በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2

የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 2

የዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያው ሰው አዳም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ያለውን የ2,369 ዓመታት ታሪክ ይዟል። ስለ ፍጥረት ከሚናገረው ዘገባ ጀምሮ የባቢሎን ግንብ እስከተሠራበት ጊዜ ድረስ ያለውን ታሪክ የሚሸፍኑት የመጀመሪያዎቹ 10 ምዕራፎችና የምዕራፍ 11 ዘጠኝ ቁጥሮች ከዚህ በፊት በወጣው የዚህ መጽሔት እትም ላይ ተብራርተዋል። a ይህ ርዕስ አምላክ ከአብርሃም፣ ከይስሐቅ፣ ከያዕቆብና ከዮሴፍ ጋር ስለነበረው ግንኙነት በሚተርኩት የዘፍጥረት መጽሐፍ ቀሪ ምዕራፎች ውስጥ ባሉት ጎላ ያሉ ነጥቦች ላይ ያተኩራል።

አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ሆነ

(ዘፍጥረት 11:10 እስከ 23:20)

የጥፋት ውኃ ከደረሰ ከ350 ዓመታት ገደማ በኋላ በኖኅ ልጅ በሴም የትውልድ መስመር ከአምላክ ጋር ልዩ ዝምድና ለመመሥረት የበቃ አንድ ሰው ተወለደ። አብራም ተብሎ ይጠራ የነበረው ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ አብርሃም ተብሏል። አብራም አምላክ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት የከለዳውያን ከተማ የነበረችውን ዑርን ለቅቆ ይሖዋ ለእርሱና ለዘሮቹ ሊሰጠው ቃል በገባለት ምድር በድንኳን መኖር ጀመረ። አብርሃም በእምነቱና በታዛዥነቱ የተነሳ ‘የእግዚአብሔር ወዳጅ’ ለመባል በቅቷል።—ያዕቆብ 2:23

ይሖዋ በሰዶምና በአጎራባች ከተሞች ውስጥ በሚኖሩት ክፉ ሰዎች ላይ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ሎጥንና ሴቶች ልጆቹን ከጥፋቱ አድኗቸዋል። የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ በተወለደ ጊዜ አምላክ ለአብርሃም የገባለት ቃል ተፈጸመ። ከዓመታት በኋላ ልጁን እንዲሠዋለት ይሖዋ አብርሃምን ሲጠይቀው እምነቱ ተፈትኖ ነበር። አንድ መልአክ ደርሶ ባይከለክለው ኖሮ አብርሃም የታዘዘውን ለመፈጸም ዝግጁ ነበር። አብርሃም የእምነት ሰው ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። በዚህም ምክንያት በዘሩ የምድር አሕዛብ ሁሉ ራሳቸውን እንደሚባርኩ ቃል ተገብቶለታል። አብርሃም የሚወዳት ሚስቱ ሣራ ስትሞት በጣም አዝኖ ነበር።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

12:1-3—የአብርሃም ቃል ኪዳን ተግባራዊ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? ለምን ያህል ጊዜስ? ይሖዋ “የምድር ነገዶችም ሁሉ በአንተ ይባረካሉ” በማለት ከአብራም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ተግባራዊ መሆን የጀመረው አብራም ወደ ከነዓን ምድር ለመግባት የኤፍራጥስን ወንዝ በተሻገረበት ወቅት ይመስላል። ይህ የሆነው እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከመውጣታቸው ከ430 ዓመታት በፊት ማለት ኒሳን 14, 1943 ከክርስቶስ ልደት በፊት መሆን አለበት። (ዘጸአት 12:2, 6, 7, 40, 41) የአብርሃም ቃል ኪዳን ‘ለዘላለም የቆመ ኪዳን’ ነው። የምድር ሕዝቦች እስከሚባረኩበትና የአምላክ ጠላቶች እስከሚጠፉበት ጊዜ ድረስ ይጸናል።—ዘፍጥረት 17:7፤ 1 ቆሮንቶስ 15:23-26

15:13—የአብራም ዘር ለ400 ዓመታት እንደሚጨቆን የተነገረው ትንቢት የተፈጸመው መቼ ነው? ይህ የጭቆና ጊዜ የጀመረው የአብርሃም ልጅ ይስሐቅ በ5 ዓመት ዕድሜው ጡት በጣለበት ወቅት የ19 ዓመት ወንድሙ እስማኤል ‘በሳቀበት’ ወይም ባሾፈበት ጊዜ ማለትም በ1913 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነበር። (ዘፍጥረት 21:8-14፤ ገላትያ 4:29) ያበቃው ደግሞ እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ በወጡበት በ1513 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው።

16:2—ሦራ አገልጋይዋን አጋርን በቁባትነት ለአብራም መስጠቷ ተገቢ ነበር? ሦራ ይህን ያደረገችው በዘመኑ በነበረው ልማድ መሠረት አንዲት መካን ሴት ባሏ ወራሽ እንዳያጣ ቁባት የመስጠት ግዴታ ስለነበረባት ነው። ከአንድ በላይ የማግባት ልማድ የጀመረው በቃየን የትውልድ መስመር ነበር። እየዋለ እያደር ግን እየተስፋፋ የሄደ ሲሆን አንዳንድ የይሖዋ አምላኪዎችም ይህን ልማድ ተከትለዋል። (ዘፍጥረት 4:17-19፤ 16:1-3፤ 29:21-28) ይሁን እንጂ ይሖዋ አንድ ሰው አንድ የትዳር ጓደኛ ብቻ እንዲኖረው የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ አልቀየረም። (ዘፍጥረት 2:21, 22) “ብዙ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት” የሚለው ትእዛዝ በድጋሚ የተሰጣቸው ኖኅና ልጆቹ አንድ አንድ ሚስት ብቻ ነበራቸው። (ዘፍጥረት 7:7፤ 9:1፤ 2 ጴጥሮስ 2:5) ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንኑ የአንድ ለአንድ ጋብቻ በመደገፍ ተናግሯል።—ማቴዎስ 19:4-8፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:2, 12

19:8—ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ለሰዶም ሰዎች ለመስጠት ማሰቡ ስህተት አልነበረም? በምሥራቃውያን ደንብ መሠረት ሰዎችን በእንግድነት የተቀበለ ሰው አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የሕይወት መሥዋዕትነት እንኳን ከፍሎ እንግዶቹን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነት ነበረበት። ሎጥ እንዲህ ለማድረግ ዝግጁ ነበር። ከሰዎቹ ጋር ለመነጋገር በድፍረት ወደ ደጅ የወጣ ሲሆን በሩን ከኋላው ዘግቶ ሕዝቡን ብቻውን ተጋፍጧል። ሎጥ ሴቶች ልጆቹን ሊሰጣቸው እንደሚችል በነገራቸው ወቅት በቤቱ ያረፉት እንግዶች ከአምላክ የተላኩ መልእክተኞች መሆናቸውን ተገንዝቦ መሆን አለበት። በመሆኑም አምላክ የአጎቱን ሚስት ሣራን በግብፅ ጥበቃ እንዳደረገላት ሁሉ የእርሱንም ሴቶች ልጆች ሊጠብቃቸው እንደሚችል አስቦ ሊሆን ይችላል። (ዘፍጥረት 12:17-20) ደግሞም በኋላ እንደታየው እርሱና ልጆቹ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል።

19:30-38—ይሖዋ ሎጥ መስከሩንና ከሁለት ሴቶች ልጆቹ ወንዶች ልጆች ማፍራቱን ደግፎት ነበር? ይሖዋ በቅርብ ዘመዳሞች መካከል የሚደረገውን የጾታ ግንኙነትም ሆነ ስካርን አይደግፍም። (ዘሌዋውያን 18:6, 7, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ሎጥም ቢሆን የሰዶም ነዋሪዎች የሚፈጽሙትን ‘የዓመፅ ሥራ’ ይጸየፈው ነበር። (2 ጴጥሮስ 2:6-8) የሎጥ ሴቶች ልጆች ሎጥ እንዲሰክር ማድረጋቸው ራሱ ባይሰክር ኖሮ ከእነርሱ ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም እንደማይስማማ አውቀው እንደነበር ያሳያል። ቢሆንም ለአካባቢው እንግዳ ስለነበሩ የሎጥ ዘር እንዳይጠፋ ማድረግ የሚችሉበት ብቸኛው አማራጭ ይህ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ታሪኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውም ሞዓባውያን (የሞዓብ ዘሮች) እና አሞናውያን (የቤንአሚ ዘሮች) የአብርሃም ዘሮች ከሆኑት እስራኤላውያን ጋር የነበራቸውን የሥጋ ዝምድና ለማሳየት ነው።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

13:8, 9 አብርሃም አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ለገንዘብ፣ ለግል ምርጫዎቻችን ወይም ለክብራችን ብለን ከሰዎች ጋር ያለን ሰላማዊ ግንኙነት እንዲሻክር ማድረግ አይኖርብንም።

15:5, 6 አብርሃም ዕድሜው እየገፋ እንደሆነና ልጅም እንዳልወለደ ሲመለከት ስለ ጉዳዩ ወደ አምላክ ጸልዮአል። ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚፈጽምለት ማረጋገጫ ሰጠው። ውጤቱስ ምን ነበር? አብርሃም “በእግዚአብሔር አመነ።” እኛም ለይሖዋ በጸሎት የልባችንን ከነገርነው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚሰጠንን ማረጋገጫዎች የምንቀበልና የምንታዘዘው ከሆነ እምነታችን ይጠናከራል።

15:16 ይሖዋ ለአራት ትውልዶች ያህል በአሞራውያን (ወይም በከነዓናውያን) ላይ የፍርድ እርምጃ ሳይወስድ ቆይቷል። ለምን? ታጋሽ አምላክ ስለሆነ ነው። ይሻሻላሉ የሚለው ተስፋው ሙሉ በሙሉ እስኪሟጠጥ ድረስ ጠብቋቸዋል። እኛም ልክ እንደ ይሖዋ ታጋሽ መሆን ይኖርብናል።

18:23-33 ይሖዋ ሰዎችን በጅምላ አያጠፋም። ለጻድቃን ጥበቃ ያደርግላቸዋል።

19:16 ሎጥ ከሰዶም ከተማ ለመውጣት “በዘገየ ጊዜ” ሁለቱ መላእክት የእርሱንና የቤተሰቡን እጅ እየጎተቱ አውጥተዋቸዋል። እኛም ይህ ክፉ ዓለም የሚጠፋበትን ጊዜ ስንጠባበቅ የጊዜውን አጣዳፊነት መዘንጋት አይኖርብንም።

19:26 በዚህ ዓለም የተውናቸውን ነገሮች ለማግኘት መጓጓታችን ወይም መናፈቃችን እንዴት ያለ ሞኝነት ነው!

ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት

(ዘፍጥረት 24:1 እስከ 36:43)

አብርሃም ልጁ ይስሐቅ ይሖዋን የምታመልከውን ርብቃን እንዲያገባ ሁኔታዎችን አመቻቸለት። ርብቃም ዔሳውና ያዕቆብ የተባሉ መንትያ ልጆች ወለደች። ዔሳው ብኩርናውን አቅልሎ በመመልከት ለያዕቆብ የሸጠለት ሲሆን ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ የአባቱን በረከት አግኝቷል። ያዕቆብ ወደ መስጴጦሚያ ሸሽቶ ሄደ፤ እዚያም ልያንና ራሔልን ያገባ ሲሆን ቤተሰቡን ይዞ ወደ ትውልድ አገሩ እስከተመለሰበት ጊዜ ድረስ ለ20 ዓመታት የአባታቸውን በጎች ጠበቀ። ከልያ፣ ከራሔልና ከሁለት አገልጋዮቻቸው 12 ወንዶች ልጆችና አንዲት ሴት ልጅ ተወለዱለት። እንዲሁም ከአንድ መልአክ ጋር ታግሎ በረከት ያገኘ ከመሆኑም በላይ ስሙም ተለውጦ እስራኤል ተባለ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

28:12, 13—ያዕቆብ ስለ “መሰላል” የተመለከተው ሕልም ትርጉሙ ምንድን ነው? በድንጋይ ከተሠራ ደረጃ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው ይህ “መሰላል” በምድርና በሰማይ መካከል የሐሳብ ግንኙነት መኖሩን ያመለክታል። የአምላክ መላእክት በመሰላሉ ላይ ይወጡና ይወርዱ የነበረ መሆኑ መላእክት በይሖዋና ሞገሱን በሚያገኙ ሰዎች መካከል አንዳንድ ጠቃሚ አገልግሎቶችን እንደሚያከናውኑ ያሳያል።—ዮሐንስ 1:51

30:14, 15ራሔል ከባሏ ጋር በማደር ለመጸነስ የነበራትን አጋጣሚ በእንኮይ የለወጠችው ለምን ነበር? በጥንት ጊዜ እንኮይ ለሥቃይ ማስታገሻነትና ድንገተኛ የጡንቻ መኮማተርን ለመከላከል ወይም ለማስታገስ ተብሎ በመድኃኒትነት ይወሰድ ነበር። በተጨማሪም ይህ ፍሬ የጾታ ፍላጎትን ያነሳሳል እንዲሁም የመጸነስ አጋጣሚን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይታመን ነበር። (መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 7:13) ራሔል ከባልዋ ጋር ለማደር የነበራትን አጋጣሚ በእንኮይ ለመለወጥ የተነሳሳችበትን ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ባይገልጽልንም እንኮዩ እንድትጸንስ አስችሏት በመካንነቷ ከሚደርስባት ነቀፋ ለመገላገል አስባ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ ‘ማኅፀንዋን የከፈተላት’ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ነበር።—ዘፍጥረት 30:22-24

ምን ትምህርት እናገኛለን?

25:23 ይሖዋ በማኅፀን ውስጥ ያለን ሕፃን በራሂያዊ ቅንብር (genetic makeup) በመመልከት ምን ዓይነት ሰው እንደሚሆን አስቀድሞ የማወቅና ዓላማውን ለማስፈጸም የሚስማማውን ሰው የመምረጥ ችሎታ አለው። ቢሆንም የሰዎችን የወደፊት ዕጣ አስቀድሞ አይወስንም።—ሆሴዕ 12:3፤ ሮሜ 9:10-12

25:32, 33፤ 32:24-29 ያዕቆብ የብኩርና መብት ለማግኘት ያደረገው ጥረትና አንድ መልአክ እንዲባርከው ሲል አንድ ሌሊት ሙሉ ሲታገል ማደሩ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች ትልቅ ቦታ ይሰጥ እንደነበረ ያሳያል። ይሖዋ ከእርሱና ከድርጅቱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና፣ የቤዛውን ዝግጅት፣ መጽሐፍ ቅዱስንና የመንግሥቱን ተስፋዎች የመሳሰሉ እንደ ቅዱስ ተደርገው የሚታዩ ነገሮችን ሰጥቶናል። እኛም ለእነዚህ ነገሮች አድናቆት በማሳየት የያዕቆብን ምሳሌ እንኮርጅ።

34:1, 30 ዲና ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መመሥረቷ ትልቅ መዘዝ ያስከተለ ሲሆን ይህም ያዕቆብ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ‘እንዲጠላ’ አድርጎታል። እኛም በጓደኛ አመራረጥ ረገድ አስተዋዮች መሆን ይኖርብናል።

ይሖዋ ዮሴፍን በግብፅ ባረከው

(ዘፍጥረት 37:1 እስከ 50:26)

የያዕቆብ ልጆች በቅናት ተነሳስተው ወንድማቸውን ዮሴፍን ለባርነት ሸጡት። ዮሴፍ በግብፅ ሳለ የአምላክን የሥነ ምግባር መስፈርቶች በታማኝነትና በድፍረት በመጠበቁ ለእስር ተዳረገ። ከጊዜ በኋላ ፈርዖን ሕልሙን እንዲፈታለት ከወኅኒ ያስወጣው ሲሆን ሕልሙም ከሰባት ዓመት ጥጋብ በኋላ የሰባት ዓመት ረሃብ እንደሚመጣ የሚተነብይ ነበር። ከዚያም ዮሴፍ በግብፅ የምግብ አስተዳዳሪ ተደረገ። ወንድሞቹ በረሃቡ ሳቢያ ምግብ ፍለጋ ወደ ግብፅ መጡ። ቤተሰቡ ዳግም የተገናኘ ሲሆን ለም በሆነው በጌሤም ምድር ሠፈረ። ያዕቆብ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ልጆቹን ባረካቸው፤ ከዘመናት በኋላ አስደሳች በረከቶች እንደሚጠብቋቸው አስተማማኝ ተስፋ የሚሰጥ ትንቢት ተናገረ። ያዕቆብ ከሞተ በኋላ አስከሬኑ ወደ ከነዓን ተወስዶ ተቀበረ። ዮሴፍ በ110 ዓመቱ በሞተ ጊዜ አስከሬኑ በመድኃኒት ታሽቶ የተቀመጠ ሲሆን ከጊዜ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ተወስዷል።—ዘጸአት 13:19

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

43:32—ግብፃውያን ከዕብራውያን ጋር መብላትን እንደመርከስ የሚቆጥሩት ለምን ነበር? ይህ በዋነኝነት በሃይማኖታዊ ጥላቻ ወይም በዘር ኩራት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ግብፃውያን በግ ጠባቂዎችንም እንደ ርኩስ ይመለከቱ ነበር። (ዘፍጥረት 46:34) ለምን? በግ ጠባቂዎች በግብፅ ማኅበረሰብ ውስጥ በመጨረሻው የኑሮ ደረጃ ላይ ይገኙ ስለነበር ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ለእርሻ ሊውል የሚችለው መሬት በጣም ውስን በመሆኑ ለመንጎቻቸው የግጦሽ መሬት የሚፈልጉ ሰዎች ይህን መሬት ስለሚሻሟቸው ሊሆን ይችላል።

44:5—ዮሴፍ ምስጢርን ለማወቅ የሚጠቀምበት የብር ጽዋ ነበረው? የብሩ ጽዋና አለው የተባለው ኃይል ዮሴፍ ዓላማውን ለማስፈጸም የተጠቀመበት ዘዴ ክፍል ነው። ዮሴፍ ታማኝ የይሖዋ አምላኪ ነበር። ብንያም ጽዋውን እንዳልሰረቀው ሁሉ ዮሴፍም ምስጢር ለማወቅ በጽዋው አይጠቀምም ነበር።

49:10—“በትረ መንግሥት” እና ‘የገዥ ዘንግ’ ምን ትርጉም አላቸው? በትረ መንግሥት አንድ ገዥ ንጉሣዊ ሥልጣን እንዳለው ለማሳየት የሚይዘው በትር ነው። የገዥ ዘንግ ደግሞ የአዛዥነት ሥልጣኑን ለማሳየት የሚይዘው ረጅም ዘንግ ነው። ያዕቆብ እነዚህን መጥቀሱ የመግዛት መብት ያለው ሴሎ እስኪመጣ ድረስ ንጉሣዊ ሥልጣንና አዛዥነት ከይሁዳ ነገድ እንደማይወጣ ለማመልከት ነው። ይህ በይሁዳ ነገድ የሚመጣ ገዥ ይሖዋ በሰማይ የመግዛት ሥልጣን የሰጠው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ንጉሣዊ ሥልጣንም ሆነ የአዛዥነት መብት ይኖረዋል።—መዝሙር 2:8, 9፤ ኢሳይያስ 55:4፤ ዳንኤል 7:13, 14

ምን ትምህርት እናገኛለን?

38:26 ይሁዳ መበለት ከሆነችው ከምራቱ ከትዕማር ጋር ግንኙነት መፈጸሙ ስህተት ነበር። ይሁን እንጂ ትዕማር የጸነሰችው ከእርሱ መሆኑን ስትናገር ስህተቱን ምንም ሳያንገራግር አምኗል። እኛም ስህተታችንን ለመቀበል ማንገራገር እንደሌለብን ያሳያል።

39:9 ዮሴፍ የጲጥፋራ ሚስት ላቀረበችለት ጥያቄ የሰጠው ምላሽ በሥነ ምግባር ረገድ የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ እንደነበረውና በአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ይመራ እንደነበረ ያሳያል። እኛስ ትክክለኛውን የእውነት እውቀት እያገኘን ስንሄድ ሕሊናችን በአምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲመራ ጥረት ማድረግ አይኖርብንም?

41:14-16, 39, 40 ይሖዋ እርሱን የሚፈሩ ሰዎች ካሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲወጡ ሊረዳቸው ይችላል። መከራ ሲደርስብን ትምክህታችንን በይሖዋ ላይ መጣላችንና ታማኝነታችንን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ ነው።

ጠንካራ እምነት ነበራቸው

በእርግጥም አብርሃም፣ ይስሐቅ፣ ያዕቆብና ዮሴፍ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው የእምነት ሰዎች ነበሩ። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘው የሕይወት ታሪካቸው እምነታችንን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ በርካታ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያስጨብጠናል።

አንተም በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም መሠረት እነዚህን ዘገባዎች በማንበብ ጥቅም ማግኘት ትችላለህ። ከላይ ያሉትን ሐሳቦች መመርመርህም ታሪኩን በአእምሮህ ሕያው አድርገህ ለመሳል ይረዳሃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በጥር 1, 2004 መጠበቂያ ግንብ እትም ላይ የወጣውን “የይሖዋ ቃል ሕያው ነው—የዘፍጥረት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች—ክፍል 1” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ዮሴፍን ባርኮታል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አብርሃም የእምነት ሰው ነበር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጻድቁ ሎጥና ሴቶች ልጆቹ ከጥፋት በሕይወት ተርፈዋል

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያዕቆብ ቅዱስ ለሆኑ ነገሮች አድናቆት ነበረው። አንተስ?