በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች አንብበሃል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር:-

የሚክያስ መጽሐፍ ስንት ምዕራፎች አሉት? የተጻፈው መቼ ነበር? በተጻፈበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ምን ይመስላል?

የሚክያስ መጽሐፍ ሰባት ምዕራፎች አሉት። ነቢዩ ሚክያስ ይህን መጽሐፍ የጻፈው በስምንተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን በወቅቱ የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች እስራኤልና ይሁዳ ተብለው በሁለት ብሔራት ተከፍለው ነበር።​—8/15, ገጽ 9

በሚክያስ 6:​8 መሠረት ይሖዋ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው?

‘ፍትሕ ማድረግ’ ይኖርብናል። የፍትሕ መሥፈርቱ ይሖዋ ነገሮችን የሚያደርግበት መንገድ ስለሆነ ለሐቀኝነትና ለጨዋነት ትልቅ ቦታ እንደምንሰጥ እናሳያለን። ይሖዋ ‘ምሕረትን እንድንወድ’ ይነግረናል። ክርስቲያኖች ሌሎች እንደ ተፈጥሮ አደጋ ያሉ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው በችግራቸው በመድረስ ደግነት አሳይተዋል። ከይሖዋ ጋር ‘ልካችንን አውቀን’ ለመመላለስ የአቅማችንን ውስንነት መገንዘብና በአምላክ መታመን ይኖርብናል።​—8/15, ገጽ 20-22

አንድ ክርስቲያን ከሥራ ቢቀነስ ምን ሊያደርግ ይችላል?

አኗኗሩን መለስ ብሎ መገምገሙ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። አነስ ወዳለ ቤት በመዛወር ወይም የማያስፈልጉ ዕቃዎችን በመቀነስ ኑሮውን ቀለል ማድረግ ይችላል። የዕለት ተዕለት ፍላጎቶቹን በሚመለከት መጨነቁን ማቆምና የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንደሚያሟላለት ትምክህቱን በአምላክ ላይ መጣሉ አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 6:33, 34)​—9/1, ገጽ 14-15

የሠርግ ስጦታዎች ስንሰጥ ወይም ስንቀበል ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

ውድ የሆኑ ስጦታዎች መስጠት አስፈላጊ አይደለም፤ ሌሎች እንዲሰጡንም መጠበቅ ተገቢ አይደለም። ትልቁ ነገር የሰጪው የልብ ዝንባሌ ነው። (ሉቃስ 21:1-4) ስጦታውን የሰጡትን ሰዎች ስም ማስታወቁም ሰዎቹ እንዲያፍሩ ወይም እንዲሸማቀቁ ሊያደርግ ስለሚችል ጥሩ አይደለም። (ማቴዎስ 6:3)​—9/1, ገጽ 29

ሳናቋርጥ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

አዘውትሮ መጸለይ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያጠናክርልን ሲሆን ከባድ ፈተናዎችን እንድንቋቋም ያዘጋጀናል። በግል የምናቀርበው ጸሎት እንደሚያስፈልገን ነገርና እንደ ሁኔታው አጭር ወይም ረዥም ሊሆን ይችላል። ጸሎት እምነታችንን የሚገነባልን ከመሆኑም በላይ ችግሮቻችንን ለመፍታት ይረዳናል።​—9/15, ገጽ 15-​18

በአንዳንድ ትርጉሞች ላይስለ ሙታን መጠመቅተብሎ የተተረጎመውን የአንደኛ ቆሮንቶስ 15:29ን ጥቅስ የምንረዳው እንዴት ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ሲናገር በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ የሚከተሉት የሕይወት ጎዳና እንደ ክርስቶስ እስከ ሞት ድረስ ታማኝ መሆንን እንደሚጠይቅባቸው ማመልከቱ ነበር። ከዚያም ልክ እንደ ክርስቶስ ትንሣኤ አግኝተው መንፈሳዊ ሕይወት ይሰጣቸዋል።​—10/1, ገጽ 29

ክርስቲያን መሆን ማለት በአንደኛ ቆሮንቶስ 6:9-11 ላይ የተጠቀሱትን መጥፎ ነገሮች አለማድረግ ብቻ እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?

ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንደ ዝሙት፣ ምንዝርና ስካር ያሉ መጥፎ ነገሮችን ማድረግ እንደሌለባቸው ብቻ ጠቅሶ አላበቃም። ሌሎች ለውጦችም ሊያስፈልጉ እንደሚችሉ ሲጠቁም በቁጥር 12 ላይ “ሁሉ ተፈቅዶልኛል፣ ሁሉ ግን አይጠቅምም” ብሏል።​—10/15, ገጽ 18-​19

• የይሖዋን ልብ ደስ ካሰኙ የጥንት ሴቶች መካከል እነማን ይገኙበታል?

አዲስ የሚወለዱትን እስራኤላዊ ወንዶች እንዲገድሉ ፈርዖን የሰጣቸውን ትእዛዝ ያልፈጸሙት ሲፓራ እና ፉሐ የተባሉ አዋላጆች ይገኙበታል። (ዘጸአት 1:15-20) ከነዓናዊቷ ጋለሞታ ረዓብ ሁለት እስራኤላውያን ሰላዮችን ደብቃለች። (ኢያሱ 2:1-13፤ 6:22, 23) አቢግያ በማስተዋል የወሰደችው እርምጃ የብዙዎችን ሕይወት ከማትረፉም በላይ የወደፊቱን የእስራኤል ንጉሥ ዳዊትን በደም ዕዳ ተጠያቂ ከመሆን ጠብቆታል። (1 ሳሙኤል 25:2-35) እነዚህ በዛሬው ጊዜ ለሚኖሩት ሴቶች ግሩም ምሳሌዎች ናቸው።​—11/1, ገጽ 8-​11

በመሳፍንት 5:​20 ላይ “ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ” ይላል። ከዋክብት ከሲሣራ ጋር የተዋጉት እንዴት ነው?

አንዳንዶች ይህ አባባል መለኮታዊ እርዳታን እንደሚያመለክት ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ መላእክታዊ እርዳታን፣ የተወርዋሪ ኮከቦች መውደቅን፣ ወይም ከንቱ ሆነው የቀሩትን ሲሣራ የታመነባቸውን የኮከብ ቆጠራ ትንበያዎች ያመለክታል ይላሉ። በዚህ ውጊያ ከዋክብት የተዋጉት እንዴት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለማይገልጽ ጥቅሱ የእስራኤል ሠራዊት ያገኘውን አንድ ዓይነት መለኮታዊ እርዳታ ያመለክታል ብሎ መደምደሙ በቂ ይመስላል።​—11/15, ገጽ 30

ለሃይማኖት ግዴለሽነትና ቸልተኝነት በጣም በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ብዙዎች አሁንም ቢሆን በአምላክ እንደሚያምኑ የሚናገሩት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ነው። ሌሎች ደግሞ ከሞቱ በኋላ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ወይም አሁን ጥሩ ጤንነት፣ ሀብትና ስኬት ለማግኘት ብለው ነው። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች የኮሚኒስት ርዕዮተ ዓለም በካፒታሊዝም መበረዙ ያስከተለባቸውን መንፈሳዊ ባዶነት የሚያስወግድ ነገር ይፈልጋሉ። አንድ ክርስቲያን እነዚህን ምክንያቶች ማወቁ ከሚያነጋግራቸው ሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት እንዲያደርግ ሊረዳው ይችላል።​—12/1, ገጽ 3