የአንባቢያን ጥያቄዎች
የአንባቢያን ጥያቄዎች
በዘፍጥረት 38:15, 16 ላይ እንደተገለጸው ይሁዳ ጋለሞታ ከመሰለችው ሴት ጋር የጾታ ግንኙነት የፈጸመው ለምንድን ነው?
ይሁዳ ጋለሞታ ከመሰለችው ሴት ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸሙ እውነት ነው፤ ይሁን እንጂ ሴትየዋ ጋለሞታ አልነበረችም። ዘፍጥረት ምዕራፍ 38 ላይ የተመዘገበው ታሪክ ይህን ይመስላል።
የይሁዳ የበኩር ልጅ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ” ስለነበረ ከሚስቱ ከትዕማር ልጆች ከመውለዱ በፊት ይሖዋ ቀሰፈው። (ዘፍጥረት 38:7) በጊዜው የወንድምን ሚስት የማግባት ልማድ ይሠራበት ነበር። በዚህ ልማድ መሠረት አንድ ሰው ወራሽ ሳያገኝ ከሞተ ወንድሙ መበለት የሆነችውን የወንድሙን ሚስት በማግባት ዘር መተካት ነበረበት። ሆኖም የይሁዳ ሁለተኛ ልጅ የነበረው አውናን ይህን ግዴታውን ለመወጣት ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም አምላክ ስለቀሰፈው ሞተ። በዚህን ጊዜ ይሁዳ ሦስተኛ ልጁ ሴሎም አድጎ እስኪያገባት ድረስ ምራቱን ትዕማርን በአባቷ ቤት እንድትቀመጥ ላካት። ይሁን እንጂ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይሁዳ ልጁን ሴሎምን ለትዕማር ሳይድረው ቀረ። ስለሆነም የይሁዳ ሚስት ስትሞት ትዕማር ከእስራኤላዊው አማቿ ወራሽ ለማግኘት አንድ መላ ዘየደች። የጋለሞታ ልብስ በመልበስ ይሁዳ በሚያልፍበት መንገድ ላይ ተቀምጣ ጠበቀችው።
ይሁዳ ማንነቷን ስላላወቀ ከእርሷ ጋር የጾታ ግንኙነት ፈጸመ። ከዚያም ለመያዣነት በሚል ሰበብ አንዳንድ የግል ንብረቶቹን የወሰደች ሲሆን በኋላም ያረገዘችው ከእርሱ እንደሆነ ለማሳየት በማስረጃነት ተጠቅማበታለች። እውነቱ ሲወጣ ይሁዳ ጥፋተኛ ናት ብሎ አልኮነናትም፤ ከዚህ ይልቅ “ከእኔ ይልቅ እርስዋ እውነተኛ ሆነች፤ ልጄን ሴሎምን አልሰጠኋትምና” በማለት ስህተቱን አምኗል። ከዚያ በኋላ ከእርሷ ጋር ግንኙነት አለመፈጸሙ ተገቢ ነበር።—ዘፍጥረት 38:26
ይሁዳ በገባው ቃል መሠረት ልጁ ሴሎም ትዕማርን እንዲያገባት አለማድረጉ ስህተት ነበር። እንዲሁም ጋለሞታ ከመሰለችው ሴት ጋር የጾታ ግንኙነት መፈጸሙ በትዳር ውስጥ ብቻ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጸም ከሚያዘው የአምላክ ዓላማ ጋር የሚጋጭ ነው። (ዘፍጥረት 2:24) እንደ እውነቱ ከሆነ ይሁዳ የጾታ ግንኙነት የፈጸመው ከጋለሞታ ጋር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ የወንድሙን ሚስት ማግባት ይጠበቅበት የነበረውን የልጁን የሴሎምን ቦታ ሳያውቀው የወሰደ ሲሆን የተወለደው ልጅም ሕጋዊ ወራሽ ሆኗል።
ትዕማርም ብትሆን ይህ ድርጊቷ ዝሙት ፈጽማለች ሊያስብላት አይችልም። የወለደቻቸው መንትያ ልጆችም በዝሙት የተገኙ ልጆች ተደርገው አይቆጠሩም። በቤተ ልሔም ይኖር የነበረው ቦዔዝ ለሟች ዘመዱ ወራሽ ለማስገኘት ሞዓባዊቷን ሩትን ባገባ ጊዜ የቤተ ልሔም ሽማግሌዎች “ቤትህም እግዚአብሔር ከዚህች ቆንጆ ከሚሰጥህ ዘር ትዕማር ለይሁዳ እንደ ወለደችው እንደ ፋሬስ ቤት ይሁን” ብለው በመመረቅ የትዕማርን ልጅ ፋሬስን በበጎ አንስተውት ነበር። (ሩት 4:12) እንዲሁም ፋሬስ በኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ሐረግ ውስጥ ተጠቅሷል።—ማቴዎስ 1:1-3፤ ሉቃስ 3:23-33