እምነት የሚጣልባቸው ተስፋዎች
እምነት የሚጣልባቸው ተስፋዎች
የአምላክ ነቢይ የነበረው ሚክያስ ቃል የተገቡ ነገሮች ብዙውን ጊዜ እንደማይፈጸሙ ተገንዝቦ ነበር። በእርሱ ዘመን የልብ ወዳጅ የሚባለው እንኳን ቃሉን ይጠብቃል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነበር። በመሆኑም ሚክያስ “ባልንጀራን አትመኑ፣ በወዳጅም አትታመኑ፤ የአፍህን ደጅ በብብትህ ከምትተኛው ጠብቅ” በማለት አስጠንቅቋል።—ሚክያስ 7:5
ታዲያ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ሚክያስ ማንኛውንም ተስፋ እንዲጠራጠር አድርጎት ነበር? በፍጹም! አምላኩ ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ያለውን ሙሉ እምነት ሲገልጽ “እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፣ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ጽፏል።—ሚክያስ 7:7
ሚክያስ እንዲህ ያለ ትምክህት ሊኖረው የቻለው ለምን ነበር? ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ ያውቅ ስለነበር ነው። አምላክ ለሚክያስ ቅድመ አያቶች የገባቸው ቃሎች በሙሉ አንድም ሳይቀሩ ተፈጽመዋል። (ሚክያስ 7:20) ይሖዋ የገባውን ቃል በታማኝነት መፈጸሙ ወደፊትም ቃሉን እንደሚጠብቅ ሚክያስ እንዲተማመን አድርጎታል።
‘አንድም ቃል ሳይፈጸም አልቀረም’
ለምሳሌ ያህል ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብጽ ባርነት ነጻ እንዳወጣቸው ሚክያስ ያውቅ ነበር። (ሚክያስ 7:15) እስራኤላውያን ከግብጽ ሲወጡ በዓይኑ የተመለከተው ኢያሱ አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ሁሉ ላይ እምነት እንዲጥሉ እስራኤላውያንን አበረታቷቸዋል። እምነት እንዲጥሉ የሚያደርግ ምን መሠረት ነበራቸው? ኢያሱ እንዲህ በማለት አስታወሳቸው:- “እናንተም እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር እንዳልቀረ በልባችሁ ሁሉ በነፍሳችሁም ሁሉ እወቁ፤ ሁሉ ደርሶላችኋል፤ ከእርሱም አንድ ነገር አልቀረም።”—ኢያሱ 23:14
እስራኤላውያን ይሖዋ አስደናቂ ነገሮች እንዳደረገላቸው ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ፈሪሃ አምላክ ለነበረው ቅድመ አያታቸው ለአብርሃም ዘሮቹ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደሚበዙና የከነዓንን ምድር እንደሚወርሱ የገባውን ቃል ፈጽሟል። በተጨማሪም ይሖዋ የአብርሃም ዘሮች በግብጽ ለ400 ዓመታት መከራ እንደሚደርስባቸውና “በአራተኛው ትውልድ” ወደ ከነዓን እንደሚመለሱ ነግሮት ነበር። ይህ ሁሉ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ዘፍጥረት 15:5-16፤ ዘጸአት 3:6-8
እስራኤላውያን በያዕቆብ ልጅ በዮሴፍ ዘመን ወደ ግብጽ ሲሄዱ የተደረገላቸው አቀባበል ሞቅ ያለ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ግብጻውያን ባሪያዎች አድርገው የጉልበት ሥራ ያሠሯቸው ጀመር። ሆኖም ግብጽን ከረገጡበት ጊዜ አንስቶ አራት ትውልዶች ካለፉ በኋላ አምላክ በገባው ቃል መሠረት እነዚህን የአብርሃም ዘሮች ከግብጽ የባርነት ቀንበር ነጻ አውጥቷቸዋል። a
በቀጣዮቹ 40 ዓመታትም እስራኤላውያን ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን የሚጠብቅ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎች አይተዋል። አማሌቃውያን በጠብ አጫሪነት በእስራኤላውያን ላይ ጥቃት በሰነዘሩ ጊዜ አምላክ ለሕዝቡ በመዋጋት ጥበቃ አድርጎላቸዋል። ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ በተጓዙበት ወቅትም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ያሟላላቸው ሲሆን በመጨረሻም ወደ ተስፋይቱ ምድር አግብቷቸዋል። ኢያሱ ይሖዋ ለአብርሃም ዘሮች ስላደረገላቸው ነገሮች የሚገልጸውን ታሪክ መለስ ብሎ በማስታወስ “እግዚአብሔር ለእስራኤል ቤት ከተናገረው መልካም ነገር ሁሉ ተፈጸመ እንጂ ምንም አልቀረም” በማለት በእርግጠኝነት ተናግሯል።—ኢያሱ 21:45
አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ እምነት አዳብሩ
እንደ ሚክያስና ኢያሱ ሁሉ አንተም ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ያለህን እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ ያህል፣ በሌሎች ላይ ያለህን እምነት የምታዳብረው እንዴት ነው? በተቻለህ መጠን ስለ እነርሱ ብዙ ለማወቅ ትሞክራለህ። የገቡትን ቃል በታማኝነት ለመፈጸም ጥረት ሲያደርጉ ስትመለከት ምን ያህል እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች እንደሆኑ ትገነዘባለህ። ይበልጥ እያወቅካቸው በሄድህ መጠን በእነርሱ ላይ ያለህ እምነት እየተጠናከረ ይሄዳል። አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለህን እምነት ለማዳበርም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ።
ይህን ማድረግ የምትችልበት አንዱ መንገድ በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎችና በተፈጥሮ ሕጎች ላይ በማሰላሰል ነው። አንዲት የሰው ሕዋስ እየተከፈለችና እየተባዛች በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሕዋሶችን በመፍጠር ሰውነትን የምትገነባበት የተፈጥሮ ሕግ ከእነዚህ መካከል አንዱ ነው። ሳይንቲስቶች እንደ እነዚህ ባሉ ሕጎች ላይ ሙሉ ትምክህት አላቸው። እንዲያውም በመላው ጽንፈ መዝሙር 139:14-16፤ ኢሳይያስ 40:26፤ ዕብራውያን 3:4
ዓለም ውስጥ ቁስ አካልንና ኃይልን የሚገዙት ሕጎች እምነት በሚጣልበት አንድ ሕግ አውጪ የተዘጋጁ መሆን አለባቸው። በእርግጥም በተፈጥሮ ሕጎቹ ላይ እንደምትተማመን ሁሉ እርሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይም እምነት መጣል ትችላለህ።—ይሖዋ በሚክያስ ዘመን በኖረው በነቢዩ ኢሳይያስ በኩል የቃሉን ተአማኒነት ለማስረዳት የወቅቶችን መፈራረቅና አስገራሚ የሆነውን የውኃ ዑደት እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። ወቅቱን ጠብቆ በየዓመቱ የሚዘንበው ዝናብ መሬቱን በማራስ ሰዎች ዘር ዘርተው ምርት እንዲሰበስቡ ያስችላቸዋል። ይሖዋ ይህን በሚመለከት እንዲህ ብሏል:- “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ ምድርን እንደሚያረካት፣ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፣ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፣ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:10, 11
የተረጋገጠ የገነት ተስፋ
የፍጥረት ሥራዎቹን መመርመርህ በፈጣሪ ላይ ያለህን ትምክህት ሊያሳድግልህ ይችላል። ሆኖም ‘ከአፉ የሚወጣው ቃል’ ክፍል ስለሆኑት ተስፋዎች ለመማር ግን ከዚህ የበለጠ ነገር ይጠይቅብሃል። በእነዚህ ተስፋዎች ላይ እምነት ለመጣል የሚያስችል እውቀት ለማግኘት አምላክ ለምድር ስላለው ዓላማና ከሰው ልጆች ጋር ስላለው ግንኙነት የሚናገሩትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቅዱሳን ጽሑፎች መመርመር ይኖርብሃል።—2 ጢሞቴዎስ 3:14-17
ነቢዩ ሚክያስ ይሖዋ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ትምክህት ነበረው። አንተ ደግሞ በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክን ቃል ከሚክያስ ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ማግኘት ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና ባነበብከው ነገር ላይ ስታሰላስል አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ያለህ እምነት ይጠናከራል። እነዚህ ተስፋዎች የአብርሃምን ዘሮች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የሰው ዘር የሚመለከቱ ናቸው። ይሖዋ ፈሪሃ አምላክ ለነበረው ለአብርሃም “የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፣ ቃሌን ሰምተሃልና” በማለት ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) ዋነኛው የአብርሃም “ዘር” መሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።—ገላትያ 3:16
ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ለታዛዥ የሰው ልጆች በረከቱን አትረፍርፎ ይሰጣል። በጊዜያችን አምላክ ምን ለማድረግ ቃል ገብቷል? በሚክያስ 4:1, 2 ላይ የሚገኙት ትንቢታዊ ቃላት መልሱን ይሰጡናል። “በመጨረሻውም ዘመን የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፣ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፤ አሕዛብም ወደ እርሱ ይጎርፋሉ። ከጽዮን ሕግ፣ ከኢየሩሳሌምም የእግዚአብሔር ቃል ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው:- ኑ፣ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፣ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፣ በፍለጋውም እንሄዳለን ይላሉ።”
የይሖዋን መንገዶች የሚማሩ ሰዎች “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ።” የጦረኝነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አይኖሩም። በቅርቡ ምድር ጻድቅ በሆኑ ሰዎች የምትሞላ ሲሆን ምንም የሚያስፈራቸው ነገር አይኖርም። (ሚክያስ 4:3, 4) አዎን፣ ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚመራው መንግሥት አማካኝነት ጨቋኞችን በሙሉ ከምድር ጠራርጎ እንደሚያጠፋ የአምላክ ቃል ተስፋ ይሰጠናል።—ኢሳይያስ 11:6-9፤ ዳንኤል 2:44፤ ራእይ 11:18
የሰው ዘር በአምላክ ላይ በማመጹ ምክንያት ስቃይ የደረሰባቸውና ሕይወታቸውን ያጡት እንኳን በምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ትንሣኤ ያገኛሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) ዋነኛ የክፋት ጠንሳሾች የሆኑት ሰይጣንና አጋንንቱ የሚጠፉ ሲሆን የአዳም ኃጢአት ያስከተላቸው ችግሮች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ይወገዳሉ። (ማቴዎስ 20:28፤ ሮሜ 3:23, 24፤ 5:12፤ 6:23፤ ራእይ 20:1-3) ታዛዥ የሰው ልጆች የወደፊት ዕጣቸው ምን ይሆናል? ፍጹም ጤንነት አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ!—መዝሙር 37:10, 11፤ ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3-5
እንዴት ያሉ አስደናቂ ተስፋዎች ናቸው! በእነዚህ ተስፋዎች ላይ እምነት መጣል ትችላለህ? እንዴታ! እነዚህ ተስፋዎች አቅማቸው ውስን በመሆኑ የተነሳ በበጎ ፈቃድ ተነሳስተው የሚገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚያቅታቸው የሰው ልጆች የሰጧቸው ተስፋዎች አይደሉም። ሊዋሽ የማይችለውና ‘የተስፋ ቃሉን ለመፈጸም የማይዘገየው’ ሁሉን ቻይ አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች ናቸው። (2 ጴጥሮስ 3:9፤ ዕብራውያን 6:13-18) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ተስፋዎች የሰጠው “የእውነት አምላክ” የሆነው ይሖዋ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ልትተማመንባቸው ትችላለህ።—መዝሙር 31:5
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 911-12 ተመልከት።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
‘እግዚአብሔር ስለ እናንተ ከተናገረው ከመልካም ነገር ሁሉ አንድ ነገር አልቀረባችሁም።’—ኢያሱ 23:14
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ለእስራኤላውያን የገባላቸውን ቃል በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ ፈጽሟል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ለአብርሃም የገባውን ቃል ፈጽሟል። መላው የሰው ዘር የአብርሃም ዘር በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት ይባረካል