በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ወጣ’

‘ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ወጣ’

‘ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ወጣ’

“አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።”—ማቴዎስ 28:19

1, 2. (ሀ) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው ተልእኮ ምንድን ነው? (ለ) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ብዙ ሥራ ሊያከናውኑ የቻሉት እንዴት ነው?

 ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ከጥቂት ጊዜ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ አንድ ተልእኮ ሰጣቸው። “አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፣ . . . ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴዎስ 28:19) የሰጣቸው ሥራ እጅግ ታላቅ ነበር!

2 እስቲ አስበው! በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት 120 የሚያህሉ ደቀ መዛሙርት መንፈስ ቅዱስ ከፈሰሰላቸው በኋላ ኢየሱስ መዳን የሚገኝበት ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው መሲሕ መሆኑን ለሌሎች በመንገር ይህን ተልእኮ መፈጸም ጀመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 2:1-36) ሆኖም እነዚህ ጥቂት ሰዎች “አሕዛብን ሁሉ” ማዳረስ የሚችሉት እንዴት ነው? በሰው ዓይን ሲታይ የሚቻል ባይመስልም “በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ሁሉ ይቻላል።” (ማቴዎስ 19:26) የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች የይሖዋን ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ያገኙ ከመሆኑም ሌላ የጥድፊያ ስሜት ነበራቸው። (ዘካርያስ 4:6፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2) በመሆኑም በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ምስራቹ “ከሰማይ በታች ባለው ፍጥረት ሁሉ ዘንድ” በመሰበክ ላይ ነበር።—ቆላስይስ 1:23

3. ትክክለኛው የክርስትና “ስንዴ” ከእይታ እንዲሰወር ያደረገው ነገር ምንድን ነው?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን እውነተኛው አምልኮ ለበርካታ ዓመታት መስፋፋቱን ቀጥሎ ነበር። ይሁን እንጂ ሰይጣን “እንክርዳድ” እንደሚዘራበትና እውነተኛ የክርስትና “ስንዴ” የመከር ወቅት እስከሚደርስ ድረስ ለብዙ መቶ ዓመታት ተውጦ እንደሚቆይ ኢየሱስ ተንብዮ ነበር። ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ትንቢቱ ተፈጽሟል።—ማቴዎስ 13:24-39

በዛሬው ጊዜ ያለ ፈጣን እድገት

4, 5. ከ1919 ጀምሮ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኛውን ሥራ ማከናወን ጀመሩ? ሥራው ቀላል አልነበረም የምንለው ለምንድን ነው?

4 በ1919 ንጹሑ የክርስትና ስንዴ ከእንክርዳዱ የሚለይበት ጊዜ ደረሰ። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ኢየሱስ የሰጠው ታላቅ ተልእኮ በዚህ ጊዜም እንደሚሠራ ተገነዘቡ። የሚኖሩት “በመጨረሻው ቀን” እንደሆነ ጽኑ እምነት ነበራቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” ሲል የተናገረውን ትንቢት ተገንዝበው ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ማቴዎስ 24:14) አዎን፣ ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ አውቀው ነበር።

5 ይሁንና በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደነበሩት ደቀ መዛሙርት ሁሉ እነዚህ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖችም ከፊታቸው ታላቅ ሥራ ይጠብቃቸው ነበር። ብዛታቸው በጥቂት ሺዎች የሚቆጠር ሲሆን የሚገኙትም በተወሰኑ አገሮች ውስጥ ነበር። ታዲያ ምሥራቹን “በዓለም ሁሉ” መስበክ የሚችሉት እንዴት ነው? የምድር ሕዝብ በሮም አገዛዝ ዘመን በግምት 300 ሚሊዮን ከነበረበት ተነስቶ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በኋላ ወደ 2 ቢሊዮን ገደማ መድረሱን አስታውሱ። በ20ኛው መቶ ዘመን ደግሞ እድገቱ በከፍተኛ ፍጥነት ቀጥሏል።

6. በ1930ዎቹ በምሥራቹ ስብከት ሥራ ምን እድገት ታይቶ ነበር?

6 የሆነ ሆኖ፣ በይሖዋ መንፈስ የተቀቡት አገልጋዮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ወንድሞቻቸው ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታምነው የተመደበላቸውን ሥራ ተያያዙት፤ ይሖዋም መንፈሱን ሰጣቸው። በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ 56,000 ገደማ የሚሆኑ ወንጌላውያን በ115 አገሮች ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አውጀዋል። እስከዚህ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ብዙ ሥራ የተከናወነ ቢሆንም ገና ብዙ ይቀር ነበር።

7. (ሀ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተከፈተላቸው አዲስ ሥራ ምንድን ነው? (ለ) “ሌሎች በጎች” የሚሰጡት ድጋፍ ተጨምሮ የስብከቱ ሥራ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

7 ከዚያም ራእይ 7:9 ላይ የተጠቀሱትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ማንነት በጥልቅ መረዳታቸው በአንድ በኩል አዲስ ተፈታታኝ ሁኔታ እንዲፈጠርባቸው ያደረገ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ ትጉ ክርስቲያኖች እርዳታ እንደሚያገኙ ተስፋ የሚሰጥ ሆኖላቸዋል። ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ “ሌሎች በጎች” ማለትም በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ያላቸው አማኞች “ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” መሰባሰብ ነበረባቸው። (ዮሐንስ 10:16) እነዚህ አማኞች ‘ይሖዋን ሌሊትና ቀን ያመልኩታል።’ (ራእይ 7:15) ይህም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ እርዳታ ያበረክታሉ ማለት ነው። (ኢሳይያስ 61:5) በመሆኑም ቅቡዓን ክርስቲያኖች የወንጌላውያኑ ቁጥር በአሥር ሺዎች ከዚያም በሚሊዮን የሚቆጠር ደረጃ ላይ ሲደርስ በማየታቸው ተደስተዋል። በ2003 ቁጥራቸው 6,429,351 የደረሰ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ ተሳትፈዋል። ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የእጅግ ብዙ ሰዎች ክፍል ናቸው። a ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን ድጋፍ በማግኘታቸው አመስጋኞች ሲሆኑ ሌሎች በጎች ደግሞ በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞቻቸውን የመደገፍ መብት በማግኘታቸው አመስጋኞች ናቸው።—ማቴዎስ 25:34-40

8. የይሖዋ ምሥክሮች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ለደረሰባቸው ከባድ ስደት ምን ምላሽ ሰጡ?

8 የስንዴው ክፍል እንደገና በይፋ ሲታወቅ ሰይጣን በዚህ ቡድን ላይ ከፍተኛ ጦርነት አወጀ። (ራእይ 12:17) እጅግ ብዙ ሰዎች መሰባሰብ ሲጀምሩስ ምን አደረገ? ከፍተኛ ጥቃት ይሰነዝር ጀመር! በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በመላው ዓለም በእውነተኛ አምላኪዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት በስተጀርባ የነበረው እርሱ መሆኑን እንጠራጠራለን? ክርስቲያኖች ከሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ከባድ ፈተና ደርሶባቸዋል። ተወዳጅ የሆኑ ብዙ ወንድሞችና እህቶች አሰቃቂ መከራ የደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ አንዳንዶች ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል። ይሁንና የመዝሙራዊው ዓይነት አቋም እንዳላቸው በተግባር አሳይተዋል:- “በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፣ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?” (መዝሙር 56:4፤ ማቴዎስ 10:28) ቅቡዓን ክርስቲያኖችና ሌሎች በጎች በይሖዋ መንፈስ ተጠናክረው በሕብረት ጸንተው ቆመዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ከዚህም የተነሳ “የእግዚአብሔር ቃል እየሰፋ ሄደ።” (የሐዋርያት ሥራ 6:7) በ1939 ጦርነት በጀመረበት ጊዜ በስብከቱ ሥራ መካፈላቸውን ሪፖርት ያደረጉ 72,475 ታማኝ ክርስቲያኖች ነበሩ። ይሁን እንጂ ጦርነቱ ባበቃበት በ1945 የተሰባሰበው ሪፖርት ያልተሟላ ቢሆንም ምሥራቹን የሚያውጁ 156,299 ትጉ ምሥክሮች መኖራቸውን አሳይቷል። ይህ ለሰይጣን እንዴት ያለ ሽንፈት ነው!

9. በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የተከፈቱት ሁለት አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የትኞቹ ናቸው?

9 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለው ቀውስ የይሖዋ አገልጋዮች የስብከቱን ሥራ መካሄድ በተመለከተ እንዲጠራጠሩ አላደረጋቸውም። እንዲያውም ጦርነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት በ1943 ሁለት አዳዲስ ትምህርት ቤቶች መከፈታቸው ይፋ ሆነ። በአሁኑ ጊዜ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የሚባለው አንደኛው ትምህርት ቤት ምሥክሮቹን ለስብከቱና ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ በግለሰብ ደረጃ ለማሰልጠን በሁሉም ጉባኤዎች እንዲካሄድ የተዘጋጀ ነበር። ሌላው ደግሞ ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሲሆን ወደ ሌላ አገር ሄደው የስብከቱን ሥራ የሚያስፋፉ ሚስዮናውያንን ለማሰልጠን የተቋቋመ ነበር። አዎን፣ ጦርነቱ ባበቃበት ጊዜ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከበፊቱ በበለጠ በሥራው ለመሳተፍ ተዘጋጅተው ነበር።

10. በ2003 የይሖዋ ምሥክሮችን ቀናተኝነት የሚያሳይ ምን ነገር ተከናውኗል?

10 ደግሞም የሚደነቅ ሥራ አከናውነዋል! ወጣቶችም ሆኑ ጎልማሶች፣ ወላጆችም ሆኑ ልጆች እንዲሁም የአካል ጉዳተኛ የሆኑትን ጨምሮ ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሥልጠና ያገኙ ሁሉ ኢየሱስ በሰጠው ታላቅ ተልእኮ ተካፍለዋል፤ እየተካፈሉም ናቸው። (መዝሙር 148:12, 13፤ ኢዮኤል 2:28, 29) በ2003፣ በየወሩ በአማካይ 825,185 የሚያህሉ አስፋፊዎች አልፎ አልፎ ወይም በቋሚነት አቅኚ ሆነው በማገልገል የጥድፊያ ስሜት እንዳላቸው አሳይተዋል። በዚሁ ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምስራች ለሌሎች በመስበክ 1,234,796,477 ሰዓት አሳልፈዋል። በእርግጥም ይሖዋ ሕዝቦቹ በሚያሳዩት ቅንዓት ተደስቷል!

ወደ ሌሎች አገሮች ሄዶ ማገልገል

11, 12. ሚስዮናውያን መልካም ሥራ ማከናወናቸውን የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው?

11 ባለፉት ዓመታት፣ ከጊልያድ የተመረቁ ሚስዮናውያንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ከአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት የተመረቁ ወንድሞች አስደናቂ የሆነ ሥራ አከናውነዋል። ለምሳሌ ያህል በብራዚል በ1945 የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን እዚያ ሲደርሱ በአገሪቱ የነበሩት አስፋፊዎች 400 ገደማ ያህሉ ነበር። እነዚህ ሚስዮናውያንና ከእነርሱ በኋላ የመጡት ሌሎች ሚስዮናውያን፣ ቀናተኛ ከሆኑት ብራዚላውያን ወንድሞቻቸው ጋር በትጋት የሠሩ ሲሆን ይሖዋም ጥረታቸውን አብዝቶ ባርኮላቸዋል። የድሮውን ጊዜ የሚያስታውሱ አስፋፊዎች ብራዚል በ2003፣ 607,362 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት ማድረጓን ሲሰሙ ምንኛ ይደሰቱ ይሆን!

12 የጃፓንንም ሁኔታ እንመልከት። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት በአገሪቱ የነበሩት የመንግሥቱ ሰባኪዎች ወደ አንድ መቶ ገደማ ያህሉ ነበር። በጦርነቱ ወቅት የደረሰባቸው ጭካኔ የተሞላበት ስደት በቁጥር እንዲመናመኑ ያደረጋቸው ሲሆን ጦርነቱ ሲያበቃ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ ሁኔታ ሕያው የነበሩት በጣም ጥቂት ምሥክሮች ናቸው። (ምሳሌ 14:32) አቋማቸውን ጠብቀው የጸኑት እነዚህ በጣም የሚደነቁ ጥቂት ምሥክሮች በ1949 ከጊልያድ የተመረቁ 13 ሚስዮናውያንን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀበሉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ሚስዮናውያኑም ሞቅ ያለ ስሜትና የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያላቸውን ጃፓናውያን ወንድሞቻቸውን ለመውደድ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ከ50 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ በ2003 ጃፓን 217,508 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት አድርጋለች! ይሖዋ በዚያ አገር የሚኖሩ ሕዝቦቹን በእርግጥ አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። ከሌሎች በርካታ አገሮችም ተመሳሳይ ሪፖርቶች ተገኝተዋል። ወደ ሌሎች አገሮች ሄደው ለመስበክ ሁኔታቸው የፈቀደላቸው ወንጌላውያን ለምሥራቹ መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከታቸው በ2003 ምሥራቹ በዓለም ዙሪያ በ235 አገሮች፣ ደሴቶችና ክልሎች ሊዳረስ ችሏል። አዎን፣ ‘ከአሕዛብ ሁሉ’ እጅግ ብዙ ሰዎች እየመጡ ናቸው።

“ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ”

13, 14. ይሖዋ ምሥራቹን ሰዎች በሚሰሙት “ቋንቋ” መስበኩ ጠቃሚ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

13 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ ከተቀቡ በኋላ የተከናወነው በጽሑፍ ሰፍሮ የሚገኘው የመጀመሪያው ተዓምር ለተሰበሰቡት ሰዎች በልሳን መናገራቸው ነበር። እነርሱን ያዳመጧቸው ሰዎች ሁሉ በዓለም ዙሪያ የሚነገር አንድ ቋንቋ ምናልባትም ግሪክኛ መናገር ይችሉ ይሆናል። “በጸሎት የተጉ አይሁድ” እንደመሆናቸው መጠን ኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ የሚካሄዱትን የአምልኮ ሥርዓቶች የሚያውቁ ሊሆኑም ይችላሉ። ሆኖም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ምስራቹን ሲሰሙ በትኩረት ማዳመጥ ጀምረዋል።—የሐዋርያት ሥራ 2:5, 7-12

14 በዛሬው ጊዜም የስብከቱ ሥራ የሚካሄደው በተለያዩ ቋንቋዎች ነው። እጅግ ብዙ ሰዎች ከሕዝብ ብቻ ሳይሆን “ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ” እንደሚመጡ በትንቢት ተነግሮ ነበር። ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ ይሖዋ በዘካርያስ አማካኝነት የሚከተለውን ትንቢት አስነግሮ ነበር:- “ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው:- እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።” (ዘካርያስ 8:23) የይሖዋ ምሥክሮች በአሁኑ ጊዜ በልሳን የመናገር ስጦታ ባይኖራቸውም ሰዎችን በቋንቋቸው ማስተማር ጠቃሚ እንደሆነ ይገነዘባሉ።

15, 16. ሚስዮናውያንም ሆኑ ሌሎች በአገሬው ቋንቋ ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ያጋጠሟቸውን ችግሮች የተወጡት እንዴት ነው?

15 እርግጥ በዛሬው ጊዜ እንደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ስፓንኛ የመሳሰሉ የብዙዎች መግባቢያ የሆኑ ጥቂት ቋንቋዎች አሉ። ይሁን እንጂ በሌሎች አገሮች ለማገልገል የተወለዱበትን ቦታ ትተው የሄዱ ሰባኪዎች “ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ ሁሉ” ምሥራቹ በሚገባቸው ቋንቋ እንዲደርሳቸው በአገሩ የሚነገረውን ቋንቋ ለመማር ጥረት ያደርጋሉ። (የሐዋርያት ሥራ 13:48) ይህ በጣም አድካሚ ሊሆን ይችላል። በደቡብ ፓስፊክ በምትገኘው ቱቫሉ በተባለች አገር የሚኖሩ ወንድሞች በቋንቋቸው ጽሑፍ ባስፈለጋቸው ጊዜ ከሚስዮናውያኑ መካከል አንዱ ይህን አድካሚ ሥራ ተያያዘው። በቋንቋው የተዘጋጀ መዝገበ ቃላት ስላልነበረ በቱቫሉ ቋንቋ የሚነገሩ ቃላትን መዝግቦ መያዝ ጀመረ። ከጊዜ በኋላ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ b የተባለው መጽሐፍ በቱቫሉ ቋንቋ ለመታተም በቅቷል። በኩራሳው የተመደቡ ሚስዮናውያን እዚያ ሲደርሱ በአገሩ በሚነገረው ቋንቋ፣ በፓፒያሜንቶ የተዘጋጀ የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፍም ሆነ መዝገበ ቃላት አልነበረም። ከዚህም ሌላ ቋንቋው እንዴት ይጻፍ የሚለው ጉዳይ በጣም ያወዛግብ ነበር። ይሁን እንጂ ሚስዮናውያኑ በመጡ በሁለት ዓመት ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የያዘ የመጀመሪያው ትራክት በዚያ ቋንቋ ሊዘጋጅ ችሏል። በዛሬው ጊዜ ፓፒያሜንቶ፣ መጠበቂያ ግንብ ከእንግሊዝኛ እኩል በወር ሁለት ጊዜ ከሚታተምባቸው 133 ቋንቋዎች መካከል አንዱ ነው።

16 ናሚቢያ ውስጥ የመጀመሪያዎቹን ሚስዮናውያን በትርጉም ሥራ ሊረዳቸው የሚችል የአገሩ ተወላጅ የሆነ ምሥክር አልነበረም። ከዚህም ሌላ በአገሩ ከሚነገሩት ቋንቋዎች አንዱ የሆነው ናማ በጽሑፎቻችን ላይ በብዛት የሚጠቀሱ “ፍጹም” እንደሚሉት ዓይነት ቃላት አልነበሩትም። አንድ ሚስዮናዊ እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በአብዛኛው ጽሑፎች እንዲተረጉሙልኝ የምጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስ ያጠኑ የነበሩ መምህራንን ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እውቀታቸው አነስተኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር በትክክል መተርጎሙን ለማረጋገጥ አብሬያቸው ተቀምጬ መከታተል ነበረብኝ።” ይሁንና ውሎ አድሮ ሕይወት በአዲሱ ዓለም የተባለው ትራክት ናሚቢያ ውስጥ በሚነገሩ አራት ቋንቋዎች ለመተርጎም በቅቷል። በዛሬው ጊዜ መጠበቂያ ግንብ በኳኛማ እና በንዶንጋ በወር አንድ ጊዜ ይታተማል።

17, 18. በሜክሲኮም ሆነ በሌሎች አገሮች ምስራቹን ለማዳረስ ምን ዓይነት ጥረት እየተደረገ ነው?

17 በሜክሲኮ አብዛኛው ሕዝብ የሚናገረው ቋንቋ ስፓንኛ ነው። ይሁን እንጂ ስፔናውያን አገሪቱን ከመቆጣጠራቸው በፊት በርካታ ቋንቋዎች ይነገሩ የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹም እስከ አሁን ድረስ አሉ። በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎች በአሁኑ ጊዜ በሰባት የሜክሲኮ ቋንቋዎችና በሜክሲኮ የምልክት ቋንቋ ይዘጋጃሉ። በማያ የተዘጋጀው የመንግሥት አገልግሎት በአሜሪካ ሕንዶች ቋንቋ ለመታተም የመጀመሪያው ነው። በእርግጥም ሜክሲኮ ውስጥ ካሉት 572,530 የመንግሥቱ አስፋፊዎች መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የማያ፣ የአዝቴክ እና ሌሎች ሕዝቦች ይገኙበታል።

18 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከአገራቸው ተሰድደው ወይም ደግሞ ኑሯቸውን ለማሻሻል ሲሉ ወደ ሌሎች አገሮች ሄደዋል። ከዚህም የተነሳ በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ አገር ዜጎች ይገኛሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ምስራቹን ለእነዚህ ሰዎች ለማዳረስ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል ጣሊያን ውስጥ ከጣሊያንኛ በተጨማሪ በሌሎች 22 ቋንቋዎች የሚካሄዱ ጉባኤዎችና ቡድኖች አሉ። የውጭ አገር ቋንቋ ተናጋሪ ለሆኑ ሰዎች ምስራቹን መስበክ እንዲችሉ ወንድሞችን ለመርዳት የጣሊያንኛ ምልክት ቋንቋን ጨምሮ 16 ቋንቋዎችን ለማስተማር በቅርቡ ኮርሶች ተሰጥተዋል። በሌሎች በርካታ አገሮችም የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው የውጭ አገር ሰዎች ምስራቹን ለማድረስ ተመሳሳይ ጥረት እያደረጉ ነው። አዎን፣ በይሖዋ እርዳታ እጅግ ብዙ ሰዎች ከተለያዩ ቋንቋዎች እየተሰባሰቡ ነው።

“በምድር ሁሉ ላይ”

19, 20. በዛሬው ጊዜ አስደናቂ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉት ጳውሎስ የተናገራቸው የትኞቹ ቃላት ናቸው? አብራራ።

19 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ባይሰሙ ነው ወይ? . . . በእውነት:- ድምፃቸው በምድር ሁሉ ላይ ቃላቸውም እስከ ዓለም ዳርቻ ወጣ።” (ሮሜ 10:18) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምስራቹ ያን ያህል ተዳርሶ ከነበረ በዘመናችን ደግሞ ከዚያ በበለጠ ሁኔታ ተሰብኳል! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ምናልባትም ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን “እግዚአብሔርን ሁልጊዜ እባርከዋለሁ፣ ምስጋናውም ዘወትር በአፌ ነው” እያሉ ነው።—መዝሙር 34:1

20 ከዚህም በላይ ሥራው አሁንም እያደገ ነው። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ማደጉን ቀጥሏል። በስብከቱ ሥራ ላይ ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ እየዋለ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተመላልሶ መጠየቆች እየተደረጉ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም እየተመሩ ነው። እንዲሁም ፍላጎት ያላቸው አዳዲስ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል። ባለፈው ዓመት በኢየሱስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ 16,097,622 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር ተገኝቷል። ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ እንዳለ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። ከባድ ስደት ተቋቁመው ያሳለፉ ወንድሞቻችን ያሳዩትን የአቋም ጽናት መኮረጃችንን እንቀጥል። በተጨማሪም ከ1919 ጀምሮ በይሖዋ አገልግሎት ተጠምደው የነበሩት ወንድሞቻችን ያሳዩት ዓይነት ቅንዓት እናንጸባርቅ። መዝሙራዊው “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ” በማለት ላሰማው ዝማሬ ምላሽ መስጠታችንን እንቀጥል።—መዝሙር 150:6

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በዚህ መጽሔት ከገጽ 18 እስከ 21 ድረስ የወጣውን ዓመታዊ ሪፖርት ተመልከት።

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ወንድሞች በ1919 ማከናወን የጀመሩት የትኛውን ሥራ ነው? ሥራው ምን ተፈታታኝ ገጽታዎች ነበሩት?

• ለስብከቱ ሥራ ድጋፍ ለመስጠት የተሰባሰቡት እነማን ናቸው?

• ሚስዮናውያንና ከአገራቸው ውጪ የሚያገለግሉ ሌሎች አስፋፊዎች ምን ሥራ አከናውነዋል?

• በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ሕዝቦቹ እያከናወኑት ያለውን ሥራ እየባረከው እንዳለ የሚያሳይ ምን ማስረጃ መጥቀስ ትችላለህ?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[ከገጽ 18-21 የሚገኝ ሰንጠረዥ]

የ2003 የአገልግሎት ዓመት የይሖዋ ምሥክሮች ዓለም አቀፍ ሪፖርት

(መጽሔቱን ተመልከት)

[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለው ቀውስ ክርስቲያኖች ምስራቹ እንደሚሰበክ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አላደረገም

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍንዳታ:- U.S. Navy photo፤ ሌሎቹ:- U.S. Coast Guard Photo

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እጅግ ብዙ ሰዎች ከነገድና ከቋንቋ ሁሉ ይሰባሰባሉ