ሃይማኖት የሚያሳድረው ተጽዕኖ በጎ ነው ወይስ ጎጂ?
ሃይማኖት የሚያሳድረው ተጽዕኖ በጎ ነው ወይስ ጎጂ?
“ክርስትና ትልቅ ውለታ እንደዋለልኝ ይሰማኛል፤ ላለፉት 2000 ዓመታት የኖርንበት ዓለምም ክርስትና ላበረከተው አስተዋጽኦ አመስጋኝ እንደሚሆን አምናለሁ።”—መቅድም፣ ቱ ታውዘንድ ይርስ—ዘ ፈርስት ሚሌኒየም:- ዘ በርዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ ቱ ዘ ክሩሴድስ
‘ክርስትናን’ አስመልክተው ይህን የተናገሩት እንግሊዛዊው ደራሲና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ሜልቪን ብራግ ናቸው። የእኚህ ሰው አነጋገር ሃይማኖታቸው ከፍተኛ ውለታ እንደዋለላቸው የሚሰማቸውን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምድር ነዋሪዎች አመለካከት የሚያስተጋባ ነው። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖት በሕይወታቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይሰማቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንድ ደራሲ እስልምና “ለመላው ዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ . . . ከፍተኛ ሥልጣኔ አስተዋውቋል” ሲሉ ጽፈዋል።
ሃይማኖት የተጫወተው ሚና በጎ ነው ወይስ ጎጂ?
ይሁን እንጂ ብራግ ቀጥሎ የተናገሩት ቃል ሃይማኖት በጥቅሉ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል ወይስ አያሳድርም የሚል አንገብጋቢ ጥያቄ ያስነሳል። “ይሁንና ክርስትና በአንድ ጉዳይ ላይ መልስ እንዲሰጠኝ እሻለሁ” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። እኚህ ሰው መልስ የሚሹለት ጉዳይ ምንድን ነው? “የክርስትና ‘ታሪክ’ በጽንፈኝነት፣ በክፋት፣ በጭካኔና በቸልተኝነት የተሞላው” ለምንድን ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል።
ብዙ ሰዎች በታሪክ ዘመናት የታዩት አብዛኞቹ የዓለም ሃይማኖቶች ጽንፈኝነት፣ ክፋት፣ ጭካኔና ቸልተኝነት የሚንጸባረቅባቸው ናቸው የሚል አመለካከት አላቸው። እነዚህ ሰዎች ሃይማኖት ከላይ ሲታይ ለሰው ልጅ የሚጠቅም ቅዱስ ነገር ቢመስልም ውስጡ ግን በግብዝነትና በውሸት የተሞላ ነው የሚል አስተሳሰብ አላቸው። (ማቴዎስ 23:27, 28) ኤ ራሽናሊስት ኢንሳይክሎፒዲያ “ሃይማኖት ለሥልጣኔ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የሚገልጹ ጽሑፎችን ማንበብ የተለመደ ነው” ሲል ገልጿል። አክሎም “የታሪክ ሐቅ ግን ይህ አባባል ከእውነታው የራቀ መሆኑን ያሳያል” በማለት ዘግቧል።
በዛሬው ጊዜ የትኛውንም ጋዜጣ ብታነብ በአንድ በኩል ፍቅርን፣ ሰላምንና ርኅራኄን እያስተማሩ በሌላ በኩል ግን ጥላቻን ስለሚያስፋፉና በአምላክ ስም ጭካኔ የተሞላባቸውን ድርጊቶች ስለሚፈጽሙ የሃይማኖት መሪዎች የሚገልጹ ዘገባዎችን በብዛት እንደምታገኝ የታወቀ ነው። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ሃይማኖት ወደ መጥፎ ድርጊት የሚገፋፋ ኃይል እንደሆነ አድርገው ቢያስቡ አያስደንቅም።
ሃይማኖት ባይኖር የተሻለ ይሆናል?
አንዳንዶች “ሁሉም ሃይማኖት” ቀስ በቀስ ቢጠፋ መልካም ነበር ሲል እንደተናገረው እንግሊዛዊ ፈላስፋ እንደ
በርትራንድ ራስል ዓይነት አመለካከት አላቸው። ሃይማኖት ከምድር ገጽ መጥፋቱ ለሰው ልጅ ችግሮች ብቸኛ ዘላቂ መፍትሔ እንደሚሆን ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች አንድ የዘነጉት ነገር አለ፤ ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎችም የዚያኑ ያህል ጥላቻን ሊያስፋፉና ጽንፈኛ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለ ሃይማኖታዊ ርዕሰ ጉዳዮች የሚጽፉት ካረን አርምስትሮንግ “በናዚ ጀርመን የተፈጸመው ጭፍጨፋ ሃይማኖት የለሽ ርዕዮተ ዓለምም እንኳ በሃይማኖት ስም የሚካሄዱ ግጭቶችን ያህል አደገኛ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።—ዘ ባትል ፎር ጎድ—ፈንደሜንታሊዝም ኢን ጁዳይዝም፣ ክርስቲያኒቲ ኤንድ ኢስላምእንግዲያው ሃይማኖት በሰው ልጆች ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው ወይስ ለሰው ልጅ ችግሮች ዋነኛው መንስኤ? ሃይማኖቶችን በሙሉ ማስወገድ ለችግሮቹ መፍትሔ ይሆናል? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ የሚሰጠውን ሐሳብ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ተመልከት። ምናልባት ያልጠበቅኸው መልስ ልታገኝ ትችላለህ።