በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ታላቅ የምህንድስና ሥራ’

‘ታላቅ የምህንድስና ሥራ’

‘ታላቅ የምህንድስና ሥራ’

ከ3,000 ዓመታት በፊት በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን የይሖዋ ቤተ መቅደስ ኢየሩሳሌም ውስጥ በተገነባበት ወቅት የሚያምር የውኃ ገንዳ ከነሐስ ተሠርቶ በቤተ መቅደሱ መግቢያ አጠገብ ተቀምጦ ነበር። ይህ የውኃ ገንዳ 30 ቶን የሚመዝን ሲሆን 40,000 ሊትር ገደማ ውኃ ይይዝ ነበር። (1 ነገሥት 7:23-26) በካናዳ ብሔራዊ የምርምር ተቋም ውስጥ በቴክኒክ ባለሙያነት ይሠሩ የነበሩት አልበርት ዞይዶፍ ይህን የውኃ ገንዳ አስመልክተው ቢብሊካል አርኪኦሎጂስት በተባለው መጽሔት ላይ “በዕብራውያን ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑት ታላላቅ የምህንድስና ሥራዎች መካከል የሚመደብ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም” በማለት ተናግረዋል።

ይህ የውኃ ገንዳ የተሠራው እንዴት ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ “ንጉሡም [የነሐስ ዕቃዎቹን] በማቅለጥ በሸክላ ቅርጽ ውስጥ ፈሰው እንዲወጡ ያደረገው . . . በዮርዳኖስ ሸለቆ ነበር” ይላል። (1 ነገሥት 7:45, 46 አ.መ.ት) ዞይዶፍ እንዲህ ብለዋል:- “የቅርጽ አወጣጡ ሂደት ትላልቅ የነሐስ ደውሎችን ለመሥራት አሁን ድረስ ጥቅም ላይ ከሚውለው ዘዴ ጋር ተመሳሳይ መሆን አለበት። በመጀመሪያ ገንዳውን የሚመስል በአፉ የተደፋ ቅርጽ ማውጫ ከሸክላ ተሠርቶ በደንብ ከደረቀ በኋላ ከላይ ሙሉ በሙሉ ወፍራም ሰም ይጋገርበታል። . . . ከዚያም አንጥረኞቹ በሰሙ ላይ ሸክላ ይመርጉበትና እስኪደርቅ ይጠብቁታል። በመጨረሻም በሸክላዎቹ መካከል ያለውን ሰም አቅልጠው ያወጡትና በቦታው የቀለጠውን ነሐስ ይጨምሩበታል።”

የነሐሱ ገንዳ ከፍተኛ መጠንና ክብደት ያለው በመሆኑ የረቀቀ የምህንድስና ጥበብ ሳይጠይቅ አይቀርም። ውስጠኛው የሸክላ ቅርጽ ማውጫም ይሁን ከሰሙ በላይ የተመረገው ሸክላ ወደ 30 ቶን የሚመዝነውን የቀለጠ ነሐስ የሚቋቋም መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም ገንዳው ስንጥቅ እንዳይኖረው የቀለጠውን ነሐስ የማፍሰሱ ሒደት ያለማቋረጥ መከናወን ይኖርበታል። ይህም የቀለጠውን ነሐስ በቅርጽ ማውጫው ውስጥ ለማፍሰስ እርስ በርሳቸው የተቀጣጠሉ በርካታ ማቅለጫ ምድጃዎችን መጠቀም ይጠይቅ ይሆናል። በእርግጥም አስገራሚ የምህንድስና ሥራ ነበር!

ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ መቅደሱ በተመረቀበት ወቅት ባቀረበው ጸሎት ላይ “በአፍህ ተናገርህ፣ እንደ ዛሬው ቀንም በእጅህ ፈጸምኸው” በማለት በቤተ መቅደሱ ለተከናወነው የግንባታ ሥራ ሁሉ መመስገን ያለበት ይሖዋ አምላክ መሆኑን ገልጿል።—1 ነገሥት 8:24