በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በዓለም ያሉ ሁኔታዎች አስተማማኝ አለመሆናቸው የሚያሳድርብህን ጭንቀት መቋቋም

በዓለም ያሉ ሁኔታዎች አስተማማኝ አለመሆናቸው የሚያሳድርብህን ጭንቀት መቋቋም

በዓለም ያሉ ሁኔታዎች አስተማማኝ አለመሆናቸው የሚያሳድርብህን ጭንቀት መቋቋም

“እርግጠኛ ሁን!” “ያለቀለት ነገር ነው!” “ጥርጣሬ አይግባህ!” እነዚህን አባባሎች ብዙ ጊዜ ሳትሰማ አትቀርም። ይሁን እንጂ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን እርግጠኛ መሆን የማንችልባቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ሕይወት አስተማማኝ ካለመሆኑ የተነሳ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ መሆን የምንችልበት ነገር ስለመኖሩ አብዛኛውን ጊዜ ጥርጣሬ ያድርብናል። ጥርጣሬ አብሮን የሚኖር ነገር ይመስላል።

አብዛኞቹ ሰዎች ለራሳቸውም ሆነ ለቤተሰባቸው አስተማማኝ ሕይወትና ደስታ ማግኘት እንደሚፈልጉ ግልጽ ነው። ደስታና አስተማማኝ ሕይወት ያስገኙልናል የሚሏቸውን እንደ ገንዘብና ቁሳዊ ሀብት የመሳሰሉ ነገሮች ለማግኘት በጣም ይደክማሉ። ይሁን እንጂ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ አውሎ ነፋስ፣ ድንገተኛ አደጋ ወይም ከባድ ዓመፅ እነዚህን ነገሮች በድንገት ሊያወድማቸው ይችላል። ከባድ በሽታ፣ ፍቺ ወይም ሥራ ማጣት በሕይወታችን ላይ ያልተጠበቀ ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። እርግጥ እነዚህ ነገሮች በአንተ ላይ አይደርሱ ይሆናል። ሆኖም በማንኛውም ጊዜ አንድ አሳዛኝ ነገር ሊደርስብህ እንደሚችል ማወቁ በራሱ እረፍት የሚነሳና የሚያስጨንቅ ስሜት ያስከትላል። ይሁንና ችግሩ በዚህ አያበቃም።

አንድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ጥርጣሬ የሚለውን ቃል “እርግጠኛ ያለመሆን ሁኔታ” በማለት ፈትቶታል። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ ውሳኔ ለማድረግ እንቅፋት ይሆናል። በተጨማሪም ማኔጂንግ ዮር ማይንድ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው “በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አንድ ጉዳይ እርግጠኛ መሆን አለመቻል የጭንቀትና የስጋት ዋነኛ መንስኤ ነው።” በጥርጣሬ መኖር ጭንቀት፣ ግራ መጋባትና ብስጭት ሊያስከትል ይችላል። አዎን፣ ምን ይፈጠር ይሆን ብሎ መጨነቅ በአእምሯዊም ሆነ በአካላዊ ጤንነታችን ላይ ጉዳት ያስከትል ይሆናል።

ከዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች ወደ ሌላኛው ጽንፍ ይሄዳሉ። “ምን ይመጣ ይሆን ብዬ የምጨነቅበት ምን ምክንያት አለ? ዛሬ ራሱን የቻለ ቀን ነው፤ ነገ ደግሞ ሌላ ቀን ነው” በማለት የተናገረው ብራዚላዊ ወጣት ዓይነት አስተሳሰብ አላቸው። እንዲህ ያለው አደገኛ የሆነ “እንብላና እንጠጣ” የሚል አመለካከት ተስፋ መቁረጥ፣ ጭንቀትና በመጨረሻም ሞት ከማስከተል ሌላ የሚያስገኘው ነገር የለም። (1 ቆሮንቶስ 15:32) መጽሐፍ ቅዱስ “መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ” ብሎ ወደሚናገርለት ወደ ፈጣሪያችን ወደ ይሖዋ አምላክ ዞር ማለታችን በጣም ይጠቅመናል። (ያዕቆብ 1:17) የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች መቋቋም የምንችልበትን ጥሩ ምክርና መመሪያ እናገኛለን። በተጨማሪም ሁኔታዎች ይህን ያህል አስተማማኝ ያልሆኑት ለምን እንደሆነ እንድንረዳም ያስችለናል።

ጥርጣሬ የሚፈጥሩ ነገሮች

ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ ሕይወት ከእውነታው ያልራቀ አመለካከት የያዙ ከመሆኑም ሌላ አስተማማኝ ስላልሆኑ ነገሮችና በሕይወታችን ስለሚያጋጥሙን ለውጦች ተገቢውን አመለካከት እንድናዳብር ይረዱናል። የቤተሰብ ዝምድና፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለን ቦታ፣ እውቀት፣ ጥሩ ጤንነትና የመሳሰሉት ነገሮች በተወሰነ ደረጃ የደኅንነት ስሜት ሊያስገኙልን ቢችሉም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ነገሮች እንዲሁ ይቀጥላሉ ብለን መጠበቅ እንደሌለብን ወይም የተደላደለ ሕይወት እንኖራለን ብለን ማሰብ እንደሌለብን ይገልጻል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ ብሏል፦ “ሩጫ ለፈጣኖች፣ ሰልፍም ለኃያላን፣ እንጀራም ለጠቢባን፣ ባለጠግነትም ለአስተዋዮች፣ ሞገስም ለአዋቂዎች እንዳልሆነ አየሁ።” ለምን? “ጊዜና እድል ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል።” በመሆኑም ሰሎሞን “በክፉ መረብ እንደ ተጠመዱ ዓሣዎች፣ በወጥመድም እንደ ተያዙ ወፎች፣ እንዲሁ የሰው ልጆች በክፉ ጊዜ በድንገት ሲወድቅባቸው ይጠመዳሉ” የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—መክብብ 9:11, 12

ኢየሱስ ክርስቶስም በጣም አስጨናቂና አስተማማኝ ያልሆነ ጊዜ በአንድ ትውልድ ላይ እንደሚመጣ ተናግሯል። ሁኔታውን እንዲህ በማለት ግልጽ በሆነ መንገድ አስቀምጦታል፦ “በፀሐይና በጨረቃም በከዋክብትም ምልክት ይሆናል፤ በምድር ላይም አሕዛብ ከባሕሩና ከሞገዱም ድምፅ የተነሣ እያመነቱ ይጨነቃሉ፤ ሰዎችም ከፍርሃትና በዓለም የሚመጣበትን ከመጠበቅ የተነሣ ይደክማሉ፤ የሰማያት ኃይላት ይናወጣሉና።” ሆኖም ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ላሉ ልበ ቅን ሰዎች የሚያበረታታ ነገር ተናግሯል፦ “እናንተ ይህ ሁሉ መሆኑን ስታዩ የእግዚአብሔር መንግሥት እንደ ቀረበች እወቁ።” (ሉቃስ 21:25, 26, 31) በተመሳሳይ እርግጠኛ ያልሆነውን የወደፊቱን ጊዜ በፍርሃት ከመመልከት ይልቅ፣ በአምላክ ላይ ያለን እምነት አስተማማኝ ካልሆነው ዓለም ባሻገር ያለውን እርግጠኛ የሆነ ግሩም የወደፊት ተስፋ እንድንመለከት ያስችለናል።

“ተስፋ እስኪሞላ ድረስ”

የምንሰማውን፣ የምናነበውን ወይም የምናየውን ነገር ሁሉ በእርግጠኝነት ማመን ባንችልም በፈጣሪ እንድንታመን የሚያስችል አጥጋቢ ምክንያት አለን። እርሱ የመጨረሻው ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ከመሆኑም ሌላ በምድር ላሉት ልጆቹ የሚያስብ አፍቃሪ አባት ነው። አምላክ ከአፉ የሚወጣውን ቃል በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”—ኢሳይያስ 55:11

ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ የተቀበለውን እውነት ያስተማረ ሲሆን ትምህርቱን ያዳመጡት ብዙ ሰዎች ቃሉን በእምነትና በእርግጠኝነት ተቀብለዋል። ለምሳሌ ያህል ቅን ልቦና ያላቸው አንዳንድ የሰማርያ ሰዎች መጀመሪያ ከኢየሱስ ጋር ለተነጋገረችው ሴት እንዲህ ብለዋታል፦ “አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፣ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን።” (ዮሐንስ 4:42) ዛሬም በተመሳሳይ የምንኖረው አስተማማኝ ባልሆነ ጊዜ ውስጥ ቢሆንም ምን ማመን እንደሚገባን ግራ መጋባት አይኖርብንም።

ሃይማኖታዊ እምነቶችን በተመለከተ ብዙዎች አንድን ነገር ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ እንዲሁ አምኖ መቀበል ይሻላል የሚል አመለካከት አላቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበረው። ሌሎች እርሱ የጻፋቸውን ነገሮች በተመለከተ ‘እርግጡን እንዲያውቁ’ ምርምር አድርጎ ትክክለኛውን መረጃ አቅርቧል። (ሉቃስ 1:4) እምነታችንን የማይጋሩ የቤተሰባችን አባላትና ወዳጆቻችን በመጨረሻ ግራ ተጋብተንና ተስፋ ቆርጠን እንዳንቀር በማሰብ ሊጨነቁ ስለሚችሉ እምነታችንን ለሌሎች ማስረዳት መቻላችን በጣም አስፈላጊ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:15) ሌሎች በአምላክ እንዲያምኑ መርዳት የምንችለው አንድን ነገር እንድናምንበት ያደረገንን ትክክለኛውን ምክንያት የምናውቅ ከሆነ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “እርሱ አምላክ ነው፤ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው።”—ዘዳግም 32:4

“እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” በሚለው የጥቅሱ ክፍል ላይ እስቲ ትኩረት እናድርግ። በዚህ ላይ እምነት እንድናሳድር የሚያስችል ምን ማስረጃ አለ? ሐዋርያው ጴጥሮስ አምላክ እውነተኛና ቅን ስለመሆኑ እርግጠኛ ነበር። ለአንድ ሮማዊ የጦር መኮንንና ለቤተሰቡ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ብሏቸዋል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ጴጥሮስ እንዲህ ሊል የቻለው በፊት እንደ ርኩስ ተቆጥረው ይገለሉ ከነበሩት አሕዛብ መካከል አንድ ቤተሰብ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ ለማሳየት ይሖዋ እንዴት ጣልቃ ገብቶ ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ በማየቱ ነው። የቀድሞ አኗኗራቸውን ትተው በጽድቅ ጎዳና መጓዝ የጀመሩ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከ230 ከሚበልጡ አገሮች ሲሰበሰቡ በማየታችን እንደ ጴጥሮስ ሁሉ እኛም አምላክ የማያዳላና ጻድቅ መሆኑን አምነን መቀበል ችለናል።—ራእይ 7:9፤ ኢሳይያስ 2:2-4

እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን አክራሪ ወይም ጭፍን አቋም ያለን መሆን አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ትሑትና ምክንያታዊ መሆን ይገባናል። ሆኖም ስለምናምንበት ነገርና የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስላለን ተስፋ እርግጠኞች ነን። ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች “ተስፋ እስኪሞላ ድረስ እያንዳንዳችሁ ያን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን” በማለት ጽፎላቸዋል። (ዕብራውያን 6:11) በተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምሥራች ‘ተስፋው እንደሚሞላ’ አረጋግጦልናል። በአምላክ ቃል ላይ በጽኑ የተመሠረተው ይህ ተስፋ ጳውሎስ እንደገለጸው “አያሳፍርም።”—ሮሜ 5:5

ከዚህ በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምሥራች ለሌሎች መንገር በመንፈሳዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን በስሜታዊም ሆነ በአካላዊ ሁኔታ የመተማመንና የእርግጠኝነት ስሜት እንዲሰማቸው እንደሚያደርግ አንጠራጠርም። እኛም እንደ ጳውሎስ “ወንጌላችን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ በብዙ መረዳትም እንጂ በቃል ብቻ ወደ እናንተ አልመጣም” ብለን መናገር እንችላለን።—1 ተሰሎንቄ 1:5

መንፈሳዊ ደኅንነት ያስገኘልን በረከት

ምንም እንኳ በዛሬው ጊዜ ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነ ሕይወት ለማግኘት ባንጠብቅም በአንጻራዊ ሁኔታ የተረጋጋና አስተማማኝ ሕይወት ለመኖር ማድረግ የምንችላቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ስንገኝ ትክክለኛና ጥሩ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችንና የሥነ ምግባር ደንቦችን ስለምንማር የተረጋጋ ሕይወት ያስገኝልናል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአሁኑ ዘመን ባለ ጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ፣ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለ ጠግነት ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው።” (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ትምክህታቸውን አላፊ በሆነ ቁሳዊ ነገር ወይም በጊዜያዊ ደስታ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ መጣልን በመማር ብዙዎች በፊት ይሰማቸው ከነበረው ጭንቀትና ስጋት መገላገል ችለዋል።—ማቴዎስ 6:19-21

በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞች ሞቅ ያለ ፍቅር የሚያሳዩን ከመሆኑም በላይ በተለያዩ መንገዶች እርዳታና ድጋፍ ይሰጡናል። ሐዋርያው ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ አገልግሎት ላይ በነበሩበት በአንድ ወቅት ‘ስለ ሕይወታቸው እንኳ ተስፋ እስኪቆርጡ ድረስ ከብዷቸው’ ነበር። ጳውሎስ እርዳታና ማጽናኛ ያገኘው ከየት ነበር? እርግጥ ነው፣ በአምላክ ላይ የነበረውን እምነት አላጣም። ሆኖም ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ከሰጡት እርዳታ ማበረታቻና ማጽናኛ አግኝቷል። (2 ቆሮንቶስ 1:8, 9፤ 7:5-7) በዛሬው ጊዜ የተፈጥሮ አደጋዎች ወይም ሌሎች ችግሮች ሲከሰቱ ችግር ላይ ለወደቁት ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸውና ሌሎች ሰዎች በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠት ክርስቲያን ወንድሞቻችን ቀዳሚ ሆነው እንደሚገኙ በተደጋጋሚ ታይቷል።

በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን አስተማማኝ ያልሆኑ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚረዳን ሌላው ነገር ጸሎት ነው። አንድ ዓይነት ያልጠበቅነው ፈተና ሲያጋጥመን በሰማይ የሚኖረው አፍቃሪ አባታችን እንዲረዳን ምንጊዜም መጠየቅ እንችላለን። “እግዚአብሔር ለድሆች መጠጊያ ሆናቸው፣ እርሱም በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው።” (መዝሙር 9:9) ሰብዓዊ ወላጆች ልጆቻቸውን ከችግር ማዳን የማይችሉበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። ይሁን እንጂ አምላክ ያደረብንን ስጋትና ያለመተማመን ስሜት መቋቋም እንድንችል እኛን ለመርዳት ፈቃደኛ ነው። በጸሎት ጭንቀታችንን በይሖዋ ላይ የምንጥል ከሆነ “ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ ይልቅ እጅግ አብልጦ ሊያደርግ[ልን]” እንደሚችል እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ኤፌሶን 3:20

አምላክ እንዲረዳህ በጸሎት የመጠየቅ ልማድ አለህ? አምላክ ጸሎትህን እንደሚሰማ ታምናለህ? በሳኦ ፓውሎ የምትኖር አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ወደ አምላክ መጸለይ እንዳለብኝ ነግራኛለች። እኔ ግን ‘ፈጽሞ የማላውቀውን አካል የማናግረው ለምንድን ነው?’ ብዬ ራሴን ጠየቅሁ። ሆኖም ምሳሌ 18:10 የአምላክ እርዳታ እንደሚያስፈልገንና በጸሎት እርሱን ማነጋገር እንዳለብን እንድገነዘብ አስችሎኛል።” ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “የእግዚአብሔር ስም የጸና ግምብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።” ደግሞስ እርሱን የማነጋገር ልማድ ካላዳበርን እንዴት በይሖዋ መታመንና መመካት እንችላለን? መንፈሳዊ ደኅንነት የሚያስገኛቸውን በረከቶች ለመውረስ በየዕለቱ ልባዊ ጸሎት የማቅረብ ልማድ ሊኖረን ይገባል። ኢየሱስ “እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ” ብሏል።—ሉቃስ 21:36

ሌላው በእርግጠኝነት መጠባበቅ የምንችለው ነገር በአምላክ መንግሥት ላይ ያለን ተስፋ ነው። ዳንኤል 2:44 ምን እንደሚል ልብ በሉ፦ “የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።” ይህ ተስፋ እርግጠኛ ከመሆኑም በላይ መፈጸሙ እንደማይቀር መተማመን እንችላለን። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የገቡት ቃል ሳይፈጸም ይቀራል፤ በይሖዋ ቃል ላይ ግን ምንጊዜም እምነት ማሳደር እንችላለን። አምላክ ልንታመንበት የምንችል ጠንካራ አለት በመሆኑ አስተማማኝነቱን መጠራጠር አይገባንም። ዳዊት የነበረው ዓይነት ስሜት ማሳየት እንችላለን፦ “እግዚአብሔር ጠባቂዬ [“ዐለቴ፣” አ.መ.ት] ነው፣ በእርሱም እታመናለሁ፤ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፣ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፣ መድኃኒቴ ሆይ፣ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ።”—2 ሳሙኤል 22:3

ከላይ የተጠቀሰው ማኔጂንግ ዮር ማይንድ የተባለው መጽሐፍ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “አንድ ሰው ሊከሰቱ ይችላሉ ስለሚላቸው መጥፎ ነገሮች ብዙ ባሰበ መጠን በአእምሮው ላይ የተፈጸሙ ያህል ሆኖ ይሰማዋል፤ ከዚያም እንዴት ሊቋቋማቸው እንደሚችል ይባስ ግራ እየገባው ይሄዳል።” ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ፣ ይህ ዓለም የሚያመጣቸው ጭንቀቶችና አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሸክም እንዲሆኑብን ለምን እንፈቅዳለን? ከዚህ ይልቅ ትምክህታችሁን በዚህ ዓለም በሚገኙ አስተማማኝ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ሳይሆን አምላክ በገባቸው እርግጠኛ ተስፋዎች ላይ ጣሉ። ይሖዋ ቃል በገባልን አስተማማኝ ነገሮች ላይ ያለንን እምነት አጽንተን ከያዝን “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም” የሚለው ቃል ይፈጸምልናል።—ሮሜ 10:11

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሰው ልጆች ወደፊት የተሻለ ሕይወት እንደሚያገኙ የአምላክ ቃል ዋስትና ይሰጣል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም”

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመንግሥቱ ምሥራች ሰዎች ተማምነው እንዲኖሩ ያስችላቸዋል