በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ባለኝ ረክቼ መኖሬ እንድጸና አስችሎኛል

ባለኝ ረክቼ መኖሬ እንድጸና አስችሎኛል

የሕይወት ታሪክ

ባለኝ ረክቼ መኖሬ እንድጸና አስችሎኛል

ቤንጃሚን ኢኪቹኩ ኦስዌኬ እንደተናገረው

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሳተፍ ከጀመርኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወላጆቼን ለመጠየቅ ሄድኩ። አባቴ ገና እንዳየኝ አንቆ ይዞ “አንተ ሌባ!” ብሎ ጮኸብኝ። ሰይፉን አውጥቶ በጠፍጣፋው ጎን መታኝ። የመንደራችን ሰዎች ጫጫታውን ሰምተው ወደ ቤታችን መጡ። የሰረቅሁት ነገር ምንድን ነው? እስቲ ልንገራችሁ።

የተወለድኩት በደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ በምትገኘው ኡሙሪያም በምትባል መንደር፣ በ1930 ነበር። ከሰባት ልጆች ውስጥ የመጀመሪያው ነኝ። ከእህቶቼ መካከል ትልቋ ገና በ13 ዓመቷ ሞተች። ወላጆቼ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን አማኞች ሲሆኑ አባቴ ገበሬ፣ እናቴ ደግሞ ችርቻሮ ነጋዴ ነበረች። እማዬ ከመንደራችን 30 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ገበያ ሄዳ የቆርቆሮ ዘይት ትገዛና የዚያኑ ዕለት አመሻሹ ላይ ወደ ቤት ትመለሳለች። ከዚያም ዘይቱን ለመሸጥ በሚቀጥለው ቀን በጠዋት ተነስታ 40 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ባቡር ጣቢያ ትሄዳለች። ተሳካላት ቢባል የምታገኘው ትርፍ ከአንድ ብር ከሰላሣ ሳንቲም የማይበልጥ ሲሆን በዚህ ገንዘብ የሚበላ ነገር ገዛዝታ በዚያው ዕለት ወደ ቤት ትመለሳለች። በ1950 እስከ ሞተችበት ዕለት ድረስ ለ15 ዓመታት ሥራዋ ይኼው ነበር።

ትምህርት የጀመርኩት በተወለድኩባት መንደር ውስጥ በሚገኝ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ቤት ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት ደግሞ ከመንደራችን 35 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ለቤትና ለምግብ እየከፈልኩ ነበር። ወላጆቼ የገንዘብ አቅም ስላልነበራቸው ትምህርቴን አቁሜ ሥራ ለመፈለግ ተገደድሁ። መጀመሪያ ላይ በምዕራብ ናይጄሪያ፣ ሌጎስ የባቡር ጣቢያ ጠባቂ በሆነ ሰው ቤት ከዚያም በሰሜናዊ ናይጄሪያ፣ በካዱና በአንድ የመንግሥት ሠራተኛ ቤት ውስጥ ተቀጥሬ ሠራሁ። በኋላም በመካከለኛው ምዕራብ ናይጄሪያ በምትገኘው ቤኒን ሲቲ ለአንድ ጠበቃ በጸሐፊነት ሠራሁ፤ ቆየት ብሎ ደግሞ በእንጨት መሰንጠቂያ ውስጥ የቀን ሠራተኛ ሆኜ ተቀጠርኩ። በ1953 ከአጎቴ ጋር ለመኖር ወደ ካሜሩን የሄድኩ ሲሆን እርሱም በጎማ እርሻ ውስጥ ሥራ እንዳገኝ ረዳኝ። የማገኘው ደሞዝ በወር 78 ብር ገደማ ነበር። ሥራዬ ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝልኝ ባይሆንም የምበላውን እስካገኘሁ ድረስ ተደስቼ እኖር ነበር።

አንድ ድሃ ሀብት አወረሰኝ

የሥራ ባልደረባዬ የነበረው ሲልቬነስ ኦኬሚሪ የይሖዋ ምሥክር ሲሆን ሣር ስናጭድም ሆነ የጎማ ዛፎቹን ማዳበሪያ ስናሳቅፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ያካፍለኝ ነበር። የሚነግረኝን በጥሞና ባዳምጠውም ያደረግሁት ለውጥ አልነበረም። ይሁንና አጎቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር እንደምገናኝ ሲሰማ ግንኙነቴን እንዳቋርጥ የተቻለውን ሁሉ አደረገ። “ቤንጂ፣ ከአቶ ኦኬሚሪ ጋር ባትገናኝ ይሻልሃል። አንደኛ ነገር ሰውየው ጅሆቫ ነው፤ በዚህ ላይ ደግሞ ያጣ የነጣ ድሃ ነው። ከእርሱ ጋር የገጠመ ሰው መጨረሻው እንደ እርሱ ሆኖ መቅረት ነው” በማለት አስጠነቀቀኝ።

ተቀጥሬ በምሠራበት ድርጅት ከባድ የሆነውን የሥራ ጠባይ መቋቋም ስላልቻልኩ በ1954 መጀመሪያ ላይ ወደ አገሬ ተመለስኩ። በዚያን ጊዜ የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ሥነ ምግባርን በተመለከተ ጥብቅ አቋም ስለነበራት እኔም ከልጅነቴ አንስቶ ለሥነ ምግባር ብልግና ጥላቻ ነበረኝ። ይሁን እንጂ ሁኔታው ተቀይሮ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት በግብዝነት እንደሚኖሩ ሳይ በጣም ተናደድኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች እንደሚከተሉ በአፋቸው ቢናገሩም ተግባራቸው ግን ከዚያ የራቀ ነበር። (ማቴዎስ 15:8) በዚህ ጉዳይ ላይ ከአባቴ ጋር ብዙ ጊዜ ተጨቃጭቀናል፤ በዚህም የተነሳ በመካከላችን ያለው ግንኙነት ሻከረ። አንድ ቀን ማታ ቤቱን ጥዬ ሄድኩ።

የባቡር መስመር በሚያልፍባት ኦሞባ በምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ መኖር ጀመርኩ። እዚያም እንደገና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁ። ባደግሁበት መንደር ውስጥ የማውቃት ፕሪሲለ ኢሲኦቻ “ይህ የመንግሥት ምሥራች” እና ከአርማጌዶን በኋላ የአምላክ አዲስ ዓለም ይመጣል (እንግሊዝኛ) a የተባሉትን ቡክሌቶች ሰጠችኝ። ቡክሌቶቹን በከፍተኛ ጉጉት አነበብኳቸው፤ እውነትን እንዳገኘሁም እርግጠኛ ሆንኩ። የእኛ ቤተ ክርስቲያን ትኩረት የሚሰጠው ለሰዎች ወግ ስለነበረ መጽሐፍ ቅዱስን አልተማርንም። የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፍ ግን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይገኝበታል።

ከእህት ፕሪሲለ ጋር ከተገናኘን ገና አንድ ወር ሳይሞላኝ እርሷና ባለቤቷ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱት መቼ እንደሆነ ጠየቅኋቸው። በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘሁበት ዕለት የቀረበው ትምህርት ምንም አልገባኝም ነበር። የተጠናው የመጠበቂያ ግንብ ትምህርት በሕዝቅኤል ትንቢት ላይ የተጠቀሰው ‘የማጎጉ ጎግ’ ስለሚሰነዝረው ጥቃት የሚያብራራ ነበር። (ሕዝቅኤል 38:1, 2) የሚናገሯቸው አብዛኞቹ ቃላት ለእኔ እንግዳ ነበሩ። ሆኖም ባደረጉልኝ ሞቅ ያለ አቀባበል በጣም ስለተደሰትኩ በቀጣዩ እሁድ ተመልሼ ለመሄድ ወሰንኩ። ለሁለተኛ ጊዜ ስብሰባ ላይ በተገኘሁበት ወቅት ስለ ስብከት ትምህርት ሲሰጥ ሰማሁ። በመሆኑም ለስብከት የሚወጡት መቼ እንደሆነ ፕሪሲለን ጠየቅኋት። በሦስተኛው እሁድ ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ይዤ አብሬያቸው አገልግሎት ወጣሁ። የአገልግሎት ቦርሳም ሆነ የሚበረከቱ ጽሑፎች አልያዝኩም ነበር። ሆኖም እንደ ምሥራቹ ሰባኪ ተቆጥሬ ወሩ መጨረሻ ላይ ያገለገልኩትን ሰዓት ሪፖርት አደረግሁ!

መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ሰው ባይኖርም እንኳ እነ እህት ፕሪሲለ ቤት በሄድኩ ቁጥር የሚያነቡልኝ ጥቅስ እምነቴን ያጠናከረልኝ ሲሆን አንዳንድ ጽሑፎችም ይሰጡኝ ነበር። ታኅሣሥ 11, 1954 በአባ በተካሄደ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። በዚህ ጊዜ አብሬው እየኖርኩና እየሠራሁ የሥራ ልምድ እንዳገኝ ይረዳኝ የነበረው ዘመዴ ምግብም፣ ሥልጠናውንም ከለከለኝ። እስከዚያ ጊዜ ለሠራሁበት ሥራም አምስት ሳንቲም እንኳ አልከፈለኝም፤ ሆኖም ቂም አልያዝኩበትም። ከአምላክ ጋር የግል ዝምድና መመሥረት መቻሌ በራሱ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር። ይህ ዝምድና መጽናኛና የአእምሮ ሰላም አስገኝቶልኛል። በዚያ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የደረሰብኝን ሲሰሙ የእርዳታ እጃቸውን ዘረጉልኝ። እህት ፕሪሲለ እና ባለቤቷ ምግብ ይሰጡኝ የነበረ ሲሆን ሌሎች ደግሞ አንዳንድ ነገሮች መነገድ እንድጀምር ገንዘብ አበደሩኝ። በ1955 አጋማሽ ላይ አንድ ያገለገለ ብስክሌት ገዛሁ፤ መጋቢት 1956 ላይ ደግሞ የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ተበድሬ የነበረውን ገንዘብ ከፈልኩ። ዕቃዎች በመሸጥ የማገኘው ትርፍ በጣም ትንሽ ቢሆንም እንኳ ራሴን ችዬ እንድኖር አስችሎኛል። ይሖዋ ባደረገልኝ ዝግጅት ረክቼ ኖሬያለሁ።

ወንድሞቼንና እህቶቼን “ሰረቅሁ”

ራሴን ችዬ መኖር እንደጀመርኩ ያሳሰበኝ የመጀመሪያው ነገር ወንድሞቼንና እህቶቼን በመንፈሳዊ የመርዳቱ ጉዳይ ነበር። አባዬ ከነበረው ጭፍን ጥላቻና ጥርጣሬ የተነሳ የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ አልተደሰተም። ታዲያ ወንድሞቼና እህቶቼ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲማሩ መርዳት የምችለው እንዴት ነው? ታናሽ ወንድሜን ለመርዳት ባቀረብኩለት ሐሳብ አባዬ በመስማማቱ ኧርነስት እኔ ጋር መጥቶ መኖር ጀመረ። ኧርነስት ወዲያውኑ እውነትን የተቀበለ ከመሆኑም በላይ በ1956 ተጠመቀ። የእርሱ እውነትን መቀበል አባታችንን ይባስ ተቃዋሚ አደረገው። ሆኖም በትዳር ዓለም ውስጥ የነበረችው ታናሽ እህቴም ከባሏ ጋር ወደ እውነት መጣች። የእርሷ ታናሽ እህት የሆነችው ፈሊሺያ ትምህርት ቤት ሲዘጋ እኔ ጋር መጥታ እንድታርፍ አባዬን ስጠይቀው በነገሩ ብዙም ባይደሰትም ፈቀደላት። ፈሊሺያም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።

በ1959 ሦስተኛዋን እህቴ በርኒስን አምጥቼ ከኧርነስት ጋር እንድትኖር ለማድረግ ወደ ወላጆቼ ቤት ሄድኩ። አባዬ ልጆቼን ሰረቅኸኝ ብሎ የደበደበኝ በዚህ ጊዜ ነበር። ይሖዋን ለማምለክ የመረጡት በራሳቸው ፍላጎት እንደሆነ አላስተዋለም ነበር። አባዬ በርኒስን ይዣት እንድሄድ እንደማይፈቅድልኝ ዛተ። ሆኖም የይሖዋ እጅ አጭር ባለመሆኑ በርኒስ በሚቀጥለው ዓመት የትምህርት ቤት እረፍቷን ኧርነስት ጋር ለማሳለፍ መጣች። እርሷም እንደ እህቶቿ እውነትን ተቀብላ ተጠመቀች።

‘ምስጢሩን መማር’

በመስከረም 1957 ልዩ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ፤ ይህም በስብከቱ ሥራ በወር 150 ሰዓት እንዳሳልፍ ይጠይቅብኝ ነበር። እኔና የአገልግሎት ጓደኛዬ ሰንዴይ ኢሮቤላኪ የምንሰብከው በኤቼ፣ አክፑ ናኦቡኦ በሚገኝ ሰፊ ክልል ውስጥ ነበር። በዚያ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገኘንበት የወረዳ ስብሰባ ላይ ከቡድናችን 13 ሰዎች ተጠመቁ። በአሁኑ ጊዜ በክልሉ 20 ጉባኤዎች ተቋቁመው በማየታችን በጣም ተደስተናል!

በ1958 በአባ ኢስት ጉባኤ የዘወትር አቅኚ ከሆነችው ከክሪስትያና አዙኢኬ ጋር ተዋወቅሁኝና የአገልግሎት ቅንዓቷ በጣም ማረከኝ። ከዚያም በዚያው ዓመት ታኅሣሥ ላይ ተጋባን። በ1959 መጀመሪያ ላይ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ፤ ይህም ጉባኤዎችን መጎብኘትንና መንፈሳዊ ወንድሞቻችንን ማበረታታትን ይጠይቃል። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እስከ 1972 ድረስ እኔና ባለቤቴ በምሥራቃዊና በማዕከላዊ ምዕራብ ናይጄሪያ የሚገኙትን ጉባኤዎች በሙሉ ጎብኝተናል ማለት ይቻላል።

ጉባኤዎቹ የሚገኙት በጣም ተራርቀው ሲሆን ከቦታ ቦታ ለመጓጓዝ በዋነኝነት የምንጠቀመው በብስክሌት ነበር። በትልልቅ ከተማዎች ውስጥ ጉባኤዎችን ስንጎበኝ ወንድሞች ታክሲ ተኮናትረው ወደ ቀጣዩ ጉባኤ ይሸኙን ነበር። አንዳንድ ጊዜ የምናድረው ወለሉ አፈር በሆነና ኮርኒስ በሌለው ክፍል ውስጥ ሲሆን የምንተኛው ደግሞ ከቃጫ በተሠራ አልጋ ላይ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ምንጣፍ የለበሰ የሣር ፍራሽ ላይ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ባዶ አልጋ ላይ እንተኛ ነበር። የሚቀርብልን ምግብ ብዛቱም ሆነ ጥራቱ አሳስቦን አያውቅም። በትንሽ ነገር ረክቶ መኖር ስለለመድን ምግብ አናማርጥም ነበር፤ ይህም ወንድሞችን አስደስቷቸዋል። በዚያን ጊዜ አንዳንድ ከተሞች መብራት ስላልነበራቸው ፋኖስ አይለየንም። አንዳንድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም እንኳ ጉባኤዎችን ስንጎበኝ ብዙ አስደሳች ጊዜያት አሳልፈናል።

ባሳለፍናቸው ዓመታት፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “ምግብና ልብስ ካለን፣ ያ ይበቃናል” ሲል የሰጠው ምክር በጣም ተገቢ እንደሆነ ተገንዝበናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:8) ጳውሎስ ካሳለፈው መከራ ባለው ረክቶ የመኖርን ምስጢር ተምሯል። ምስጢሩ ምንድን ነው? እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብም፣ ባገኝም ሆነ ባጣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ።” እኛም ይህን ምስጢር ተምረናል። ከዚህም በላይ ጳውሎስ “ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ [በአምላክ] ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:12, 13) የእነዚህን ቃላት እውነተኝነት በራሳችን ሕይወት ተመልክተናል! እርካታ የተሞላበት ሕይወት፣ አስደሳች ክርስቲያናዊ አገልግሎትና የአእምሮ ሰላም አግኝተናል።

በቤተሰብ መልክ ጉባኤዎችን ማገልገል

በ1959 መገባደጃ ላይ የመጀመሪያ ልጃችን ጆኤል፣ በ1962 ደግሞ ሁለተኛ ልጃችን ሳሙኤል ተወለደ። እኔና ክርስቲያና ጉባኤዎችን መጎብኘታችንን የቀጠልን ሲሆን ልጆቹም አብረውን ይሄዱ ነበር። በ1967 የናይጄሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ። የማያባራ የአየር ድብደባ ስለነበር ትምህርት ቤቶች ተዘጉ። ባለቤቴ አብራኝ ማገልገል ከመጀመሯ በፊት አስተማሪ ስለነበረች በጦርነቱ ወቅት ልጆቹን ቤት ውስጥ ታስተምራቸው ጀመር። ሳሙኤል በስድስት ዓመቱ ማንበብና መጻፍ ይችል ነበር። ከጦርነቱ በኋላ ትምህርት ቤት ሲገባ እኩዮቹን በሁለት ክፍል ቀደማቸው።

በወረዳ ሥራ ላይ እያለን ልጆችን ማሳደግ በጣም እንደሚከብደን በወቅቱ አልተገነዘብንም። ሆኖም በ1972 ልዩ አቅኚ ሆነን መመደባችን አንድ ቦታ እንድንቀመጥና ለቤተሰባችን መንፈሳዊነት አስፈላጊውን ትኩረት እንድንሰጥ ስላስቻለን በጣም ጠቅሞናል። ለልጆቻችን ባላቸው ነገር ረክተው የመኖርን ጠቀሜታ ያስተማርናቸው ገና ትንንሾች እያሉ ነው። በ1973 ሳሙኤል የተጠመቀ ሲሆን ጆኤል ደግሞ በዚያው ዓመት የዘወትር አቅኚ ሆነ። ሁለቱም ልጆቻችን ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ክርስቲያን ሴቶች አግብተው ልጆቻቸውን በእውነት ውስጥ እያሳደጉ ናቸው።

የእርስ በርስ ጦርነት ያስከተለው ሰቆቃ

የእርስ በርስ ጦርነቱ በፈነዳበት ወቅት በኦኒቻ ከቤተሰቤ ጋር ሆኜ አንድ ጉባኤ እየጎበኘሁ ነበር። ጦርነቱ ቁሳዊ ነገሮችን መሰብሰብም ሆነ በሀብት መታመን ከንቱ መሆኑን ይበልጥ እንድንገነዘብ አስቻለን። ሰዎች ብዙ ዋጋ የሚያወጣ ንብረታቸውን በየመንገዱ ጥለው ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሯሯጡ አይቻለሁ።

ጦርነቱ እየተባባሰ ሲሄድ ጤናማ የሆኑ ወንዶች በሙሉ ለውትድርና እንዲመዘገቡ አዋጅ ወጣ። ብዙ ወንድሞች ለመመዝገብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ተደበደቡ። ከቦታ ቦታ እንደልብ መንቀሳቀስ አቃተን። የምግብ እጥረት በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከተለ። በ60 ሳንቲም ይገዛ የነበረው ግማሽ ኪሎ ካሳቫ ዋጋው ጨምሮ 122 ብር ደረሰ። የአንድ ኩባያ ጨው ዋጋ ደግሞ ከ70 ብር ወደ 365 ብር ወጣ። ወተት፣ ቅቤና ስኳር የሚባል ነገር ጭራሽ ጠፋ። በሕይወት ለመቆየት ስንል ጥሬ ፓፓያ ከወቀጥን በኋላ ከካሳቫ ዱቄት ጋር ለውሰን መብላት ጀመርን። ከዚህ በተጨማሪ ፌንጣ፣ የካሳቫ ልጣጭ፣ ሙጃ እንዲሁም ያገኘነውን ቅጠል ሁሉ በልተናል። ሥጋ ማግኘት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር በመሆኑ ለልጆቹ እንሽላሊት እየያዝኩ አመጣ ነበር። ሁኔታው ምንም ያህል አስከፊ ቢሆንም ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልገንን አሟልቶልናል።

ይሁን እንጂ ጦርነቱ ያስከተለው መንፈሳዊ ረሃብ ከዚያ ይበልጥ አስከፊ ነበር። አብዛኞቹ ወንድሞች ከጦርነት ቀጠናው ሸሽተው ወደ ጫካ ወይም ወደ ሌሎች መንደሮች የተሰደዱ ሲሆን በዚህ መሃል በርካታ ጽሑፎችን አንዳንዶቹም የነበራቸውን በሙሉ አጥተዋል። ከዚህ በተጨማሪ የመንግሥት ወታደሮች መንገዶችን በመዝጋታቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ወደ ቢያፍራ ማስገባት አልተቻለም። አብዛኞቹ ጉባኤዎች መሰብሰባቸውን ለመቀጠል ጥረት ቢያደርጉም እንኳ ከቅርንጫፍ ቢሮው የሚላከውን መመሪያ ማግኘት ስላልቻሉ ወንድሞች በመንፈሳዊ ተጎዱ።

መንፈሳዊ ረሃብን መቋቋም

ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ለጉባኤዎች የሚያደርጉትን ጉብኝት ለመቀጠል የቻሉትን ሁሉ አድርገዋል። ብዙ ወንድሞች ከሚኖሩባቸው ከተሞች ሸሽተው ስለነበር እነርሱን ባሉበት ቦታ ለማግኘት ፍለጋ ጀመርኩ። በአንድ ወቅት ባለቤቴንና ልጆቼን ለደኅንነታቸው የማያሰጋ ቦታ ላይ ትቼ ወንድሞችን ፍለጋ ለስድስት ሳምንት ያህል ወደተለያዩ መንደሮችና ጫካዎች ብቻዬን ተጓዝኩ።

በኦግቡንኮ የሚገኘውን ጉባኤ እየጎበኘሁ ሳለ ኦኪግዌ ክልል ውስጥ፣ ኢሱኦቺ በሚባል ቦታ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸውን ሰማሁ። ስለዚህ በዚያ አካባቢ የሚገኙ ወንድሞች ኡምዋኩ መንደር ውስጥ በሚገኘው የእርሻ ቦታ ተሰብስበው እንዲቆዩኝ መልእክት ላክሁባቸው። እኔና አንድ በዕድሜ የገፉ ወንድም በብስክሌት 15 ኪሎ ሜትር ተጉዘን እርሻው ቦታ ስንደርስ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ 200 የይሖዋ ምሥክሮች ተሰብስበው አገኘን። በሌላ ጊዜ አንዲት አቅኚ፣ ሎማራ ወደሚባል ጫካ ይዛኝ ሄደችና በዚያ ተሸሽገው የነበሩ ወደ አንድ መቶ ገደማ ወንድሞችን ማግኘት ቻልኩ።

ላውሬንስ ኡግዌቡ በጦርነት በተጎዳችው የኦዌረሪ ከተማ ከሚኖሩት ደፋር ወንድሞች መካከል አንዱ ሲሆን ኦሃጂ በሚባለው አካባቢ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች መኖራቸውን ነገረኝ። አካባቢውን ወታደሮች ተቆጣጥረውት ስለነበር ወንድሞች ከቦታ ቦታ በነፃነት መንቀሳቀስ አይችሉም ነበር። ከዚህ ወንድም ጋር ጨለማን ተገን አድርገን በብስክሌት ወደ ኦሃጂ የተጓዝን ሲሆን በአንድ ወንድም ግቢ ውስጥ 120 ወንድሞችና እህቶች ተሰብስበው አገኘን። በዚያ አጋጣሚ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮችንም ተደብቀው የነበሩበት ቦታ ድረስ ሄደን ጠየቅናቸው።

ወንድም አይዛክ ዋግዉ ለሕይወቱ ሳይሳሳ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሌሎች ወንድሞች ጋር አድርሶኛል። በኤግቡ ኤቻ ተሰብስበው ከነበሩ ከ150 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘት እንድችል የኦታሚሪን ወንዝ በታንኳ አሻገረኝ። በዚያ ከነበሩት ወንድሞች አንዱ እንዲህ አለ፦ “እንደ ዛሬዋ ቀን ተደስቼ አላውቅም! በሕይወት እያለሁ ከወረዳ የበላይ ተመልካች ጋር እገናኛለሁ የሚል ተስፋ አልነበረኝም። በዚህ ጦርነት መሃል ብሞት እንኳ አይቆጨኝም።”

ለውትድርና የመታፈስ አደጋ ተደቅኖብኝ ነበር፤ ሆኖም ይሖዋ ብዙ ጊዜ ሰውሮኛል። አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ 250 ከሚያክሉ ወንድሞች ጋር ያካሄድኩትን ስብሰባ ጨርሼ ወዳረፍኩበት ቤት እየተመለስኩ ሳለ ወታደሮች ኬላ ላይ አስቆሙኝ። “የሠራዊቱ አባል ያልሆንከው ለምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁኝ የአምላክ መንግሥት ሰባኪ መሆኔን ነገርኳቸው። ሆኖም እንደማይለቁኝ ስለገባኝ በልቤ አጭር ጸሎት ካቀረብኩ በኋላ አዛዡን “እባክህ ልቀቀኝ” አልኩት። በነገሩ በመገረም “እህ፣ ልቀቁኝ ነው እንዴ የምትለው?” አለኝ። እኔም “አዎን፣ ልቀቁኝ” አልኩት፤ እሱም “እሺ መሄድ ትችላለህ” አለኝ። የተቀሩት ወታደሮች አንድም ቃል አልተነፈሱም።—መዝሙር 65:1, 2

ባለን ረክተን መኖራችን ተጨማሪ በረከት አስገኝቶልናል

ጦርነቱ በ1970 ካበቃ በኋላ በወረዳ ሥራ ማገልገሌን ቀጠልኩ። ጉባኤዎቹን በአዲስ መልክ በማደራጀት ሥራ መካፈል ትልቅ መብት ነበር። ከዚያም እኔና ክርስቲያና እስከ 1976 ድረስ በልዩ አቅኚነት ስናገለግል ቆይተን በዚያው ዓመት እንደገና የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። በዓመቱ አጋማሽ ላይ በአውራጃ ሥራ እንዳገለግል ተመደብኩ። ከሰባት ዓመታት በኋላ እኔና ባለቤቴ ናይጄሪያ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተጠራን፤ እስካሁን ድረስ በዚያ እያገለገልን ነው። በቅርንጫፍ ቢሮው ማገልገላችን በእርስ በርስ ጦርነቱ ወቅትም ሆነ በሌሎች ጊዜያት ከምናውቃቸውና አሁንም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር እንደገና የመገናኘት አጋጣሚ ሰጥቶናል፤ ይህም ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል።

አብረን ባሳለፍናቸው ዓመታት ሁሉ ክርስቲያና ጥሩ ረዳትና ታማኝ አጋር ሆናኛለች። ከ1978 ጀምሮ ካለባት የጤና ችግር ጋር ለመኖር ብትገደድም አዎንታዊ አመለካከቷና የመንፈስ ጥንካሬዋ በኃላፊነቴ እንድቀጥል ረድቶኛል። “ታሞ ባለበት ዐልጋ ላይ እግዚአብሔር ይንከባከበዋል” የሚሉት የመዝሙራዊው ቃላት ትክክል መሆናቸውን ማየት ችለናል።—መዝሙር 41:3

አምላክን በማገልገል ያሳለፍኳቸውን ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ለሰጠኝ አስደናቂ በረከቶች ይሖዋን ከልብ አመሰግነዋለሁ። ይሖዋ ባደረገልኝ ነገር ረክቼ መኖሬ ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልኛል ብዬ መናገር እችላለሁ። ወንድሞቼና እህቶቼ እንዲሁም ልጆቼ ከነቤተሰባቸው ከእኔና ከባለቤቴ ጋር ይሖዋን ሲያገለግሉ ማየት ወደር የሌለው በረከት ነው። ይሖዋ አርኪና ትርጉም ያለው ሕይወት እንድኖር አስችሎኛል፤ ጎደለኝ የምለው ነገር የለም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ። ሁለቱም መታተም አቁመዋል።

[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ወንድሞች መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ ያስቻለ ወሳኝ ዝግጅት

በ1960ዎቹ አጋማሽ በሰሜንና በምሥራቅ ናይጄሪያ በሚገኙ ጎሳዎች መካከል የተፈጠረ የከረረ ጥላቻ ሁከት፣ ዓመፅ፣ ሥርዓት አልበኝነትና የጎሳ ግጭት አስከተለ። ይህ ክስተት በግጭቱ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ለሚፈልጉት የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ፈተና ሆነባቸው። ወደ 20 የሚያህሉ የተገደሉ ሲሆን አብዛኞቹ ንብረታቸውን በሙሉ አጥተዋል።

ግንቦት 30, 1967 ላይ በስተ ምሥራቅ የሚገኙት የናይጄሪያ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥት ተገንጥለው የቢያፍራን ሪፑብሊክ አቋቋሙ። የፌዴራሉ ሠራዊት ወደ ቦታው ተንቀሳቅሶ ከቢያፍራ መውጣትም ሆነ ወደዚያ መግባት እንዳይቻል ከበባ አካሄደ። ይህን ተከትሎ ለብዙ ደም መፋሰስ ምክንያት የሆነ ከባድ የእርስ በርስ ጦርነት ፈነዳ።

በቢያፍራ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ገለልተኛ አቋም መያዛቸው የጥቃት ዒላማ አደረጋቸው። ጋዜጦች በምሥክሮቹ ላይ የሚሰነዝሩት ከባድ ነቀፋ በሕዝቡ ዘንድ እንዲጠሉ አደረጋቸው። ይሁን እንጂ ይሖዋ ሕዝቦቹ መንፈሳዊ ምግብ የሚያገኙበትን ዝግጅት አድርጓል። እንዴት?

በ1968 መጀመሪያ ላይ ሁለት የመንግሥት ሠራተኞች፣ አንደኛው በአውሮፓ ሌላው ደግሞ ቢያፍራ በሚገኝ አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ተሰጣቸው። እነዚህ ሁለት ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ። የተሰጣቸው የሥራ ምድብ ቢያፍራና የተቀረው ዓለም ሊገናኙ በሚችሉበት ብቸኛ መስመር ሁለት ጫፎች ላይ እንዲቀመጡ አስቻላቸው። እነዚህ ሁለት ምሥክሮች ከባድ ችግር ሊያስከትልባቸው የሚችል ቢሆንም እንኳ ወደ ቢያፍራ መንፈሳዊ ምግብ ለማስገባት ፈቃደኞች ሆነዋል። ከዚህ በተጨማሪ በችግር ላይ ለነበሩት ወንድሞቻችን የእርዳታ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ጦርነቱ በ1970 አስካበቃበት ጊዜ ድረስ ሁለቱ ወንድሞች በዚህ ወሳኝ ዝግጅት አማካኝነት ወንድሞችን ሲረዱ ቆይተዋል። አንደኛው ወንድም “ይህ ዝግጅት ሰዎች ሊያቅዱ ከሚችሉት ከማንኛውም ነገር በላይ ነው” ሲል ተናግሯል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1956

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1965 ከልጆቻችን ከጆኤልና ከሳሙኤል ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በቤተሰብ መልክ ይሖዋን ማገልገል እንዴት ያለ በረከት ነው!

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ እኔና ክርስቲያና ናይጄሪያ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እናገለግላለን