በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሰው ሳይሆን ለአምላክ ክብር ስጡ

ለሰው ሳይሆን ለአምላክ ክብር ስጡ

ለሰው ሳይሆን ለአምላክ ክብር ስጡ

ባለፉት ወራት በምድር ዙሪያ የሚገኙ ጽድቅ ወዳድ ሕዝቦች “ለአምላክ ክብር ስጡት” በተሰኘው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለአምላክ እንዴት ክብር መስጠት እንደሚችሉ ተምረዋል። እስቲ በስብሰባው ላይ የቀረበውን ትምህርት እንከልስ።

ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትምህርት ፕሮግራም በአብዛኞቹ ቦታዎች ለሦስት ቀናት የተካሄደ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ደግሞ ለአራት ቀናት የዘለቀ ልዩ ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ተደርጎ ነበር። በስብሰባው ላይ መንፈሳዊ አድናቆትን የሚገነቡ ንግግሮችን፣ እምነት የሚያጠነክሩ ተሞክሮዎችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳዩ ሠርቶ ማሳያዎችንና የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያጋጠሟቸውን ፈተናዎች የሚያሳይ ጥንታዊ አለባበስ የተንጸባረቀበት ድራማን ጨምሮ ከ30 በላይ ክፍሎች ቀርበው ነበር። በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ከነበረ ይህን ርዕስ ስታነብብ በስብሰባው ላይ የያዝከውን ማስታወሻ መከለስ ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ የቀረበበትን ያንን ግብዣ እንደሚያስታውስህና ተጨማሪ እውቀት እንደሚያስገኝልህ እንተማመናለን።

የመጀመሪያው ቀን ጭብጥ:- ‘ይሖዋ ሆይ፣ ክብር ልትቀበል ይገባሃል’

ስብሰባው በመዝሙርና በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የመጀመሪያው ተናጋሪ “የተሰበሰብነው ለአምላክ ክብር ለመስጠት ነው” በሚለው የስብሰባውን ዋነኛ ዓላማ የሚገልጽ ንግግር ለተሰብሳቢዎቹ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገላቸው። ተናጋሪው ራእይ 4:10, 11 በመጥቀስ የስብሰባውን አጠቃላይ ጭብጥ አጎላ። በንግግሩ መግቢያ አካባቢ ለአምላክ ክብር መስጠት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ጠቀሰ። ከዚያም የመዝሙርን መጽሐፍ በመጥቀስ ለአምላክ ክብር መስጠት “ማምለክን፣” “ማመስገንን” እና “ማወደስን” እንደሚጨምር ጎላ አድርጎ ገለጸ።—መዝሙር 95:6 አ.መ.ት፤ 100:4, 5 አ.መ.ት፤ 111:1, 2

የሚቀጥለው ንግግር “ለአምላክ ክብር የሚሰጡ ሁሉ ይባረካሉ” የሚል ነበር። ተናጋሪው አንድ ትኩረት የሚስብ ነጥብ ጠቀሰ። በዓለም ዙሪያ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች በ234 አገሮች ውስጥ ስለሚያገለግሉ ይሖዋን ለሚያወድሱ ሰዎች ምንጊዜም ፀሐይ አትጠልቅም ሊባል ይቻላል። (ራእይ 7:15) በዚህ ንግግር ላይ በተለያየ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፎች ከተሰማሩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ቃለ ምልልስ የተደረገ ሲሆን ይህም የአድማጮችን ልብ በእጅጉ ደስ አሰኝቷል።

ቀጣዩ ንግግር “ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል” የሚል ርዕስ ነበረው። ግዑዙ ሰማይ አፍ አውጥቶ ባይናገርም የአምላክን ታላቅነት የሚያጎላ ሲሆን እርሱ ለሚያደርግልን ፍቅራዊ እንክብካቤ ልባዊ አድናቆት እንዲኖረን ያደርጋል። ይህ በንግግሩ ውስጥ በስፋት ተብራርቷል።—ኢሳይያስ 40:26

ስደት፣ ተቃውሞ፣ ዓለማዊ ተጽዕኖዎችና የኃጢአት ዝንባሌዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያላሉ ይፈታተኗቸዋል። በዚህም ምክንያት ተሰብሳቢዎቹ “በንጹሕ አቋማችሁ ጸንታችሁ ኑሩ” የሚለውን ንግግር በጥሞና ማዳመጥ ያስፈልጋቸው ነበር። መዝሙር 26 ቁጥር በቁጥር የተብራራ ሲሆን የደረሰበትን የሥነ ምግባር ፈተና በጽናት ለተቋቋመ አንድ ተማሪና አጠያያቂ በሆነ መዝናኛ ብዙ ጊዜ ያጠፋ ለነበረ ሆኖም ችግሩን ለማሸነፍ እርምጃ ለወሰደ ወጣት ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸዋል።

የጠዋቱ ፕሮግራም የተደመደመው “ክብር የተላበሱት ትንቢታዊ ራእዮች ለተግባር ያንቀሳቅሱናል!” በሚለው የስብሰባውን ጭብጥ የሚያብራራ ንግግር ነበር። ተናጋሪው ስለ አምላክ መሲሐዊ መንግሥት መቋቋምና እንቅስቃሴ መጀመር በተመለከቷቸው ክብር የተላበሱ ትንቢታዊ ራእዮች እምነታቸው የተጠናከረውን እንደ ነቢዩ ዳንኤል፣ ሐዋርያው ዮሐንስና ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሉ ምሳሌዎች ጠቀሰ። ወንድም በመጨረሻው ዘመን እንደምንኖር የሚያሳዩትን ግልጽ ማስረጃዎች የዘነጉትን አስመልክቶ እንዲህ አለ:- “እንደነዚህ ያሉት ሰዎች ክርስቶስ በመንግሥቱ ክብር መገኘቱን በእምነት ዓይናቸው ማየት እንደሚጀምሩና ከዚህም መንፈሳዊ ብርታት ለማግኘት የሚያስችል እርዳታ እንደሚያገኙ ከልብ ተስፋ እናደርጋለን።”

የከሰዓት በኋላው ፕሮግራም የጀመረው “ይሖዋ ክብሩን ለትሑታን ሰዎች ይገልጣል” በሚለው ንግግር ነበር። ተናጋሪው ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ቢሆንም ትሕትና በማሳየት ረገድ እንዴት ምሳሌ እንደሚሆነን ተናገረ። (መዝሙር 18:35) ይሖዋ ከልብ ትሑት የሆኑ ሰዎችን ይወድዳል፤ ሆኖም ከእኩዮቻቸው ወይም ከበላዮቻቸው ጋር ሲሆኑ ትሑት መስለው የበታቾቻቸውን ግን የሚያመናጭቁትን ይጠላል።—መዝሙር 138:6

ከዚያም “የአሞጽ ትንቢት—ለዘመናችን የሚያስተላልፈው መልእክት” የሚለውን ጭብጥ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚያጎላ ተከታታይ ንግግር ቀረበ። የመጀመሪያው ተናጋሪ አሞጽን በምሳሌነት በመጥቀስ መጪውን የይሖዋ ፍርድ በሚመለከት ሰዎችን የማስጠንቀቅ ኃላፊነት እንደተጣለብን ተናገረ። የንግግሩ ርዕስ “የአምላክን ቃል በድፍረት ተናገሩ” የሚል ነበር። ሁለተኛው ተናጋሪ “ይሖዋ አምላክ ክፋትንና ሥቃይን ከዚህች ምድር ያስወግድ ይሆን?” የሚል ጥያቄ አቀረበ። “በክፉዎች ላይ የሚወርድ መለኮታዊ ፍርድ” በሚል ጭብጥ ያቀረበው ንግግር መለኮታዊ ፍርድ ምንጊዜም ፍትሐዊ መሆኑን፣ ከፍርዱ ማምለጥ እንደማይቻል እንዲሁም ፍርዱ የሚፈጸመው ጥፋት በሚገባቸው ሰዎች ላይ እንጂ በጅምላ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነበር። የመጨረሻው ተናጋሪ ንግግሩን ያቀረበው “ይሖዋ ልብን ይመረምራል” በሚል ጭብጥ ነበር። ይሖዋን ለማስደሰት የሚሹ ሁሉ በአሞጽ 5:15 ላይ የሚገኘውን “ክፉውን ጥሉ፣ መልካሙንም ውደዱ” የሚለውን ምክር ይታዘዛሉ።

የወይን ጠጅን የመሰሉ ልብን ደስ የሚያሰኙ የአልኮል መጠጦች ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ። “የአልኮል መጠጥ ወጥመድ እንዳይሆንባችሁ ተጠንቀቁ” በሚል ርዕስ ንግግር ያቀረበው ወንድም አንድ ሰው ባይሰክርም እንኳን ከልክ በላይ መጠጣቱ ሊያስከትልበት የሚችለውን አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳት ዘረዘረ። ከዚያም እንደ መመሪያ ሊያገለግል የሚችለውን የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ጠቀሰ:- መጠጥን የመቋቋም ችሎታ ከሰው ወደ ሰው የሚለያይ በመሆኑ የማሰብንና የማመዛዘን ችሎታን የሚያዛባ ከሆነ መጠኑ ምንም ይሁን ምን ከመጠን አልፏል ሊባል ይችላል።—ምሳሌ 3:21, 22

የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ውስጥ በመሆኑ “ይሖዋ ‘በመከራችን ጊዜ መጠጊያችን ነው’” በሚል ጭብጥ የቀረበው ቀጣዩ ንግግር በእርግጥም አድማጮችን የሚያጽናና ነበር። ጸሎት፣ መንፈስ ቅዱስና ክርስቲያን ወንድሞቻችን ችግሮችን እንድንቋቋም ሊረዱን ይችላሉ።

“ለመጪዋ ገነት አምሳያ የምትሆነው ‘መልካሚቱ ምድር’” በሚል ጭብጥ በቀረበው የዕለቱ የመጨረሻ ንግግር ላይ መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ የተሰኘ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ካርታዎችን የያዘ አዲስ ጽሑፍ መውጣቱ ሲገለጽ ተሰብሳቢዎቹ ሁሉ በእጅጉ ተደስተዋል።

የሁለተኛው ቀን ጭብጥ:- “ክብሩን . . . ለአሕዛብ ንገሩ”

የዕለቱ ጥቅስ ከተብራራ በኋላ “የይሖዋን ክብር እንደ መስተዋት እናንጸባርቃለን” የሚል ጭብጥ ያለው የአውራጃ ስብሰባው ሁለተኛ ተከታታይ ንግግር ቀረበ። የመጀመሪያው ንግግር “በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን በመስበክ” ላይ ያተኮረ ሲሆን ከመስክ አገልግሎት የተገኙ ተሞክሮዎችም በሠርቶ ማሳያ ቀርበዋል። “በመንፈሳዊ የታወሩ ሰዎች ዓይናቸው እንዲበራ በማድረግ” የሚል ጭብጥ በነበረው በቀጣዩ ንግግር ሥር ደግሞ ተናጋሪው ተመላልሶ መጠየቅ ሲደረግ የሚያሳይ ሠርቶ ማሳያ እንዲቀርብ አድርጓል። “በአገልግሎታችን ይበልጥ በመሥራት” በሚል ርዕስ የቀረበው የመጨረሻው የተከታታይ ንግግሮቹ ክፍል ከመስክ አገልግሎት የተገኙ ተሞክሮዎችን ባካተቱ አስደሳች ቃለ ምልልሶች የተደገፈ ነበር።

ቀጣዩ የፕሮግራሙ ክፍል “ያለ ምክንያት መጠላት” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ከአምላክ ባገኙት ብርታት የደረሰባቸውን ተቃውሞ በጽናት ከተወጡ ታማኝ ክርስቲያኖች ጋር አበረታች ቃለ ምልልሶች ተደርገዋል።

በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በጉጉት ከሚጠበቁት ክፍሎች መካከል የጥምቀት ንግግርና ብቃቱን የሚያሟሉ ዕጩ ተጠማቂዎችን ሙሉ በሙሉ ውኃ ውስጥ በማጥለቅ የሚከናወነው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ነው። ጥምቀት አንድ ሰው ራሱን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ መወሰኑን ያሳያል። ስለሆነም የጥምቀት ንግግሩ “ራሳችንን ስንወስን የገባነውን ቃል ጠብቀን መኖራችን ለአምላክ ክብር ያመጣል” የሚል ጭብጥ ያለው መሆኑ የተገባ ነው።

የከሰዓት በኋላው ስብሰባ የጀመረው ራሳችንን እንድንመረምር በሚያበረታታ ንግግር ሲሆን “በሌሎች ዘንድ ክብር ስለማግኘት የክርስቶስ ዓይነት አመለካከት ማዳበር” የሚል ርዕስ ነበረው። ተናጋሪው የሚከተለውን ነጥብ ጠቀሰ:- ክርስቶስ በትሕትና ረገድ የተወልንን ምሳሌ በመኮረጅ በሌሎች ዘንድ አክብሮት ማግኘት እንችላለን። ስለሆነም አንድ ክርስቲያን በሌሎች ዘንድ ልቆ ለመታየት ሲል ኃላፊነት ለማግኘት መጓጓት የለበትም። ራሱን እንዲህ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል:- ‘ሰዎች ትኩረት ቢሰጡኝም ባይሰጡኝም ሌሎችን የሚጠቅም እስከሆነ ድረስ የትኛውንም ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ ነኝ?’

ደክሞህ ያውቃል? ምን ጥያቄ አለው ትል ይሆናል። “ሰውነታችን ቢዝልም መንፈሳችን አይደክምም” የሚለው ንግግር የብዙዎችን አድናቆት አትርፏል። ለረጅም ዓመታት በእውነት ቤት ከቆዩ ክርስቲያኖች ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ ይሖዋ ‘በመንፈሱ አማካኝነት በኃይል እንድንጠነክር’ ሊያደርገን እንደሚችል የሚያሳይ ነበር።—ኤፌሶን 3:16

ልግስና በውርስ የምናገኘው ሳይሆን ተምረን የምናዳብረው ባሕርይ ነው። “ለመርዳትና ለማካፈል የተዘጋጀን እንሁን” የሚለው ንግግር ይህን ቁልፍ ነጥብ የሚያጎላ ነበር። ተናጋሪው አድማጮች በጉዳዩ ላይ በጥሞና እንዲያስቡበት ለማድረግ የሚከተለውን ጥያቄ አቀረበ:- “እኛስ አረጋውያንን፣ የታመሙትን፣ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸውን ወይም የብቸኝነት ስሜት የሚሰማቸውን ለመርዳት በቀን ውስጥ የተወሰኑ ደቂቃዎችን መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ነን?”

“‘እንግዳ ለሆኑ ድምፆች’ ጆሯችሁን እንዳትሰጡ ተጠንቀቁ” የሚለው ንግግር የአድማጮችን ትኩረት ስቦ ነበር። በዚህ ንግግር ላይ የኢየሱስ ተከታዮች “መልካም እረኛ” የሆነውን የክርስቶስን ድምፅ ብቻ በሚሰሙና በዲያብሎስ ተጽዕኖ ሥር ካሉት አካላት የሚመጡትን ‘እንግዳ ድምፆች’ በማያዳምጡ በጎች ተመስለዋል።—ዮሐንስ 10:5, 14, 27

አንድ የመዘምራን ጓድ መዝሙሩ በግልጽ እንዲሰማ በኅብረት መዘመር ይኖርበታል። በዓለም ዙሪያ ያሉ እውነተኛ አምላኪዎችም ለአምላክ ክብር ለመስጠት አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። በመሆኑም “‘በአንድ አፍ’ አምላክን አክብሩ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር ሁላችንም “ንጹሕን ልሳን” መናገርና ይሖዋን ‘አንድ ሆነን’ ማገልገል የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ጠቃሚ ሐሳቦችን አስጨብጦናል።—ሶፎንያስ 3:9

“ልጆቻችን—ውድ ስጦታ ናቸው” የሚለው የዕለቱ የመጨረሻ ንግግር በተለይም ትንንሽ ልጆች ያሏቸውን ወላጆች ያስደሰተ ነበር። አድማጮች 256 ገጽ ያለው አዲስ መጽሐፍ መውጣቱን ሲሰሙ በጣም ተደስተዋል። ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተሰኘው ይህ አዲስ መጽሐፍ ወላጆች የይሖዋ ስጦታ ከሆኑት ልጆቻቸው ጋር አስደሳች መንፈሳዊ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለመርዳት ተብሎ የተዘጋጀ ነው።

የሦስተኛው ቀን ጭብጥ:- “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት”

የአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ቀን የተጀመረው በዕለቱ ጥቅስ ላይ በተደረገው መንፈሳዊ ውይይት ነበር። የዕለቱ ፕሮግራም የመጀመሪያ ክፍል በቤተሰብ ሕይወት ላይ ያተኮረ ነበር። “ወላጆች፣ ቤተሰባችሁን ገንቡ” የሚለው የመጀመሪያው ንግግር የአድማጮችን አእምሮ ለቀጣዩ ክፍል ያዘጋጀ ነበር። ንግግሩን ያቀረበው ወንድም ወላጆች የቤተሰባቸውን ቁሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ከጠቀሰ በኋላ ዋነኛ ኃላፊነታቸው ግን የልጆቻቸውን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላት መሆኑን አስረዳ።

ቀጥሎ የቀረበው ንግግር ያተኮረው በልጆች ላይ ሲሆን “ወጣቶች ይሖዋን ማወደስ የሚችሉት እንዴት ነው?” የሚል ርዕስ ነበረው። ተናጋሪው ወጣቶች በቁጥር በጣም ብዙ ስለሆኑና የወጣትነት ቅንዓታቸው የሚያረካ በመሆኑ ‘በጠዋት ጤዛ’ እንደሚመሰሉ ተናገረ። ትልልቅ ወንድሞችና እህቶች ከወጣቶች ጋር ይሖዋን ማገልገል መቻላቸው በጣም ያስደስታቸዋል። (መዝሙር 110:3 NW) በዚህ ንግግር ውስጥ ምሳሌ ከሚሆኑ ወጣቶች ጋር የተደረጉ አስደሳች ቃለ ምልልሶችም ተካትተዋል።

ጥንታዊ አለባበስ የተንጸባረቀበት ድራማ የአውራጃ ስብሰባዎች ልዩ ገጽታ ነው። በዚህ የአውራጃ ስብሰባ ላይም እንዲህ ያለ ድራማ ቀርቧል። “ተቃውሞ ቢኖርም በድፍረት መመስከር” የተሰኘው ድራማ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበሩት የኢየሱስ ተከታዮች የሚያሳይ ሲሆን አዝናኝ ብቻ ሳይሆን ትምህርታዊም ነበር። ከድራማው በኋላ “ምሥራቹን ‘ያለማሰለስ’ ስበኩ” በሚል ርዕስ የቀረበው ንግግር የድራማውን ዋና ዋና ነጥቦች ያስጨበጠ ነበር።

በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ የእሁዱ ፕሮግራም ዋነኛ ክፍል የሆነውን የሕዝብ ንግግር በጉጉት ይጠባበቁ የነበረ ሲሆን ርዕሱ “በአሁኑ ጊዜ ለአምላክ ክብር እየሰጡ ያሉት እነማን ናቸው?” የሚል ነበር። ተናጋሪው በአጠቃላይ ሲታይ ሳይንስም ሆነ ሃይማኖት ለአምላክ ክብር እንዳልሰጡ የሚያሳዩ ማስረጃዎች አቀረበ። በአሁኑ ጊዜ ለአምላክ ክብር የሚሰጡት ስለ ይሖዋ እውነቱን ለሰዎች እየሰበኩና እያስተማሩ ያሉት እንዲሁም ለስሙ የቆሙት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።

ከሕዝብ ንግግሩ በኋላ የሳምንቱ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ፍሬ ሐሳብ በአጭሩ የቀረበ ሲሆን ከዚያም “‘ብዙ ፍሬ በማፍራት’ ለይሖዋ ክብር ስጡ” የሚል ርዕስ ያለው የመደምደሚያ ንግግር ቀረበ። ተናጋሪው ፈጣሪ ለሆነው ለይሖዋ ክብር ልንሰጥባቸው በምንችላቸው የተለያዩ መንገዶች ላይ ያተኮረ ባለ አሥር ነጥብ የአቋም መግለጫ ለአድማጮች አቀረበ። አድማጮች በአቋም መግለጫው መስማማታቸውን ለማሳየት “አዎ” በማለት የሰጡት ምላሽ በምድር ዙሪያ የአውራጃ ስብሰባው በተካሄደባቸው ቦታዎች ሁሉ አስተጋብቷል።

የአውራጃ ስብሰባው ሲደመደም “ለአምላክ ክብር ስጡት” የሚለው የስብሰባው ጭብጥ በእያንዳንዱ ተሰብሳቢ ጆሮ ውስጥ ያቃጭል ነበር። እኛም በይሖዋ መንፈስና በምድራዊ ድርጅቱ እርዳታ ለሰዎች ሳይሆን ለአምላክ ክብር መስጠታችንን እንድንቀጥል የሁላችንም ምኞች ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች

በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በአውስትራሊያ፣ በአውሮፓ እንዲሁም በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ ለአራት ቀናት የቆዩ ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች ተደርገው ነበር። ከዓለም ዙሪያ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ልዑካን ሆነው በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ተገኝተው ነበር። በዚህም የአካባቢው ወንድሞችና ልዑካኑ ‘እርስ በርስ ሊበረታቱ’ ችለዋል። (ሮሜ 1:12 አ.መ.ት) ከዚህ ቀደም ይተዋወቁ የነበሩ ምሥክሮች እንደገና የተገናኙ ሲሆን ከሌሎች ምሥክሮች ጋር ለመተዋወቅ የሚያስችል አጋጣሚም ተፈጥሮላቸዋል። “ከሌሎች አገሮች የተገኙ ሪፖርቶች” የሚለው የስብሰባው ክፍልም ለብሔራት አቀፍ ስብሰባዎቹ ልዩ ገጽታ አላብሷቸዋል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለአምላክ ክብር የሚሰጡ አዳዲስ ጽሑፎች

“ለአምላክ ክብር ስጡት” በተሰኙት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ሁለት አዳዲስ ጽሑፎች ወጥተዋል። መልካሚቱን ምድር ተመልከቱ በሚል ርዕስ የወጣው ባለ 36 ገጽ ጽሑፍ ጠንካራ ሽፋን ያለው ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ቦታዎችን የሚያሳዩ ካርታዎችና ፎቶግራፎች ይዟል። እያንዳንዱ ገጽ ባለ ሙሉ ቀለም ሥዕሎች ያሉት ከመሆኑም በላይ የአሦርን፣ የባቢሎንን፣ የሜዶ ፋርስን፣ የግሪክንና የሮምን ግዛቶች የሚያሳዩ ካርታዎችን አካትቷል። ኢየሱስ ያገለገለባቸውን ቦታዎችና የክርስትናን መስፋፋት የሚያሳዩ ሌሎች ካርታዎችም አሉት።

ከታላቁ አስተማሪ ተማሩ የተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ 256 ገጾች ያሉት ሲሆን 230 የሚያህሉ ሥዕሎችም ይዟል። ሥዕሎቹን በመመልከትና በመጽሐፉ ውስጥ የቀረቡትን አመራማሪ ጥያቄዎች በመመለስ ብቻ እንኳ ከልጆች ጋር አስደሳች የጥናት ጊዜ ማሳለፍ ይቻላል። ይህ አዲስ ጽሑፍ ሰይጣን የትናንሽ ልጆቻችንን አእምሮ ለመበከል የሚሰነዝረውን ጥቃት ለመከላከል ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሚስዮናውያን እምነት የሚያጠነክሩ ተሞክሮዎችን ተናግረዋል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጥምቀት ሥነ ሥርዓት “ለአምላክ ክብር ስጡት” የተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ዋነኛ ክፍል ነበር

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወጣቶችም ሆኑ አዋቂዎች በቀረበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድራማ ተደስተዋል