በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የይሖዋ ዛፎች ይጠግባሉ’

‘የይሖዋ ዛፎች ይጠግባሉ’

ዕጹብ ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት

‘የይሖዋ ዛፎች ይጠግባሉ’

የፀሐይ ጮራ በረጃጅም ዛፎች መካከል እየሰነጠቀ ብርሃኑን በሚፈነጥቅበት ጥቅጥቅ ያለ ደን ውስጥ ተጉዘህ ታውቃለህ? ነፋስ በቅጠሎቹ መካከል ሲነፍስ የሚፈጠረውን ድምፅስ ልብ ብለህ አዳምጠህ ታውቃለህ?—ኢሳይያስ 7:2

በአንዳንድ የምድር ክፍሎች በተወሰኑ ወራት የተለያዩ ዛፎች ቀይ፣ ብርቱካንማ፣ ቢጫና ሌሎች ቀለሞች ባሏቸው ቅጠሎች ያሸበርቃሉ። ጫካው በእሳት የተያያዘ ይመስላል! “እናንተም ተራሮች አንተም ዱር በአንተም ያለ ዛፍ ሁሉ፣ እልል በሉ” የሚለው የአድናቆት መግለጫ ከዚህ ጋር ምንኛ ይስማማል!—ኢሳይያስ 44:23 a

የፕላኔቷ ምድራችን አንድ ሦስተኛ የሚሆነው የየብስ ክፍል በደን የተሸፈነ ነው። ደኑም ሆነ በውስጡ የሚኖሩት ሕይወት ያላቸው ነገሮች ንድፍ አውጪና ፈጣሪያቸው የሆነውን ይሖዋ አምላክን ያወድሱታል። መዝሙራዊው በመንፈስ አነሳሽነት ‘የሚያፈራም ዛፍ ዝግባም ሁሉ ይሖዋን አመስግኑት’ በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 148:7-9

ዘ ትሪስ አራውንድ አስ የተባለው መጽሐፍ “ዛፎች የሰው ልጅ ያለውን ውብ የሆኑ ነገሮች የማየት ፍላጎትና ለሕይወት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት በጣም አስፈላጊ ናቸው” በማለት ይናገራል። ደኖች ለሰዎች የሚያስፈልገውን ውኃ ከብክለት ይከላከላሉ፣ ጠብቀው ያቆያሉ እንዲሁም ያጣራሉ። በተጨማሪም አየሩ ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆን ያደርጋሉ። በቅጠሎች ውስጥ የሚገኙት ሕዋሳት ተአምራዊ ሊባል በሚችለው ፎቶሲንተሲስ በተባለው ሂደት አማካኝነት ካርቦን ዳይኦክሳይድን፣ ውኃን፣ ማዕድናትንና የፀሐይ ብርሃንን ወደ ምግብና ወደ ኦክስጂን ይለውጣሉ።

ደኖች አስደናቂ ውበትና ንድፍ የሚንጸባረቅባቸው ድንቅ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ለደኖች ይበልጥ ግርማ ሞገስ የሚሰጡት ግዙፍ የሆኑ ዛፎች ናቸው። በእነዚህ ዛፎች መካከል የእንጨትና የድንጋይ ሽበቶች፣ ሃረጎች፣ ቁጥቋጦዎች እንዲሁም ቁጥር ሥፍር የሌላቸው የዕፅዋት ዓይነቶች ይበቅላሉ። ትልልቆቹ ዛፎች የሚፈጥሩት ጥላና የጫካው እርጥበት ለእነዚህ ትናንሽ ዕፅዋት ሕልውና በጣም አስፈላጊ ነው።

ወቅት ጠብቀው ቅጠላቸውን የሚቀይሩ ዛፎች ባሉባቸው አንዳንድ ደኖች ውስጥ በዓመቱ መገባደጃ አካባቢ በአንድ ሄክታር ውስጥ 25 ሚሊዮን የሚያህሉ ቅጠሎች ይረግፋሉ። እነዚህ ሁሉ ቅጠሎች ምን ይሆናሉ? ነፍሳት፣ ፈንገሶች፣ ትላትሎች እንዲሁም ሌሎች ሕዋሳት እነዚህን ቅጠሎች ቀስ በቀስ በማበስበስ መሬቱን ያዳብሩታል። አዎን፣ እነዚህ የማይታዩ ሠራተኞች አፈሩን ለሚቀጥለው የእድገት ዘመን ለማዘጋጀት ቅጠሎቹን ስለሚጠቀሙባቸው ምንም የሚባክን ነገር አይኖርም።

ከረገፉት ቅጠሎች በታች በአፈሩ ውስጥ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ነፍሳት ይርመሰመሳሉ። ዘ ፎረስት የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “30 ሴንቲ ሜትር ስፋት በ2.5 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ባለው አፈር ውስጥ 1,350 የሚያህሉ ነፍሳት ማግኘት የሚቻል ሲሆን ይህ ደግሞ በአንድ እፍኝ አፈር ውስጥ የሚገኙትን በቢሊዮን የሚቆጠሩ በዓይን የማይታዩ ሕዋሳት አይጨምርም።” ከዚህም በላይ ደን በተሳቢ እንስሳት፣ በአእዋፋት፣ በበራሪ ነፍሳትና በአጥቢ እንስሳት የተሞላ ነው። በውበቱም ሆነ በዓይነቱ አስደናቂ ለሆነው ለዚህ የፍጥረት ሥራ መመስገን የሚገባው ማን ነው? የእነዚህ ሁሉ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ “የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸውና” ብሎ መናገሩ በእርግጥም የተገባ ነው።—መዝሙር 50:10

አንዳንድ እንስሳት ከፍተኛ ቅዝቃዜና የምግብ እጥረት የሚኖርባቸውን የክረምት ወራት በእንቅልፍ የማሳለፍ አስገራሚ ተሰጥኦ አላቸው። እንዲህ የሚያደርጉት ግን ሁሉም እንስሳት አይደሉም። በክረምቱ አጋማሽ ላይ እንኳን አጋዘኖች በሜዳ ላይ ሲፈነጩ ልትመለከት ትችላለህ። አጋዘኖች ምግብ ማከማቸትም ሆነ ክረምቱን በእንቅልፍ ማሳለፍ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ ከጀርመን ከተገኘው በዚህ ገጽ ላይ በሚገኘው ፎቶ ግራፍ ላይ መመልከት እንደምትችለው ቀንበጦችንና ለስላሳ ቅርንጫፎችን በመብላት ክረምቱን ያሳልፋሉ።

ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ዕፅዋት በሰፊው ይናገራሉ። አንድ ቆጠራ እንደሚያሳየው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 30 የሚያህሉ የዛፍ ዓይነቶችን ጨምሮ 130 የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎች ተጠቅሰዋል። ማይክል ዞሃሪ የተባሉ አንድ የሥነ ዕፅዋት ተመራማሪ ይህን አስመልክተው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “ከሙያ ጋር ባልተያያዙ ዓለማዊ ጽሑፎች ላይ እንኳን የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ከተለያየ የሕይወት ዘርፎች ጋር ግንኙነት ያላቸው ዕፅዋት አይጠቀሱም።”

ዛፎችና ደኖች አፍቃሪ ከሆነው ፈጣሪያችን ያገኘናቸው ዕጹብ ድንቅ ስጦታዎች ናቸው። ደን ውስጥ ተንሸራሽረህ የምታውቅ ከሆነ “የእግዚአብሔር ዛፎች እርሱም የተከላቸው የሊባኖስ ዝግባዎች ይጠግባሉ። በዚያም ወፎች ይዋለዳሉ” በሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት እንደምትስማማ አያጠራጥርም።—መዝሙር 104:16, 17

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የ2004ን የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ በጥርና በየካቲት ላይ ያሉትን ሥዕሎች ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙት ማራኪ የፍራፍሬ ዛፎች መካከል አንዱ የለውዝ ዛፍ (almond tree) ነው። የለውዝ ዛፍ በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ከአብዛኞቹ ዛፎች ቀድሞ ከክረምት እንቅልፉ ይነቃል። የጥንት ዕብራውያን የለውዝ ዛፍ ከሌሎች ዛፎች ቀድሞ ማበቡን ለማመልከት “የሚነቃው ዛፍ” በማለት ይጠሩት ነበር። ዛፉ ፈዘዝ ያለ ሮዝ ወይም ነጭ ቀለም ባላቸው አበቦች አሸብርቆ ሲታይ ቃል በቃል ከእንቅልፉ የነቃ ይመስላል።—መክብብ 12:5

በዓለማችን ካሉት 9,000 የሚያክሉ የአእዋፋት ዝርያዎች መካከል 5,000 የሚያህሉት ከአዝማሪ ወፎች የሚመደቡ ናቸው። እነዚህ ወፎች በመዝሙራቸው ረጭ ያለውን ጥቅጥቅ ያለ ደን ሕይወት ይዘሩበታል። (መዝሙር 104:12) ለምሳሌ ያህል አዝማሪዋ ድንቢጥ በጣም የሚያስደስት ዜማ አላት። በፎቶ ግራፉ ላይ እንደምትታየው ሞርኒንግ ዎርብለር የተባለች ወፍ ያሉ ግራጫ፣ ቢጫና ፈዛዛ አረንጓዴ ቀለም ባላቸው ላባዎች ያጌጡ ትናንሽ አዝማሪ ወፎችም አሉ።—መዝሙር 148:1, 10

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በኖርማንዲ፣ ፈረንሳይ ውስጥ የሚገኝ ደን