በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት የተናገረው ሐሳብ ክፉ መላእክት ገና ከሰማይ ሳይባረሩ የአምላክ ፈቃድ በዚያ ተፈጽሞ እንደነበር ያሳያል?

ኢየሱስ በማቴዎስ 6:​10 ላይ “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብሎ ነበር። ይህን ጸሎት በሁለት የተለያዩ መንገዶች ልንረዳው እንችላለን። የመጀመሪያው አማራጭ የአምላክ ፈቃድ ቀደም ሲል በሰማይ እንደተፈጸመው ሁሉ በምድርም እንዲፈጸም የቀረበ ልመና ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአምላክ ፈቃድ በሰማይም ሆነ በምድር በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጸም የቀረበ ጸሎት ነው የሚል ነው። a ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቀደም ሲል “መንግሥትህ ትምጣ” በማለት የተናገረው ሐሳብ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ይበልጥ የሚስማማው ሁለተኛው አማራጭ እንደሆነ ይጠቁማል። የሚያመለክተውም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የነበረውንና ወደፊት ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚሆነውን ሁኔታ ነው። እንዴት?

የራእይ መጽሐፍ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መቋቋሙ ሁለት የተለያዩ ውጤቶችን እንዳስከተለ ይገልጻል። አንደኛው ውጤት የታየው በሰማይ ላይ ሲሆን ሁለተኛው በምድር ላይ ነው። ራእይ 12:7-9, 12 እንዲህ ይላል:- “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ። . . . ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”

ሰይጣንና አጋንንቱ በ1914 ከሰማይ በመባረራቸው ሰማያዊ ግዛቱ በይሖዋ ላይ ካመጹት መንፈሳዊ ፍጥረታት ጸድቷል። ይህም ከይሖዋ መንፈሳዊ ፍጥረታት ውስጥ ብዙኃኑን ለሚወክሉት ታማኝ መላእክት ከፍተኛ ደስታ አምጥቶላቸዋል። (ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1–7፤ ራእይ 12:10) በመሆኑም ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ ሰማይን በሚመለከት ያቀረበው ልመና ፍጻሜውን አግኝቷል። በሰማይ የቀሩት ለይሖዋ ታማኝ የሆኑና ሉዓላዊነቱን ሙሉ በሙሉ የሚደግፉ ብቻ ናቸው።

ክፉዎቹ መላእክት ከሰማይ ከመባረራቸውም በፊት ከአምላክ ቤተሰብ ተገልለውና እገዳ ተጥሎባቸው እንደነበረ ልብ ሊባል ይገባዋል። ለምሳሌ ያህል ይሁዳ 6 እነዚህ ክፉ መላእክት በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንኳን “በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ” እየተጠበቁ እንደነበረ ይናገራል። በተመሳሳይም 2 ጴጥሮስ 2:4 “እግዚአብሔር ኃጢአትን ላደረጉ መላእክት ሳይራራላቸው ወደ ገሃነም ጥሎ በጨለማ ጕድጓድ ለፍርድ ሊጠበቁ አሳልፎ” እንደሰጣቸው ይናገራል። b

ክፉ መላእክት በሰማይ ሳሉ ተገልለው የነበረ ቢሆንም በምድር ላይ ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። እንዲያውም የአምላክ ቃል ሰይጣንን “የዚህ ዓለም ገዥ” አጋንንቱን ደግሞ ‘የጨለማ ዓለም ገዦች’ በማለት ይጠራቸዋል። (ዮሐንስ 12:31፤ ኤፌሶን 6:11, 12፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ዲያብሎስ ኢየሱስ ወድቆ ቢሰግድለት ‘የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን’ እንደሚሰጠው የነገረውም የዓለም ገዥ ስለነበረ ነው። (ማቴዎስ 4:8, 9) በመሆኑም የአምላክ መንግሥት መምጣት በምድር ላይ ወሳኝ ለውጦች እንደሚያስከትል ግልጽ ነው።

የአምላክ መንግሥት ‘መምጣት’ በምድር ላይ አዲስ ሥርዓት እንዲሰፍን ያደርጋል። ሰብዓዊ አገዛዝን በሙሉ ጠራርጎ የሚያስወግድ ሲሆን በምድር ላይ ብቸኛው መስተዳድር ይሆናል። ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰብዓዊ ተገዥዎቹም “አዲስ ምድር” ይሆናሉ። (2 ጴጥሮስ 3:13፤ ዳንኤል 2:44) የአምላክ መንግሥት ታዛዥ የሰው ልጆችን ከኃጢአት ባርነት ነጻ የሚያወጣቸው ሲሆን ምድርን ቀስ በቀስ ወደ ገነትነት በመለወጥ የሰይጣንን አገዛዝ ርዝራዥ ለዘለቄታው ያስወግዳል።​—⁠ሮሜ 8:20, 21፤ ራእይ 19:17–21

በሺህ ዓመቱ ማብቂያ ላይ መሲሐዊው መንግሥት የአምላክን ፈቃድ አከናውኖ ሲጨርስ “እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።” (1 ቆሮንቶስ 15:28) ከዚያም የመጨረሻ ፈተና የሚኖር ሲሆን በኋላም ሰይጣን፣ አጋንንቱና ፈተናውን የወደቁ ዓመጸኛ የሰው ልጆች በሙሉ ዳግም ላይገኙ ‘በሁለተኛው ሞት’ ይጠፋሉ። (ራእይ 20:7-15) ከዚያ በኋላ በሰማይም ሆነ በምድር የሚኖሩት የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ሁሉ ለይሖዋ ሉዓላዊነት በደስታ እየተገዙ ለዘላለም ይኖራሉ። ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ የተናገራቸው ቃላት በዚህ መንገድ ሙሉ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።​—⁠1 ዮሐንስ 4:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዘ ባይብል​—⁠አን አሜሪካን ትራንስሌሽን የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን የኢየሱስ የናሙና ጸሎት “መንግሥትህ ይምጣ! ፈቃድህ በሰማይም በምድርም ይሁን!” በማለት ተርጉሞታል።​—⁠ማቴዎስ 6:10

b ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህን ሲል በመንፈሳዊ መገለልን “በወኅኒ” ከመታሰር ጋር ማወዳደሩ ነበር እንጂ ወደፊት አጋንንት ለአንድ ሺህ ዓመታት ስለሚታሰሩበት ስለ ‘ጥልቁ’ እየተናገረ አልነበረም።​—⁠1 ጴጥሮስ 3:19, 20፤ ሉቃስ 8:30, 31፤ ራእይ 20:1-3