በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ዕለታዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል

ይሖዋ ዕለታዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል

ይሖዋ ዕለታዊ ፍላጎታችንን ያሟላልናል

“ልባችሁ አይጨነቅ፤ . . . አባታችሁ እኮ ይህ ሁሉ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃል።”—ሉቃስ 12:29, 30 አ.መ.ት

1. ይሖዋ እንስሳትን የሚመግባቸው እንዴት ነው?

 አንዲት ድንቢጥ ወይም ሌላ ዓይነት ወፍ ምንም ከሌለበት አፈር ላይ ስትለቃቅም አይተህ ታውቃለህ? መሬቱን በመጫር ምን የሚበላ ነገር ልታገኝ ትችላለች ብለህ ሳትገረም አትቀርም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ይሖዋ ወፎችን ከሚመግብበት መንገድ ትምህርት ማግኘት እንደምንችል ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ሰማይ ወፎች ተመልከቱ፤ አይዘሩም አያጭዱምም በጎተራም አይከቱም፣ የሰማዩ አባታችሁም ይመግባቸዋል፤ እናንተ ከእነርሱ እጅግ አትበልጡምን?” (ማቴዎስ 6:26) ይሖዋ ፍጡራኖቹን በሙሉ አስገራሚ በሆነ መንገድ ይመግባቸዋል።—መዝሙር 104:14, 21፤ 147:9

2, 3. ኢየሱስ ስለ ዕለት እንጀራችን እንድንጸልይ ከሰጠን ትምህርት ምን መንፈሳዊ መመሪያ ማግኘት እንችላለን?

2 ታዲያ ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ “የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን” ብለን እንድንጠይቅ ያስተማረን ለምንድን ነው? (ማቴዎስ 6:11) ከዚህ ቀላል አባባል ከፍተኛ ትርጉም ያዘለ መንፈሳዊ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በመጀመሪያ ደረጃ የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ የሚያሟላልን ይሖዋ መሆኑን ያስታውሰናል። (መዝሙር 145:15, 16) የሚተክሉትና የሚኮተኩቱት ሰዎች ቢሆኑም ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚያሳድገው አምላክ ብቻ ነው። (1 ቆሮንቶስ 3:7) የምንበላውንም ሆነ የምንጠጣውን የሚሰጠን አምላክ ነው። (የሐዋርያት ሥራ 14:17) በየዕለቱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንዲሰጠን እርሱን መጠየቃችን ስጦታዎቹን አቅልለን እንደማንመለከት ያሳያል። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ልመና መሥራት የምንችል እስከሆነ ድረስ ይህን ኃላፊነታችንን ከመወጣት ነፃ አያደርገንም።—ኤፌሶን 4:28፤ 2 ተሰሎንቄ 3:10

3 በሁለተኛ ደረጃ፣ “የዕለት እንጀራችንን” እንዲሰጠን መጠየቃችን ስለ ወደፊቱ ጊዜ ከሚገባው በላይ መጨነቅ እንደሌለብን ያሳያል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ተጨማሪ ሐሳብ ተናግሯል፦ “ምን እንበላለን? ምንስ እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ ይህንስ ሁሉ አሕዛብ ይፈልጋሉ፤ ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና። ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል። ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ።” (ማቴዎስ 6:31-34) ስለ ‘ዕለት እንጀራችን’ መጸለያችን ‘ኑሮዬ ይበቃኛል ብለን እግዚአብሔርን በመምሰል’ ቀላል ሕይወት ለመኖር ያስችለናል።—1 ጢሞቴዎስ 6:6-8

በየዕለቱ የምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ

4. የመንፈሳዊ ምግብን አስፈላጊነት የሚያጎሉ በኢየሱስና በእስራኤላውያን ሕይወት ላይ የተከሰቱት የትኞቹ ሁኔታዎች ናቸው?

4 የዕለት እንጀራችንን ለማግኘት የምናቀርበው ጸሎት በየዕለቱ ለሚያስፈልገን መንፈሳዊ ምግብም ትኩረት እንድንሰጥ ሊያደርገን ይገባል። ኢየሱስ ለረጅም ጊዜ ከጾመ በኋላ በጣም ተርቦ የነበረ ቢሆንም ድንጋዩን እንጀራ እንዲያደርግ ሰይጣን ላቀረበለት ፈተና “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም ተብሎ ተጽፎአል” ሲል መልሶለታል። (ማቴዎስ 4:4) ኢየሱስ እዚህ ላይ የጠቀሰው ሙሴ ለእስራኤላውያን የተናገረውን ሐሳብ ነበር፦ “ሰውም ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ነገር ሁሉ በሕይወት እንዲኖር እንጂ ሰው በእንጀራ ብቻ በሕይወት እንዳይኖር ያስታውቅህ ዘንድ አስጨነቀህ፣ አስራበህም፣ አንተም ያላወቅኸውን አባቶችህም ያላወቁትን መና አበላህ።” (ዘዳግም 8:3) ይሖዋ እስራኤላውያን መና እንዲያገኙ ያደረገበት መንገድ ሥጋዊ ምግብ እንዲያገኙ ከማድረጉም በተጨማሪ መንፈሳዊ ትምህርት አስገኝቶላቸዋል። አንደኛ ነገር “ለዕለት ለዕለት የሚበቃቸውን ይልቀሙ” ተብለው ታዝዘው ነበር። ለዕለቱ ከሚበቃቸው በላይ ከሰበሰቡ የተረፈው መና መሽተትና መትላት ይጀምራል። (ዘጸአት 16:4, 20) ለሰንበት የሚያስፈልጋቸውን ጨምሮ እጥፍ አድርገው በሚሰበስቡበት በስድስተኛው ቀን ግን መናው አልተበላሸም። (ዘጸአት 16:5, 23, 24) ስለዚህ መና እንዲመገቡ የተደረገላቸው ዝግጅት ታዛዥ መሆን እንዳለባቸውና ሕይወታቸው በእንጀራ ላይ ብቻ ሳይሆን ‘ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ነገር ሁሉ’ ላይ የተመካ እንደሆነ የማይረሳ ትምህርት ሰጥቷቸዋል።

5. ይሖዋ በየዕለቱ መንፈሳዊ ምግብ የሚሰጠን እንዴት ነው?

5 በተመሳሳይ እኛም ይሖዋ በልጁ አማካኝነት የሚያቀርብልንን መንፈሳዊ ምግብ በየዕለቱ መመገብ ይኖርብናል። ለዚህም ሲባል ለእምነት ቤተሰብ “ምግባቸውን በጊዜው” እንዲሰጥ ኢየሱስ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሾሟል። (ማቴዎስ 24:45) ይህ የታማኝ ባሪያ ክፍል መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በሚረዱ ጽሑፎች አማካኝነት ከሚያቀርበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በተጨማሪ በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብ ያበረታታናል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 1:1-3) እኛም እንደ ኢየሱስ የይሖዋን ፈቃድ ለመማርና ለመፈጸም በየዕለቱ ጥረት በማድረግ በመንፈሳዊ ራሳችንን መመገብ እንችላለን።—ዮሐንስ 4:34

የኃጢአት ይቅርታ

6. ምሕረት የምንጠይቀው ለየትኛው ዕዳ ነው? ይሖዋ ዕዳችንን ለመሰረዝ ፈቃደኛ የሚሆነው ምን ካደረግን ነው?

6 በናሙና ጸሎቱ ላይ ቀጥሎ የቀረበው ልመና “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” ይላል። (ማቴዎስ 6:12) በደል ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “ዕዳ” ማለት ነው። እዚህ ላይ ኢየሱስ ስለ ገንዘብ ዕዳ መናገሩ አልነበረም። ለማስተላለፍ የፈለገው ሐሳብ የኃጢአት ይቅርታ የማግኘታችንን ጉዳይ ነበር። ሉቃስ ባሠፈረው የናሙና ጸሎት ላይ ይህ ልመና እንዲህ ይላል፦ “ኃጢአታችንንም ይቅር በለን፣ እኛ ደግሞ የበደሉንን ሁሉ ይቅር ብለናልና።” (ሉቃስ 11:4) በመሆኑም ኃጢአት ስንሠራ የይሖዋ ባለዕዳ የሆንን ያህል ነው። ሆኖም ከልብ ተጸጽተን ‘ከተመለስን’ እንዲሁም በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ባለን እምነት መሠረት ይቅር እንዲለን ከጠየቅነው አፍቃሪው አምላካችን ዕዳችንን ‘ለመደምሰስ’ ወይም ለመሰረዝ ዝግጁ ነው።—የሐዋርያት ሥራ 3:19፤ 10:43፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6

7. የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት በየዕለቱ መጸለይ ያለብን ለምንድን ነው?

7 በሌላ በኩል ደግሞ የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች አለማሟላታችን ኃጢአት እንደፈጸምን ተደርጎ ይቆጠራል። በወረስነው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም በቃል፣ በድርጊትና በሐሳብ ኃጢአት እንሠራለን ወይም ማድረግ ያለብንን ነገር ሳናደርግ እንቀራለን። (መክብብ 7:20፤ ሮሜ 3:23፤ ያዕቆብ 3:2፤ 4:17) ስለዚህ በቀን ውስጥ ኃጢአት መሥራታችንን አወቅንም አላወቅን በየዕለቱ በምናቀርበው ጸሎት ላይ የኃጢአት ይቅርታ መጠየቅ ይኖርብናል።—መዝሙር 19:12፤ 40:12

8. የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት የምናቀርበው ጸሎት ምን እንድናደርግ ሊያነሳሳን ይገባል? ምን ጠቃሚ ውጤቶችስ እናገኛለን?

8 ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን ከመጸለያችን በፊት ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመር፣ መጸጸትና የፈሰሰው የክርስቶስ ደም ባለው የመቤዠት ኃይል በማመን ንስሐ መግባት አለብን። (1 ዮሐንስ 1:7-9) ጸሎታችን ልባዊ መሆኑን ለማሳየት የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ያቀረብነው ልመና ‘ለንስሐ የሚገባ ነገር በማድረግ’ መደገፍ አለበት። (የሐዋርያት ሥራ 26:20) እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆኑን ማመን እንችላለን። (መዝሙር 86:5፤ 103:8-14) ይህም ወደር የሌለውን “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” የሚያስገኝልን ሲሆን ይህ ደግሞ ‘ልባችንንና አሳባችንን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቅልናል።’ (ፊልጵስዩስ 4:7) ሆኖም የኢየሱስ የናሙና ጸሎት የኃጢአት ይቅርታ ለማግኘት ምን ተጨማሪ ነገር ማድረግ እንዳለብን ያስተምረናል።

ይቅርታ ለማግኘት ይቅር ባዮች መሆን አለብን

9, 10. (ሀ) ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ ያቀረበው ተጨማሪ ሐሳብ ምንድን ነው? ይህስ የትኛውን ነጥብ ያጎላል? (ለ) ኢየሱስ ይቅር ባዮች መሆን እንዳለብን በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ ከናሙና ጸሎቱ ውስጥ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጠው “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” በሚለው ክፍል ላይ ብቻ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። የናሙናውን ጸሎት ተናግሮ ከጨረሰ በኋላ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ለሰዎች ኃጢአታቸውን ይቅር ብትሉ፣ የሰማዩ አባታችሁ እናንተን ደግሞ ይቅር ይላችኋልና፤ ለሰዎች ግን ኃጢአታቸውን ይቅር ባትሉ፣ አባታችሁም ኃጢአታችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴዎስ 6:14, 15) በመሆኑም በይሖዋ ዘንድ የኃጢአት ይቅርታ ማግኘታችን ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ በመሆናችን ላይ የተመካ መሆኑን ኢየሱስ በግልጽ አስረድቷል።—ማርቆስ 11:25

10 በሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ይሖዋ ይቅር እንዲለን ከፈለግን እኛም ይቅር ባዮች መሆን እንዳለብን በምሳሌ ገልጿል። አንድ ባሪያ የነበረበትን ከፍተኛ የገንዘብ ዕዳ በደግነት ስለተወለት ንጉሥ የሚገልጽ ታሪክ ተናገረ። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው ባልንጀራው የሆነ ሌላ ባሪያ የተበደረውን በጣም ትንሽ ገንዘብ ለመተው ፈቃደኛ ባለመሆኑ ንጉሡ ከባድ ቅጣት በየነበት። ኢየሱስ ምሳሌውን እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “ከእናንተ እያንዳንዱ ወንድሙን ከልቡ ይቅር ካላለ፣ እንዲሁ ደግሞ የሰማዩ አባቴ ያደርግባችኋል።” (ማቴዎስ 18:23-35) ነጥቡ ግልጽ ነው፦ ይሖዋ እያንዳንዳችንን ይቅር ያለን የኃጢአት ዕዳ አንድ ሰው በእኛ ላይ ከፈጸመው በደል ጋር ሲነጻጸር እጅግ ከፍተኛ ነው። ከዚህም በላይ ይሖዋ በየዕለቱ ይቅር ይለናል። በመሆኑም ሌሎች አልፎ አልፎ በደል ሲፈጽሙብን ይቅር ልንላቸው ይገባል።

11. ይሖዋ ይቅር እንዲለን ከፈለግን ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠንን የትኛውን ምክር መከተል ይኖርብናል? ይህስ ምን ጥሩ ውጤት ያስገኝልናል?

11 ሐዋርያው ጳውሎስ “እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ” ሲል ጽፏል። (ኤፌሶን 4:32) ክርስቲያኖች እርስ በርስ ይቅር መባባላቸው በመካከላቸው ሰላም እንዲሰፍን ያስችላል። በተጨማሪም ጳውሎስ ይህን ምክር ሰጥቷል፦ “እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ [“ይሖዋ፣” NW] ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።” (ቆላስይስ 3:12-14) ኢየሱስ “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” ብለን እንድንጸልይ ሲያስተምረን ይህን ሁሉ ማለቱ ነበር።

ፈተና ሲያጋጥመን የምናገኘው ጥበቃ

12, 13. (ሀ) በናሙናው ጸሎት ላይ የተጠቀሰውን “ወደ ፈተና አታግባን” የሚለውን አባባል ምን ብለን መረዳት የለብንም? (ለ) ታላቁ ፈታኝ ማን ነው? ወደ ፈተና ላለመግባት የምናቀርበው ጸሎት ትርጉምስ ምንድን ነው?

12 ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ የጠቀሰው ሌላው ልመና “ወደ ፈተና አታግባን” የሚል ነው። (ማቴዎስ 6:13) እንዲህ ሲል ይሖዋ እንዳይፈትነን መጠየቅ አለብን ማለቱ ነው? እንደዚያ ማለት ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በመንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ማንም ሲፈተን፦ በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ከዚህ በተጨማሪ መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል?” ብሏል። (መዝሙር 130:3) ይሖዋ እያንዳንዷን ስህተት አይለቃቅምብንም፤ ስህተት እንድንሠራም ፈጽሞ አይፈትነንም። ታዲያ የዚህ የናሙናው ጸሎት ክፍል ትርጉም ምንድን ነው?

13 እኛን ለመፈተን፣ በተንኰል ለማጥመድ ብሎም ለመዋጥ የሚጥረው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (ኤፌሶን 6:11) ታላቁ ፈታኝ እርሱ ነው። (1 ተሰሎንቄ 3:5) ወደ ፈተና ላለመግባት ስንጸልይ ፈተና በሚደርስብን ጊዜ ይሖዋ በፈተናው ከመውደቅ እንዲጠብቀን መጠየቃችን ነው። “በሰይጣን እንዳንታለል” ማለትም በፈተና እንዳንሸነፍ እንዲረዳን መለመናችን ነው። (2 ቆሮንቶስ 2:11) የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደሚቀበሉ በሚያደርጉት ነገር ሁሉ ለሚያሳዩ ሰዎች ቃል የተገባላቸውን መንፈሳዊ ጥበቃ አግኝተን “በልዑል መጠጊያ” ለመኖር እንጸልያለን።—መዝሙር 91:1-3

14. ፈተና ሲደርስብን ይሖዋን እንዲረዳን የምንጠይቀው ከሆነ እንደማይተወን ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ዋስትና ሰጥቶናል?

14 ይህ ልባዊ ፍላጎታችን መሆኑን በጸሎታችንና በድርጊታችን ካሳየን ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ዋስትና ሰጥቶናል፦ “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13

‘ከክፉውም አድነን’

15. ከክፉው አድነን ብለን መጸለያችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?

15 በብራና የተዘጋጁ አስተማማኝ የሆኑ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ባሠፈሩት መሠረት የኢየሱስ የናሙና ጸሎት የሚደመደመው “ከክፉ[ው]ም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” በሚሉት ቃላት ነው። a (ማቴዎስ 6:13) በዚህ የፍጻሜ ዘመን ዲያብሎስ ከሚያመጣብን ፈተና ጥበቃ ማግኘታችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ አንገብጋቢ ነው። ሰይጣንና አጋንንቱ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን” ቅቡዓን ክርስቲያኖችና አጋሮቻቸው የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” እየተዋጉ ናቸው። (ራእይ 7:9፤ 12:9, 17) ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል መክሯል፦ “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ . . . በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) ሰይጣን የስብከት ሥራችንን ለማስቆም ይፈልጋል። እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ የሃይማኖት፣ የንግድና የፖለቲካ ድርጅቶቹን ተጠቅሞ ለማስፈራራት ይፈልጋል። ይሁን እንጂ ጸንተን ከቆምን ይሖዋ ያድነናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” ሲል ጽፏል።—ያዕቆብ 4:7

16. ይሖዋ ፈተና የሚደርስባቸውን አገልጋዮቹን ለመርዳት በማን ይጠቀማል?

16 ይሖዋ ልጁ ፈተና እንዲደርስበት ፈቅዷል። ሆኖም ኢየሱስ የአምላክን ቃል መከላከያ አድርጎ በመጠቀም ዲያብሎስን ከተቃወመው በኋላ ይሖዋ መላእክቱን ልኮ አበረታቶታል። (ማቴዎስ 4:1-11) በተመሳሳይ በእምነት ከጸለይንና እርሱን መሸሸጊያችን ካደረግነው ይሖዋ እኛን ለመርዳት መላእክቱን ይልካል። (መዝሙር 34:7፤ 91:9-11) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጌታ እግዚአብሔርን የሚያመልኩትን ከፈተና እንዴት እንዲያድን፣ በደለኞችንም . . . ለፍርድ ቀን እንዴት እንዲጠብቅ ያውቃል።”—2 ጴጥሮስ 2:9

መዳናችን ቀርቧል

17. ኢየሱስ የናሙናውን ጸሎት ሲሰጠን ነገሮችን በተገቢው ቅደም ተከተል ያስቀመጠው እንዴት ነው?

17 ኢየሱስ በናሙና ጸሎቱ ላይ ነገሮችን በተገቢው ቅደም ተከተል አስቀምጧቸዋል። በዋነኝነት ሊያሳስበን የሚገባው የይሖዋ ቅዱስና ታላቅ ስም መቀደስ ሊሆን ይገባል። ይህ የሚከናወነው በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ስለሆነ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፍጹም ያልሆኑ ሰብዓዊ መንግሥታትን ወይም መስተዳድሮችን በሙሉ አጥፍቶ በሰማይ ላይ የተፈጸመው የአምላክ ፈቃድ በምድርም ላይ እንዲሆን እንጸልያለን። ገነት በሆነች ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው የይሖዋ ስም በመቀደሱና በመላው አጽናፈ ዓለም የጽድቅ ሉዓላዊነቱ በመረጋገጡ ላይ ነው። በጣም አንገብጋቢ የሆኑትን እነዚህን ጉዳዮች ከጠቀስን በኋላ በየዕለቱ የሚያስፈልጉን ነገሮች እንዲሟሉልን፣ ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን እንዲሁም ከፈተናዎችና ክፉው ሰይጣን ዲያብሎስ ከሚሸርብብን ወጥመድ እንዲያድነን መጸለይ እንችላለን።

18, 19. ኢየሱስ ያስተማረን የናሙና ጸሎት ነቅተን እንድንኖርና ተስፋችንን “እስከ መጨረሻው አጽንተን” እንድንጠብቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

18 ከክፉውና እርሱ ከሚያስተዳድረው ብልሹ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የምንገላገልበት ጊዜ እየቀረበ ነው። ሰይጣን በምድር ላይ በተለይ ደግሞ ታማኝ በሆኑት የይሖዋ አገልጋዮች ላይ ‘ታላቅ ቁጣውን’ የሚገልጽበት “ጥቂት ዘመን” ብቻ እንደቀረው በሚገባ ያውቃል። (ራእይ 12:12, 17) ኢየሱስ የሥርዓቱን ወይም ‘የዓለምን መጨረሻ’ በተመለከተ ምልክቶች ሲሰጥ አስደናቂ የሆኑ ክስተቶች እንደሚፈጸሙ የተናገረ ሲሆን አንዳንዶቹም ገና ወደፊት የሚፈጸሙ ናቸው። (ማቴዎስ 24:3, 29-31) እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ ስናይ የመዳን ተስፋችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ብሩህ ይሆናል። ኢየሱስ “ይህም ሊሆን ሲጀምር ቤዛችሁ ቀርቦአልና አሻቅባችሁ ራሳችሁን አንሡ” ብሏል።—ሉቃስ 21:25-28

19 ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተማረው እጥር ምጥን ያለ የናሙና ጸሎት የፍጻሜው ዘመን እየቀረበ ሲመጣ በጸሎታችን ውስጥ ምን ነገሮችን ማካተት እንደምንችል ጥሩ መመሪያ ይሆነናል። ይሖዋ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ በየዕለቱ የሚያስፈልጉንን ነገሮች መስጠቱን እንደሚቀጥል እስከ መጨረሻው ድረስ ትምክህት ይኑረን። በጸሎት መትጋታችንና ንቁ መሆናችን “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን [እንድንጠብቅ]” ያስችለናል።—ዕብራውያን 3:14፤ 1 ጴጥሮስ 4:7

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የ1954ን እትም የመሳሰሉ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች የጌታን ጸሎት የሚደመድሙት “መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን” በሚሉት የውዳሴ ቃላት ነው። ዘ ጀሮም ቢብሊካል ኮሜንታሪ እንዲህ ይላል፦ “መደምደሚያው ላይ የሚገኙት የውዳሴ ቃላት . . . አስተማማኝ በሆኑት [ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች] ውስጥ አይገኙም።”

ለክለሣ ያህል

• “የዕለት እንጀራችንን” ስጠን ብለን ስንጸልይ ምን ማለታችን ነው?

• “እኛም ደግሞ የበደሉንን ይቅር እንደምንል በደላችንን ይቅር በለን” የሚለው የጸሎቱ ክፍል ምን ትርጉም እንዳለው አብራራ።

• ወደ ፈተና አታግባን ብለን ይሖዋን ስንለምን ምን መጠየቃችን ነው?

• ‘ከክፉው አድነን’ ብለን መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኃጢአታችን ይቅር እንዲባልልን ከፈለግን ሌሎችን ይቅር ማለት አለብን

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Lydekker