በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መንፈሳዊ ፍላጎትህን ማርካት የምትችለው እንዴት ነው?

መንፈሳዊ ፍላጎትህን ማርካት የምትችለው እንዴት ነው?

መንፈሳዊ ፍላጎትህን ማርካት የምትችለው እንዴት ነው?

ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት የተሰኘው መጽሔት “ባለፉት አሥርተ ዓመታት መንፈሳዊነት በሥራ ቦታ የሚጫወተውን ሚና በተመለከተ ጂሰስ ቺፍ ኤግዘኪዩቲቭ ኦፊሰር (ኢየሱስ ዋና አስተዳዳሪ) ከሚለው አንስቶ ዘ ዳው ኦቭ ሊደርሺፕ (ዳው ለተባለው ሃይማኖት ተከታዮች የተዘጋጀ ታላቅ መሪ መሆን ስለሚቻልበት መንገድ የሚናገር መጽሐፍ) እስከተባለው መጽሐፍ ያሉ የተለያዩ ርዕሶችን የያዙ ከ300 የሚበልጡ መጻሕፍት መደብሮችን አጥለቅልቀዋል” ብሏል። ይህ አዝማሚያ በቁሳዊ ረገድ ሀብታም በሆኑ አገሮች ሰዎች መንፈሳዊ መመሪያ ለማግኘት በጣም እንደሚፈልጉ የሚያሳይ ነው። የንግድ መጽሔት የሆነው ትሬይኒንግ ኤንድ ዲቨሎፕመንት በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት ሲሰጥ “ቴክኖሎጂ እያንዳንዱን የሕይወት ዘርፍ በሚቆጣጠርበት በዚህ ዘመን የሕይወትን እውነተኛ ትርጉምና ዓላማ እንዲሁም እርካታ ለማግኘት እየጣርን ነው” ብሏል።

ይሁንና የሚያረካ መንፈሳዊ አመራር የት ልታገኝ ትችላለህ? ባለፉት ዘመናት ሰዎች የታወቁ ሃይማኖቶች የሕይወትን “ጥልቅ ትርጉም” እና “ዓላማ” ለማወቅ ይረዱናል ብለው ያስቡ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ብዙዎች ለታወቁት ሃይማኖቶች ጀርባቸውን ሰጥተዋል። ከፍተኛ ማዕረግ ባላቸው 90 ሥራ አስኪያጆችና አስተዳዳሪዎች ላይ የተካሄደ ጥናት “ሰዎች በሃይማኖትና በመንፈሳዊነት መካከል ትልቅ ልዩነት እንዳለ እንደሚሰማቸው” ያሳየ መሆኑን ትሬይኒንግ ኤንድ ዲቨሎፕመንት የተሰኘው መጽሔት ገልጿል። ጥናቱ የተካሄደባቸው ሰዎች ሃይማኖት “መቻቻል የማይታይበትና ከፋፋይ” እንደሆነ የሚያስቡ ሲሆን መንፈሳዊነት ግን “ዓለም አቀፍና ሁሉን የሚያቅፍ” እንደሆነ ይሰማቸዋል።

በተመሳሳይም እንደ አውስትራሊያ፣ ኒውዚላንድ፣ ዩናይትድ ኪንግደምና አውሮፓ ባሉት እምብዛም ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ማኅበረሰቦች ውስጥ ያደጉ ወጣቶች በሃይማኖትና በመንፈሳዊነት መካከል ልዩነት እንዳለ ይሰማቸዋል። ፕሮፌሰር ሩት ዌበር ዩዝ ስተዲስ አውስትራሊያ በተሰኘው ጽሑፍ ላይ “አብዛኞቹ ወጣቶች በአምላክ ወይም ከሰው በላይ በሆነ አንድ ኃይል የሚያምኑ ቢሆንም መንፈሳዊ ሰው ሆኖ ለመኖር ግን ቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ እንደሆነ አያስቡም” ብለዋል።

እውነተኛ ሃይማኖት መንፈሳዊነትን ያበረታታል

ሰዎች ሃይማኖትን በዚህ መልኩ በጥርጣሬ ዓይን መመልከታቸው የሚያስገርም አይደለም። ብዙ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች በፖለቲካዊ ውዝግቦችና በሥነ ምግባራዊ ግብዝነት የተዘፈቁ እንዲሁም በአያሌ ሃይማኖታዊ ጦርነቶች በሞቱት ንጹሐን ሰዎች ደም የጎደፉ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንዶች በግብዝነትና በማታለል ከተበከሉት ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ሲርቁ፣ እንደዚህ ዓይነቶቹን ድርጊቶች ይፈቅዳል ብለው በማሰብ መጽሐፍ ቅዱስንም ገሸሽ በማድረጋቸው የተሳሳተ እርምጃ ወስደዋል።

እንደ እውነቱ ከሆነ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ግብዝነትንና ዓመፅን ያወግዛል። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን የሃይማኖት መሪዎች “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጥ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፣ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፣ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል” ብሏቸዋል።—ማቴዎስ 23:27, 28

ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ከፖለቲካ ጉዳዮች ገለልተኛ እንዲሆኑ ያበረታታል። በተጨማሪም አማኞቹ እርስ በርሳቸው እንዲገዳደሉ ሳይሆን አንዳቸው ለሌላው ለመሞት እንኳ ፈቃደኞች እንዲሆኑ ያስተምራል። (ዮሐንስ 15:12, 13፤ 18:36፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12) በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ሃይማኖት “መቻቻል የማይታይበትና ከፋፋይ” ሳይሆን “ሁሉን አቀፍ” ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደሆነ” ተናግሯል።—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

ለመንፈሳዊ ጤንነት አስተማማኝ መመሪያ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ

መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች በአምላክ መልክ እንደተፈጠሩ ይነግረናል። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ይህ ማለት ሰዎች በአካል አምላክን ይመስላሉ ማለት ባይሆንም መንፈሳዊ ነገሮችን የመቀበል ችሎታን ወይም መንፈሳዊነትን ጨምሮ የአምላክን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አላቸው ማለት ነው።

ይህም በመሆኑ አምላክ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን የምናረካበትን መንገድና በመንፈሳዊ ረገድ የሚጠቅሙንንና የሚጎዱንን ነገሮች መለየት የምንችልበትን ተገቢ አመራር ያዘጋጅልናል ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ ነው። አምላክ ሲፈጥረን በሽታን መቋቋምና ጤነኞች ሆነን መቀጠል እንድንችል ድንቅ የሆነ በሽታ የመከላከል አቅም እንደሰጠን ሁሉ ትክክለኛ ውሳኔ እንድናደርግና በአካልም ሆነ በመንፈሳዊ ከሚጎዱን ተግባራት እንድንርቅ የሚረዳን ሕሊና ወይም ውስጣዊ ድምፅም ሰጥቶናል። (ሮሜ 2:14, 15) እንደምናውቀው በሽታ የመከላከል አቅም እንዲኖረን ከተፈለገ በተገቢው መንገድ መመገብ አለብን። በተመሳሳይም ሕሊናችን እንዲሠራ ጤናማ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ልንመግበው ያስፈልጋል።

ኢየሱስ በመንፈሳዊ ጤናሞች ሆነን እንድንቀጥል የሚረዳንን ምግብ ለይቶ ሲናገር “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” ብሏል። (ማቴዎስ 4:4) የይሖዋ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተመዘገበልን ሲሆን እሱም “ለትምህርት፣ ለተግሣጽ፣ ልብንም ለማቅናት . . . ይጠቅማል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ስለዚህ ይህንን መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ጥረት ማድረግ የእኛ ፈንታ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ባወቅንና መሠረታዊ ሥርዓቶቹን በሕይወታችን በሥራ ላይ ለማዋል በጣርን መጠን በመንፈሳዊም ሆን በአካላዊ ሁኔታ እንጠቀማለን።—ኢሳይያስ 48:17, 18

የሚደረገው ጥረት ይበዛበታልን?

እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት መንፈሳዊ ጤንነታችንን ማሻሻል ጊዜ ይጠይቃል፤ ጊዜ ማግኘቱ ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ አዳጋች እየሆነ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥረት በረከት ያስገኛል! ሥራ የሚበዛባቸው አንዳንድ ባለሞያዎች መንፈሳዊ ጤንነታቸውን ለመንከባከብ ጊዜ መመደባቸው አስፈላጊ ሆኖ ያገኙት ለምን እንደሆነ ሲናገሩ አዳምጥ።

የሕክምና ዶክተር የሆነችው ማሪና እንዲህ ብላለች:- “በሆስፒታል ውስጥ መሥራት ጀምሬ የሌሎች ሥቃይ በጥልቅ እስከተሰማኝ ጊዜ ድረስ ስለመንፈሳዊነቴ አስቤ አላውቅም ነበር። ከዚያም በእኔ ሙያ ለተሰማራ ሰው የኑሮ ሩጫና የተጨነቁ ሰዎችን መንከባከብ ከአቅም በላይ ሊሆንበት ስለሚችል እርካታና መረጋጋት ለማግኘት ከፈለግሁ መንፈሳዊ ነገር እንደሚያስፈልገኝ ማመንና ይህንንም ማሟላት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።

“አሁን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጠናለሁ። ይህ ጥናት ድርጊቶቼንና ውስጣዊ ዝንባሌዬን በመመርመር ማስተካከያ እንዳደርግ የሚረዳኝ ከመሆኑም በላይ አስተሳሰቤ ይበልጥ አዎንታዊ እንዲሆን ያሠለጥነኛል፤ ይህም ሚዛናዊ ሕይወት ለመምራት አስችሎኛል። በሰብዓዊ ሥራዬ በጣም እረካለሁ። ይሁን እንጂ አሉታዊ ስሜቶችን እንድቆጣጠርና ውጥረትን እንድቀንስ፣ እንዲሁም ለሰዎች ይበልጥ ታጋሽና ርኅሩኅ እንድሆን በመርዳት ስሜታዊ ጤንነቴን ያሻሻለልኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ማዋል በትዳሬም ጠቅሞኛል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ለማወቅና ለሕይወቴ ትልቅ ትርጉም የሰጠኝ መንፈሱን አለገደብ ማግኘት ችያለሁ።”

መሃንዲስ የሆነው ኒኮላስ እንዲህ ይላል:- “ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናቴ በፊት ምንም መንፈሳዊ ፍላጎት አልነበረኝም። ብቸኛው ግቤ በመረጥኩት የሥራ መስክ ስኬት ማግኘት ነበር። በሕይወት ውስጥ ከሙያዬ የበለጠ ነገር እንዳለና የይሖዋን ፈቃድ ማድረግ እውነተኛና ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኝ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ተማርኩ።

“ሰብዓዊ ሥራዬ እርካታ የሚሰጠኝ ቢሆንም በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ በማተኮር ኑሮን ቀላል የማድረግን አስፈላጊነት ያስተማረኝ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንዲህ በማድረግ እኔና ባለቤቴ በቁሳዊ ነገሮች ላይ ያተኮረ አኗኗር የሚያስከትላቸውን ብዙ ውጥረቶች አስወግደናል። በተጨማሪም በሕይወታቸው ውስጥ ተመሳሳይ መንፈሳዊ አመለካከት ካላቸው ሰዎች ጋር በመቀራረብ ብዙ እውነተኛ ወዳጆችን አፍርተናል።”

ጠበቃ የሆነው ቪንሰንት እንዲህ ይላል:- “ጥሩ ሥራ መጠነኛ እርካታ ሊያስገኝ ይችላል። ይሁን እንጂ ደስታና እርካታ ለማግኘት ከዚህ የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልግ ተገንዝቤያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እውነተኛ ደስታና እርካታ ምን እንደሚያስተምር ከማወቄ በፊት ሕይወት ፍጹም ከንቱ መሆኑ ይከነክነኝ ነበር። ሕይወት ማለት መወለድ፣ ማደግ፣ ማግባት፣ ልጆችን ለማሳደግ የሚያስፈልገውን ቁሳዊ ነገር ለማቅረብ መሥራት፣ ልጆቹ ደግሞ ያንኑ የሕይወት ዑደት እንዲከተሉ ማሠልጠንና በመጨረሻም አርጅቶ መሞት ከሆነ ትርጉም የለሽ እንደሚሆን ተሰምቶኝ ነበር።

“ስለ ሕይወት ዓላማ ለነበሩኝ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ያገኘሁት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ካጠናሁ በኋላ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ይሖዋን እንደ አንድ አካል እንዳውቀውና ለእርሱም ጥልቅ ፍቅር እንዲያድርብኝ አስችሎኛል። ይህም ሕይወቴን ከይሖዋ ዓላማ ጋር በማስማማት ለመኖር በምጥርበት ጊዜ ጤናማ መንፈሳዊ አመለካከት እንዲኖረኝ መሠረት ጥሎልኛል። አሁን እኔና ባለቤቴ ሕይወታችንን ትርጉም ባለው መንገድ እየተጠቀምንበት እንዳለ በማወቃችን እርካታ አግኝተናል።”

አንተም መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ሕይወትህ ዓላማና ትርጉም ያለው እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ። የይሖዋ ምሥክሮች ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው። እንደ ማሪና፣ ኒኮላስና ቪንሰንት ሁሉ አንተም ስለ ይሖዋና እርሱ ለሰው ልጆች በጥቅሉ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአንተ ስላለው ዓላማ በመማር የሚገኘውን እርካታ ልታገኝ ትችላለህ። አሁን መንፈሳዊ ፍላጎትህን በማሟላት ከመደሰትም በተጨማሪ ፍጹም በሆነ አካላዊ ጤንነት ለዘላለም የመኖር ተስፋ ታገኛለህ። ይህ ተስፋ የተዘረጋው ‘ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ ለሆኑ’ ሰዎች ብቻ ነው።—ማቴዎስ 5:3 NW

መንፈሳዊነታችንን ለማሳደግ ከሚረዱን ነገሮች አንዱ ጸሎት ነው። ኢየሱስ ጊዜ ወስዶ ለደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚጸልዩ በመንገር በተለምዶ የጌታ ጸሎት ተብሎ የሚጠራውን ጸሎት አስተምሯቸዋል። ዛሬ ይህ ጸሎት ለአንተ ምን ትርጉም አለው? ከዚህ ጸሎት ልትጠቀም የምትችለውስ እንዴት ነው? በሚቀጥሉት ሁለት ርዕሰ ትምህርቶች ውስጥ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ታገኛለህ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማሪና

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒኮላስ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቪንሰንት