በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጦርነት መልኩን ቀይሯል

ጦርነት መልኩን ቀይሯል

ጦርነት መልኩን ቀይሯል

ጦርነት ምንጊዜም ቢሆን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ነው። የትኛውም ጦርነት ቢሆን የወታደሮችን ሕይወት ያመሰቃቅላል እንዲሁም በሰላማውያን ሰዎች ላይ መከራ ያስከትላል። ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጦርነት መልኩን እየቀየረ መጥቷል። እንዴት?

በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ጦርነቶች የአንድ አገር ዜጎች በሆኑ ተቃራኒ አንጃዎች መካከል የሚካሄዱ የእርስ በርስ ግጭቶች ናቸው። ከዚህም በላይ የእርስ በርስ ጦርነቶች በአብዛኛው ለረጅም ጊዜ ይዘልቃሉ፣ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ ያስከትላሉ እንዲሁም በሁለት አገሮች መካከል ከሚካሄዱ ጦርነቶች ይበልጥ በአገሪቱ ላይ ውድመት ያስከትላሉ። “የእርስ በርስ ጦርነቶች በሺዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ሞት የሚያስከትሉ፣ ለጾታ መነወርና ለስደት ብሎም ለዘር ማጥፋት ወንጀል ምክንያት የሚሆኑ ጭካኔ የተሞላባቸው ደም አፋሳሽ ዘመቻዎች ናቸው” ሲሉ ሁሊያን ካሳኖቫ የተባሉ ስፔናዊ ታሪክ ጸሐፊ ተናግረዋል። በእርግጥም አንድ ጎሳ በሌላው ላይ ግፍ ከፈጸመ ጠባሳው እስኪሽር ድረስ ረጅም ዘመን ሊፈጅ ይችላል።

ቀዝቃዛው ጦርነት ካበቃ በኋላ በአገራት መካከል የተካሄዱ ጦርነቶች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ አይደሉም። የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም “ከ1990-2000 ባለው ጊዜ ውስጥ ከተመዘገቡት ትላልቅ ጦርነቶች መካከል ከሦስቱ በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች ነበሩ” ሲል ዘግቧል።

እርግጥ፣ የእርስ በርስ ጦርነቶች ያን ያህል አስጊ ላይመስሉና በዓለም አቀፉ የመገናኛ ብዙኃንም ላይዘገቡ ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ ጦርነቶች የሚያስከትሉት ሥቃይና ውድመት ከሌላው ጦርነት የሚተናነስ አይደለም። በእርስ በርስ ጦርነቶች ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል። እንዲያውም ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት፣ በጦርነት በሚታመሱ ሦስት አገሮች ውስጥ ብቻ ማለትም በሱዳን፣ በአፍጋኒስታንና በኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል። በባልካን አገሮች የከረረ የጎሳ ግጭት ወደ 250,000 ገደማ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን በኮሎምቢያ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በዘለቀው የሽምቅ ውጊያ ሳቢያ 100,000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

የእርስ በርስ ጦርነት በጭካኔ የተሞላ መሆኑ ይበልጥ የሚታየው በተለይ በልጆች ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ነው። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሪፖርት እንደሚያመለክተው ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ልጆች ለሞት ተዳርገዋል። ሌሎች ስድስት ሚሊዮን የሚያህሉ ቆስለዋል። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ልጆች ወደ ውትድርና ዓለም እንዲገቡ እየተገደዱ ነው። ወታደር የሆነ አንድ ልጅ እንዲህ ብሏል:- “ሥልጠና ሰጡኝ። መሣሪያ አስታጠቁኝ። ዕፅ እወስድ ነበር። ሰላማውያን ሰዎችን ገድያለሁ። ብዙ ሰዎች ገድያለሁ። ይህን ያደረግሁት ጦርነት ላይ ስለነበርን ነው . . . የተሰጠኝን መመሪያ ነው የፈጸምኩት። የምሠራው ነገር መጥፎ መሆኑን አውቅ ነበር። ፈልጌ ያደረግሁት አይደለም።”

የእርስ በርስ ጦርነት የዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ክፍል በሆነባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች ሰላማዊ ኑሮ ምን እንደሚመስል እንኳ አያውቁም። የሚኖሩት ትምህርት ቤቶች በፈራረሱበትና ተፋላሚ አንጃዎች አመለካከታቸውን በአፈሙዝ በሚገልጹበት የዓለም ክፍል ነው። የ14 ዓመቷ ዱንጃ እንዲህ ትላለች:- “በጣም ብዙ ሰዎች ተገድለዋል . . . በአዕዋፍ ዝማሬ ፋንታ አሁን የሚሰማው እናታቸውን ወይም አባታቸውን፣ ወንድማቸውን ወይም እህታቸውን በሞት ያጡ ሕፃናት ለቅሶ ሆኗል።”

መንስዔዎቹ ምንድን ናቸው?

እንደዚህ ያሉ በጭካኔ የተሞሉ የእርስ በርስ ጦርነቶች እንዲቆሰቆሱ የሚያደርገው ምንድን ነው? የዘርና የጎሳ ጥላቻ፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የፍትሕ መዛባትና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት በዋነኝነት የሚጠቀሱ መንስዔዎች ናቸው። ሌላው መሠረታዊ መንስዔ ደግሞ ለሥልጣንና ለገንዘብ መስገብገብ ነው። የፖለቲካ መሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በሥልጣን ጥመኝነት በመነሳሳት ግጭቱ እንዲባባስ የሚያደርግ ጥላቻ ይቆሰቁሳሉ። የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደገለጸው ብዙዎች የትጥቅ ትግል ውስጥ የሚገቡት “የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ነው።” ሪፖርቱ አክሎም እንዲህ ብሏል:- “ፖለቲካዊና ወታደራዊ ባለ ሥልጣናት ከሚያካሂዱት መጠነ ሰፊ የአልማዝ ንግድ አንስቶ መሣሪያ የታጠቁ ወጣቶች መንደር ውስጥ እስከሚፈጽሙት ዝርፊያ ድረስ ስግብግብነት በብዙ መልኩ ይታያል።”

አደገኛ የሆኑ መሣሪያዎች በቀላል ዋጋ እንደልብ መገኘታቸው እልቂቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል። በዓመት ወደ 500,000 ገደማ ሰዎች፣ በአብዛኛው ሴቶችና ሕፃናት የሚገደሉት በነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች ነው። በአንድ የአፍሪካ አገር ውስጥ ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ዶሮ በሚገዛበት ዋጋ ማግኘት ይቻላል። የሚያሳዝነው ነገር በአንዳንድ ቦታዎች ጠመንጃ የዶሮን ያህል በገፍ የሚገኝ እየሆነ መምጣቱ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 500 ሚሊዮን ቀላልና የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎች እንደሚገኙ የሚገመት ሲሆን ይህም ለ12 ሰዎች 1 ይደርሳል ማለት ነው።

ከባድ የእርስ በርስ ግጭቶች 21ኛው መቶ ዘመን ተለይቶ የሚታወቅበት ገጽታ ይሆን? የእርስ በርስ ጦርነቶችን በቁጥጥር ሥር ማዋል ይቻላል? ሰዎች መግደል የሚያቆሙበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የእርስ በርስ ጦርነት የሚያስከትለው አሳዛኝ ውጤት

በቴክኖሎጂ የተራቀቁ መሣሪያዎች ጥቅም ላይ ባልዋሉባቸው ሆኖም ጭካኔ በሚንጸባረቅባቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች ከሚሞቱት ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ወታደሮች ሳይሆኑ ሰላማውያን ሰዎች ናቸው። ጦርነት በልጆች ላይ የሚያደርሰውን ችግር የሚከታተሉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዋና ጸሐፊው አማካሪ የሆኑት ግራሰ ማሼል “በብዙ ሁኔታዎች እንደታየው በጦርነት መሃል ሕፃናት የሚሞቱት በአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ ተገድለው እንደሆነ ግልጽ ነው” ብለዋል።

አስገድዶ መድፈር አንዱ ወታደራዊ ስልት ሆኗል። በጦርነት በሚታመሱ አንዳንድ አካባቢዎች አማጺያን በተቆጣጠሯቸው መንደሮች ውስጥ የሚገኙ ኮረዳዎችን በሙሉ ይደፍራሉ። ዓላማቸው ሽብር መንዛት አሊያም በቤተሰብ መካከል ያለውን ትስስር መበጠስ ነው።

ጦርነትን ተከትሎ ረሃብና በሽታ ይከሰታል። የእርስ በርስ ጦርነት በሚኖርበት ጊዜ የሚዘራውም ሆነ የሚሰበሰበው እህል በጣም ጥቂት ይሆናል፣ የሕክምና አገልግሎት ይዳከማል እንዲሁም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚላከውን እርዳታ ለችግረኞች ማድረስ አዳጋች ይሆናል። በአፍሪካ በተደረገ የእርስ በርስ ጦርነት ላይ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳሳየው 20 በመቶ የሚሆኑት ሰዎች የሞቱት በበሽታ ሲሆን 78 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ ነው። በቀጥታ በውጊያው ሳቢያ የሞቱት 2 በመቶ ብቻ ናቸው።

በአማካይ በየ22 ደቂቃው፣ የተቀበረ ፈንጂ በመርገጡ ምክንያት እግሩን ወይም ሕይወቱን የሚያጣ ሰው ይኖራል። ከ60 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ በግምት ከ60 እስከ 70 ሚሊዮን የሚያህሉ ፈንጂዎች በየቦታው ተቀብረው ይገኛሉ።

ሰዎች ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 50 ሚሊዮን ስደተኞችና ተፈናቃዮች ሲኖሩ ከእነዚህ መሃል ግማሽ ያህሉ ሕፃናት ናቸው።

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

COVER: Boy: Photo by Chris Hondros/Getty Images

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Photo by Chris Hondros/Getty Images