በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

ስለ አምላክ እውቀት ማካበት ብቻውን ለእርሱ ፍቅር እንዲያድርብን አያደርገንም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች በተሞክሮ እንዳዩት አንድ ሰው ስለ አምላክ ባሕርያት ይበልጥ ባወቀ መጠን ለእርሱ ያለው እውነተኛ ፍቅር ይጨምራል። አምላክ የሚወደውን፣ የሚጠላውንና ከሰዎች የሚፈልገውን ነገር ሲገነዘብ ፍቅሩም ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል።

ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ሲሆን በቃሉ አማካኝነት ራሱን ገልጦልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ለማወቅ ያስችለናል። ከምንወደው ሰው የተላከ ደብዳቤ በጣም እንደሚያስደስተን ሁሉ ስለ ይሖዋ ባሕርያት አዳዲስ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማርን መጠን እንደሰታለን።

ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎታችን ከሚያጋጥመን ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው አንድ ሰው ስለ አምላክ ማወቁ ብቻ ለእርሱ ፍቅር እንዲያድርበት ላያደርገው ይችላል። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩ አንዳንድ አድናቆት የጎደላቸው አይሁዳውያን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ . . . ነገር ግን እናንተን ዐውቃችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ።” (ዮሐንስ 5:39, 42) አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ለዓመታት ቢማሩም ለእርሱ ፍቅር ሳያዳብሩ ይቀራሉ። ምክንያቱ ምንድን ነው? የተማሩትን ነገር ቆም ብለው ስለማያገናዝቡት ነው። በአንጻሩ ደግሞ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሄድ ተመልክተዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ልክ እንደ እኛ እነርሱም የአሳፍን አርዓያ በመከተላቸው ነው። እንዴት?

በአድናቆት ስሜት አሰላስሉ

አሳፍ ለይሖዋ ፍቅር ለማዳበር ልባዊ ፍላጎት ነበረው። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከልቤም ጋር ተጫወትሁ፤ . . . የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤ የጥንት ታምራትህን በእርግጥ አስታውሳለሁ፤ ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።” (መዝሙር 77:6, 11, 12) የአንድ ሰው ልብ ለአምላክ ባለው ፍቅር የሚሞላው መዝሙራዊው እንዳደረገው በይሖዋ ሥራዎች ላይ ሲያሰላስል ነው።

ከዚህም በላይ ይሖዋን ስናገለግል ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች ማስታወስም ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ያስችለናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ ጋር “አብረን የምንሠራ” እንደሆንን ተናግሯል፤ በሥራ ባልደረቦች መካከል ለየት ያለ ወዳጅነት ይፈጠራል። (1 ቆሮንቶስ 3:9) ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የምንናገራቸውን ቃላትና የምናደርጋቸውን ነገሮች ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል፣ ልቡንም ደስ ያሰኙታል። (ምሳሌ 27:11) አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞን ይሖዋ እንዲረዳን ስንጠይቀውና መመሪያ ሲሰጠን ከእኛ ጋር እንደሆነ ስለሚሰማን ለእርሱ ያለን ፍቅር ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል።

ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ ወዳጅነታቸው ይበልጥ ይጠነክራል። በተመሳሳይም ራሳችንን ለእርሱ የወሰንበትን ምክንያት ለይሖዋ ስንነግረው ለእርሱ ያለን ፍቅር እየጠነከረ ይሄዳል። እንዲሁም “አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (ማርቆስ 12:30) ይሖዋን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሐሳባችንና በፍጹም ኃይላችን መውደዳችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ እንችላለን?

ይሖዋን በፍጹም ልባችን መውደድ

መጽሐፍ ቅዱስ ውስጣዊ ማንነታችንን ለመግለጽ በምሳሌያዊው ልብ የሚጠቀም ሲሆን ይህም ፍላጎታችንን፣ ዝንባሌያችንንና ስሜታችንን ያመለክታል። ስለዚህ ይሖዋን በፍጹም ልባችን እንወደዋለን ሲባል ከምንም ነገር በላይ እርሱን ለማስደሰት እንፈልጋለን ማለት ነው። (መዝሙር 86:11) በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ባሕርያት በማንጸባረቅ እንደዚህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ‘ክፉ የሆነውን ሁሉ በመጸየፍና በጎ ከሆነው ነገር ጋር በመቆራኘት’ አምላክን ለመምሰል እንጥራለን።—ሮሜ 12:9

ለአምላክ ያለን ፍቅር ለማንኛውም ነገር ያለንን ስሜት ይነካል። ለምሳሌ፣ ሥራችንን በጣም እንወደውና እንረካበት ይሆናል፤ ሆኖም ልባችን ሙሉ በሙሉ ያረፈው በሥራችን ላይ መሆን ይኖርበታል? በፍጹም። ይሖዋን በፍጹም ልባችን ስለምንወደው የመጀመሪያውን ቦታ የምንሰጠው እርሱን ለማገልገል ነው። በተመሳሳይም ወላጆቻችንን፣ የትዳር ጓደኛችንን እንዲሁም አሠሪያችንን ማስደሰት እንፈልጋለን፤ ሆኖም በዋነኝነት ይሖዋን ለማስደሰት የምንጥር ከሆነ ከልባችን እንደምንወደው እናሳያለን። ደግሞም በልባችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ መያዝ የሚገባው እርሱ ነው።—ማቴዎስ 6:24፤ 10:37

ይሖዋን በፍጹም ነፍሳችን መውደድ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” የሚለው ቃል ሁለንተናችንን እንዲሁም ሕይወታችንን ያመለክታል። በመሆኑም ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን መውደድ ሲባል ሕይወታችንን እርሱን ለማወደስና ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንጠቀምበታለን ማለት ነው።

እርግጥ ነው፣ አንድ ዓይነት ሙያ መማርን፣ የራሳችንን ድርጅት ማቋቋምን ወይም ቤተሰብ መመሥረትን የመሳሰሉ በሕይወታችን ውስጥ ልናከናውናቸው የምንፈልጋቸው ሌሎች ነገሮች ይኖሩ ይሆናል። ያም ቢሆን ግን የምናደርገውን ሁሉ ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ በማከናወንና ሌሎች ጉዳዮች በሕይወታችን ውስጥ ተገቢ ቦታቸውን እንዲይዙ በማድረግ ይሖዋን በፍጹም ነፍሳችን እንደምንወደው እናሳያለን። በዚህ መንገድ ‘ከሁሉ አስቀድመን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እንሻለን።’ (ማቴዎስ 6:33) በፍጹም ነፍስ የሚቀርብ አምልኮ ይሖዋን በቅንዓት በማገልገልም ይገለጻል። የመንግሥቱን መልእክት በቅንዓት በመስበክ፣ በስብሰባዎች ላይ የሚያንጹ ሐሳቦች በመስጠት እንዲሁም ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በመርዳት ይሖዋን እንደምንወደው እናሳያለን። በምናደርገው ሁሉ “የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከልብ በመፈጸም” እንመላለሳለን።—ኤፌሶን 6:6

ኢየሱስ ራሱን በመካድ አምላክን በፍጹም ነፍሱ እንደሚወድደው አሳይቷል። የአምላክን ፈቃድ በማስቀደም ለራሱ ፍላጎት ሁለተኛ ቦታ ሰጥቷል። እንዲሁም “ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” በማለት የእርሱን አርዓያ እንድንኮርጅ አበረታቶናል። (ማቴዎስ 16:24, 25) ራስን መካድ ሲባል ራስን ለይሖዋ መወሰን ማለት ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ እስራኤላዊ ጌታውን ከመውደዱ የተነሳ ለዘላለም ለእርሱ ባሪያ ሆኖ ለመኖር እንደሚስማማ ሁሉ እኛም አምላክን ከመውደዳችን የተነሳ ሕይወታችንን እንሰጠዋለን ማለት ነው። (ዘዳግም 15:16, 17) ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችን እርሱን እንደምንወደው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው።

ይሖዋን በፍጹም ሐሳባችን መውደድ

ይሖዋን በፍጹም ሐሳባችን መውደድ ሲባል የይሖዋን ባሕርያት፣ ዓላማዎቹንና የሚፈልግብንን ነገሮች ለማወቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ማለት ነው። (ዮሐንስ 17:3፤ የሐዋርያት ሥራ 17:11) በማሰብ ችሎታችን ተጠቅመን ሌሎችም ይሖዋን እንዲወድዱት በመርዳትና የማስተማር ችሎታችንን በማሻሻል ለይሖዋ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የልቡናችሁን ወገብ [ታጠቁ]” በማለት መክሯል። (1 ጴጥሮስ 1:13 የ1954 ትርጉም) ከዚህም በላይ ለሌሎች በተለይም ለእምነት ባልንጀሮቻችን አሳቢነት ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን፤ ያሉበትን ሁኔታ እንረዳላቸዋለን እንዲሁም ማበረታቻ ወይም ማጽናኛ ያስፈልጋቸው እንደሆነ ለማስተዋል ንቁ እንሆናለን።

ይሖዋን በፍጹም ሐሳባችን እንደምንወደው የምናሳየው አስተሳሰባችንን ለእርሱ በማስገዛት ነው። ነገሮችን ከእርሱ አመለካከት አንጻር ለመመልከት እንጥራለን፣ ውሳኔ ስናደርግ የእርሱን አስተሳሰብ ግምት ውስጥ እናስገባለን እንዲሁም የእርሱ መንገድ ከሁሉ የተሻለ መሆኑን አምነን እንቀበላለን። (ምሳሌ 3:5, 6፤ ኢሳይያስ 55:9፤ ፊልጵስዩስ 2:3-7) ይሁን እንጂ ለአምላክ ያለንን ፍቅር በማሳየት ረገድ ኃይላችንን ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው?

ይሖዋን በፍጹም ኃይላችን መውደድ

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ኃይላቸውን ወይም ጉልበታቸውን ይሖዋን ለማወደስ ይጠቀሙበታል። (ምሳሌ 20:29፤ መክብብ 12:1) በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች ይሖዋን በፍጹም ኃይላቸው እንደሚወድዱት የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ በአቅኚነት ማለትም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈል ነው። ብዙ እናቶች ልጆቻቸው ትምህርት ቤት በሚሆኑበት ጊዜ በዚህ አገልግሎት ይካፈላሉ። የራሳቸውን ቤተሰቦች ከመንከባከብ በተጨማሪ ለሌሎች እረኝነት የሚያደርጉት ታማኝ ሽማግሌዎችም ይሖዋን በፍጹም ኃይላቸው እንደሚወድዱ ያሳያሉ። (2 ቆሮንቶስ 12:15) ይሖዋ በእርሱ ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ያላቸውን ኃይል ተጠቅመው እርሱን በማወደስ ፍቅራቸውን መግለጽ እንዲችሉ ያበረታቸዋል።—ኢሳይያስ 40:29፤ ዕብራውያን 6:11, 12

ፍቅር ካዳበርነው ያድጋል። እንግዲያው ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችንን እንቀጥል። ይሖዋ ያደረገልንን ነገሮችና በቅንዓት ልናገለግለው የሚገባው ለምን እንደሆነ እናስብ። ፍጽምና የጎደለን የአዳም ልጆች እንደመሆናችን መጠን ‘እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀው’ ነገር ይገባናል የምንለው ባይሆንም እንኳ በሁለንተናችን ይሖዋን እንደምንወደው ልናሳይ እንችላለን። ምንጊዜም እንደዚህ ማድረጋችንን አናቋርጥ!—1 ቆሮንቶስ 2:9

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በድርጊቶቻችን አምላክን እንደምንወደው እናሳያለን