በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ ቤትህ የሚመጡት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ ቤትህ የሚመጡት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች በተደጋጋሚ ቤትህ የሚመጡት ለምንድን ነው?

በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮች ያለማሰለስ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማር የታወቁ ናቸው። አንዳንድ ሰዎች ‘ፍላጎት እንደሌለን እየነገርናቸው ተመልሰው ቤታችን የሚመጡት ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ። ከሩስያ የተላኩ ሁለት ደብዳቤዎች የይሖዋ ምሥክሮች ይህን የሚያደርጉበትን ምክንያት ግልጽ ያደርጉልናል።

በከባሮቭስክ የምትኖር ማሻ የተባለች አንዲት የ19 ዓመት ወጣት “እውነቱን ለመናገር ቀደም ባሉት ጊዜያት የይሖዋ ምሥክሮችን እንደ ጦር እፈራቸው ነበር” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ይሁን እንጂ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ መጽሔቶችን ካነበበች በኋላ አመለካከቷ ተለወጠ። “ያነበብኩት ነገር በጣም አስደሳች ከመሆኑም በላይ የእውቀት አድማሴን የሚያሰፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ” ስትል ጽፋለች። “ከሁሉ በላይ ግን መጽሔቶቹ የሚሰጡት ትምህርት ለዓለም ያለህን አመለካከት ይለውጠዋል። እያደር የሕይወት ዓላማ ምን እንደሆነ ተገነዘብኩ” ብላለች።

ከቭላዶቮስቶክ በስተሰሜን 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በኡሱሪስክ ከተማ የምትኖር ስቬትላና የተባለች ሴት ደግሞ እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን ማንበብ የጀመርኩት በቅርቡ ነው። እነዚህ መጽሔቶች ላለንበት ዘመን በጣም አስፈላጊ ናቸው። መጽሔቶቹን ማንበብ ያስደስተኛል። ግሩም የሆኑ ርዕሶች ያሏቸውና የእውቀት አድማስን የሚያሰፉ ናቸው። እናንተን በማግኘቴ በጣም ደስተኛ ነኝ። እያከናወናችሁ ላላችሁት መልካም ተግባር ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።”

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ሐዋርያው ጳውሎስ “ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ በቁም ነገር ይመለከቱታል። (ሮሜ 10:14) ወደፊት የይሖዋ ምሥክሮች ቤትህ ሲመጡ ለምን ትንሽ ደቂቃ አታዳምጣቸውም? የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት በመስማት ልትጽናና ትችላለህ።