በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነው’

‘የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነው’

‘የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነው’

“ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል።”—1 ቆሮንቶስ 7:29

1, 2. በሕይወት ዘመንህ በዓለም ላይ የተፈጸሙ የትኞቹን ለውጦች አይተሃል?

 በሕይወት ዘመንህ በዓለም ላይ ምን ዓይነት ለውጦችን አይተሃል? አንዳንዶቹን መጥቀስ ትችላለህ? ለምሳሌ ያህል፣ በሕክምናው መስክ የተደረገ እድገት አለ። በዚህ መስክ በተደረገው ምርምር የተነሳ በአንዳንድ አገሮች የሰዎች አማካይ የሕይወት ዘመን በ20ኛው መቶ ዘመን ከነበረበት ከ50 ዓመት በታች ተነስቶ ዛሬ ከ70 ዓመት በላይ ሆኗል! ከሬዲዮ፣ ከቴሌቪዥን፣ ከሞባይልና ከፋክስ ማሽን ያገኘናቸውንም ጥቅሞች አስብ። ሳይጠቀስ የማይታለፈው ሌላው ነገር ደግሞ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል ያስቻለው በትምህርት፣ በትራንስፖርትና በሰብዓዊ መብቶች መከበር ረገድ የተደረገው እድገት ነው።

2 እርግጥ ነው፣ የተደረጉት ለውጦች በሙሉ ጠቃሚ ናቸው ማለት አይቻልም። በፍጥነት እየጨመረ የመጣው ወንጀል፣ እያሽቆለቆለ ያለው የሥነ ምግባር አቋም፣ እያሻቀበ ያለው የዕፅ ሱሰኝነት፣ የፍቺ ቁጥር መጨመር፣ የዋጋ መናር እና በጣም አስጊ እየሆነ የመጣው ሽብርተኝነት ያስከተሉትን ጎጂ ውጤት ችላ ብሎ ማለፍ አይቻልም። ያም ሆነ ይህ ከረጅም ጊዜ በፊት ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና” ሲል በጻፈው ሐሳብ እንደምትስማማ አያጠራጥርም።—1 ቆሮንቶስ 7:31

3. ጳውሎስ ‘የዚህ ዓለም መልክ አላፊ ነው’ ሲል ምን ማለቱ ነበር?

3 ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የተናገረው ዓለምን በመድረክ በመመሰል ነበር። በመድረኩ ላይ ያሉት ተዋናዮች ማለትም የፖለቲካና የሃይማኖት መሪዎች እንዲሁም በማኅበረሰቡ ዘንድ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ወደ መድረኩ መጥተው ድርሻቸውን ከተወኑ በኋላ ቦታውን ለሌሎች ይለቅቃሉ። ይህ ሁኔታ ለብዙ መቶ ዘመናት ታይቷል። ባለፉት ዘመናት አንድ ሥርወ መንግሥት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት አንዳንድ ጊዜም ለመቶ ዓመታት ሊገዛ ይችላል። ለውጥ የሚከሰተውም ከስንት አንዴ ነበር። ዛሬ ግን እንደዚያ አይደለም! አንድ የአገር መሪ በድንገት ቢገደል በዚያው ቅጽበት የታሪክ ሂደት ሊቀየር ይችላል። በእርግጥም፣ በዚህ ባልተረጋጋ ዓለም ውስጥ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣ አናውቅም።

4. (ሀ) ክርስቲያኖች በዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ክስተቶች በተመለከተ ምን ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (ለ) ቀጥሎ የምንመረምራቸው ሁለት አሳማኝ ማስረጃዎች የትኞቹ ናቸው?

4 ዓለም መድረክ ከሆነና በዓለም ላይ ያሉት መሪዎች ደግሞ ተዋናዮች ከሆኑ ተመልካቾቹ ክርስቲያኖች ናቸው። a ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ‘የዓለም ክፍል ባለመሆናቸው’ ለተውኔቱም ሆነ ለተዋናዮቹ ማንነት ያን ያህል ትኩረት አይሰጡም። (ዮሐንስ 17:16) ከዚህ ይልቅ ድራማው በታላቅ ጥፋት የሚደመደምበት ጊዜ እየደረሰ መሆኑን የሚጠቁሙ ምልክቶችን በከፍተኛ ጉጉት ይከታተላሉ። ይህንንም የሚያደርጉት ይሖዋ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየውን ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ከማምጣቱ በፊት ይህ ሥርዓት መጥፋት እንዳለበት ስለሚያውቁ ነው። b በመሆኑም የምንኖረው በፍጻሜው ዘመን ውስጥ እንደሆነና አዲሱ ዓለም ደፍ ላይ መሆኑን የሚያሳዩ ሁለት ማስረጃዎችን እንመርምር። እነዚህም (1) የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት እና (2) እያሽቆለቆለ ያለው የዓለም ሁኔታ ናቸው።—ማቴዎስ 24:21፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

በመጨረሻ የተገለጠ ምሥጢር!

5. ‘የአሕዛብ ዘመን’ ምንድን ነው? ይህ ዘመን ለእኛ ትርጉም አለው የምንለው ለምንድን ነው?

5 የዘመናት ስሌት በጊዜና በዓለም ላይ በሚታዩ ክስተቶች መካከል ያለውን ዝምድና ለማወቅ የሚደረግ ጥናት ነው። የዓለም መሪዎች የአምላክ መንግሥት ጣልቃ ሳይገባባቸው መድረኩን ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ኢየሱስ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ይህንን ጊዜ ‘የአሕዛብ ዘመን’ ብሎ ጠርቶታል። (ሉቃስ 21:24) ይህ “ዘመን” ሲያበቃ የአምላክ መንግሥት ሥልጣን የሚይዝ ሲሆን በዚህ መንግሥት ላይ የመግዛት መብት ያለው ኢየሱስ ነው። መጀመሪያ ላይ ኢየሱስ የሚገዛው ‘በጠላቶቹ መካከል’ ይሆናል። (መዝሙር 110:2) ከዚያም ዳንኤል 2:44 እንደሚለው የአምላክ መንግሥት ሰዎች ያቋቋሟቸውን መንግሥታት በአጠቃላይ “ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”

6. ‘የአሕዛብ ዘመን’ የጀመረውና ያበቃው መቼ ነው? የቆየውስ ለምን ያህል ጊዜ ነው?

6 ‘የአሕዛብ ዘመን’ የሚያበቃውና የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምረው መቼ ነው? ‘እስከ ፍጻሜ ዘመን ድረስ ታትሞ’ የነበረው የዚህ ጥያቄ መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት ጋር የተያያዘ ነው። (ዳንኤል 12:9) አስቀድሞ የተነገረው ይህ “ዘመን” እየቀረበ ሲመጣ ይሖዋ ትሑት ለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መልሱን ለማሳወቅ እርምጃዎች ወስዷል። በአምላክ መንፈስ እርዳታ ‘የአሕዛብ ዘመን’ የጀመረው ኢየሩሳሌም በጠፋችበት በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት እንደሆነና ይህ “ዘመን” የ2,520 ዓመታት ርዝመት እንዳለው ተገነዘቡ። ይህን መሠረት በማድረግ ‘የአሕዛብ ዘመን’ በ1914 እንደሚያበቃ ማስላት ችለዋል። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ የጀመረው በ1914 እንደሆነ አስተዋሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንደመሆንህ መጠን 1914 ላይ መድረስ የተቻለው እንዴት እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ በመጠቀም ማስረዳት ትችላለህ? c

7. በዳንኤል መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ሰባት ዘመን የጀመረበትን፣ የቆየበትንና ያበቃበትን ጊዜ ለማስላት የሚረዱን የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?

7 በዳንኤል መጽሐፍ ላይ አንድ ፍንጭ ተጠቅሶ እናገኛለን። ‘በአሕዛብ ዘመን’ መጀመሪያ ላይ ማለትም በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት የተጠቀመው በባቢሎኑ ንጉሥ በናቡከደነፆር ስለነበር ብሔራት ያለ ምንም መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት በጥቅሉ ለሰባት ምሳሌያዊ ዘመናት እንደሚገዙ ለዚህ ንጉሥ ገልጾለታል። (ሕዝቅኤል 21:26, 27፤ ዳንኤል 4:16, 23-25) እነዚህ ሰባት ዘመናት ምን ያህል ርዝመት አላቸው? በራእይ 11:2, 3 እና 12:6, 14 መሠረት ሦስት ተኩል ዘመናት የ1,260 ቀናት ርዝመት አላቸው። በመሆኑም ሰባት ዘመናት የዚያን እጥፍ ወይም የ2,520 ቀናት ርዝመት አላቸው። ነገሩ በዚህ አበቃ ማለት ነው? አይደለም። ይሖዋ በዳንኤል ዘመን ለነበረው ለነቢዩ ሕዝቅኤል ምሳሌያዊውን ዘመን ማብራራት የሚቻልበት ደንብ ሰጥቶታል። “አንድን ዓመት አንድ ቀን አድርጌ . . . ሰጥቼሃለሁ።” (ሕዝቅኤል 4:6) ስለዚህ ሰባቱ ዘመናት የ2,520 ዓመታት ርዝመት ይኖራቸዋል። ከ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት መቁጠር ከጀመርንና የጊዜው ርዝመት 2,520 ዓመታት ከሆነ የአሕዛብ ዘመን የሚያበቃው በ1914 ነው ብለን መደምደም እንችላለን።

‘የፍጻሜው ዘመን’ ተረጋገጠ

8. ከ1914 ጀምሮ በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ መባባሱን በተመለከተ ምን ማስረጃ መጥቀስ ትችላለህ?

8 ከ1914 ወዲህ በዓለም ላይ የተፈጸሙት ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት ላይ የተመሠረተው ከላይ የደረስንበት መደምደሚያ ትክክል መሆኑን ያረጋግጣሉ። ጦርነት፣ ረሃብና ቸነፈር “የዓለም መጨረሻ” መቅረቡን እንደሚያመለክቱ ኢየሱስ ራሱ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:3-8፤ ራእይ 6:2-8) ከ1914 አንስቶ ምልክቱ በዓለም ላይ በትክክል ተፈጽሟል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ሲሰጥ ሰዎች እርስ በርሳቸው በሚኖራቸው ግንኙነት ረገድ ጉልህ ለውጥ እንደሚኖር ተናግሯል። የሰዎች ባሕርይ እንደሚለወጥ የሰጠው መግለጫ በጣም ትክክል ለመሆኑ ሁላችንም ምሥክሮች ነን።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5

9. ከ1914 አንስቶ በዓለም ላይ ስላለው ሁኔታ ታዛቢዎች ምን ብለዋል?

9 ከ1914 አንስቶ “የዚች ዓለም መልክ” በእርግጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል? ዘ ጀነሬሽን ኦቭ 1914 (የ1914 ትውልድ) በተባለው መጽሐፍ ላይ ፕሮፌሰር ሮበርት ቮል እንዲህ ብለዋል፦ “በሕይወት ዘመናቸው ጦርነቱን የተመለከቱ ሰዎች ነሐሴ 1914 ላይ አንድ ዓለም አክትሞ ሌላ ዓለም መጀመሩን በሚገባ ያምናሉ።” በዓለም ጤና ድርጅት የአእምሮ ሕክምና ዳይሬክተር ዶክተር ዦርዥ አልቤርቱ ኮስታ ኢ ሲልቫ እንዲህ በማለት ተመሳሳይ ሐሳብ ሰጥተዋል፦ “ባለንበት ዘመን በከፍተኛ ፍጥነት ለውጦች እየተካሄዱ ሲሆን እነዚህ ለውጦች በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ መጠን ከፍተኛ ጭንቀትና ውጥረት እያስከተሉ ናቸው።” አንተ በግልህ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞሃል?

10. መጽሐፍ ቅዱስ ከ1914 አንስቶ የዓለም ሁኔታ እየተበላሸ እንዲሄድ ምክንያት የሆነውን አካል የሚገልጽልን እንዴት ነው?

10 የዓለም ሁኔታ እየተበላሸ እንዲሄድ በማድረጉ ተጠያቂ የሚሆነው ማን ነው? ራእይ 12:7-9 የወንጀለኛውን ማንነት ይነግረናል፦ “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና [ኢየሱስ ክርስቶስ] መላእክቱ ዘንዶውን [ሰይጣን ዲያብሎስ] ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ . . . ታላቁ ዘንዶ . . . ወደ ምድር ተጣለ።” ስለዚህ ችግር በመቆስቆስ ተጠያቂ የሚሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ሲሆን ከሰማይ ከተጣለበት ከ1914 አንስቶ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” የሚለው ጥቅስ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ራእይ 12:10, 12

የመጨረሻው ትዕይንት ምን ይሆን?

11. (ሀ) ሰይጣን ‘ዓለሙን ሁሉ’ ለማሳት በምን ዘዴዎች ይጠቀማል? (ለ) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሰይጣን ምን ለየት ያለ ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል?

11 ሰይጣን የሚጠፋበት ጊዜ መቅረቡን ስለሚያውቅ ከ1914 አንስቶ ‘ዓለሙን ሁሉ’ ለማሳት የሚያደርገውን ጥረት አፋፍሟል። ቀንደኛ አታላይ የሆነው ሰይጣን መድረኩ ላይ የዓለም መሪዎችንና ፈር ቀዳጅ ታዋቂ ሰዎችን ተዋናይ አድርጎ በማቅረብ ከመድረክ በስተጀርባ ሆኖ ተግባሩን ያከናውናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:13፤ 1 ዮሐንስ 5:19) ከግቦቹ መካከል አንዱ የሰው ልጆች የእርሱ አገዛዝ እውነተኛ ሰላም ያስገኝልናል ብለው እንዲያስቡ በማድረግ ማታለል ነው። የዓለም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበላሸ መሆኑን የሚያሳይ ብዙ ማስረጃ እያለም ሰዎች ነገሮች እንደሚስተካከሉ የሚያስቡ መሆኑ በአመዛኙ ፕሮፓጋንዳው ግቡን እንደመታለት ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ሥርዓት ወደ መጥፊያው ሲቃረብ በይፋ የሚታወጅ ሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳ እንደሚኖር ተንብዮ ነበር። “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ፣ ያን ጊዜ ምጥ እርጉዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም” ሲል ጽፏል።—1 ተሰሎንቄ 5:3፤ ራእይ 16:13

12. በዘመናችን ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ምን ቀጣይ የሆነ ጥረት ተደርጓል?

12 ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የፖለቲካ ሰዎች የተለያዩ ሰብዓዊ እቅዶችን ለመግለጽ “ሰላምና ደኅንነት” የሚለውን አባባል ብዙ ጊዜ ሲጠቀሙበት ይሰማሉ። እንዲያውም 1986ን የሰላም ዓመት ብለው ሰይመውት ነበር። ሆኖም ሙከራቸው ወሬ ብቻ ሆኖ ቀርቷል። የዓለም መሪዎች የሚያደርጓቸው እነዚህን የመሳሰሉ ጥረቶች 1 ተሰሎንቄ 5:3 የተሟላ ፍጻሜውን እንዲያገኝ አስችለዋል? ወይስ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ የመላውን ዓለም ትኩረት የሚስብ አስገራሚ የሆነ አንድ ታላቅ ክስተት እንደሚኖር ያሳያል?

13. ጳውሎስ “ሰላምና ደኅንነት” ከታወጀ በኋላ የሚመጣውን ጥፋት ከምን ጋር አመሳስሎታል? ከዚህስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

13 አብዛኛውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ሙሉ በሙሉ መረዳት የሚቻለው ከተፈጸሙ በኋላ ወይም በመፈጸም ላይ ባሉበት ወቅት ብቻ ስለሆነ ትንቢቱ የሚፈጸምበትን መንገድ ለማየት በትዕግሥት መጠበቅ አለብን። ሆኖም “ሰላምና ደኅንነት” የሚለው ልፈፋ ከተሰማ በኋላ በድንገት የሚመጣውን ጥፋት ጳውሎስ ከእርጉዝ ሴት የምጥ ጣር ጋር ማመሳሰሉ ትኩረት የሚስብ ነው። ወደ ዘጠኝ ወር በሚፈጀው የእርግዝና ጊዜ አንዲት ነፍሰ ጡር ቀኗ እየደረሰ ሲመጣ በሆዷ ውስጥ እያደገ ያለው ጽንስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ይበልጥ ታስተውላለች። የጽንሱን የልብ ምት መስማት ወይም በማህጸኗ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ማስተዋል ትችል ይሆናል። አንዳንድ ጊዜም ይረግጣታል። በአብዛኛው እነዚህ ምልክቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉልህ እየሆኑ ይሄዱና አንድ ቀን ኃይለኛ ውጋት ሲሰማት ማለትም ምጥ ሲጀምራት በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው፣ ሕፃኑ የሚወለድበት ጊዜ መድረሱ ይታወቃል። በተመሳሳይም በትንቢት የተነገረው “ሰላምና ደኅንነት” የሚለው ልፈፋ በምንም መልኩ ቢፈጸም ድንገተኛና ሥቃይ የተሞላበት ሆኖም በመጨረሻ አስደሳች ወደሆነ ክንውን የሚመራ ይሆናል። ይህም የዚህ ክፉ ሥርዓት መደምሰስና አዲስ የዓለም ሥርዓት መጥባት ነው።

14. ወደፊት የሚፈጸሙት ክንውኖች ምን ዓይነት ቅደም ተከተል ይኖራቸዋል? የመጨረሻ ውጤታቸውስ ምንድን ነው?

14 ከፊታችን የሚጠብቀን ጥፋት ዳር ቆመው ሁኔታውን ለሚመለከቱት ታማኝ ክርስቲያኖች የሚያስፈራ ይሆናል። በመጀመሪያ የምድር ነገሥታት (የሰይጣን ድርጅት የሆነው የፖለቲካው ዓለም) በታላቂቱ ባቢሎን ደጋፊዎች (የሃይማኖቱ ዓለም) ላይ በመነሳት ያጠፏቸዋል። (ራእይ 17:1, 15-18) በመሆኑም ትዕይንቱ በድንገት መልኩን ይቀይርና አንዱ ክፍል በሌላው ላይ ጥቃት በመሰንዘር የሰይጣን ግዛት እርስ በርሱ ይከፋፈላል። ይህ ሲሆን ሰይጣን ሁኔታውን የሚያስቆምበት ኃይል አይኖረውም። (ማቴዎስ 12:25, 26) ይሖዋ የምድር ነገሥታት “አሳቡን እንዲያደርጉ” ማለትም አምልኮውን የሚቀናቀኑ ጠላቶቹን ከምድር ላይ ጠራርገው እንዲያጠፉ በልባቸው ውስጥ ይከትታል። የሐሰት ሃይማኖት ከተወገደ በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰማይ ያለውን ሠራዊቱን አስከትሎ ከሰይጣን ድርጅት የቀረውን የንግዱንና የፖለቲካውን መዋቅር እንዳልነበረ ያደርገዋል። በመጨረሻም ሰይጣን ራሱ በቁጥጥር ሥር ይውላል። በዚህ ጊዜ የመድረኩ መጋረጃ ይዘጋል፤ ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ድራማም ያበቃል።—ራእይ 16:14-16፤ 19:11-21፤ 20:1-3

15, 16. “ዘመኑ አጭር ሆኖአል” የሚለው ማሳሰቢያ በሕይወታችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

15 እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን አናውቅም። (ማቴዎስ 24:36) ይሁን እንጂ ‘ዘመኑ አጭር መሆኑን’ እናውቃለን። (1 ቆሮንቶስ 7:29) በመሆኑም የቀረውን ጊዜ በጥበብ መጠቀማችን በጣም አስፈላጊ ነው። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው አላስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ፋንታ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ‘ዘመኑን መዋጀት’ ያለብን ከመሆኑም ሌላ ጊዜያችንን በአግባቡ መጠቀም ይኖርብናል። ለምን? “ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና።” በተጨማሪም ይሖዋ ለእኛ ያለው ‘ፈቃድ ምን እንደሆነ ስለምናስተውል’ የቀረችውን ውድ የሆነች አጭር ጊዜ ማባከን አንፈልግም።—ኤፌሶን 5:15-17፤ 1 ጴጥሮስ 4:1-4

16 ይህ ሥርዓት በአጠቃላይ እንደሚወገድ ማወቃችን በግለሰብ ደረጃ እንዴት ሊነካን ይገባል? ሐዋርያው ጴጥሮስ “ይህ ሁሉ እንዲህ የሚቀልጥ ከሆነ፣ . . . በቅዱስ ኑሮ እግዚአብሔርንም በመምሰል” መመላለስ እንዳለብን በመግለጽ ጠቃሚ ምክር ሰጥቶናል! (2 ጴጥሮስ 3:11) በእርግጥም እንደዚህ ዓይነት ሰዎች መሆን ይገባናል! ጴጥሮስ ከሰጠን ጥበብ ያዘለ ምክር ጋር በሚስማማ መንገድ (1) አኗኗራችን ቅድስና ያለበት እንዲሆን አካሄዳችንን በጥንቃቄ መመልከት እንዲሁም (2) በይሖዋ አገልግሎት የምናከናውነው ቅንዓት የተሞላበት ተግባር ምንጊዜም ለእርሱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን መከታተል ይኖርብናል።

17. ታማኝ ክርስቲያኖች በየትኞቹ የሰይጣን ወጥመዶች ላለመያዝ መጠንቀቅ አለባቸው?

17 ለአምላክ ያለን ፍቅር በዚህ ዓለም ማታለያዎች ተስበን ከዓለም ጋር ቁርኝት እንዳንፈጥር ይረዳናል። ይህ ሥርዓት ከሚጠብቀው ጥፋት አንጻር ሲታይ ልቅ በሆነ ዓለማዊ የአኗኗር ዘይቤው በሚንጸባረቁት አታላይ መስህቦች መማረካችን ችግር ላይ ይጥለናል። የምንኖረውም ሆነ የምንሠራው በዓለም ቢሆንም እንኳ በዓለም ሙሉ በሙሉ እንዳንጠቀም የተሰጠንን ጥበብ ያዘለ ምክር መከተል ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 7:31) እንዲያውም ያለንበት ዓለም በሚያስፋፋው ፕሮፓጋንዳ እንዳንታለል የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ይህ ዓለም ጠፍረው የያዙትን ችግሮች በመፍታት ረገድ ሊሳካለት አይችልም። የአሁኑ ሥርዓት በዚህ መልኩ ለዘለቄታው አይቀጥልም። ይህን ያህል እርግጠኛ መሆን የምንችለው ለምንድን ነው? በመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የተጻፈው የአምላክ ቃል “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” ስለሚል ነው።—1 ዮሐንስ 2:17

ወደር የሌለው በረከት ይጠብቀናል!

18, 19. በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን ዓይነት ለውጦች ይኖራሉ ብለህ ትጠብቃለህ? በትዕግሥት መጠበቃችን አያስቆጭም የምንለውስ ለምንድን ነው?

18 በቅርቡ ይሖዋ ሰይጣንንና ደጋፊዎቹን ከሕልውና ውጪ ያደርጋቸዋል። ከዚያም፣ በዚህ ሥርዓት ላይ ከሚደርሰው ጥፋት የተረፉ ታማኝ ሰዎች በአምላክ እርዳታ የዓለምን “መልክ” ለዘለቄታው ለመቀየር ለተግባር ይንቀሳቀሳሉ። አምላክ ‘እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ጦርነትን ስለሚሽር’ ጦርነት የዓለምን መልክ ማበላሸቱ ያከትማል። (መዝሙር 46:9) በምግብ እጥረት ፋንታ ‘በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፈረፋል።’ (መዝሙር 72:16 አ.መ.ት) እስር ቤቶች፣ ፓሊስ ጣቢያዎች፣ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፉ በሽታዎች፣ ዕጽ አዘዋዋሪዎች፣ ፍቺ፣ የኢኮኖሚ ኪሳራም ሆነ ሽብርተኝነት ይወገዳሉ።—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 33:24፤ ራእይ 21:3-5

19 የመታሰቢያ መቃብሮች ባዶ ይሆናሉ፤ ከሞት የተነሱ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ማለትም ተጨማሪ ተዋናዮች ወደ መድረኩ ብቅ ይላሉ። አንድ ትውልድ ከሌላው ጋር ሲገናኝ እንዲሁም ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የነበሩ የሚፋቀሩ ሰዎች በደስታ ሲተቃቀፉ በጣም የሚያስደስት ሁኔታ ይኖራል! በመጨረሻ፣ ሕይወት ያለው ሁሉ ይሖዋን ያመልካል። (ራእይ 5:13) በመድረኩ ላይ የሚደረጉት ለውጦች በሙሉ ሲጠናቀቁና መጋረጃው ሲገለጥ መላዋ ምድር ገነት ሆና ትታያለች። ዞር ዞር እያልክ አካባቢህን ስትቃኝ ምን ይሰማሃል? ‘ይህን ለማግኘት ለረጅም ጊዜ በትዕግሥት ጠብቄአለሁ፤ ሆኖም ፈጽሞ አልቆጭም!’ በማለት በደስታ እንደምትናገር አያጠራጥርም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ጳውሎስ በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ለዓለም ሁሉ [ለ]መላእክትም ለሰዎችም ትርኢት” እንደሆኑ ተናግሯል።—1 ቆሮንቶስ 4:9 አ.መ.ት

b ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል 11:40, 44, 45 ላይ የተጠቀሰውን ‘የሰሜን ንጉሥ’ ማንነት ለማወቅ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! የተባለውን መጽሐፍ ገጽ 280-1 ተመልከት።

c ኢየሩሳሌም የተደመሰሰችው በግዞት የተወሰዱት አይሁዳውያን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት ወደ ትውልድ አገራቸው ከመመለሳቸው ከ70 ዓመታት በፊት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይናገራል። (ኤርምያስ 25:11, 12፤ ዳንኤል 9:1-3) ስለ ‘አሕዛብ ዘመን’ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለ መጽሐፍ ገጽ 94-6 ተመልከት።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነው” ሲል የተናገረው ሐሳብ በዘመናችን የተፈጸመው እንዴት ነው?

• የመጽሐፍ ቅዱስ የዘመናት ስሌት ‘የአሕዛብ ዘመን’ ያበቃበትን ጊዜ የሚያመላክተው እንዴት ነው?

• እየተለወጠ ያለው የዓለም ሁኔታ ‘የፍጻሜው ዘመን’ የጀመረው በ1914 እንደሆነ የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?

• “ዘመኑ አጭር” መሆኑን ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመጨረሻ ምሥጢሩ ተገለጠ!