በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና እንክብካቤ አይቻለሁ

የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና እንክብካቤ አይቻለሁ

የሕይወት ታሪክ

የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና እንክብካቤ አይቻለሁ

ፌይ ኪንግ እንደተናገረችው

ወላጆቼ ደግ ሰዎች ነበሩ፤ ሆኖም እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ እነርሱም ለሃይማኖት ከባድ ጥላቻ ነበራቸው። እማዬ “አምላክ ባይኖር ኖሮ የምናያቸውን አበቦችና ዛፎች ማን ፈጠራቸው ሊባል ነው?” ትል ነበር። ከዚህ በላይ ግን አልፋ አትሄድም።

ባቴ የሞተው በ1939 ገና የ11 ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። ያደግሁት ከእናቴ ጋር ሲሆን የምንኖረው በእንግሊዝ ከማንቸስተር በስተ ደቡብ ብዙም ሳይርቅ በሚገኘው በስቶክፖርት ነበር። ከልጅነቴ አንስቶ ስለ ፈጣሪዬ ይበልጥ የማወቅ ፍላጎት የነበረኝ ከመሆኑም ሌላ ለመጽሐፍ ቅዱስ አክብሮት ነበረኝ። ሆኖም መጽሐፉ ምን እንደሚል አላውቅም ነበር። በመሆኑም ምን ብለው እንደሚያስተምሩ ለማየት ወደ እንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ወሰንኩ።

የአምልኮ ሥርዓታቸው ብዙም ባይማርከኝም ኢየሱስ ያስተማራቸው ነገሮች ከወንጌሎች ላይ በሚነበቡበት ጊዜ ግን መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆን አለበት የሚል እምነት አደረብኝ። ያለፈውን ጊዜ መለስ ብዬ ሳስብ መጽሐፍ ቅዱስን አለማንበቤ በጣም ያስገርመኛል። ከጊዜ በኋላ አንዲት የቤተሰባችን ወዳጅ በቀላል ቋንቋ የተዘጋጀ “አዲስ ኪዳን” ከሰጠችኝ በኋላ እንኳ መጽሐፉን ለማንበብ ያደረግሁት ጥረት አልነበረም።

በ1950 የኮሪያ ጦርነት መቀስቀስ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ቆም ብዬ እንዳስብ አደረገኝ። ጦርነቱ እንደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየተስፋፋ ይሄድ ይሆን? ጦርነቱ እኛም ጋር ከደረሰ ኢየሱስ ጠላቶቻችሁን ውደዱ ሲል የሰጠውን ትእዛዝ ሳልጥስ መኖር የምችለው እንዴት ነው? በሌላ በኩል ደግሞ አገሬን ጠላት ሲወርራት እንዴት ዝም ብዬ አያለሁ? እንዲህ ማድረግ ለአገሬ ካለብኝ ግዴታ መሸሽ ይሆንብኛል። ጉዳዩ ግራ የሚያጋባ ቢሆንብኝም መጽሐፍ ቅዱስ ለጥያቄዎቼ መልስ እንደሚኖረው እርግጠኛ ነበርኩ። ሆኖም መልሱን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የት ቦታና እንዴት ማግኘት እንደምችል የማውቀው ነገር አልነበረም።

አውስትራሊያ ውስጥ እውነትን ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት

በ1954 እኔና እናቴ ታላቅ እህቴ ጂን ወደምትኖርበት ወደ አውስትራሊያ ለመሄድ ወሰንን። ከጥቂት ዓመታት በኋላ፣ ጂን መጽሐፍ ቅዱስ የመማር ፍላጎት እንዳለኝና ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደምሄድ ስላወቀች የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው እንዲያነጋግሩኝ ሁኔታዎችን እንዳመቻቸችልኝ ነገረችኝ። ስለ እነርሱ ያለኝን አመለካከት የማወቅ ፍላጎት ነበራት። “ትምህርታቸው ትክክል ይሁን አይሁን የማውቀው ነገር የለም። ቢያንስ ቢያንስ ግን ከሌሎች ቤተ ክርስቲያኖች የተሻለ ማብራሪያ ይሰጡሻል” አለችኝ።

ቤት መጥተው ያነጋገሩኝ ቢልና ሊንዳ ሽኔደር በጣም ደስ የሚሉ ባልና ሚስት ናቸው። ዕድሜያቸው በ60ዎቹ መገባደጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ በርካታ ዓመታት አስቆጥረዋል። በአዴላይድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሬዲዮ ጣቢያ ይሠሩ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በአውስትራሊያ የስብከቱ ሥራ ሲታገድ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ቢልና ሊንዳ በጣም የረዱኝ ቢሆንም እኔ ግን የተለያዩ ሃይማኖቶችን መመርመሬን አላቆምኩም።

አብሮኝ የሚሠራ አንድ ሰው ወንጌላዊው ቢሊ ግራሃም ስብከት ወደሚሰጥበት ስብሰባ ይዞኝ ሄደ። ስብከቱ ካበቃ በኋላ ጥያቄ ካለን ማቅረብ እንደምንችል ተነግሮን ስለነበር የተወሰንን ሰዎች ከአንድ ቄስ ጋር ተገናኘን። አእምሮዬ ውስጥ የሚጉላላውን ጥያቄ ጠየቅሁት፦ “አንድ ሰው ጦር ሜዳ ሄዶ የሚገድል ከሆነ ክርስቲያን መሆንና ጠላትህን ውደድ የሚለውን ሕግ ማክበር የሚችለው እንዴት ነው?” እዚያ የነበሩት ሁሉ ይኸው ጥያቄ ይከነክናቸው ስለነበር መልሱን ማወቅ እንደሚፈልጉ ገለጹ! ቄሱ ከትንሽ ቆይታ በኋላ “ለዚህ ጥያቄ መልስ የለኝም። እስካሁን ድረስ እያሰብኩበት ነው” አለ።

በዚህ ጊዜ ከቢልና ከሊንዳ ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናቴን ቀጥዬ ነበር። ከዚያም መስከረም 1958 ተጠመቅሁ። የአስጠኚዎቼን ምሳሌ የመከተል ግብ ስለነበረኝ በቀጣዩ ዓመት ነሐሴ ላይ የዘወትር አቅኚ በመሆን በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነቱ ሥራ መካፈል ጀመርኩ። ከስምንት ወር በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ጥያቄ ቀረበልኝ። ታላቅ እህቴ ጂን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷ እንደገፋችበትና እንደተጠመቀች ስሰማ በጣም ተደሰትኩ!

ተጨማሪ የአገልግሎት በር ተከፈተልኝ

በወቅቱ የተመደብኩት ሲድኒ ውስጥ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ሲሆን በርካታ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችም ነበሩኝ። አንድ ቀን ከእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን በጡረታ የተገለሉ ቄስ አገኘሁና ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለ ዓለም መጨረሻ ምን ብላ እንደምታስተምር ጠየቅዃቸው። በቤተ ክርስቲያኑ ለ50 ዓመታት ሲያስተምሩ እንደቆዩ የነገሩኝ ቢሆንም “የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ስለሌለኝ በዚህ ጥያቄ ላይ ጊዜ ወስጄ ምርምር ማድረግ ይኖርብኛል” በማለት የሰጡኝ መልስ በጣም አስገረመኝ።

ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ በፓኪስታን ማገልገል የሚፈልጉ እንዲያመለክቱ ተጠየቀ። ማስታወቂያው ነጠላ የሆኑ ወንዶችንና ባልና ሚስቶችን እንጂ ነጠላ እህቶችን እንደማይጨምር ባለማወቄ ማመልከቻ አስገባሁ። ይሁንና ያቀረብኩት ማመልከቻ ብሩክሊን ወደሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ተላከ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ የምፈልግ ከሆነ ወደ ቦምቤ፣ ሕንድ (አሁን ሙምባይ ትባላለች) ሄጄ ማገልገል እንደምችል የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰኝ። ይህ የሆነው በ1962 ነበር። እኔም ወደዚያ አቅንቼ ለ18 ወራት በቦምቤ ካገለገልኩ በኋላ ወደ አላሃባድ ተዛወርኩ።

እዚያ እንደደረስኩ ሂንዲ ቋንቋ ለመማር ቆርጬ ተነሳሁ። ይህ ቋንቋ አጻጻፉም ሆነ የቃላት አጠራሩ ወጥነት ያለው ስለሆነ ቋንቋውን መልመድ ያን ያህል አዳጋች አይደለም። ይሁን እንጂ የማናግራቸው ሰዎች በቋንቋቸው ለመናገር ከምፍጨረጨር ይልቅ በእንግሊዝኛ እንዳናግራቸው ሲጠይቁኝ ተስፋ አስቆራጭ ሆነብኝ! ሆኖም በዚህ አዲስ ቦታ አስደሳችና የሚያታግል ሁኔታ የገጠመኝ ከመሆኑም ሌላ ከአውስትራሊያ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸው አስደስቶኝ ነበር።

በወጣትነቴ የማግባት ፍላጎት ነበረኝ፤ ሆኖም በተጠመቅሁበት ወቅት ይሖዋን በማገልገል ተጠምጄ ስለነበር የጋብቻ ጉዳይ ከአእምሮዬ ወጣ። አሁን ግን የትዳር ጓደኛ እንደሚያስፈልገኝ እንደገና ይሰማኝ ጀመር። እርግጥ የአገልግሎት ምድቤን ትቶ የመሄድ ፍላጎት አልነበረኝም። በመሆኑም ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩትና ከአእምሮዬ አወጣሁት።

ያልተጠበቀ በረከት

በወቅቱ በሕንድ ቅርንጫፍ ቢሮ ለሚካሄደው ሥራ አመራር የሚሰጠው ኤድዊን ስኪነር ነበር። በቻይና የተመደቡትን ሃሮልድ ኪንግንና ስታሊን ጆንስን ጨምሮ ከበርካታ ታማኝ ወንድሞች ጋር በ1946 በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት በስምንተኛው ክፍል ተካፍሎ ነበር። a በ1958 ሃሮልድና ስታንሊ በሻንጋይ ባካሄዱት የስብከት እንቅስቃሴ ምክንያት ታሰሩ። ሃሮልድ በ1963 ከእስር ቤት ከተፈታ በኋላ ኤድዊን ደብዳቤ ጻፈለት። ሃሮልድ ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ ደርሶ ወደ ሆንግ ኮንግ ከተመለሰ በኋላ መልስ ጻፈለትና በደብዳቤው ላይ የማግባት ፍላጎት እንዳለው ገለጸ። እስር ቤት እያለ በዚህ ጉዳይ ላይ ይጸልይ እንደነበርና ለእርሱ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ልትሆን የምትችል እህት ያውቅ እንደሆነ ኤድዊንን ጠየቀው።

በሕንድ አብዛኛውን ጊዜ ጋብቻ የሚፈጸመው በአገናኞች አማካኝነት ሲሆን ኤድዊን ብዙ ጊዜ እንዲህ እንዲያደርግ ጥያቄ ይቀርብለት ነበር። እርሱ ግን በዚህ ጉዳይ እጁን ለማስገባት ፈቃደኛ አልነበረም። በመሆኑም የሃሮልድን ደብዳቤ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ለሆነው ለሆመር ባለቤት ለሩት ማክኬይ ሰጣት። ከዚያም ሩት ለብዙ ዓመታት በእውነት ውስጥ የቆየ አንድ ሚስዮናዊ ሚስት ማግባት እንደሚፈልግና ለእርሱ መጻፍ እፈልግ እንደሆነ በመግለጽ ደብዳቤ ላከችልኝ። ሆኖም ስለዚህ ወንድም ማንነት አንድም ነገር አልነገረችኝም።

የትዳር ጓደኛ እንደምፈልግ ከይሖዋ በስተቀር ማንም የሚያውቅ አልነበረም። መጀመሪያ ላይ አልጽፍም የሚል አቋም ነበረኝ። ይሁንና በጉዳዩ ላይ ይበልጥ ባሰብኩበት መጠን ይሖዋ በአብዛኛው ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠው እኛ በጠበቅነው መንገድ አይደለም የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። ስለዚህ ለሩት መልስ ጻፍኩላትና ደብዳቤ ብጽፍለትም የግድ አገባዋለሁ ማለት እንዳልሆነ የሚስማማ መሆኑን እንድትጠይቀው ነገርኳት። ሃሮልድ ኪንግ ሁለተኛ ደብዳቤውን የላከው በቀጥታ ለእኔ ነበር።

ሃሮልድ በቻይና ከእስር ከተፈታ በኋላ ፎቶግራፉና የሕይወት ታሪኩ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ ወጥቶ ነበር። በዚህ ወቅት በዓለም ዙሪያ በጣም የታወቀ ሰው ለመሆን የበቃ ቢሆንም እኔን የማረከኝ አምላክን በታማኝነት በማገልገል ያሳለፈው ሕይወት ነው። በመሆኑም ለአምስት ወራት ያህል ደብዳቤ ከተጻጻፍን በኋላ ወደ ሆንግ ኮንግ ሄድኩ። ከዚያም ጥቅምት 5, 1965 ተጋባን።

ሁለታችንም ትዳር የመመሥረትና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የመቀጠል ፍላጎት ነበረን። በዕድሜ እየገፋን ስንሄድ ደግሞ የትዳር ጓደኛ የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት አደረብን። ለሃሮልድ ያለኝ ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሄደ። ከሰዎች ጋር ባለው ግንኙነትም ሆነ ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘ የሚነሱ ችግሮችን በደግነትና በአሳቢነት የሚይዝ ሰው በመሆኑ ለእርሱ ያለኝ አክብሮት ጨመረ። ለ27 ዓመታት ያህል በጣም አስደሳች የትዳር ሕይወት ያሳለፍን ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ እጅ ብዙ በረከት አግኝተናል።

ቻይናውያን ጠንካራ ሠራተኞች በመሆናቸው በጣም እወዳቸዋለሁ። በሆንግ ኮንግ የሚነገረው ቋንቋ ከቻይንኛ የመጣው ካንቶኒዝ ሲሆን ከማንዳሪን የበለጠ ብዙ ቃናዎች ወይም የድምፅ አሰባበር ያሉት በመሆኑ ለመልመድ በጣም አስቸጋሪ ነው። እኔና ሃሮልድ በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ በሚገኘው የሚስዮናውያን ቤት መኖር ጀመርን፤ ከዚያም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተመድበን አገልግለናል። አብረን ያሳለፍነው ጊዜ በጣም አስደሳች ነው፤ ሆኖም በ1976 ከባድ የጤና እክል አጋጠመኝ።

ከጤና እክል ጋር መኖር

ለተወሰኑ ወራት ደም ይፈስሰኝ ስለነበር በሰውነቴ ውስጥ ያለው የደም መጠን በጣም ወረደ። ቀዶ ሕክምና ማድረግ ነበረብኝ፤ ሆኖም በሆስፒታሉ የሚሠሩት ዶክተሮች ያለ ደም ሕክምና ከሰጡኝ ልሞት እንደምችል ስለሰጉ ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ። አንድ ቀን ዶክተሮቹ በእኔ ጉዳይ ላይ እየመከሩ ሳሉ ነርሶቹ ሕይወትሽን በከንቱ ማጣት የለብሽም በማለት አስተሳሰቤን ለማስቀየር ሞከሩ። በዚያን ዕለት 12 ቀዶ ሕክምናዎች ይደረጉ የነበረ ሲሆን አሥሩ ጽንስ ለማስወረድ የሚከናወኑ ናቸው። ሆኖም ውርጃውን የሚፈጽሙት ነፍሰ ጡር ሴቶች የልጆቻቸውን ሕይወት እያጠፉ መሆናቸውን በመግለጽ የተቃወማቸው ሰው አለመኖሩ አስገረመኝ።

በመጨረሻ ሃሮልድ ብሞት ሆስፒታሉ ተጠያቂ እንደማይሆን በደብዳቤ ገለጸ፤ ዶክተሮቹም ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ፈቃደኞች ሆኑ። ወደ ቀዶ ሕክምና ክፍሉ ተወስጄ ማደንዘዣ ሊሰጡኝ በዝግጅት ላይ እያሉ ማደንዘዣ የሚሰጠው ሐኪም በመጨረሻዋ ደቂቃ ላይ ፈቃደኛ ሳይሆን በመቅረቱ ከሆስፒታሉ ለመውጣት ተገደድኩ።

ከዚያም በግሉ የሚሠራ የማህጸን ሐኪም አነጋገርን። በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደምገኝ በመገንዘቡ፣ ምን ያህል እንዳስከፈለን ለማንም የማንናገር እስከሆነ ድረስ በዝቅተኛ ዋጋ ቀዶ ሕክምናውን ለማድረግ ተስማማ። ቀዶ ሕክምናውን ያለ ደም በተሳካ ሁኔታ አደረገልኝ። በዚህ ወቅት እኔና ሃሮልድ የይሖዋን ፍቅራዊ ደግነትና እንክብካቤ በግልጽ አይተናል።

በ1992 ሃሮልድ በጠና በመታመሙ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው እንድንመጣ ተደረግን፤ እዚያም ሁለታችንንም በፍቅር ተንከባከቡን። ውዱ ባለቤቴ በ81 ዓመቱ በ1993 ምድራዊ ሕይወቱን አጠናቀቀ።

ወደ እንግሊዝ ተመለስኩ

የሆንግ ኮንግ ቤቴል ቤተሰብ አባል በመሆኔ ደስተኛ የነበርኩ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሙቀቱንና ወበቁን መቋቋም እያቃተኝ መጣ። ከዚያም ከጤንነቴ አኳያ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ላገኝ ወደምችልበት ቅርንጫፍ ቢሮ መዛወር እፈልግ እንደሆነ የሚገልጽ ያልተጠበቀ ደብዳቤ ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ደረሰኝ። በመሆኑም በ2000 ወደ እንግሊዝ ተመልሼ በለንደን ከሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ ጋር መኖር ጀመርኩ። ይህ ፍቅራዊ ዝግጅት በጣም ጠቅሞኛል! በዚያ ያሉት ቤቴላውያን ደግነት አሳይተውኛል፤ ተመድቤ በምሠራባቸው የተለያዩ ሥራዎችም ከፍተኛ ደስታ አግኝቻለሁ። ከእነዚህም መካከል 2,000 መጻሕፍት ባሉት የቤቴል ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የማከናውነው ሥራ ይገኝበታል።

የምሰበሰበው በለንደን በሚገኘው የቻይንኛ ጉባኤ ሲሆን በጉባኤው አንዳንድ ለውጦች ይታያሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሰዎች በብዛት የሚመጡት ከሆንግ ኮንግ ሳይሆን ከቻይና ሆኗል። ቋንቋቸው ማንዳሪን በመሆኑ የስብከቱ ሥራ አዲስ ፈታኝ ሁኔታ አስከትሏል። ከቻይና ከመጡ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ጋር የሚደረጉ ብዙ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዳሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሪፖርቶች ይላካሉ። እነዚህ ጥናቶች ታታሪና የሚማሩትን እውነት በአድናቆት የሚመለከቱ በመሆናቸው እነርሱን ማስጠናት በጣም ያስደስታል።

ጸጥታ በሰፈነበት አዲሱ መኖሪያዬ ውስጥ ቁጭ ብዬ ሳስብ ያሳለፍኩት አስደሳች ሕይወት ትዝ የሚለኝ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ያሳየኝ ፍቅራዊ ደግነት አሁንም ያስደንቀኛል። ፍቅራዊ ደግነቱ ከዓላማው ጋር በተያያዙ ነገሮች ሁሉ ላይ ይንጸባረቃል። እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ በሚያሳያቸው አሳቢነት በግልጽ ይታያል። ላሳየኝ ፍቅራዊ አሳቢነት አመስጋኝ የምሆንበት በቂ ምክንያት አለኝ።—1 ጴጥሮስ 5:6, 7

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የእነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን የሕይወት ታሪክ በሐምሌ 15, 1963 ገጽ 437-42 እና በታኅሣሥ 15, 1965 ገጽ 756-67 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ ወጥቷል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሕንድ ሳገለግል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃሮልድ ኪንግ በ1963 እና በ1950ዎቹ ቻይና ውስጥ ሲያገለግል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጥቅምት 5, 1965 ሆንግ ኮንግ ውስጥ በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሆንግ ኮንግ ቤቴል አባላት ጋር፤ መሃል ላይ ያሉት ወንድም ሊያንግና ባለቤቱ ሲሆኑ በቀኝ በኩል ያሉት ደግሞ ወንድም ጋናዌይ እና ባለቤቱ ናቸው