በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል”

“መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል”

“መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል”

በጦር ግንባር ያለ አንድ ወታደር “ወደ ቤትህ ተመልሰህ ከሚስትህና ከቤተሰብህ ጋር የተወሰነ ጊዜ እንድታሳልፍ ተፈቅዶልሃል” ቢባል ቅር የሚለው ይመስልሃል?

በንጉሥ ዳዊት ዘመን የነበረ አንድ ወታደር እንዲህ ያለ መመሪያ ተሰጥቶት ነበር። ንጉሡ ኬጤያዊውን ኦርዮን ከጦር ግንባር አስጠርቶ ወደ ቤቱ እንዲመለስ አዝዞት ነበር። ኦርዮ ግን ወደ ቤቱ መሄድ እምቢ አለ። ንጉሡ በዚህ የኦርዮ አቋም ተገርሞ ሲጠይቀው አምላክ በሕዝቡ መካከል መገኘቱን የሚያመለክተው የቃል ኪዳኑ ታቦትና የእስራኤል ሠራዊት በውጊያ ላይ እያለ እሱ ወደ ቤቱ ሊመለስ እንደማይችል ገለጸለት። “እኔ ልበላና ልጠጣ ወይስ ከሚስቴ ጋር ልተኛ ወደ ቤቴ እሄዳለሁን?” አለው። ኦርዮ እንዲህ ባለ ወሳኝ ወቅት ይህን ማድረግ ፈጽሞ ሊያስበው የማይችለው ነገር እንደሆነ መግለጹ ነበር።—2 ሳሙኤል 11:8-11

እኛም በውጊያ ላይ ያለን እንደመሆናችን መጠን ኦርዮ ከወሰደው እርምጃ የምንማረው ትልቅ ቁም ነገር አለ። በአሁኑ ጊዜ የዓለም ብሔራት ከሚያካሂዱት ጦርነት ፈጽሞ የተለየ ውጊያ በመካሄድ ላይ ነው። ሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ከዚህ ውጊያ ጋር ሲነጻጸሩ እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደሉም። በዚህ ውጊያ አንተም የምትካፈል ሲሆን በቀላሉ የማይበገር ጠላት ከፊትህ የተጋረጠ በመሆኑ ሕይወትህን ልታጣ የምትችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። በዚህ ውጊያ የሚተኮስ ጥይትም ሆነ የሚጣል ቦምብ ባይኖርም ውጊያው የረቀቀ የጦር ስልት ይጠይቃል።

በዚህ ውጊያ ከመካፈልህ በፊት የውጊያው ዓላማ ምን እንደሆነና በውጊያው መካፈል ተገቢ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብሃል። ይህ ውጊያ በእርግጥ መሥዋዕትነት ሊከፈልለት የሚገባ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ “መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል” በማለት በዓይነቱ ልዩ የሆነው የዚህ ውጊያ ዓላማ ምን እንደሆነ ገልጿል። አዎን፣ በዚህ ውጊያ ከጠላት የምትከላከለውና የምትጠብቀው አንድን ምሽግ ሳይሆን ‘እምነትን’ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን አጠቃላይ ክርስቲያናዊ እውነት ነው። ለዚህ እምነት ለመጋደልና በውጊያው ለማሸነፍ ይህ “እምነት” እውነት መሆኑን ሙሉ በሙሉ አምነህ መቀበል እንዳለብህ የታወቀ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 6:12

አስተዋይ የሆነ ተዋጊ ጠላቱን ጠንቅቆ ለማወቅ ይጥራል። በዚህ ውጊያ የምትፋለመው ጠላት የብዙ ዓመት ልምድ ያለው ከመሆኑም በላይ የጦር መሣሪያዎችን ጨምሮ ለውጊያው የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሚገባ የታጠቀ ነው። በተጨማሪም ከሰብዓዊ ፍጡራን የላቀ ኃይል ያለው ሲሆን ጨካኝና ለማንም ደንታ የሌለው ነው። ይህ ጠላት ማን ነው? ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሰው ሠራሽ መሣሪያዎችም ሆኑ ሰብዓዊ ብልሃቶችና ዘዴዎች አይበግሩትም። (2 ቆሮንቶስ 10:4) ታዲያ በዚህ ውጊያ ልትጠቀምበት የምትችለው መሣሪያ ምንድን ነው?

ዋነኛው መሣሪያ ‘የመንፈስ ሰይፍ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ነው።’ (ኤፌሶን 6:17) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ መሣሪያ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ ሲገልጽ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፣ የሚሠራም፣ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፣ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፣ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል” ብሏል። (ዕብራውያን 4:11, 12) በጣም የተሳለና ወደ ውስጥ ጠልቆ የሚገባ ከመሆኑ የተነሳ የአንድን ሰው ሐሳብና ውስጣዊ ስሜት ሊነካ የሚችለውን ይህን መሣሪያ በጥንቃቄና በብልሃት ልንጠቀምበት ይገባል።

አንድ ሠራዊት በጣም የተራቀቁ መሣሪያዎችን የታጠቀ ቢሆንም ወታደሮቹ የመሣሪያዎቹን አጠቃቀም የማያውቁ ከሆነ ምንም ዋጋ የለውም። አንተም ሰይፍህን በሚገባ እንድትጠቀምበት ሥልጠና ማግኘት ያስፈልግሃል። ደግነቱ ከፍተኛ የውጊያ ልምድ ባካበቱ ተዋጊዎች የተሟላ ሥልጠና ማግኘት የምትችልበት አጋጣሚ አለህ። ኢየሱስ እነዚህን የውጊያ ልምድ ያላቸው አሠልጣኞች “ታማኝና ልባም ባሪያ” ሲል የጠራቸው ሲሆን ይህ ባሪያ ለኢየሱስ ተከታዮች በጊዜው መንፈሳዊ ምግብ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎበታል። (ማቴዎስ 24:45) የባሪያው ቡድን ለማሠልጠንም ሆነ የጠላትን ስልት አስቀድሞ ለማጋለጥ በሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት ተለይቶ ይታወቃል። ካሉት ሁኔታዎች በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ይህ ባሪያ በይሖዋ ምሥክሮች የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ በመንፈስ የተቀቡ አባላትን ያቀፈ ነው።—ራእይ 14:1

የባሪያው ቡድን በማስተማርና በማሠልጠን ብቻ አልተወሰነም። ከዚህ ይልቅ “ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፣ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤ እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፣ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና” ሲል የጻፈውን የሐዋርያው ጳውሎስን መንፈስ አንጸባርቋል። (1 ተሰሎንቄ 2:7, 8) ታማኙ ባሪያ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ከሚሰጠው ከዚህ ማሠልጠኛ በሚገባ መጠቀም የእያንዳንዱ ክርስቲያን ወታደር ኃላፊነት ነው።

የተሟላ የጦር ትጥቅ

ራስህን መከላከልና መጠበቅ እንድትችል ልትታጠቀው የሚገባ ምሳሌያዊ የሆነ የተሟላ የጦር ትጥቅ አለ። ይህ የጦር ትጥቅ በኤፌሶን 6:13-18 ላይ በዝርዝር ተገልጿል። ጠንቃቃ የሆነ ወታደር ከመንፈሳዊ የጦር ትጥቁ መካከል አንዱ እንደጎደለ ወይም ጥገና እንደሚያስፈልገው እያወቀ በጀብደኝነት ራሱን ለአደጋ አያጋልጥም።

አንድ ክርስቲያን የተሟላ የጦር ትጥቅ መታጠቅ የሚያስፈልገው ቢሆንም ከሁሉ በላይ ግን የእምነት ጋሻ ሊኖረው ይገባል። ጳውሎስ “በሁሉም ላይ [“ከዚህም ሁሉ በላይ፣” የ1980 ትርጉም] ጨምራችሁ የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ልታጠፉ የምትችሉበትን የእምነትን ጋሻ አንሡ” ሲል የጻፈው በዚህ ምክንያት ነው።—ኤፌሶን 6:16

እዚህ ላይ የተጠቀሰው ጋሻ መላ ሰውነትን የሚከልል ሲሆን ይህም እምነትን ያመለክታል። ይሖዋ የገባው ቃል ሙሉ በሙሉ እንደሚፈጸም እርግጠኛ በመሆን በሚሰጠን አመራር ላይ ጠንካራ እምነት ሊያድርብህ ይገባል። እንዲያውም አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች የተፈጸሙ ያህል ሆነው ሊታዩህ ይገባል። መላው የሰይጣን ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ፣ ምድር ወደ ገነትነት እንደምትለወጥና ለአምላክ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ፍጽምናን እንደሚላበሱ ቅንጣት ታክል ጥርጣሬ ሊያድርብህ አይገባም።—ኢሳይያስ 33:24፤ 35:1, 2፤ ራእይ 19:17-21

ይሁን እንጂ በዓይነቱ ልዩ በሆነው በዚህ ውጊያ በምትፋለምበት ጊዜ የቅርብ አጋር ማግኘትም ያስፈልግሃል። በውጊያ ወቅት ተዋጊዎች እርስ በርስ ሲደጋገፉና ሲረዳዱ ብሎም አንዱ የሌላውን ሕይወት ከሞት ሲታደግ በመካከላቸው የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠረታል። ከዚህ ውጊያ በሕይወት ለመትረፍ የትግል አጋሮች የሚያስፈልጉህ ቢሆንም ከሁሉ በላይ ግን ከይሖዋ ጋር መወዳጀትህ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ልንታጠቀው የሚገባንን የጦር ትጥቅ አስመልክቶ የሰጠውን መግለጫ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ” በማለት የደመደመው በዚህ ምክንያት ነው።—ኤፌሶን 6:18

ከቅርብ ወዳጃችን ጋር መሆን እንደሚያስደስተን የታወቀ ነው። አብረነው ጊዜ ለማሳለፍ የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን። ይሖዋን ዘወትር በጸሎት የምናነጋግረው ከሆነ እምነት እንደምንጥልበት የቅርብ ወዳጅ ይሆንልናል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል” የሚል ምክር ሰጥቶናል።—ያዕቆብ 4:8

ጠላት የሚጠቀምበት የውጊያ ስልት

ይህ ዓለም የሚያሳድርብንን ተጽዕኖ ለመቋቋም የምናደርገው ጥረት ፈንጂዎች በተቀበሩበት ቦታ ከመራመድ ጋር ሊነጻጸር ይችላል። ከዚህም ሌላ ካልታሰበ አቅጣጫ ጥቃት ሊሰነዘርብህ ይችላል፤ ወይም ደግሞ ጠላት አዘናግቶ ሊያጠቃህ ይችላል። ቢሆንም አይዞህ፣ ይሖዋ ጥበቃ ያደርግልሃል።—1 ቆሮንቶስ 10:13

ጠላት ለእምነትህ ወሳኝ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ላይ ትችት በመሰንዘር ሊያጠቃህ ይሞክር ይሆናል። ከሐዲዎች የማባበያ ቃላትን፣ ሽንገላንና እውነት የሚመስል የተጣመመ ሐሳብን መሣሪያ አድርገው በመጠቀም በእጃቸው ሊያስገቡህ ይሞክራሉ። ይህን የሚያደርጉት ግን ለአንተ ደኅንነት አስበው አይደለም። ምሳሌ 11:9 [የ1980 ትርጉም] “ከሐዲዎች በንግግራቸው ሰውን ያጠፋሉ፤ ደጋግ ሰዎች ግን በጥበባቸው ሰውን ያድናሉ” በማለት ይገልጻል።

ከሐዲዎች የሚያቀርቧቸውን የመከራከሪያ ሐሳቦች ውድቅ ለማድረግ በሚል የሚሉትን ለመስማት ወይም ጽሑፎቻቸውን ለማንበብ መሞከር ትልቅ ስህተት ነው። የተጣመመና መርዘኛ አስተሳሰባቸው መንፈሳዊ ጉዳት ሊያስከትልብህና በሰውነት ውስጥ እንደሚሰራጭ የማይሽር ቁስል እምነትህን ሊበክል ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 2:16, 17 አ.መ.ት) በመሆኑም ከሐዲዎችን በተመለከተ የአምላክ ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል። ኢዮብ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ዝንጉ [“ከሐዲ፣” NW] ሰው በፊቱ አይገባም” ብሏል።—ኢዮብ 13:16

ጠላት በተወሰነ ደረጃ ውጤታማ ሆኖ ያገኘውን ሌላ ስልት ሊጠቀም ይችላል። ለምሳሌ ያህል ለውጊያ በመንቀሳቀስ ላይ ካለ ሠራዊት መካከል የተወሰኑ ወታደሮች በጾታ ብልግና ተታልለው ከምድባቸው ወደኋላ ቢቀሩ ትልቅ ችግር ሊፈጠር ይችላል።

እንደ ብልግና ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና መረን የለቀቀ ሙዚቃ ያሉ ዓለማዊ መዝናኛዎች ሊያታልሉንና ወጥመድ ሊሆኑብን ይችላሉ። አንዳንዶች የብልግና ፊልሞችን ቢመለከቱ ወይም በጾታ ብልግና ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ጽሑፎችን ቢያነቡ ምንም ተጽዕኖ እንደማያደርግባቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የጾታ ብልግናን በገሃድ የሚያሳዩ ፊልሞችን አዘውትሮ ይመለከት የነበረ አንድ ሰው እንዲህ ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል፦ “እነዚህ ፊልሞች ፈጽሞ ከአእምሯችሁ አይጠፉም። ስላያችሁት ነገር ባሰባችሁ ቁጥር ያንን ድርጊት ለመፈጸም ያላችሁ ጉጉት እየጨመረ ይሄዳል። . . . አንድ ጥሩ ነገር እንደቀረባችሁ ሆኖ እንዲሰማችሁ ያደርጋችኋል።” ራስን እንዲህ ላለው ስውር ጥቃት ማጋለጥ ተገቢ ነው?

ጠላት የሚጠቀምበት ሌላው መሣሪያ ወይም ፍላጻ ደግሞ ፍቅረ ነዋይ ነው። ሁላችንም ቁሳዊ ነገሮች የሚያስፈልጉን በመሆኑ የዚህን የማጥቂያ ስልት አደገኛነት ላናስተውል እንችላለን። ማንኛችንም ብንሆን መጠለያ፣ ምግብና ልብስ ያስፈልገናል። በተጨማሪም ጥሩ ጥሩ ነገሮች ቢኖሩን ምንም ስህተት የለውም። ችግሩ ያለው አንድ ሰው ለቁሳዊ ነገሮች ባለው አመለካከት ላይ ነው። ገንዘብን ከመንፈሳዊ ነገሮች አስበልጠን መመልከት ልንጀምርና ፍቅረ ነዋይ ሊጠናወተን ይችላል። በመሆኑም ሀብት ሁሉን ነገር ሊያስገኝ እንደማይችል ዘወትር ማስታወስ ይኖርብናል። መንፈሳዊ ሀብት ዘላለማዊ ሲሆን ገንዘብ ግን አላፊ ጠፊ ነው።—ማቴዎስ 6:19, 20

የአንድ ሠራዊት የውጊያ ሞራል ከላሸቀ ድል የማድረግ ዕድሉ የመነመነ ነው። “በመከራ ቀን ብትላላ [ተስፋ ብትቆርጥ] ጉልበትህ ጥቂት ነው።” (ምሳሌ 24:10) ሰይጣን ሰዎችን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚጥር ሲሆን ይህንንም ዘዴ ውጤታማ ሆኖ ስላገኘው ለብዙ ዘመናት ተጠቅሞበታል። ‘የመዳንን ተስፋ እንደ ራስ ቁር ከለበስን’ የተስፋ መቁረጥን ስሜት ልናሸንፍ እንችላለን። (1 ተሰሎንቄ 5:8) ልክ እንደ አብርሃም ተስፋህ ምንጊዜም ብሩህ ሆኖ ይታይህ። አብርሃም አንድ ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብ ሲታዘዝ ምንም አላንገራገረም። አምላክ በዘሩ አማካኝነት አሕዛብን ሁሉ እንደሚባርክ የገባውን ቃል እንደሚፈጽምና ይህንንም ለማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ይስሐቅን ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል ሙሉ እምነት ነበረው።—ዕብራውያን 11:17-19

እጅ አትስጥ

ለረጅም ዓመታት ሲፋለሙ የቆዩ አንዳንዶች ሊዝሉና መጀመሪያ ላይ የነበራቸው የውጊያ ሞራል ሊዳከም ይችላል። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ኦርዮ በመንፈሳዊው ውጊያ እየተካፈሉ ያሉ ሁሉ ትክክለኛውን አመለካከት እንዲይዙ ጥሩ ምሳሌ ሊሆናቸው ይችላል። ከጎናችን ተሰልፈው በመዋጋት ላይ ያሉት ብዙዎቹ ክርስቲያኖች መከራ ሊደርስባቸው፣ ለአደጋ ሊጋለጡ ወይም ሐሩርና ቁር ሊፈራረቅባቸው ይችላል። ይሁንና ሁላችንም የኦርዮን ምሳሌ ልንከተል ይገባል። ምቾት ለማግኘትና ከውጥረት ነፃ የሆነ ዘና ያለ ኑሮ ለመኖር ስንል ከውጊያው ለመውጣት ማሰብ አይኖርብንም። በዓለም ዙሪያ ከሚገኘው የይሖዋ ታማኝ ሠራዊት ጎን ተሰልፈን ይሖዋ ያዘጋጀልንን በረከት እስክናገኝ ድረስ በውጊያው ወደፊት እንገፋለን።—ዕብራውያን 10:32-34

ውጊያው የሚጠናቀቅበት ጊዜ ገና ሩቅ እንደሆነ አድርገን በማሰብ መዘናጋት አደገኛ ነው። በንጉሥ ዳዊት ላይ የደረሰው ሁኔታ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ዳዊት በሆነ ምክንያት ወደ ዐውደ ግንባሩ አልሄደም ነበር። በዚህም ሳቢያ ከባድ ኃጢአት በመሥራቱ ቀሪው ሕይወቱ በመከራና በሥቃይ የተሞላ ሊሆን ችሏል።—2 ሳሙኤል 12:10-14

በዚህ ውጊያ መካፈል፣ መከራውን መጋፈጥ፣ የሚደርስብንን ፌዝ መቋቋምና አጠያያቂ ከሆኑ ዓለማዊ መዝናኛዎች መራቅ የሚያስገኘው ጥቅም ይኖራል? በውጊያው ድል በማድረግ ወደፊት እየገሰገሱ ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ዓለም የሚያቀርባቸው ብልጭልጭ ነገሮች ከላይ ሲታዩ ማራኪ ቢመስሉም ጠለቅ ብለው ሲታዩ ግን ዋጋ ቢስ እንደሆኑ ይገነዘባሉ። (ፊልጵስዩስ 3:8) እንዲያውም ደስታ ይሰጣሉ ተብለው የሚታሰቡት እነዚህ ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ ለሐዘንና ለብስጭት ይዳርጋሉ።

በዚህ መንፈሳዊ ውጊያ በመካፈል ላይ ያለ ክርስቲያን እውነተኛ ወዳጆች ያፈራል፣ ንጹሕ ሕሊና ይኖረዋል እንዲሁም አስደሳች ተስፋ ይጠብቀዋል። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሰማይ ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር የማይጠፋ ሕይወት ያገኛሉ። (1 ቆሮንቶስ 15:54) አብዛኞቹ ክርስቲያን ተዋጊዎች ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም ሆነው ይኖራሉ። በእርግጥም እነዚህ ሽልማቶች ማንኛውም መሥዋዕትነት ቢከፈልላቸው አያስቆጩም። በዓለም ላይ የሚካሄዱት ጦርነቶች መጨረሻቸው ምን እንደሚሆን መገመት አይቻልም። እኛ በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ግን እስከ መጨረሻው ከጸናን ድል እንደምንቀዳጅ የተረጋገጠ ነው። (ዕብራውያን 11:1) ከዚህ በተቃራኒው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ጥፋት ነው።—2 ጴጥሮስ 3:10

በዚህ ውጊያ ወደፊት በገፋህ መጠን “አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት አስታውስ። (ዮሐንስ 16:33) ኢየሱስ ዓለምን ሊያሸንፍ የቻለው ላፍታም ሳይዘናጋ ዘወትር ነቅቶ በመኖርና በፈተና ወቅት በታማኝነት በመጽናት ነው። እኛም እንዲሁ ማድረግ እንችላለን።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በዚህ ውጊያ የሚተኮስ ጥይትም ሆነ የሚጣል ቦምብ ባይኖርም ውጊያው የረቀቀ የጦር ስልት ይጠይቃል

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

እኛ በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ እስከ መጨረሻው ከጸናን ድል እንደምንቀዳጅ የተረጋገጠ ነው

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመዳን ራስ ቁር የተስፋ መቁረጥ ስሜትን እንድናሸንፍ ይረዳናል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰይጣን የሚወረውራቸውን ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ ለመከላከል መላ ሰውነትን የሚከልለውን የእምነት ጋሻ እናንሣ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እምነት ሊኖረን ይገባል