በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ከጥፋት ውኃው በኋላ ኖኅ የላካት ርግብ “የወይራ ቅጠል” ይዛ ተመልሳለች። ቅጠሉን ያገኘችው ከየት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ውኃውም በምድር ላይ እጅግ በጣም አሸነፈ፤ ከሰማይም በታች ያሉ ታላላቆች ተራሮች ሁሉ ተሸፈኑ” በማለት ይገልጽልናል። (ዘፍጥረት 7:19) ውኃው እየጎደለ ሲሄድ ኖኅ በየአንድ ሳምንት ልዩነት ሦስት ጊዜ ርግብ ላከ። ለሁለተኛ ጊዜ ርግብ ሲልክ “በአፍዋም እነሆ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ” ተመለሰች። “ኖኅም ከምድር ላይ ውኃ እንደ ቀለለ አወቀ።”—ዘፍጥረት 8:8-11

መልክዓ ምድሩ በጥፋት ውኃው ተለዋውጦ ሊሆን ስለሚችል አንድ የተወሰነ የምድር ክፍል ለምን ያህል ጊዜ በውኃ ተሸፍኖ እንደቆየ መገመት አዳጋች ነው። የሆነ ሆኖ ውኃው ረዘም ላለ ጊዜ ምድርን ሸፍኖ እንደቆየና በዚህም ሳቢያ አብዛኞቹ ዛፎች ከሕልውና ውጪ እንደሆኑ መገመት ይቻላል። ይሁንና አንዳንዶቹ ዛፎች ውኃው ከጎደለ በኋላ እንደገና ማቆጥቆጥ ችለዋል።

ዘ ኒው ባይብል ዲክሽነሪ የወይራ ዛፍን በተመለከተ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “የወይራ ዛፍ ከተቆረጠ ጉቶው ግንድ ሊሆኑ የሚችሉ እስከ አምስት የሚደርሱ ቁጥቋጦዎች ሊያወጣ ይችላል። ሙሉ በሙሉ ሊከስሙ የተቃረቡ የወይራ ዛፎችም እንኳ ብዙውን ጊዜ በዚህ መንገድ ዳግመኛ ሊያቆጠቁጡ ይችላሉ።” ዘ ኒው ሻፍ-ሄርትሶክ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ የተባለው መጽሐፍ “የወይራ ዛፍ በቀላሉ አይጠፋም” ሲል ገልጿል። በዛሬው ጊዜ የጥፋት ውኃው የነበረውን የጨው ይዘትም ሆነ የሙቀት መጠን እንዲሁም ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች የሚያውቅ የለም። በመሆኑም የጥፋት ውኃው በወይራ ዛፍም ሆነ በሌሎች እጽዋት ላይ ያስከተለው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።

ይሁን እንጂ ዱር በቀል የሆነ የወይራ ዛፍ ቀዝቃዛ የአየር ንብረት አይስማማውም። ለምሳሌ ያህል ቀዝቃዛ በሆነ ተራራማ ቦታ ላይ ሊበቅል አይችልም። በአብዛኛው የሚበቅለው ከባሕር ወለል በላይ ከ1,000 ሜትር ያነሰ ከፍታ ባላቸው ቦታዎች ሲሆን በእነዚህ አካባቢዎች ያለው የሙቀት መጠን ደግሞ በአማካይ ከ10 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ነው። “በመሆኑም” ይላል ዘ ፍለድ ሪከንሲደርድ የተባለው መጽሐፍ፣ “ኖኅ ርግቧ ቀጥፋ ያመጣችውን ለምለም የወይራ ቅጠል ሲመለከት ዝቅተኛ በሆኑ ቦታዎች እንኳ ሳይቀር ውኃው እንደደረቀ መገንዘብ ይችላል።” ይህ ከሆነ ከሳምንት በኋላ ኖኅ እንደገና የላካት ርግብ አልተመለሰችም። ይህም ብዙ እጽዋት እንደበቀሉና ርግቧም ማረፊያ ቦታ እንዳገኘች የሚጠቁም ነው።—ዘፍጥረት 8:12