በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

“በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”—ቆላስይስ 2:8

1-3. (ሀ) ማታለል በሁሉም የኑሮ ዘርፍ እየተንጸባረቀ እንዳለ የሚያሳዩት የትኞቹ ምሳሌዎች ናቸው? (ለ) ዓለም በማታለል ድርጊት የተሞላ መሆኑ ሊያስገርመን የማይገባው ለምንድን ነው?

 ተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ የሕግ ፕሮፌሰር “ከእናንተ መካከል የሚዋሽ ደንበኛ አጋጥሞት የማያውቅ አለ?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ አንድ ጥናት አካሂደው ነበር። ለዚህ ጥያቄ ያገኙት መልስ ምን ነበር? ፕሮፌሰሩ “ይህ ጥያቄ ከቀረበላቸው በሺህ የሚቆጠሩ ጠበቆች መካከል የሚዋሽ ደንበኛ አጋጥሞት እንደማያውቅ የተናገረው አንድ ጠበቃ ብቻ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ይህ ጠበቃ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ያላጋጠመው ለምን ነበር? “በአንድ ድርጅት ውስጥ ገና በልምምድ ላይ ስለነበር ደንበኞችን ለማነጋገር አጋጣሚ አላገኘም።” ይህ ሁኔታ ውሸትና ማታለል በዓለም ላይ ምን ያህል እንደተስፋፋ የሚያሳይ አሳዛኝ እውነታ ነው።

2 ማታለል ብዙ መልክ ያለው ሲሆን በዛሬው ጊዜ በሁሉም የኑሮ ዘርፍ ይንጸባረቃል ለማለት ይቻላል። ፖለቲከኞች እንደሚዋሹ፣ የሒሳብ ሠራተኞችና ጠበቆች የንግድ ድርጅቶችን ትርፍ አጋንነው እንደሚያቀርቡ፣ የንግድ ማስታወቂያዎችን የሚሠሩ ድርጅቶች ሸማቾችን እንደሚያሳስቱ፣ ነገረፈጆች የኢንሹራንስ ድርጅቶችን እንደሚያጭበረብሩ የሚገልጹ ዘገባዎች በመገናኛ ብዙኃን በስፋት ይቀርባሉ። ከሃይማኖት ጋር በተያያዘም የማታለል ድርጊት ይፈጸማል። ቀሳውስት ነፍስ አትሞትም፣ ሲኦል የማቃጠያ ስፍራ ነው እንዲሁም አምላክ ሥላሴ ነው እንደሚሉት ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን በማስተማር ብዙኃኑን ያሳስታሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4

3 ይህ ሊያስገርመን ይገባል? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻውን ቀን’ አስመልክቶ ሲናገር “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ” በማለት ይገልጻል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከእውነት መንገድ እንድንወጣ ሊያደርጉን በሚችሉ አሳሳች አመለካከቶች እንዳንታለል መጠንቀቅ ይኖርብናል። እዚህ ላይ ሁለት ጥያቄዎች ይነሳሉ፦ በዛሬው ጊዜ ማታለል የበዛው ለምንድን ነው? እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

በዛሬው ጊዜ ማታለል የበዛው ለምንድን ነው?

4. መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም በማታለል የተሞላው ለምን እንደሆነ የሚገልጸው እንዴት ነው?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም በማታለል የተሞላው ለምን እንደሆነ በግልጽ ይነግረናል። ሐዋርያው ዮሐንስ ‘ዓለም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ’ ገልጿል። (1 ዮሐንስ 5:19) እዚህ ላይ “ክፉው” ተብሎ የተገለጸው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ኢየሱስ ሰይጣንን አስመልክቶ ሲናገር “እውነትም በእርሱ ስለ ሌለ በእውነት አልቆመም። ሐሰትን ሲናገር ከራሱ ይናገራል፣ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነውና” ብሏል። ታዲያ ይህ ዓለም የገዥውን የዲያብሎስን መንፈስ፣ ምግባርና የማታለል ባሕርይ ቢያንጸባርቅ ምን ያስገርማል?—ዮሐንስ 8:44፤ 14:30፤ ኤፌሶን 2:1-3

5. በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰይጣን የማታለል ድርጊቱን ይበልጥ አጠናክሮ የገፋበት እንዴት ነው? ዋነኛ ዒላማው ያደረገውስ እነማንን ነው?

5 በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰይጣን የማታለል ድርጊቱን ይበልጥ አጠናክሮ ገፍቶበታል። ከሰማይ ወደ ምድር የተወረወረ ከመሆኑም በላይ የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ እጅግ ‘ተቆጥቷል።’ የተቻለውን ያህል ብዙ ሰዎችን ይዞ ለመጥፋት ቆርጦ ስለተነሳ ‘ዓለሙን ሁሉ በማሳት’ ላይ ይገኛል። (ራእይ 12:9, 12) ሰይጣን ሰዎችን የሚያታልለው እንዲሁ አልፎ አልፎ ብቻ አይደለም። የሰው ልጆችን ከማሳት የቦዘነበት ጊዜ የለም። a የማያምኑ ሰዎችን ልቦና ለማሳወርና ወደ አምላክ እንዳይቀርቡ ለማድረግ ያሉትን የማታለያ ዘዴዎች ሁሉ ይጠቀማል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ይህ የወጣለት አታላይ በተለይ አምላክን “በመንፈስና በእውነት” የሚያመልኩትን ለመዋጥ ቆርጦ ተነስቷል። (ዮሐንስ 4:24፤ 1 ጴጥሮስ 5:8) ሰይጣን ‘ማንኛውንም ሰው ከአምላክ እንዲርቅ ማድረግ እችላለሁ’ ብሎ በተዘዋዋሪ መንገድ እንደተከራከረ አትዘንጋ። (ኢዮብ 1:9-12) ሰዎችን ‘ለመሸንገል’ ወይም ለማታለል የሚጠቀምባቸው አንዳንድ ዘዴዎች ምን እንደሆኑና በእነዚህ የተንኮል ዘዴዎች እንዳንታለል እንዴት መጠንቀቅ እንደምንችል እስቲ እንመልከት።—ኤፌሶን 6:11

በከሃዲዎች እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

6, 7. (ሀ) ከሃዲዎች ምን ብለው ሊናገሩ ይችላሉ? (ለ) ቅዱሳን ጽሑፎች የከሃዲዎችን ዓላማ በግልጽ የሚጠቁሙት እንዴት ነው?

6 ሰይጣን የአምላክ አገልጋዮችን ለማሳሳት ከሃዲዎችን ለረጅም ጊዜ መሣሪያ አድርጎ ሲጠቀም ኖሯል። (ማቴዎስ 13:36-39) ከሃዲዎች ይሖዋን እንደሚያመልኩና በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያምኑ ሊናገሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የይሖዋን ምድራዊ ድርጅት አይቀበሉም። እንዲያውም አንዳንዶች ወደ ኋላ ተመልሰው የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” የምታስተምራቸውን አምላክን የማያስከብሩ ትምህርቶች መከተል ይጀምራሉ። (ራእይ 17:5፤ 2 ጴጥሮስ 2:19-22) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በአምላክ መንፈስ መሪነት የከሃዲዎችን ዓላማና የሚጠቀሙባቸውን ዘዴዎች የሚያጋልጡ ኃይለኛ መልእክቶችን ጽፈዋል።

7 ከሃዲዎች ዓላማቸው ምንድን ነው? አብዛኞቹ በአንድ ወቅት እውነት ነው ብለው ይከተሉት የነበረውን እምነት ጥለው በመሄድ ብቻ አይወሰኑም። ብዙውን ጊዜ ሌሎችንም ከእውነት መንገድ ማስወጣት ይፈልጋሉ። የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ከማፍራት ይልቅ የክርስቶስን ‘ደቀ መዛሙርት ወደ ኋላቸው መሳብ’ ወይም የእነሱ ተከታዮች ማድረግ ይፈልጋሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ሐዋርያው ጳውሎስ የሐሰት አስተማሪዎችን በተመለከተ “በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” ሲል ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ቆላስይስ 2:8) የብዙዎቹ ከሃዲዎች ዓላማ ይህ አይደለም? ከሃዲዎች አንድን ያልጠረጠረ ሰው ከቤተሰቡ ነጥለው እንደሚወስዱ አፋኞች ቅን የሆኑ የጉባኤ አባላትን ከመንጋው ነጥለው ለመውሰድ ይሞክራሉ።

8. ከሃዲዎች ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ ምን ዘዴዎችን ይጠቀማሉ?

8 ከሃዲዎች ዓላማቸውን ዳር ለማድረስ ምን ዘዴዎች ይጠቀማሉ? ብዙውን ጊዜ እውነቱን ያጣምማሉ፣ ውሸት ይቀላቅላሉ እንዲሁም ዓይን ያወጣ ውሸት ይናገራሉ። ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘ክፉውን ሁሉ በውሸት በሚናገሩባቸው’ ሰዎች ጥቃት እንደሚደርስባቸው ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 5:11) እንዲህ ያሉ ተንኮለኛ ተቃዋሚዎች ሌሎችን ለማታለል ሲሉ ከእውነት የራቀ ወሬ ያስፋፋሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የፈጠራ ወሬ” ስለሚነዙ፣ “አታላይ ትምህርቶችን” ስለሚያስፋፉና የራሳቸውን ግብ ዳር ለማድረስ ሲሉ ‘መጻሕፍትን ስለሚያጣምሙ’ ከሃዲዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (2 ጴጥሮስ 2:3, 13 NW፤ 3:16) የሚያሳዝነው ከሃዲዎች ‘የአንዳንዶችን እምነት በመገልበጥ’ ረገድ ተሳክቶላቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 2:18

9, 10. (ሀ) በከሃዲዎች እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) ስለ አምላክ ዓላማ ባለን ግንዛቤ ረገድ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ቢያስፈልገን የማንረበሸው ለምንድን ነው?

9 በከሃዲዎች እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክ ቃል “እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፣ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፣ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በመከተል ነው። (ሮሜ 16:17) በአካል፣ በጽሑፍም ይሁን በኢንተርኔት የሚያቀርቧቸውን ሐሳቦች ባለመቀበል ‘ከእነርሱ ፈቀቅ’ እንላለን። እንዲህ የምናደርገው ለምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ቃል እንዲህ እንድናደርግ የሚያዘን ሲሆን ይሖዋ ደግሞ ምንጊዜም ለእኛ የሚበጀውን እንደሚያስብ እርግጠኞች ነን።—ኢሳይያስ 48:17, 18

10 በሁለተኛ ደረጃ ከታላቂቱ ባቢሎን ሙሉ በሙሉ የተለየን እንድንሆን የሚያደርጉንን ውድ እውነቶች ላስተማረን ድርጅት ጥልቅ ፍቅር አለን። በተጨማሪም ስለ አምላክ ዓላማ ፍጹም የተሟላ ግንዛቤ አለን የሚል እምነት የለንም፤ በመሆኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ አስፈልጎናል። ታማኝ ክርስቲያኖች ይሖዋ እንደዚህ የመሳሰሉ አንዳንድ ማስተካከያዎችን የሚያደርግበትን ጊዜ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ እንጂ የራሳቸውን እርምጃ አይወስዱም። (ምሳሌ 4:18) ይሖዋ ድርጅቱን እየባረከው እንዳለ የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ስላሉ አምላክ እየተጠቀመበት ያለውን ይህን ድርጅት ትተን ለመውጣት አናስብም።—የሐዋርያት ሥራ 6:7፤ 1 ቆሮንቶስ 3:6

ራሳችሁን እንዳታታልሉ ተጠንቀቁ

11. ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን የሚያታልሉት ለምንድን ነው?

11 ፍጽምና የሌላቸው የሰው ልጆች ራሳቸውን የማታለል ዝንባሌ ያላቸው በመሆኑ ሰይጣን ዓላማውን ለማሳካት ይህን ዝንባሌ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምበታል። ኤርምያስ 17:9 “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ተንኰለኛ እጅግም ክፉ ነው” በማለት ይገልጻል። በተጨማሪም ያዕቆብ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 1:14) ልባችን አንድን መጥፎ ነገር ከተመኘ ማራኪና ምንም ጉዳት የሌለው እንደሆነ እንዲሰማን በማድረግ ሊያታልለን ይችላል። በኃጢአት ድርጊት መሸነፍ ከባድ ውድቀት ስለሚያስከትል እንዲህ ያለው አስተሳሰብ አደገኛ ነው።—ሮሜ 8:6

12. ራስን የማታለል ዝንባሌ ወጥመድ ሊሆንብን የሚችለው እንዴት ነው?

12 ራስን የማታለል ዝንባሌ በቀላሉ ወጥመድ ሊሆንብን ይችላል። ተንኮለኛ የሆነው ልባችን ላለብን ሰብዓዊ ድክመት ወይም ለሠራነው ከባድ ኃጢአት ሰበብ ሊያቀርብ ይችላል። (1 ሳሙኤል 15:13-15, 20, 21) በተጨማሪም ክፉ የሆነው ልባችን አጠያያቂ የሆኑ ነገሮችን ለማድረግ የማይመስል ምክንያት ሊደረድር ይችላል። መዝናኛን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አንዳንድ መዝናኛዎች ጥሩና አስደሳች ናቸው። ይሁን እንጂ ይህ ዓለም በፊልሞች፣ በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በኢንተርኔት የሚያቀርባቸው አብዛኞቹ መዝናኛዎች አስጸያፊና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ናቸው። መጥፎ መዝናኛ ምንም ጉዳት እንደማያስከትልብን አድርገን ራሳችንን በቀላሉ ልናሳምን እንችላለን። እንዲያውም አንዳንዶች “ሕሊናዬን እስካልረበሸኝ ድረስ ምን ችግር አለው?” ብለው ያስባሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ‘ራሳቸውን እያሳቱ’ ነው።—ያዕቆብ 1:22

13, 14. (ሀ) ሕሊናችን ሁልጊዜ አስተማማኝ ሊሆን እንደማይችል የሚያሳየው ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌ የትኛው ነው? (ለ) ራሳችንን እንዳናታልል ምን ሊረዳን ይችላል?

13 ራሳችንን እንዳናታልል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ የሰው ሕሊና ሁልጊዜ አስተማማኝ ሊሆን እንደማይችል መዘንጋት የለብንም። ሐዋርያው ጳውሎስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት የክርስቶስን ተከታዮች ያሳድድ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 9:1, 2) በዚያን ጊዜ ሕሊናው አልረበሸው ይሆናል። ግን ትክክል ነበር ማለት አይደለም። ጳውሎስ ይህን ያደረገው ‘ባለማወቅና ባለማመን’ እንደነበር ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 1:13) ስለዚህ አንድ መዝናኛ ሕሊናችንን ስላልረበሸው ብቻ የመረጥነው መዝናኛ ትክክል ነው ልንል አንችልም። ሕሊናችን አስተማማኝ መመሪያ ሊሰጠን የሚችለው በአምላክ ቃል በሚገባ የሰለጠነ ከሆነ ብቻ ነው።

14 ራሳችንን እንዳናታልል ከፈለግን ልብ ልንላቸው የሚገቡ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች አሉ። በጸሎት ራስህን መርምር። (መዝሙር 26:2፤ 2 ቆሮንቶስ 13:5) ራስህን በሐቀኝነት መመርመርህ በአመለካከትህ ወይም በአካሄድህ ላይ አንዳንድ ለውጦች ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ሊያስገነዝብህ ይችላል። ሌሎች የሚሰጡህን ምክር ስማ። (ያዕቆብ 1:19) ራሳችንን በምንመረምርበት ጊዜ ለራሳችን ልናደላ ስለምንችል የጎለመሱ ክርስቲያኖች የሚሰጡንን ትክክለኛ አስተያየት መስማቱ የተሻለ ነው። የምታደርገው ውሳኔ ወይም የምትወስደው እርምጃ ሚዛናዊ በሆኑና ተሞክሮ ባላቸው የእምነት ባልንጀሮችህ ዓይን አጠያያቂ ከሆነ ‘እንዲህ እያደረግኩ ያለሁት ሕሊናዬ በሚገባ ስላልሰለጠነ ይሆን? ወይስ ልቤ እያታለለኝ?’ ብለህ ራስህን መጠየቅ ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ዘወትር አንብብ። (መዝሙር 1:2) እንዲህ ማድረግህ አስተሳሰብህ፣ አመለካከትህና ስሜትህ አምላክ ካወጣቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚስማማ እንዲሆን ሊረዳህ ይችላል።

በሰይጣን ውሸቶች እንዳትታለሉ ተጠንቀቁ

15, 16. (ሀ) ሰይጣን እኛን ለማታለል የትኞቹን ውሸቶች ይጠቀማል? (ለ) እንዲህ ባሉት ውሸቶች እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 ሰይጣን እኛን ለማታለል የተለያዩ ውሸቶችን ይጠቀማል። ሐቁ ሌላ ሆኖ ሳለ ቁሳዊ ሀብት ደስታና እርካታ ያስገኛል ብሎ ሊያሳምነን ይጥራል። (መክብብ 5:10-12) “በመጨረሻው ቀን” እንደምንኖር የሚያረጋግጡ ግልጽ ማስረጃዎች ቢኖሩም ይህ ክፉ ሥርዓት እንዳለ ይቀጥላል ብለን እንድናምን ሊያደርገን ይሞክራል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ምንም እንኳ ሥጋዊ ፍላጎታቸውን ለማርካት የሚሯሯጡ ሰዎች ብዙውን ጊዜ መጥፎ ውጤት የሚያጭዱ ቢሆንም ሥነ ምግባር የጎደለው የአኗኗር ዘይቤ ምንም ጉዳት የለውም የሚል አመለካከት ያስፋፋል። (ገላትያ 6:7) እንዲህ ባሉ ውሸቶች እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

16 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሰፈሩት የማስጠንቀቂያ ምሳሌዎች ተማር። መጽሐፍ ቅዱስ በሰይጣን ውሸቶች የተታለሉ ሰዎችን ታሪክ ይዞልናል። እነዚህ ሰዎች በፍቅረ ነዋይ ተታልለዋል፣ የነበሩበትን ዘመን ማስተዋል ተስኗቸዋል ወይም በጾታ ብልግና ተሸንፈዋል። በዚህም ሳቢያ ሁሉም አስከፊ ውድቀት ደርሶባቸዋል። (ማቴዎስ 19:16-22፤ 24:36-42፤ ሉቃስ 16:14፤ 1 ቆሮንቶስ 10:8-11) በዘመናች ባሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ከደረሰው ሁኔታ ተማር። የሚያሳዝነው አንዳንድ ክርስቲያኖች የጊዜውን አጣዳፊነት ከመዘንጋታቸውም በላይ አምላክን በማገልገላቸው ጥሩ ነገር እንደቀረባቸው ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ደስታ የሞላበት ኑሮ ብለው የሚያስቡትን የአኗኗር ዘይቤ ለመከተል ሲሉ እውነትን ሊተዉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ ይህ አኗኗራቸው የሚያስከትልባቸውን መጥፎ ውጤት ማጨዳቸው ስለማይቀር “በድጥ ስፍራ” የቆሙ ያህል ነው። (መዝሙር 73:18, 19) ስለዚህ ከሌሎች ስህተት መማር ብልህነት ነው።—ምሳሌ 22:3

17. ሰይጣን፣ ይሖዋ እንደማይወደን ወይም ከቁብ እንደማይቆጥረን እንዲሰማን ለማድረግ የሚጥረው ለምንድን ነው?

17 ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል የሚጠቀምበት ሌላም ውሸት አለ። ሰዎች፣ ይሖዋ አይወደኝም ወይም ከቁብ አይቆጥረኝም የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ሰይጣን በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ፍጽምና የሌላቸውን የሰው ልጆች ባሕርይ ሲያጠና ኖሯል። ተስፋ ከቆረጥን በመንፈሳዊ ልንዳከም እንደምንችል ያውቃል። (ምሳሌ 24:10) በመሆኑም በአምላክ ፊት ምንም ዋጋ እንደሌለን ሆኖ እንዲሰማን ለማድረግ ይጥራል። ‘እንደተጣልንና’ ይሖዋ ምንም እንደማያስብልን ከተሰማን ተስፋ ወደ መቁረጥ ልናዘነብል እንችላለን። (2 ቆሮንቶስ 4:9 አ.መ.ት) የወጣለት አታላይ የሆነው ሰይጣን የሚፈልገውም ይህንኑ ነው! ታዲያ ሰይጣን በሚያስፋፋው በዚህ ውሸት እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

18. መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ እንደሚወደን የሚያረጋግጥልን እንዴት ነው?

18 አምላክ ለእኛ ያለውን ፍቅር በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ሐሳብ ላይ አሰላስል። የአምላክ ቃል ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወደንና እንደሚያስብልን የሚያረጋግጡ ሕያው የሆኑ መግለጫዎችን ይዟል። ይሖዋ እንባህን ‘በአቁማዳ’ ያጠራቅማል፤ ይህም በታማኝነት ለመጽናት በምታደርገው ትግል የምታፈስሰውን እንባ እንደሚያይና እንደሚያስታውስ ያመለክታል። (መዝሙር 56:8 አዲሱ መደበኛ ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ‘ልብህ በሐዘን በሚሰበርበት’ ጊዜ የሚሰማህን ስሜት የሚረዳልህ ከመሆኑም በላይ እንዲህ ባሉ ጊዜያት ከአጠገብህ አይለይም። (መዝሙር 34:18) ስለ አንተ እያንዳንዱን ነገር ጠንቅቆ ያውቃል። ‘የራስህን ጠጉር’ ቁጥር እንኳ ሳይቀር በትክክል ያውቃል። (ማቴዎስ 10:29-31) ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ “አንድያ ልጁን” ለአንተ ሲል አሳልፎ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 3:16፤ ገላትያ 2:20) አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያሉ ጥቅሶች አንተን በግለሰብ ደረጃ እንደሚመለከቱ አድርገህ ለማሰብ ትቸገር ይሆናል። ይሁን እንጂ የይሖዋን ቃል ልናምን ይገባል። ይሖዋ በቡድን ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም እንደሚወደን እንድናምን ይፈልጋል።

19, 20. (ሀ) ሰይጣን፣ ይሖዋ አይወደንም ብለው እንዲያስቡ በማድረግ ሰዎችን ለማታለል እንደሚጥር መገንዘብ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ያዘኑ ወንድሞችንና እህቶችን የረዳው እንዴት ነው?

19 እንዳትታለል ውሸቱን ለይተህ እወቅ። አንድ ሰው እየዋሸ እንዳለ ካወቅህ እንዳትታለል ትጠነቀቃለህ። በተመሳሳይም ሰይጣን፣ ይሖዋ አይወደኝም ብለህ በማሰብ እንድትታለል የሚፈልግ መሆኑን ማወቅህ በእጅጉ ይጠቅምሃል። አንዲት ክርስቲያን በአንድ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ ሰይጣን ስለሚጠቀምባቸው የተንኮል ዘዴዎች የወጣውን ርዕስ በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ሰይጣን የራሴን ስሜት እንደ መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም ተስፋ ሊያስቆርጠኝ እንደሚሞክር አልተገነዘብኩም ነበር። ይህን መገንዘቤ እንዲህ ያለውን ስሜት አጥብቄ እንድዋጋ አነሳስቶኛል።”

20 በደቡብ አሜሪካ በምትገኝ አንዲት አገር የሚያገለግል ተጓዥ የበላይ ተመልካች ምን እንዳደረገ ተመልከት። ያዘኑና የተጨነቁ ወንድሞችንና እህቶችን በሚያበረታታበት ጊዜ ‘በሥላሴ ታምናለህ?’ ብሎ ይጠይቃቸዋል። ግለሰቡ ይህ ትምህርት ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ውሸቶች አንዱ እንደሆነ ስለሚያውቅ ‘አላምንም’ ብሎ ይመልሳል። ከዚያም ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ‘ሲኦል ማቃጠያ ሥፍራ ነው ብለህ ታምናለህ?’ ብሎ ይጠይቀዋል። አሁንም ግለሰቡ ‘አላምንም’ ብሎ ይመልሳል። በዚህ ጊዜ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ብዙውን ጊዜ ልብ የማንለው ሰይጣን የሚያስፋፋው አንድ ሌላ ውሸት አለ ብሎ ይነግረዋል። ከዚያም ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ አይወደንም ብለው እንዲያስቡ በማድረግ ሰይጣን ሰዎችን እንደሚያታልል የሚገልጸውን ወደ ይሖዋ ቅረብ b (እንግሊዝኛ) በተባለው መጽሐፍ ገጽ 249 አንቀጽ 21 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ያሳያቸዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ያደረባቸው ወንድሞችና እህቶች ሰይጣን የሚያስፋፋውን ይህን ውሸት እንዲገነዘቡና በዚህ እንዳይታለሉ ለመርዳት ያደረገው ጥረት ጥሩ ውጤት እንዳስገኘለት ሪፖርት አድርጓል።

እንዳትታለል ተጠንቀቅ

21, 22. የሰይጣንን የማታለያ ዘዴዎች የማንስተው ለምንድን ነው? ቁርጥ ውሳኔያችንስ ምን መሆን አለበት?

21 እየተገባደደ ባለው በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰይጣን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ውሸቶችና ማታለያዎች እያስፋፋ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ደግነቱ ይሖዋ የሰይጣንን የማታለያ ዘዴዎች ለይተን እንድናውቅ ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያዘጋጃቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች የዲያብሎስን የተንኮል ዘዴዎች በማጋለጥ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጡናል። (ማቴዎስ 24:45) አስቀድሞ ማስጠንቀቅ አስቀድሞ ማስታጠቅ ነው።—2 ቆሮንቶስ 2:11

22 እንግዲያው ከሃዲዎች የሚያቀርቧቸው አሳሳች ሐሳቦች እንዳያታልሉን እንጠንቀቅ። ራስን የማታለል ዝንባሌ ወጥመድ እንዳይሆንብን ንቁዎች እንሁን። በተጨማሪም ሰይጣን የሚያስፋፋቸውን ውሸቶች ለይተን በማወቅ ራሳችንን እንዲህ ካሉት ማታለያዎች እንጠብቅ። እንዲህ ካደረግን አታላይነትን ከሚጠላው “የእውነት አምላክ” ጋር ያለንን ዝምድና ጠብቀን መኖር እንችላለን።—መዝሙር 31:5፤ ምሳሌ 3:32

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው በራእይ 12:9 ላይ “የሚያስተው” ተብሎ የተተረጎመው ግስ “ቀጣይ የሆነን ልማዳዊ ድርጊት ያመለክታል።”

b በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

ታስታውሳለህ?

• በዛሬው ጊዜ ዓለም በማታለል የተሞላው ለምንድን ነው?

• በከሃዲዎች እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• ራስን የማታለል ዝንባሌ እንዳይጠናወተን መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

• ሰይጣን በሚያስፋፋቸው ውሸቶች እንዳንታለል መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በመዝናኛ ረገድ ራስህን እንዳታታልል ተጠንቀቅ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን የማታለል ዝንባሌ እንዳይጠናወትህ ራስህን በጸሎት መመርመር፣ ሌሎች የሚሰጡህን ምክር መስማትና የአምላክን ቃል አዘውትረህ ማንበብ ይኖርብሃል