በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ጌታ ሆይ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን’

‘ጌታ ሆይ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን’

‘ጌታ ሆይ እንጸልይ ዘንድ አስተምረን’

“ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ፦ ጌታ ሆይ፣ . . . እንጸልይ ዘንድ አስተምረን አለው።”—ሉቃስ 11:1

1. ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አንዱ መጸለይ እንዲያስተምራቸው የጠየቀው ለምን ነበር?

 በ32 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአንድ አጋጣሚ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ ኢየሱስ ሲጸልይ ተመለከተው። ምናልባትም ኢየሱስ ጸሎቱን ያቀረበው በልቡ በመሆኑ ወደ አባቱ ምን ብሎ እንደጸለየ ደቀ መዝሙሩ መስማት አልቻለም። ያም ሆኖ ኢየሱስ ጸሎቱን ሲያበቃ ደቀ መዝሙሩ “ጌታ ሆይ፣ . . . እንጸልይ ዘንድ አስተምረን” አለው። (ሉቃስ 11:1) እንዲህ ብሎ ለመጠየቅ ያነሳሳው ምንድን ነው? ጸሎት በአይሁዳውያን ሕይወትና አምልኮ ውስጥ የሚዘወተር ነገር ነበር። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች በመዝሙር መጽሐፍና በሌሎች መጻሕፍት ውስጥ በርካታ ጸሎቶችን አካትተዋል። ስለዚህ ይህ ደቀ መዝሙር ጨርሶ የማያውቀውን ወይም ከዚያ ቀደም ያላደረገውን ነገር እንዲያስተምረው መጠየቁ አልነበረም። የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች ለይስሙላ የሚያቀርቧቸውን ጸሎቶች እንደሚያውቅ ጥርጥር የለውም። ሆኖም ኢየሱስ ሲጸልይ ሲመለከት የሃይማኖት አስተማሪዎቹ በሚያቀርቡት ግብዝነት የሚንጸባረቅበት ጸሎትና ኢየሱስ በጸለየበት መንገድ መካከል ትልቅ ልዩነት መኖሩን ልብ ሳይል አልቀረም።—ማቴዎስ 6:5-8

2. (ሀ) ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ቃል በቃል እንድንደግመው አስቦ እንዳልነበር እንዴት ማወቅ እንችላለን? (ለ) እንዴት መጸለይ እንዳለብን ማወቅ የምንፈልገው ለምንድን ነው?

2 ይህ ከመሆኑ ከ18 ወራት ገደማ በፊት ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ናሙና የሚሆን ጸሎት አስተምሯቸው ነበር። (ማቴዎስ 6:9-13) ይህ ደቀ መዝሙር በዚያ ወቅት በቦታው የነበረ አይመስልም፤ በመሆኑም ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ዋና ዋና ነጥቦች ደግነት በተሞላበት መልኩ በድጋሚ ነገረው። ኢየሱስ ቃል በቃል ጸሎቱን እንዳልደገመለት ግልጽ ነው፤ ይህም የናሙናውን ጸሎት በቃል እንዲያጠኑት አስቦ እንዳልነበር ያሳያል። (ሉቃስ 11:1-4) ስሙ እንዳልተገለጸው እንደዚያ ደቀ መዝሙር ሁሉ እኛም በጸሎት አማካኝነት ይበልጥ ወደ ይሖዋ መቅረብ እንድንችል እንዴት መጸለይ እንዳለብን መማር እንፈልጋለን። እንግዲያው ሐዋርያው ማቴዎስ ያሰፈረውን የናሙና ጸሎቱን የተሟላ ዘገባ እንመርምር። ጸሎቱ ሰባት ልመናዎችን ያካተተ ነው፤ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ከአምላክ ዓላማ ጋር የተያያዙ ሲሆኑ አራቱ በቁሳዊና በመንፈሳዊ ፍላጎቶቻችን ላይ ያተኮሩ ናቸው። በዚህ ርዕስ ላይ የመጀመሪያዎቹን ሦስት ልመናዎች እንመረምራለን።

አፍቃሪ አባት

3, 4. ይሖዋን “አባታችን” ብለን መጥራታችን ምን ትርጉም አለው?

3 ኢየሱስ ገና ከመግቢያው ጀምሮ ጸሎታችን ከይሖዋ ጋር ያለንን በአክብሮት ላይ የተመሰረተ ጥብቅ ዝምድና የሚያሳይ መሆን እንዳለበት ገልጿል። በተራራው ላይ በተለይ በዙሪያው ተቀምጠው ለነበሩት ደቀ መዛሙርቱ በሰጠው ትምህርት ላይ ይሖዋን “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ” ብለው እንዲጠሩት ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር እንደገለጹት ኢየሱስ የተናገረው በብዙዎች ዘንድ በሚታወቅ የዕብራይስጥ አጠራርም ይሁን በአረማይክ፣ ‘አባት’ ለማለት የተጠቀመበት ቃል አንድ ሕፃን ‘በልጅ አንደበቱ’ አባቱን ከሚጠራበት መንገድ ጋር የሚመሳሰል ነው። ይሖዋን “አባታችን” ብለን መጥራታችን ከእርሱ ጋር በፍቅርና በመተማመን ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት እንዳለን ያሳያል።

4 “አባታችን” ስንል ይሖዋ ፈጣሪያቸው መሆኑን የሚቀበሉ ወንዶችና ሴቶችን ያቀፈ ትልቅ ቤተሰብ አባላት መሆናችንን እንደምንገነዘብም እናሳያለን። (ኢሳይያስ 64:8፤ የሐዋርያት ሥራ 17:24, 28) በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች “የእግዚአብሔር ልጆች” ሆነው የተቆጠሩ ሲሆን “አባ አባት” ብለው ይሖዋን መጥራት ይችላሉ። (ሮሜ 8:14, 15) በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችም በታማኝነት እየደገፏቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ የወሰኑ ሲሆን ይህንንም በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል። እነዚህ “ሌሎች በጎች” በሙሉ በኢየሱስ ስም ወደ ይሖዋ መቅረብ ከመቻላቸውም በላይ “አባታችን” ብለው ሊጠሩት ይችላሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ 14:6) በሰማይ የሚኖረው አባታችን እንደሚያስብልን በመተማመን እርሱን ለማወደስ፣ ላሳየን ደግነት ለማመስገን እንዲሁም የሚያስጨንቁንን ነገሮች ለእርሱ ለመንገር አዘውትረን ወደ እርሱ መጸለይ እንችላለን።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7

ለይሖዋ ስም ያለን ፍቅር

5. በናሙና ጸሎቱ መግቢያ ላይ ምን ልመና ቀርቧል? ይህስ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

5 የናሙና ጸሎቱ የሚጀምረው መቅደም ያለበትን ነገር በማስቀደም ነው። “ስምህ ይቀደስ” ይላል። (ማቴዎስ 6:9) በእርግጥም ይሖዋን ስለምንወደውና በስሙ ላይ የተሰነዘረው ነቀፋ ስለሚያሳዝነን የስሙ መቀደስ በዋነኝነት ሊያሳስበን ይገባል። ሰይጣን ማመፁና የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት የይሖዋ አምላክን ትእዛዝ እንዲጥሱ ማነሳሳቱ አምላክ አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን የሚጠቀምበትን መንገድ አጠያያቂ ያደረገ ሲሆን ይህም በስሙ ላይ ነቀፋ አምጥቷል። (ዘፍጥረት 3:1-6) ከዚህም በላይ ባለፉት ዘመናት ሁሉ የእርሱ አገልጋዮች ነን የሚሉ ሰዎች በፈጸሙት አሳፋሪ ድርጊትና በትምህርታቸው የይሖዋ ስም ሲነቀፍ ቆይቷል።

6. የይሖዋ ስም እንዲቀደስ የምንጸልይ ከሆነ ምን ከማድረግ እንቆጠባለን?

6 የይሖዋ ስም እንዲቀደስ የምናቀርበው ጸሎት የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ገዥነት በተመለከተ ያለንን አቋም ይኸውም የይሖዋን የመግዛት መብት ሙሉ በሙሉ እንደምንደግፍ ያሳያል። የይሖዋ ዓላማ ለእርሱና ስሙ ለሚወክለው ነገር ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው በጽድቅ ላይ ለተመሠረተው ሉዓላዊነቱ በፈቃደኝነት የሚገዙ ማስተዋል ያላቸው ፍጥረታት አጽናፈ ዓለሙን እንዲሞሉ ነው። (1 ዜና መዋዕል 29:10-13፤ መዝሙር 8:1፤ 148:13) ለይሖዋ ስም ያለን ፍቅር በዚህ ቅዱስ ስም ላይ ነቀፋ ሊያመጣ የሚችል ማንኛውንም ነገር ከማድረግ እንድንቆጠብ ያስችለናል። (ሕዝቅኤል 36:20, 21፤ ሮሜ 2:21-24) አጽናፈ ዓለምና በውስጡ ያሉት ነዋሪዎች ሰላም ማግኘታቸው የተመካው በይሖዋ ስም መቀደስና ለሉዓላዊነቱ በፍቅር በመገዛት ላይ ስለሆነ “ስምህ ይቀደስ” ብለን መጸለያችን የይሖዋ ዓላማ ለእርሱ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ እንደሚፈጸም ያለንን ትምክህት ያሳያል።—ሕዝቅኤል 38:23

እንዲመጣ የምንጸልይለት መንግሥት

7, 8. (ሀ) ኢየሱስ ይምጣ ብለን እንድንጸልይለት ያስተማረን መንግሥት ምንድን ነው? (ለ) በዳንኤልና በራእይ መጽሐፎች ውስጥ ስለዚህ መንግሥት ምን እንማራለን?

7 በናሙና ጸሎቱ ላይ የቀረበው ሁለተኛው ልመና “መንግሥትህ ትምጣ” የሚል ነው። (ማቴዎስ 6:10) ይህ ልመና ከመጀመሪያው ጋር የተያያዘ ነው። ይሖዋ ቅዱስ ስሙን ለማስቀደስ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ በሾመበት መሲሐዊ መንግሥት ማለትም በሰማይ በሚገኘው መስተዳድር አማካኝነት ነው። (መዝሙር 2:1-9) በዳንኤል ትንቢት ላይ መሲሐዊው መንግሥት ‘ከተራራ’ ተፈንቅሎ በወጣ “ድንጋይ” ተመስሏል። (ዳንኤል 2:34, 35, 44, 45) ተራራው የይሖዋን አጽናፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነት የሚወክል በመሆኑ በድንጋይ የተመሰለው መንግሥት የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ገዥነት አዲስ መግለጫ ነው። በትንቢቱ ላይ ድንጋዩ “ታላቅ ተራራ ሆነ ምድርንም ፈጽሞ ሞላ” ተብሏል፤ ይህም መሲሐዊው መንግሥት አምላክ ምድርን ለመግዛት ያለውን ሙሉ ሥልጣን እንደሚወክል ያሳያል።

8 በዚህ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሆነው እንዲገዙ “ከሰዎች የተዋጁ” 144,000 ተባባሪዎች አሉ። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-4፤ 20:6) ዳንኤል እነዚህን ሰዎች “የልዑሉ ቅዱሳን” ብሎ ጠርቷቸዋል። መሪያቸው ከሆነው ከክርስቶስ ጋር የሚያገኙትን ቦታ እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “መንግሥትም ግዛትም ከሰማይም ሁሉ በታች ያሉ የመንግሥታት ታላቅነት ለልዑሉ ቅዱሳን ሕዝብ ይሰጣል፤ መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት ነው፣ ግዛቶችም ሁሉ ይገዙለታል ይታዘዙለትማል።” (ዳንኤል 7:13, 14, 18, 27) ክርስቶስ ተከታዮቹን እንዲጸልዩለት ያስተማራቸው እንዲህ ስላለው በሰማይ የሚገኝ መንግሥት ነው።

መንግሥቱ እንዲመጣ

አሁንም የምንጸልየው ለምንድን ነው?

9. የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ መጸለያችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

9 ክርስቶስ ለናሙና በሰጠው ጸሎት ላይ የአምላክ መንግሥት ይምጣ ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚያሳዩት መሲሐዊው መንግሥት በ1914 በሰማይ ተቋቁሟል። a እንዲህ ከሆነ ይህ መንግሥት ‘ይምጣ’ ብለን መጸለያችን አሁንም አስፈላጊ ነው? አዎን! ምክንያቱም በዳንኤል ትንቢት ላይ በድንጋይ የተመሰለው መሲሐዊው መንግሥት በግዙፍ ምስል ከተመሰሉት ሰብዓዊ የፖለቲካ መንግሥታት ጋር ይጋጠማል። ድንጋዩ ምስሉን መትቶ የሚፈጨው ገና ወደፊት ነው። የዳንኤል ትንቢት ይህንን መንግሥት በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”—ዳንኤል 2:44

10. የአምላክን መንግሥት መምጣት በጉጉት የምንጠባበቀው ለምንድን ነው?

10 የአምላክ መንግሥት በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ላይ እርምጃ መውሰዱ የይሖዋ ስም እንዲቀደስና የአምላክን ሉዓላዊነት የሚቃወሙ በሙሉ እንዲወገዱ ስለሚያስችል መንግሥቱ የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። “መንግሥትህ ትምጣ” በማለት አጥብቀን እንጸልያለን እንዲሁም ከሐዋርያው ዮሐንስ ጋር በመተባበር “አሜን፣ ጌታ ኢየሱስ ሆይ፣ ና” እንላለን። (ራእይ 22:20) በእርግጥም “ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ ኢየሱስ የይሖዋን ስም ለማስቀደስና ሉዓላዊነቱን ለማረጋገጥ እንዲመጣ እንመኛለን።—መዝሙር 83:18

‘ፈቃድህ ይሁን’

11, 12. (ሀ) የአምላክ ፈቃድ “በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን ስንጸልይ ምን እንዲፈጸም እየጠየቅን ነው? (ለ) የይሖዋ ፈቃድ እንዲፈጸም የምናቀርበው ጸሎት ምን ተጨማሪ ትርጉም አለው?

11 ኢየሱስ ቀጥሎ “ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩ ደቀ መዛሙርቱን አስተማራቸው። (ማቴዎስ 6:10) አጽናፈ ዓለም የተፈጠረው የይሖዋ ፈቃድ ስለሆነ ነው። በሰማይ የሚኖሩ ኃያላን ፍጥረታት “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” በማለት ዘምረዋል። (ራእይ 4:10, 11) ይሖዋ ‘በሰማይና በምድር ላሉት ነገሮች’ ዓላማ አለው። (ኤፌሶን 1:8-10) የአምላክ ፈቃድ እንዲሆን ስንጸልይ ይሖዋ ዓላማውን እንዲፈጽም መጠየቃችን ነው። ከዚህም በላይ የአምላክ ፈቃድ በአጽናፈ ዓለም በሙሉ ሲፈጸም ለማየት እንደምንጓጓ እናሳያለን።

12 ይህንን ጸሎት ስናቀርብ ሕይወታችንን ከይሖዋ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ፈቃደኞች መሆናችንንም እያሳየን ነው። ኢየሱስ “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 4:34) ራሳችንን የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እኛም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ያስደስተናል። ለይሖዋና ለልጁ ያለን ፍቅር “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት” እንዳንኖር ይገፋፋናል። (1 ጴጥሮስ 4:1, 2፤ 2 ቆሮንቶስ 5:14, 15) ከይሖዋ ፈቃድ ጋር እንደሚጋጩ የምናውቃቸውን ነገሮች ላለማድረግ እንጠነቀቃለን። (1 ተሰሎንቄ 4:3-5) መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብና ለማጥናት ጊዜ በመዋጀት “የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ” እናስተውላለን፤ ይህም ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በትጋት መስበክን ይጨምራል።—ኤፌሶን 5:15-17፤ ማቴዎስ 24:14

በሰማይ የተፈጸመው የይሖዋ ፈቃድ

13. ሰይጣን ከማመፁ ከረጅም ጊዜ በፊት የአምላክ ፈቃድ ይፈጸም የነበረው እንዴት ነው?

13 ከይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች አንዱ ዓምፆ ሰይጣን ከመሆኑ በፊት የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ ይፈጸም ነበር። የምሳሌ መጽሐፍ የአምላክን የበኩር ልጅ ስብዕና የተላበሰ ጥበብ አድርጎ ይገልጸዋል። ይኸው መጽሐፍ ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ዓመታት የአምላክ አንድያ ልጅ የአባቱን ፈቃድ በደስታ በመፈጸም ‘በፊቱ ሁልጊዜ ደስ ይለው እንደነበር’ ይገልጻል። ከጊዜ በኋላ “የሚታዩትና የማይታዩትም . . . በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ” ሲፈጠሩ የይሖዋ “ዋና ሠራተኛ” ሆኖ አገልግሏል። (ምሳሌ 8:22-31፤ ቆላስይስ 1:15-17) ይሖዋ ኢየሱስን እንደ ቃል አቀባዩ አድርጎ ይጠቀምበት ስለነበር ቃል ተብሎ ተጠርቷል።—ዮሐንስ 1:1-3

14. መላእክት በሰማይ የይሖዋን ፈቃድ ስለሚፈጽሙበት መንገድ መዝሙር 103 ምን ያስተምረናል?

14 መዝሙራዊው፣ ይሖዋ የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ እንደሆነና ሥፍር ቁጥር የሌላቸው መላእክቱ የእርሱን ቃልና መመሪያዎች እንደሚያዳምጡ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፣ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃያላን፣ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፣ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ [ወይም በሉዓላዊ ግዛቱ] ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ።”—መዝሙር 103:19-22

15. ኢየሱስ መንግሥታዊ ሥልጣኑን መቀበሉ የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ እንዲፈጸም ያደረገው እንዴት ነው?

15 የኢዮብ መጽሐፍ እንደሚያሳየው ሰይጣን ካመፀም በኋላ እንኳ ወደ ሰማይ መግባት ይችል ነበር። (ኢዮብ 1:6-12፤ 2:1-7) ይሁን እንጂ የራእይ መጽሐፍ ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ የሚባረሩበት ጊዜ እንደሚመጣ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱን ሥልጣን በ1914 ከተቀበለ ብዙም ሳይቆይ ይህ ጊዜ እንደደረሰ ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እነዚያ ዓመፀኞች በሰማይ ሥፍራ አልተገኘላቸውም። በምድር አካባቢ ተወስነው እንዲኖሩ ተደርገዋል። (ራእይ 12:7-12) ከዚህ በኋላ በሰማይ በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ ተቃውሞ የሚያሰማ አይኖርም። ከዚህ ይልቅ የሚሰማው ለበጉ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሚቀርብ ምስጋናና ለይሖዋ በመገዛት የሚቀርብ ውዳሴ ብቻ ይሆናል። (ራእይ 4:9-11) በእርግጥም የይሖዋ ፈቃድ በሰማይ እየተፈጸመ ነው።

ይሖዋ ለምድር ያለው ፈቃድ

16. የሰውን ዘር ተስፋ በተመለከተ ሕዝበ ክርስትና የምትሰጠው ትምህርት የተሳሳተ መሆኑን የናሙና ጸሎቱ የሚያሳየው እንዴት ነው?

16 የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ በማስተማር ምድር በአምላክ ዓላማ ውስጥ እንዳልታቀፈች አድርገው ይናገራሉ። ሆኖም ኢየሱስ “መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:10) ዓመፅ፣ የፍትሕ መጓደል፣ በሽታና ሞት ተስፋፍተው በሚገኙባት ምድራችን ላይ ዛሬ የይሖዋ ፈቃድ እየተፈጸመ ነው ማለት ይቻላል? በፍጹም! እንግዲያው ሐዋርያው ጴጥሮስ ከጻፈው ተስፋ ጋር በሚስማማ መልኩ የአምላክ ፈቃድ በምድር እንዲሆን አጥብቀን ልንጸልይ ይገባል። ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና [በክርስቶስ የሚመራውን መሲሐዊ መንግሥት] አዲስ ምድር [ጻድቅ የሆነ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ] እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።”—2 ጴጥሮስ 3:13

17. ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ ምንድን ነው?

17 ይሖዋ ምድርን የፈጠረው በዓላማ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ በይሖዋ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ብሎ ጽፏል፦ “ሰማያትን የፈጠረ እግዚአብሔር፣ እርሱም ምድርን የሠራና ያደረገ ያጸናትም፣ መኖሪያም ልትሆን እንጂ ለከንቱ እንድትሆን ያልፈጠራት አምላክ፣ እንዲህ ይላል፦ እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከእኔም በቀር ሌላ የለም።” (ኢሳይያስ 45:18) አምላክ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት ገነት በሆነች የአትክልት ቦታ ውስጥ ካስቀመጣቸው በኋላ “ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሉአት፣ ግዙአትም” የሚል መመሪያ ሰጣቸው። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:15) በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው የፈጣሪ ዓላማ ምድር ለይሖዋ ሉዓላዊነት በደስታ በሚገዙ ፍጹም የሆኑ ጻድቅ ሰዎች እንድትሞላና ክርስቶስ ቃል በገባው ገነት ውስጥ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው።—መዝሙር 37:11, 29፤ ሉቃስ 23:43

18, 19. (ሀ) የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ ሙሉ በሙሉ ከመፈጸሙ በፊት ምን መከናወን አለበት? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኞቹን የኢየሱስ የናሙና ጸሎት ሌሎች ገጽታዎች እንመረምራለን?

18 በይሖዋ ሉዓላዊነት ላይ የሚያምፁ ሰዎች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ይሖዋ ለምድር ያለው ዓላማ ሙሉ በሙሉ ሊፈጸም አይችልም። አምላክ በክርስቶስ የሚመሩ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡራንን በመጠቀም ‘ምድርን የሚያጠፉትን ያጠፋል።’ ሐሰት ሃይማኖትን፣ የነቀዘ የፖለቲካ ሥርዓትን፣ ስስትና ማጭበርበር የተሞላበትን የንግድ ተቋም እንዲሁም አውዳሚ ወታደራዊ ኃይልን አቅፎ የያዘው ክፉው የሰይጣን ሥርዓት ለዝንተ ዓለም ተጠራርጎ ይጠፋል። (ራእይ 11:18፤ 18:21፤ 19:1, 2, 11-18) በዚህ ጊዜ የይሖዋ ሉዓላዊነት ከነቀፋ ነጻ ይሆናል፣ ስሙም ይቀደሳል። “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን ስንጸልይ ይህ ሁሉ እንዲፈጸም መለመናችን ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10

19 ይሁን እንጂ ኢየሱስ ባስተማረን የናሙና ጸሎት ላይ ስለ ግል ጉዳዮቻችንም መጸለይ እንደምንችል ገልጾልናል። በሚቀጥለው ርዕስ ስለ እነዚህ ጉዳዮች በናሙና ጸሎቱ ላይ የሰጠውን ትምህርት እንመረምራለን።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

ለክለሳ ያህል

• ይሖዋን “አባታችን” ብለን መጥራታችን ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

• የይሖዋ ስም እንዲቀደስ መጸለያችን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር የሆነው ለምንድን ነው?

• የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ የምንጸልየው ለምንድን ነው?

• የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እንደሆነ በምድርም እንዲሆን የምናቀርበው ጸሎት ምን ትርጉም አለው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ያቀረበው ጸሎት ግብዝነት ከሚንጸባረቅበት የፈሪሳውያን ጸሎት የተለየ ነበር

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ፣ ስሙ እንዲቀደስና ፈቃዱ እንዲፈጸም ይጸልያሉ