በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማን በሰጠው ተስፋ መተማመን ይቻላል?

ማን በሰጠው ተስፋ መተማመን ይቻላል?

ማን በሰጠው ተስፋ መተማመን ይቻላል?

‘ሲሾም ያልገባው ቃል አልነበረም፤ በተግባር ሲታይ ግን አንዱንም አልፈጸመም።’—ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ፣ በዊልያም ሼክስፒር

ሼክስፒር የተናገረው በ16ኛው መቶ ዘመን በእንግሊዝ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣን የነበራቸ ካርዲናል ቶማስ ዎልሴይ ስለሰጧቸው ተስፋዎች ነው። አንዳንዶች ይህ የሼክስፒር አባባል ዛሬም ቢሆን ለአብዛኞቹ ተስፋዎች ይሠራል ብለው ያምናሉ። ሰዎች ብዙ ነገር እንደሚደረግላቸው ቃል ይገባላቸዋል፤ የሚፈጸምላቸው ግን ከስንት አንዱ ነው። ከዚህ አንጻር ሰዎች ማንኛውንም ተስፋ ለምን እንደሚጠራጠሩ መገመት አያዳግተንም።

እንደጉም በነው የጠፉ ተስፋዎች

በ1990ዎቹ ዓመታት በባልካን አገሮች አስከፊ ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በቦስኒያ የምትገኘውን የሰሬብሬኒካ ከተማን “ከጦርነት ነጻ ቀጠና” በማለት አውጆ ነበር። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይህን አዋጅ አስተማማኝ ዋስትና አድርጎ ተስፋ ጥሎበት ነበር። በሰሬብሬኒካ ከተማ የተጠለሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊም ስደተኞችም እንዲሁ ተስፋ አድርገው ነበር። ይሁን እንጂ ከተማዋ ከጦርነት ነጻ ትሆናለች የሚለው ተስፋ መና ሆኖ ቀረ። (መዝሙር 146:3) በሐምሌ 1995 ተቃዋሚ ኃይሎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ሰላም አስከባሪ ኃይል ገፍተው በማስወጣት ከተማዋን በቁጥጥራቸው ሥር አደረጉ። በዚያ ወቅት ቢያንስ 1,200 ሙስሊም ሰላማዊ ሰዎች ሲገደሉ ከ6,000 የሚበልጡት ደግሞ የደረሱበት አልታወቀም።

የሰው ልጅ ሕይወት የሕልም እንጀራ ሆነው በቀሩ ተስፋዎች የተሞላ ነው። ሰዎች በየዕለቱ በሚሰሟቸው “ስፍር ቁጥር የሌላቸው የተጋነኑና አሳሳች ማስታወቂያዎች” እንደሚታለሉ ይሰማቸዋል። “በርካታ ፖለቲከኞች በምረጡኝ ዘመቻዎች ወቅት በሚሰጧቸው ከንቱ ተስፋዎች” ግራ ተጋብተዋል። (ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ፣ ጥራዝ 15 ገጽ 37) መንጋቸውን ለመንከባከብ ቃል የገቡ እምነት የተጣለባቸው የሃይማኖት መሪዎች በምዕመናኖቻቸው ላይ ለመናገር የሚቀፍ ድርጊት ሲፈጽሙ ይታያሉ። ርኅራኄና አሳቢነት ይጠይቃሉ በሚባሉት እንደ ትምህርትና ሕክምና ባሉት ዘርፎች የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳን የተጣለባቸውን ተስፋ ችላ ብለው በእጃቸው ያሉትን ሰዎች በዝብዘዋል፣ አልፎ ተርፎም ገድለዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ቃልን ሁሉ እንዳናምን ማስጠንቀቁ ምንም አያስደንቅም!—ምሳሌ 14:15

የገቡትን ቃል የሚጠብቁም አሉ

እርግጥ ነው፣ ከባድ መሥዋዕትነት የሚጠይቅባቸው ቢሆን እንኳን ቃላቸውን የሚጠብቁ ብዙ ሰዎች እንዳሉ እሙን ነው። (መዝሙር 15:4) ቃላቸውን ከምንም በላይ ያከብራሉ። ሌሎች ደግሞ በበጎ ዓላማ ተነሳስተው የሚገቡትን ቃል ለመጠበቅ ልባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ምክንያቶች የተነሳ ሳይፈጽሙት ይቀራሉ። በጣም የታሰበባቸው እቅዶች እንኳን በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሽፉ ይችላሉ።—መክብብ 9:11

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ብዙ ሰዎች ማንኛውንም ተስፋ ለማመን ተቸግረዋል። ስለሆነም እምነት የሚጣልባቸው ተስፋዎች ይኖሩ ይሆን? የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። መልሱ አዎን የሚል ነው። የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ተስፋዎች ልንተማመን እንችላለን። የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጉዳይ ላይ የያዘውን ሐሳብ ለምን አትመረምርም? አንተም በሚሊዮን እንደሚቆጠሩ ሰዎች ሁሉ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል እንደሚቻል ትገነዘባለህ።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

AP Photo/Amel Emric