 3:11፤ 22:7, 12, 20) ከዕብራውያን ነቢያት መካከል አብዛኞቹም ስለ ታላቁ የይሖዋ ቀን ጠቅሰው አስጠንቅቀዋል። (ኢሳይያስ 2:12, 17፤ ኤርምያስ 30:7፤ ኢዩኤል 2:11፤ ሶፎንያስ 3:8) የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበባችንና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰላችን በመንፈሳዊ ነቅተን እንድንኖር ከፍተኛ እገዛ ያበረክትልናል።

11. በመንፈሳዊ ነቅቶ ለመኖር የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

11 አዎን፣ “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያዘጋጃቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች እየታገዝን ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት ማጥናታችን በመንፈሳዊ እንደሚያነቃቃን እሙን ነው! (ማቴዎስ 24:45-47) ይሁን እንጂ ከግል ጥናት ጥቅም ለማግኘት ጥናቱ ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄድና በቋሚነት የሚደረግ መሆን ይኖርበታል። (ዕብራውያን 5:14 እስከ 6:3) ዘወትር ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ የመመገብ ልማድ ሊኖረን ይገባል። በዚህ ዘመን ለግል ጥናት የሚሆን ጊዜ ማግኘት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (ኤፌሶን 5:15, 16) ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስንና ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ጽሑፎችን ሲመቸን ብቻ ማንበቡ በቂ አይደለም። “በሃይማኖት ጤናሞች” ለመሆንና ነቅተን ለመኖር የምንፈልግ ከሆነ በቋሚነት የግል ጥናት ማድረጋችን ወሳኝ ነው።​—⁠ቲቶ 1:13, 14

12. የጉባኤ ስብሰባዎችና ትላልቅ ስብሰባዎች መንፈሳዊ ድብታን ለማሸነፍ የሚረዱን እንዴት ነው?

12 የጉባኤ ስብሰባዎችና ትላልቅ ስብሰባዎችም መንፈሳዊ ድብታ እንዳይዘን ይረዱናል። እንዴት? በሚቀርብልን ትምህርት አማካኝነት ነው። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የይሖዋ ቀን እንደቀረበ ዘወትር ማሳሰቢያ ይሰጠናል። ሳምንታዊ የጉባኤ ስብሰባዎችም ‘እርስ በርሳችን ለመልካም ሥራ እንድንነቃቃ’ የሚያስችል አጋጣሚ ይከፍቱልናል። እንዲህ ያለው ማነቃቂያ ወይም ማበረታቻ በመንፈሳዊ ንቁ ሆኖ ለመቆየት ይረዳል። ‘ቀኑ በቀረበ መጠን’ ይህን አዘውትረን እንድናደርግ የታዘዝነው ለዚህ ነው።​—⁠ዕብራውያን 10:24, 25

13. ክርስቲያናዊ አገልግሎታችን በመንፈሳዊ ንቁ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?

13 በክርስቲያናዊ አገልግሎታችንም በሙሉ ልባችን መካፈላችን ነቅተን ለመኖር ይረዳናል። የመጨረሻውን ዘመን ምልክቶችና ትርጉማቸውን በአእምሯችን ለመቅረጽ ለሌሎች ከመናገር የተሻለ ምን ዘዴ ይኖራል? እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናናቸው ሰዎች እድገት ሲያደርጉና የተማሩትን በሥራ ላይ ሲያውሉ ስንመለከት የጊዜውን አጣዳፊነት ይበልጥ እንገነዘባለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘የልቡናችሁን ወገብ ታጥቃችሁ በመጠን ኑሩ’ በማለት ተናግሯል። (1 ጴጥሮስ 1:13) መንፈሳዊ ድብታን ለማባረር የተሻለው ዘዴ ‘የጌታ ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛልን መሆን’ ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:58

በመንፈሳዊ ጎጂ የሆነ አኗኗር አትከተሉ

14. ኢየሱስ በሉቃስ 21:34-36 ላይ የትኞቹን የአኗኗር ዘይቤዎች እንዳንከተል አስጠንቅቆናል?

14 ኢየሱስ መምጫውን የሚጠቁሙ ምልክቶችን አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ውስጥ ሌላም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እንዲህ አለ:- “ልባችሁ በመጠጥ [‘በመብል፣’ የ1980 ትርጉም ] ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።” (ሉቃስ 21:34-36) ኢየሱስ ሰዎች በአብዛኛው የሚከተሉትን የአኗኗር ዘይቤ ማለትም ከልክ በላይ መብላትን፣ ስካርንና ጭንቀት የሚያስከትል አኗኗርን ጠቅሷል።

15. ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት የሌለብን ለምንድን ነው?

15 ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሲሆን ሊወገድ የሚገባው ልማድ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር ለሥጋም ከሚስገበገቡ ጋር አትቀመጥ’ ይላል። (ምሳሌ 23:20) ይሁን እንጂ መብላትና መጠጣት ለመንፈሳዊ አደጋ የሚዳርገን ስንሰክርና ቁንጣን ሲይዘን ብቻ አይደለም። እዚያ ደረጃ ላይ ከመድረሳችንም በፊት መንፈሳዊ ድብታ እንዲይዘንና ስንፍና እንዲጠናወተን ሊያደርግ ይችላል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም” ይላል። (ምሳሌ 13:4) እንዲህ ዓይነቱ ሰው የአምላክን ፈቃድ የማድረግ ፍላጎት ቢኖረውም እርምጃ ለመውሰድ ቸልተኛ ስለሆነ ፍላጎቱ ምኞት ብቻ ሆኖ ይቀራል።

16. ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት የምናደርገው ሩጫ ውጥረት እንዳይፈጥርብን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

16 ኢየሱስ ያስጠነቀቀው ስለ የትኞቹ የኑሮ ጭንቀቶች ነው? የግል ጉዳዮችን በሚመለከት መጨነቅን፣ ለቤተሰብ የሚያስፈልገውን ለማሟላት የሚደረገውን ሩጫና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች ጫና እንዳይፈጥሩብን መጠንቀቃችን የተገባ ነው። ኢየሱስ “ከእናንተ ተጨንቆ በቁመቱ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ማን ነው?” ሲል ጠይቋል። ከዚያም “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና” በማለት አድማጮቹን አበረታቷቸዋል። በሕይወታችን ውስጥ ለመንግሥቱ ጥቅሞች ቅድሚያ መስጠታችንና ይሖዋ እንደሚንከባከበን ሙሉ እምነት ማሳደራችን የኑሮን ጭንቀቶች የሚያስወግድልን ከመሆኑም በላይ ነቅተን እንድንኖር ይረዳናል።​—⁠ማቴዎስ 6:25-34

17. ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ ጭንቀት ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?

17 ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድም ጭንቀት ሊያመጣ ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ከአቅማቸው በላይ በመኖር ሕይወታቸውን ያወሳስቡታል። ሌሎች ደግሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመክበር ያስችላሉ በሚባሉ ውጥኖች ይታለላሉ፤ ወይም ለኪሳራ በሚያጋልጡ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ገንዘባቸውን ያፈሳሉ። አንዳንዶች ደግሞ ተምረው ገንዘብ ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት ወጥመድ ይሆንባቸዋል። እርግጥ ሥራ ለማግኘት የተወሰነ የትምህርት ደረጃ አስፈላጊ መሆኑ አይካድም። ሆኖም አንዳንዶች ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሙሉ ጊዜያቸውን ስለሚሻማባቸው በመንፈሳዊ ራሳቸውን ጎድተዋል። ይህ ደግሞ የይሖዋ ቀን እየቀረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት አደገኛ የሆነ ሁኔታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” በማለት ያስጠነቅቃል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 6:9

18. ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ አኗኗር ላለመከተል የትኛውን ችሎታ ማዳበር ያስፈልገናል?

18 ውሳኔ ስናደርግ ትክክል የሆነውን ከስህተቱ የመለየት ችሎታን ማዳበር ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ አኗኗር ከመከተል ይጠብቀናል። ‘የጎለመሱ ሰዎች የሚመገቡትን ጠንካራ መንፈሳዊ ምግብ’ አዘውትረን በመመገብና ‘ልቦናችንን በሥራ በማሰልጠን’ ይህን ችሎታ ማዳበር እንችላለን። (ዕብራውያን 5:13, 14) ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባቸውን ነገሮች ስንወስንም ‘የሚሻለውን ነገር መፈተናችን’ የተሳሳተ ውሳኔ ከማድረግ ይጠብቀናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 1:9, 10

19. ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የምናውለው ጊዜ እያነሰ እንደሄደ ከተሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

19 ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ ላይ ያተኮረ አኗኗር መንፈሳዊ እይታችንን ሊጋርድብንና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች የምናውለውን ጊዜ ሊሻማብን ወይም ጨርሶ ሊያሳጣን ይችላል። ራሳችንን በመመርመር በዚህ ዓይነቱ አኗኗር ከመጠመድ መራቅ የምንችለው እንዴት ነው? ሕይወታችንን እንዴትና እስከምን ድረስ ቀላል ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ በጸሎት ልናስብበት ይገባል። የጥንቱ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን “እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል” በማለት ተናግሯል። (መክብብ 5:12) አላስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ንብረቶች ጊዜያችንንና ገንዘባችንን ይሻሙብናል? ንብረቶቻችን በበዙ መጠን ለጥገና፣ ለኢንሹራንስና ለጥበቃ የምናወጣው ወጪም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። አንዳንድ ንብረቶቻችንን በመቀነስ ሕይወታችንን ቀላል ማድረግ እንችል ይሆን?

በተቻላችሁ መጠን ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ

20, 21. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ የይሖዋን ቀን በሚመለከት ምን ማረጋገጫ ሰጥቶናል? (ለ) የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን ስንጠብቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

20 በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም እንደጠፋ ሁሉ ይህ ሥርዓትም መጥፋቱ አይቀርም። ሐዋርያው ጴጥሮስ “[የይሖዋ] ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል፤ በዚያም ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፣ የሰማይም ፍጥረት በትልቅ ትኵሳት ይቀልጣል፣ ምድርም በእርስዋም ላይ የተደረገው ሁሉ ይቃጠላል” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። በሰማይ የተመሰሉት ክፉ መንግሥታትም ሆኑ ምድር የተባለው ከአምላክ የራቀው የሰው ዘር ከአምላክ የቁጣ ትኩሳት አያመልጡም። ጴጥሮስ ይህን ቀን እንዴት ተዘጋጅተን መጠበቅ እንደምንችል ሲጠቁም እንዲህ ብሏል:- “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ፣ በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል እንደ ምን ልትሆኑ ይገባችኋል?”​—⁠2 ጴጥሮስ 3:10-12

21 ቅዱስ ኑሮና እግዚአብሔርን መምሰል ወይም ለአምላክ ማደር የተባሉት አዘውትሮ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትንና ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ መካፈልን ይጨምራሉ። እንግዲያው የይሖዋን ታላቅ ቀን በትዕግሥት ስንጠባበቅ በሙሉ ልባችን ለአምላክ በማደር እነዚህን እናድርግ። አምላክ ‘ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆነን በሰላም እንዲያገኘን እንትጋ።’​—⁠2 ጴጥሮስ 3:14

ታስታውሳለህ?

• የይሖዋን ቀን ተዘጋጅተን መጠበቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ የያዙት የዕለት ተዕለት የኑሮ ሩጫዎች ከሆኑ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

• መንፈሳዊ ድብታ እንዳይዘን ሊረዳን የሚችለው ምንድን ነው?

• የትኞቹን በመንፈሳዊ ጎጂ የሆኑ የአኗኗር ዘይቤዎች ማስወገድ አለብን? እንዴት?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20, 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኖኅ ዘመን የነበሩት ሰዎች ጥፋት እየመጣ እንደነበር አላስተዋሉም​—⁠አንተስ?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ጊዜ ለማግኘት አኗኗርህን ቀላል ማድረግ ትችል ይሆን?