በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ታማኙ ባሪያ’ ፈተናውን አለፈ!

‘ታማኙ ባሪያ’ ፈተናውን አለፈ!

‘ታማኙ ባሪያ’ ፈተናውን አለፈ!

“ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶአልና።”—1 ጴጥሮስ 4:17

1. ኢየሱስ ‘ባሪያውን’ ሲመረምረው እንዴት ሆኖ አገኘው?

 በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተከበረው የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ኢየሱስ በተገቢው ጊዜ ‘ለቤተ ሰዎቹ’ ምግብ የሚያቀርብ አንድ “ባሪያ” ሾሞ ነበር። በ1914 ኢየሱስ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ሲይዝ ይህ ባሪያ የሚመረመርበት ጊዜ ደረሰ። በቡድን ደረጃ ‘ባሪያውን’ “ታማኝና ልባም” ሆኖ ያገኘው ሲሆን “ባለው ሁሉ ላይ” ሾመው። (ማቴዎስ 24:45-47 የ1954 ትርጉም) ይሁን እንጂ ታማኝም ሆነ ልባም ሆኖ ያልተገኘ አንድ ሌላ ባሪያ ነበር።

“ያ ክፉ ባሪያ”

2, 3. ‘የክፉው ባሪያ’ አባላት አስቀድሞ የየትኛው ቡድን አባላት ነበሩ? ክፉ ባሪያ የሆኑትስ እንዴት ነው?

2 ኢየሱስ ስለ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከተናገረ በኋላ ስለ አንድ ክፉ ባሪያም ተናግሮ ነበር። እንዲህ አለ፦ “ያ ክፉ ባሪያ ግን፦ ጌታዬ እስኪመጣ ይዘገያል ብሎ በልቡ ቢያስብ፣ ባልንጀሮቹን ባሮች ሊመታ ቢጀምር ከሰካሮችም ጋር ቢበላና ቢጠጣ፣ የዚያ ባሪያ ጌታ ባልጠበቃት ቀን ባላወቃትም ሰዓት ይመጣል፣ ከሁለትም ይሰነጥቀዋል፣ እድሉንም ከግብዞች ጋር ያደርግበታል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:48-51 የ1954 ትርጉም) “ያ ክፉ ባሪያ” የሚለው አገላለጽ ኢየሱስ ቀደም ሲል ስለ ታማኝና ልባም ባሪያ የተናገረውን ሐሳብ ያስታውሰናል። አዎን፣ የዚህ “ክፉ ባሪያ” አባላት በአንድ ወቅት የታማኙ ባሪያ ክፍል ነበሩ። a ታዲያ “ክፉ ባሪያ” የሆኑት እንዴት ነው?

3 ከ1914 በፊት አብዛኞቹ የታማኙ ባሪያ ክፍል አባላት በዚያ ዓመት በሰማይ ከሙሽራው ጋር እንገናኛለን ብለው በእጅጉ ተስፋ አድርገው ነበር። ሆኖም እንደጠበቁት አልሆነም። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ብዙዎቹ ቅር የተሰኙ ሲሆን ጥቂቶቹ ደግሞ በጣም ተበሳጩ። ከእነዚህም አንዳንዶቹ የቀድሞ ወንድሞቻቸውን በቃላት ‘መምታት’ የጀመሩ ከመሆኑም በላይ ‘ከሰካራሞች’ ጋር ማለትም እንደ ሕዝበ ክርስትና ካሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ጋር ተባበሩ።—ኢሳይያስ 28:1-3፤ 32:6

4. ኢየሱስ ‘ክፉውን ባሪያና’ የእርሱን ዓይነት መንፈስ ያሳዩትን ምን ያደርጋቸዋል?

4 እነዚህ ቀድሞ ክርስቲያን የነበሩ ሰዎች የኋላ ኋላ ‘የክፉው ባሪያ’ አባላት የሆኑ ሲሆን በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ‘ከሁለት ሰንጥቋቸዋል።’ እንዴት? በእርሱ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነትና ወደ ሰማይ የመሄድ መብታቸውን አጥተዋል። ወዲያውኑ ግን አላጠፋቸውም። ከዚያ በፊት ከክርስቲያን ጉባኤ ‘ውጭ ወዳለው ጨለማ’ ተጥለው ‘እያለቀሱና ጥርሳቸውን እያፋጩ’ ለተወሰነ ጊዜ ይቆያሉ። (ማቴዎስ 8:12) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ሌሎች ጥቂት የተቀቡ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ መጥፎ መንፈስ በማንጸባረቅ ‘የክፉው ባሪያ’ ክፍል መሆናቸውን አሳይተዋል። ‘ከሌሎች በጎች’ መካከልም አንዳንዶቹ የእነርሱን የክህደት ጎዳና ተከትለዋል። (ዮሐንስ 10:16) እንደነዚህ ያሉት የክርስቶስ ጠላቶች በሙሉ ‘በውጭ ወዳለው መንፈሳዊ ጨለማ ይጣላሉ።’

5. ‘ከክፉው ባሪያ’ በተቃራኒ የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት ፈተና ሲያጋጥማቸው ምን አደረጉ?

5 የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት ልክ እንደ ‘ክፉው ባሪያ’ ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሟቸው ነበር። ይሁን እንጂ እንደ ክፉው ባሪያ ከመመረር ይልቅ አንዳንድ ማስተካከያዎችን አደረጉ። ለይሖዋና ለወንድሞቻቸው የነበራቸው ፍቅር በእጅጉ ተጠናከረ። በዚህም ምክንያት ሁከት በነገሠበት በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ “የእውነት ዓምድና መሠረት” ሊሆኑ ችለዋል።—1 ጢሞቴዎስ 3:15፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1

ልባምና ሰነፍ ቆነጃጅት

6. (ሀ) ኢየሱስ የታማኙን ባሪያ ልባምነት በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው? (ለ) ከ1914 በፊት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን መልእክት ያውጁ ነበር?

6 ኢየሱስ ስለ ‘ክፉው ባሪያ’ ከተናገረ በኋላ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታማኝና ልባም ሆነው ሲገኙ ሌሎቹ ግን የማይሆኑት ለምን እንደሆነ ለማስረዳት ሁለት ምሳሌዎችን ተናገረ። b ልባም መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ ሲያስረዳ እንዲህ አለ፦ “በዚያን ጊዜ መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ የወጡ አሥር ቈነጃጅትን ትመስላለች። ከእነርሱም አምስቱ ሰነፎች አምስቱም ልባሞች ነበሩ። ሰነፎቹ መብራታቸውን ይዘው ከእነርሱ ጋር ዘይት አልያዙምና፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በማሰሮአቸው ዘይት ያዙ።” (ማቴዎስ 25:1-4 የ1954 ትርጉም) አሥሩ ቆነጃጅት ከ1914 በፊት የነበሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች ያስታውሱናል። እነዚህ ክርስቲያኖች ሙሽራው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣበት ጊዜ እንደቀረበ ተገንዝበው ነበር። ስለሆነም “የአሕዛብ ዘመን” በ1914 እንደሚፈጸም በድፍረት በመስበክ ሙሽራውን ‘ሊቀበሉት ወጡ።’—ሉቃስ 21:24

7. በመንፈስ የተቀቡት ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሁኔታ ‘የተኙት’ መቼና ለምንድን ነበር?

7 እውነትም እንደጠበቁት የአሕዛብ ዘመን በ1914 አበቃ። በዚሁ ዓመት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት መግዛት ጀመረ። እርግጥ ይህ የሆነው በሰማይ ነበር። በምድር ላይ ግን በትንቢት የተነገረው ‘ወዮታ’ መድረስ ጀመረ። (ራእይ 12:10, 12) ፈተናው የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። ነገሮችን ሙሉ በሙሉ ያልተገነዘቡት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ሙሽራው የዘገየ’ መሰላቸው። በሁኔታው ግራ ስለተጋቡና ከዓለም ከባድ ተቃውሞ ስለገጠማቸው እንቅስቃሴያቸው በአጠቃላይ የተዳከመ ሲሆን የስብከት ሥራቸውም የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። በምሳሌው ላይ የተጠቀሱት ቆነጃጅትና የኢየሱስ ሐዋርያት ሞተው ካለቁ በኋላ የተነሱት ታማኝ ያልሆኑ ክርስቲያን ነን ባዮች እንዳደረጉት በመንፈሳዊ ሁኔታ “እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።”—ማቴዎስ 25:5፤ ራእይ 11:7, 8፤ 12:17

8. ሙሽራው ከመምጣቱ በፊት ምን ነገር ተከናውኖ ነበር? ቅቡዓን ክርስቲያኖችስ ምን የሚያደርጉበት ጊዜ ደርሶ ነበር?

8 ከዚያም በ1919 አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ምሳሌው እንዲህ ይላል፦ “እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ ሙሽራው ይመጣል፣ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቈነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ።” (ማቴዎስ 25:6, 7 የ1954 ትርጉም) ሁኔታዎች ተስፋ አስቆራጭ ይመስሉ በነበረበት ወቅት ከእንቅልፋቸው እንዲነቁ ጥሪ ቀረበላቸው! በ1918 “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” የሆነው ኢየሱስ የአምላክን ጉባኤ ለመመርመርና ለማጥራት ወደ ይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ መጣ። (ሚልክያስ 3:1) በዚህ ጊዜ የተቀቡት ክርስቲያኖች ወደ ቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ ወጥተው ሊቀበሉት ይገባ ነበር። አዎን፣ ወቅቱ ብርሃናቸውን ‘የሚያበሩበት’ ጊዜ ነበር።—ኢሳይያስ 60:1፤ ፊልጵስዩስ 2:14, 15

9, 10. በ1919 አንዳንድ ክርስቲያኖች “ልባም” ሌሎቹ ደግሞ “ሰነፎች” የነበሩት ለምንድን ነው?

9 ይሁን እንጂ በምሳሌው ላይ አንዳንዶቹ ቆነጃጅት ችግር አጋጥሟቸው እንደነበር ተጠቅሷል። ኢየሱስ ሲቀጥል እንዲህ አለ፦ “ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው።” (ማቴዎስ 25:8 የ1954 ትርጉም) መብራቶቹ ያለ ዘይት ብርሃን ሊሰጡ አይችሉም። በመሆኑም እዚህ ላይ የተጠቀሰው ዘይት እውነተኛ አምላኪዎች ብርሃን እንዲያበሩ የሚያስችላቸውን በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነትና ቅዱስ መንፈሱን ያስታውሰናል። (መዝሙር 119:130፤ ዳንኤል 5:14) ከ1919 በፊት ልባሞቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሁኔታ ለጊዜው ተዳክመው የነበረ ቢሆንም አምላክ ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግባቸው ለማወቅ ትጋት የታከለበት ጥረት ያደርጉ ነበር። በመሆኑም ብርሃን እንዲያበሩ ጥሪ ሲቀርብላቸው ዝግጁዎች ነበሩ።—2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ ዕብራውያን 10:24, 25

10 አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ግን ከሙሽራው ጋር ለመሆን አጥብቀው ቢፈልጉም መሥዋዕትነት ለመክፈልም ሆነ የሚፈለግባቸውን ጥረት ለማድረግ ራሳቸውን አላቀረቡም። በመሆኑም ወንጌሉን በመስበኩ ሥራ ንቁ ተሳትፎ ሊያደርጉበት የሚገባ ጊዜ ሲደርስ ዝግጁዎች አልነበሩም። (ማቴዎስ 24:14) እንዲያውም ኃላፊነታቸውን በቅንዓት ይወጡ የነበሩትን ባልንጀሮቻቸውን ዘይት በመጠየቅ እነርሱንም ሊያዳክሟቸው ሞከሩ። ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ ልባሞቹ ቆነጃጅት ምን አደረጉ? “ያለን ዘይት ለእኛም ለእናንተም ላይበቃ ስለሚችል፤ ሄዳችሁ ከሻጮች ለራሳችሁ ግዙ” አሏቸው። (ማቴዎስ 25:9) በተመሳሳይም በ1919 የነበሩት ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብርሃን የማብራት ብቃታቸውን ሊያዳክምባቸው የሚችል ማንኛውንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች አልነበሩም። በዚህም ፈተናውን አልፈዋል።

11. ሰነፎቹ ቆነጃጅት መጨረሻቸው ምን ሆነ?

11 ኢየሱስ ምሳሌውን ሲደመድም እንዲህ አለ፦ “ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፣ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፣ ደጁም ተዘጋ። በኋላም ደግሞ የቀሩቱ ቈነጃጅት መጡና፦ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን አሉ። እርሱ ግን መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፣ አላውቃችሁም አለ።” (ማቴዎስ 25:10-12 የ1954 ትርጉም) አዎን፣ አንዳንዶች ሙሽራውን ለመቀበል ዝግጁዎች አልነበሩም። በመሆኑም ፈተናውን ማለፍ ስላልቻሉ በሰማይ በተደረገው ሠርግ ታዳሚዎች ለመሆን የነበራቸውን መብት አጥተዋል። እንዴት የሚያሳዝን ነው!

የመክሊቱ ምሳሌ

12. (ሀ) ኢየሱስ ታማኝነትን ለማብራራት ምን ምሳሌ ተጠቀመ? (ለ) “ወደ ሌላ አገር” የሄደው ሰው ማን ነበር?

12 ኢየሱስ ልባም መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በምሳሌ ካስረዳ በኋላ ስለ ታማኝነት ደግሞ ሲናገር እንዲህ አለ፦ “ወደ ሌላ አገር የሚሄድ ሰው ባሮቹን ጠርቶ ያለውን ገንዘብ እንደ ሰጣቸው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ፣ ለአንዱ አምስት መክሊት ለአንዱ ሁለት ለአንዱም አንድ ሰጠና ወደ ሌላ አገር ወዲያው ሄደ።” (ማቴዎስ 25:14, 15 የ1954 ትርጉም) በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ኢየሱስ ራሱ ሲሆን “ወደ ሌላ አገር” የሄደው በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት ነበር። ከማረጉ በፊት ግን “ያለውን ገንዘብ” ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ በአደራ ሰጥቷቸዋል። እንዴት?

13. ኢየሱስ ሰፊ የአገልግሎት መስክ ያዘጋጀውና ‘ለባሪያዎቹ’ እንዲነግዱ ኃላፊነት የሰጣቸው እንዴት ነው?

13 ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት በመላው የእስራኤል ምድር የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ሰፊ የአገልግሎት ክልል አዘጋጀ። (ማቴዎስ 9:35-38) ከዚያም “ወደ ሌላ አገር” ከመሄዱ በፊት “ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” በማለት ይህን የአገልግሎት ክልል ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ በአደራ ሰጣቸው። (ማቴዎስ 28:18-20) በዚህ መንገድ ኢየሱስ እስከሚመለስበት ጊዜ ድረስ ‘እያንዳንዳቸው እንደ ዓቅማቸው’ እንዲነግዱ ‘ለባሪያዎቹ’ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል።

14. ሁሉም ‘በንግዱ’ ሥራ እኩል ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማይጠበቅባቸው ለምንድን ነው?

14 “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ” የሚለው አባባል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ሁሉም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ሁኔታ ወይም ችሎታ እንዳልነበራቸው ይጠቁማል። እንደ ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ ሁኔታቸው ይፈቅድላቸው ነበር። ሌሎች ደግሞ የነበሩበት ሁኔታ እንቅስቃሴያቸውን በእጅጉ ይገድበው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ ክርስቲያኖች የሌሎች ባሪያዎች የነበሩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በጤና እክልና በዕድሜ መግፋት የሚቸገሩ ወይም የቤተሰብ ኃላፊነቶች ያሏቸው ነበሩ። እርግጥ፣ አንዳንድ የጉባኤ ኃላፊነቶች ለሁሉም ደቀ መዛሙርት የተሰጡ አልነበሩም። በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያን ሴቶችና አንዳንድ ወንዶች በጉባኤ ውስጥ የማስተማር ኃላፊነት አልነበራቸውም። (1 ቆሮንቶስ 14:34፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ያዕቆብ 3:1) ቢሆንም ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን በመንፈስ የተቀቡ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት በሙሉ ወንድ ሴት ሳይባል ሁኔታቸውንና በክርስቲያናዊው አገልግሎት የሚያገኟቸውን አጋጣሚዎች በሚገባ በመጠቀም ‘በንግዱ’ ሥራ እንዲካፈሉ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። በጊዜያችን የሚገኙት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ ያደርጋሉ።

የምርመራው ጊዜ ጀመረ!

15, 16. (ሀ) ጌታው ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ የተሳሰበው መቼ ነው? (ለ) ታማኝ ሆነው ለተገኙት ባሪያዎች ‘በንግዱ’ ሥራ ምን ተጨማሪ ኃላፊነቶች ተሰጣቸው?

15 ምሳሌው ሲቀጥል እንዲህ ይላል፦ “ከብዙ ዘመንም በኋላ የእነዚያ ባሮች ጌታ መጣና ተቈጣጠራቸው።” (ማቴዎስ 25:19 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ በ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ካረገ ከረጅም ጊዜ በኋላ ማለትም በ1914 ንጉሣዊ ሥልጣኑን ያዘ። ከዚያም ሦስት ዓመት ተኩል ካለፈ በኋላ በ1918 “ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት የሚጀምርበት ጊዜ ደርሶአልና” በሚሉት የጴጥሮስ ቃላት ፍጻሜ መሠረት ወደ አምላክ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ መጣ። (1 ጴጥሮስ 4:17፤ ሚልክያስ 3:1) አዎን፣ ከባሪያዎቹ ጋር ሒሳብ የሚተሳሰብበት ጊዜ ደርሶ ነበር።

16 ባሪያዎቹ ማለትም የኢየሱስ ቅቡዓን ወንድሞች ንጉሡ በሰጣቸው “መክሊት” ምን አድርገውበት ይሆን? ከ33 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ጀምሮ ከ1914 በፊት እስከነበሩት ዓመታት ድረስ ብዙዎች በኢየሱስ ‘የንግድ’ ሥራ በትጋት ሲካፈሉ ነበር። (ማቴዎስ 25:16) የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት እየተካሄደ በነበረበት ወቅት እንኳን ጌታቸውን ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አሳይተዋል። በመሆኑም እነዚህ ታማኝ ባሪያዎች ‘በንግዱ’ ሥራ አዳዲስ ተጨማሪ ኃላፊነቶች ማግኘታቸው የተገባ ነው። የሥርዓቱ መጨረሻ እየቀረበ ሲሆን ምሥራቹም በዓለም ዙሪያ መሰበክ አለበት። “የምድር መከር” መሰብሰብ ይኖርበታል። (ራእይ 14:6, 7, 14-16) የስንዴው ክፍል ቀሪ አባላት ተለይተው መታወቅና የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑትም “እጅግ ብዙ ሰዎች” መሰብሰብ ይኖርባቸዋል።—ራእይ 7:9 የ1954 ትርጉም፤ ማቴዎስ 13:24-30

17. ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ወደ ጌታቸው ደስታ የገቡት’ እንዴት ነው?

17 የመከር ወቅት አስደሳች ጊዜ ነው። (መዝሙር 126:6) በመሆኑም በ1919 ኢየሱስ ታማኝ ሆነው ለተገኙት ቅቡዓን ወንድሞቹ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጣቸው “በጥቂቱ ታመነሃል፣ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ” ማለቱ ተስማሚ ነው። (ማቴዎስ 25:21, 23 የ1954 ትርጉም) በተጨማሪም ጌታው የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መሾሙ የፈጠረው ደስታ ልንገምተው ከምንችለው በላይ ነው። (መዝሙር 45:1, 2, 6, 7) ታማኙ ባሪያ በምድር ላይ የንጉሡ እንደራሴ በመሆንና የጌታው ንብረቶች እንዲበዙ በማድረግ የደስታው ተካፋይ ይሆናል። (2 ቆሮንቶስ 5:20) በኢሳይያስ 61:10 ላይ የሚገኙት “በእግዚአብሔር እጅግ ደስ ይለኛል፤ ነፍሴ በአምላኬ ሐሤት ታደርጋለች፤ . . . የድነትን ልብስ አልብሶኛል” የሚሉት ትንቢታዊ ቃላት የታማኙን ባሪያ ደስታ በሚገባ ይገልጹታል።

18. አንዳንዶቹ ምርመራውን ያላለፉት ለምንድን ነው? ይህስ ምን አስከተለባቸው?

18 የሚያሳዝነው ግን አንዳንዶች ምርመራውን አላለፉም። ምሳሌው እንዲህ ይላል፦ “አንድ መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፦ ጌታ ሆይ፣ ካልዘራህባት የምታጭድ ካልበተንህባትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆንህን አውቃለሁ ፈራሁም ሄጄም መክሊትህን በምድር ቀበርሁት፤ እነሆ፣ መክሊትህ አለህ አለ።” (ማቴዎስ 25:24, 25 የ1954 ትርጉም) በተመሳሳይም አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘በንግዱ’ ሥራ ሳይካፈሉ ቀርተዋል። ከ1914 በፊት ስለ ተስፋቸው ለሌሎች በመንገሩ ሥራ በቅንዓት ያልተካፈሉ ከመሆኑም በላይ በ1919ም ለመጀመር ፈቃደኛ አልነበሩም። ኢየሱስ ይህን አክብሮት የጎደለው መንፈስ እንዴት ተመለከተው? የነበራቸውን መብት ሁሉ የወሰደባቸው ሲሆን ‘ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወዳለው ጨለማ’ ተጣሉ።—ማቴዎስ 25:28, 30

የምርመራው ሂደት ቀጥሏል

19. የምርመራው ሂደት እስከ ጊዜያችን ድረስ የሚቀጥለው እንዴት ነው? ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ ምን ለማድረግ ቆርጠዋል?

19 እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ በ1918 ምርመራውን በጀመረበት ወቅት በመጨረሻው ዘመን የክርስቶስ ቅቡዓን ባሪያዎች ሆነው ከሚያገለግሉት መካከል አብዛኞቹ ይሖዋን ማምለክ አልጀመሩም። ታዲያ ከምርመራው አምልጠዋል ማለት ነው? በፍጹም። የምርመራው ሂደት ታማኝና ልባም ባሪያ በቡድን ደረጃ ፈተናውን ባለፈበት በ1918/19 ጀመረ እንጂ በዚያ አላበቃም። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ታትመው እስኪያልቁ ድረስ ምርመራው በግለሰብ ደረጃ ይቀጥላል። (ራእይ 7:1-3) በመንፈስ የተቀቡት የክርስቶስ ወንድሞች ይህን ስለሚገነዘቡ ‘በንግዱ’ ሥራ በታማኝነት መካፈላቸውን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ብርሃናቸው ቦግ ብሎ መብራቱን እንዲቀጥል በቂ ዘይት በመያዝ ልባሞች ሆነው ለመገኘት ቆርጠዋል። እያንዳንዳቸው ምድራዊ ሕይወታቸውን በታማኝነት ሲያጠናቅቁ ኢየሱስ በሰማይ ባዘጋጀላቸው ሥፍራ እንደሚቀበላቸው ያውቃሉ።—ማቴዎስ 24:13፤ ዮሐንስ 14:2-4፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50, 51

20. (ሀ) በጊዜያችን የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት ክርስቲያኖች ምን ለማድረግ ቆርጠዋል? (ለ) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን ኃላፊነት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ?

20 የሌሎች በጎች ክፍል የሆኑት እጅግ ብዙ ሰዎችም የቅቡዓን ወንድሞቻቸውን አርዓያ ተከትለዋል። ስለ አምላክ ዓላማ ያላቸው ግንዛቤ ትልቅ ኃላፊነት እንደሚያስከትልባቸው ያውቃሉ። (ሕዝቅኤል 3:17-21) ስለዚህ እነርሱም ከአምላክ ቃልና ከቅዱስ መንፈሱ በሚያገኙት እርዳታ በመታገዝ በጥናትና በስብሰባዎች አማካኝነት የዘይት ማሰሯቸው እንዳይጎድልባቸው ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ በመሳተፍ ብርሃናቸውን ያበራሉ፤ ይህም ከቅቡዓን ወንድሞቻቸው ጋር ‘በንግዱ’ ሥራ ለመካፈል ያስችላቸዋል። ይሁን እንጂ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መክሊቶቹ የተሰጡት ለእነርሱ መሆኑን በሚገባ ያውቃሉ። በምድር ላይ ያሉትን የጌታቸውን ንብረቶች በሚይዙበት መንገድ ይጠየቃሉ። በቁጥር ጥቂቶች ቢሆኑም ኃላፊነቶቻቸውን ለእጅግ ብዙ ሰዎች አሳልፈው መስጠት አይችሉም። የታማኝና ልባም ባሪያ አባላት ይህን ስለሚገነዘቡ የንጉሡን ‘ንግድ’ በበላይነት መቆጣጠራቸውን የሚቀጥሉ ሲሆን የእጅግ ብዙ ሰዎች አባላት በቅንዓት ለሚያደርጉላቸው ድጋፍም አመስጋኞች ናቸው። እጅግ ብዙ ሰዎችም በመንፈስ የተቀቡት ወንድሞቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት የሚገነዘቡ ከመሆኑም በላይ በእነርሱ አመራር ሥር ሆኖ መሥራቱን እንደ ትልቅ መብት ይቆጥሩታል።

21. ከ1919 በፊት ጀምሮ እስከጊዜያችን ያሉት ክርስቲያኖች የትኛውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ሊያደርጉ ይገባል?

21 ከላይ የተመለከትናቸው ሁለት ምሳሌዎች በ1919 እና በዚያ ገደማ ስለተፈጸሙት ክንውኖች ግንዛቤ የሚያስጨብጡን ቢሆንም በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በመጨረሻው ዘመን በሚገኙት እውነተኛ ክርስቲያኖች ላይም የሚሠሩ ናቸው። በተመሳሳይም ኢየሱስ ስለ አሥሩ ቆነጃጅት በተናገረው ምሳሌ መደምደሚያ ላይ የሰጠው ማሳሰቢያ በመጀመሪያ ደረጃ ከ1919 በፊት በነበሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ላይ የሚሠራ ሲሆን መሠረታዊ ሥርዓቱ ግን ለሁሉም ክርስቲያኖች ያገለግላል። በመሆኑም ሁላችንም “እንግዲህ ቀኑን ወይም ሰዓቱን ስለማታውቁ ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት ተግባራዊ እናድርግ።—ማቴዎስ 25:13

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ከዚህ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ በመንፈስ ከተቀቡት ክርስቲያን ሽማግሌዎች መካከል “ነጣቂ ተኩላዎች” ተነስተዋል።—የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30

b ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን “የሰላሙ መስፍን” ሲገዛ በምድር ዙሪያ የሚገኝ ዋስትና ያለው ሕይወት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 5 እና 6 ተመልከት።

ልታብራራ ትችላለህ?

• ኢየሱስ ተከታዮቹን የመረመረው መቼ ነበር? እንዴትስ ሆነው አገኛቸው?

• አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘የክፉውን ባሪያ’ መንፈስ ያሳዩት ለምንድን ነው?

• በመንፈሳዊ ልባሞች መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

• በመንፈስ እንደተቀቡት ታማኝ የኢየሱስ ወንድሞች እኛም ‘በንግዱ’ ሥራ መካፈላችንን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ኢየሱስ የመጣው መቼ ነው?

በማቴዎስ 24 እና 25 ላይ ኢየሱስ በተለያየ መንገድ ‘እንደሚመጣ’ ተነግሯል። መምጣት ሲባል ግን የግድ በአካል መገኘትን አያመለክትም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ትኩረቱን ወደ ሰው ልጆች ወይም ወደ ተከታዮቹ ያደርጋል ማለት ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የሚመጣው ለፍርድ ነው። በመሆኑም በ1914 በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ ተቀምጦ ለመግዛት ‘መጣ።’ (ማቴዎስ 16:28፤ 17:1፤ የሐዋርያት ሥራ 1:11) በ1918 ይሖዋን እናገለግላለን በሚሉ ሰዎች ላይ ለመፍረድ የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ ሆኖ ‘መጣ።’ (ሚልክያስ 3:1-3፤ 1 ጴጥሮስ 4:17) በአርማጌዶን ደግሞ በይሖዋ ጠላቶች ላይ የቅጣት ፍርድ ለማስፈጸም ‘ይመጣል።’—ራእይ 19:11-16

በማቴዎስ 24:29-44 እና 25:31-46 ላይ በተደጋጋሚ የተገለጸው የኢየሱስ መምጣት የሚፈጸመው ‘በታላቁ መከራ’ ወቅት ነው። (ራእይ 7:14) በሌላ በኩል ግን ከማቴዎስ 24:45 እስከ 25:30 ድረስ ተደጋግሞ የተጠቀሰው ‘መምጣት’ ኢየሱስ ከ1918 በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ነን በሚሉ ሰዎች ላይ ፍርድ ለመስጠት ከመምጣቱ ጋር የተያያዘ ነው። ኢየሱስ ታማኙን ባሪያ የሚባርከው፣ በሰነፎቹ ቆነጃጅትና የጌታውን መክሊት ወስዶ በቀበረው ሃኬተኛ ባሪያ ላይ የሚፈርደው በታላቁ መከራ ወቅት ‘ሲመጣ’ ነው ማለቱ ትክክል አይሆንም። ምክንያቱም ይህ በታላቁ መከራ ወቅት ከቅቡዓኑ መካከል አብዛኞቹ ታማኝ ሆነው ስለማይገኙ በሌሎች መተካት ያስፈልጋቸዋል የሚል አንድምታ ይኖረዋል። ይሁን እንጂ ራእይ 7:3 ታላቁ መከራ ሲጀምር በመንፈስ የተቀቡት የክርስቶስ ባሪያዎች በሙሉ ‘ታትመው’ እንደሚጠናቀቁ ይጠቁማል።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘ክፉው ባሪያ’ በ1919 ምንም በረከት አላገኘም

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሙሽራው በመጣበት ወቅት ልባሞቹ ቆነጃጅት ዝግጁዎች ነበሩ

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታማኙ ባሪያ ‘በንግዱ’ ሥራ ተካፍሏል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃኬተኛው ባሪያ ግን አልተካፈለም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቅቡዓን ክርስቲያኖችና “እጅግ ብዙ ሰዎች” ብርሃናቸውን ማብራታቸውን ቀጥለዋል