በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ኢየሱስ ቤተሰቦች ምን ያህል ታውቃለህ?

ስለ ኢየሱስ ቤተሰቦች ምን ያህል ታውቃለህ?

ስለ ኢየሱስ ቤተሰቦች ምን ያህል ታውቃለህ?

 በብዙ የዓለም ክፍሎች በታኅሣሥ ወር ሕፃኑ ኢየሱስ በእናቱ በማርያም እቅፍ ውስጥ ሆኖ እንዲሁም አሳዳጊ አባቱ ዮሴፍ አጠገባቸው ቆሞ የሚያሳዩ ምስሎችንና ቅርጻ ቅርጾችን መመልከት የተለመደ ነው። እነዚህ ምስሎችና ቅርጻ ቅርጾች በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎችን እንኳ ትኩረት ይስባሉ። ምስሎቹ በዋነኝነት የሚያተኩሩት በኢየሱስ ላይ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም ቅዱሳን ጽሑፎች የኢየሱስን ቤተሰቦች በሚመለከት ምን ይላሉ?

ኢየሱስ ያደገበት ቤተሰብ ሁኔታ ትኩረትን በእጅጉ የሚስብ ነው። ኢየሱስ ማርያም ከምትባል ድንግል ሴት ተወልዶ የሰብዓዊው ኅብረተሰብ አባል ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሕይወቱ ከሰማይ ወደ ማርያም ማሕጸን እንዲዛወር የተደረገው በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ነበር። (ሉቃስ 1:30-35) ማርያም በተአምር ኢየሱስን መጸነሷን ከማወቋ በፊት ዮሴፍ ለተባለ ሰው ታጭታ ነበር። በዚህም ምክንያት ዮሴፍ የኢየሱስ አሳዳጊ አባት ሊሆን ችሏል።

ኢየሱስ ከተወለደ በኋላ ዮሴፍና ማርያም ሌሎች ልጆችን ስለወለዱ ኢየሱስ በእናቱ በኩል የሚዛመዱት ወንድሞችና እህቶች ነበሩት። ከጊዜ በኋላ የናዝሬት ነዋሪዎች ኢየሱስን በሚመለከት ያነሷቸው የሚከተሉት ጥያቄዎች ለዚህ እንደ ማስረጃ ይሆናሉ። “ይህ የጸራቢ ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” (ማቴዎስ 1:25፤ 13:55, 56፤ ማርቆስ 6:3) ከዚህ በመነሳት ኢየሱስ ወላጆቹን ጨምሮ አራት ወንድሞችንና ቢያንስ ሁለት እህቶችን ያቀፈ ቤተሰብ ነበረው ብለን መደምደም እንችላለን።

ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች የኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች የተባሉት የዮሴፍና የማርያም ልጆች መሆናቸውን አይቀበሉም። ለምን? ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል:- “ቤተ ክርስቲያን ከጥንት ጀምሮ ታስተምር የነበረው ማርያም ምንጊዜም ድንግል እንደሆነች ነው። ከዚህ አንጻር ማርያም ሌሎች ልጆች እንዳልነበሯት አያጠያይቅም።” ይኸው የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ወንድም” እና “እህት” ተብለው የተተረጎሙት የግሪክኛ ቃላት “በእምነት ወይም በሌላ ነገር የሚዛመዱ ግለሰቦችን” ወይም ዘመዳሞችን ምናልባትም የአጎት ወይም የአክስት ልጆችን ሊያመለክቱ እንደሚችሉ ይናገራል።

ይሁን እንጂ ሁኔታው እንደዚያ ነው? አንዳንድ የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ምሑራን እንኳን በዚህ ትምህርት የማይስማሙ ከመሆኑም በላይ ኢየሱስ ሥጋዊ ወንድሞችና እህቶች ነበሩት የሚለውን ሐሳብ ይደግፋሉ። በአሜሪካ የካቶሊክ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበሩት ጆን ፖል ሚየር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በአዲስ ኪዳን ውስጥ አዴልፎስ [በግሪክኛ ወንድም ማለት ነው] የሚለው ቃል በምሳሌያዊ መንገድ እስካልተሠራበት ድረስ ሥጋዊ ወይም ሕጋዊ ዝምድናን ለማመልከት በሚገባበት ጊዜ በእናትና በአባት ወይም በአንዳቸው በኩል ሥጋዊ ወንድም መሆንን ያመለክታል።” a አዎን፣ ቅዱሳን ጽሑፎች ኢየሱስ ከዮሴፍና ከማርያም የተወለዱ ወንድሞችና እህቶች እንደነበሩት ያመለክታሉ።

ወንጌሎች ስለ ሌሎች የኢየሱስ ዘመዶችም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከላይ በጠቀስናቸው የኢየሱስ ቤተሰብ አባላት ላይ እናተኩርና ከእነርሱ ምን ልንማር እንደምንችል እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “የኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት እይታ” በሚል ርዕስ በጆን ፖል ሚየር የተዘጋጀ። ዘ ካቶሊክ ቢብሊካል ኳርተርሊ ጥር 1992, ገጽ 21።