በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብያተ ክርስቲያናት ከመበታተን ይድኑ ይሆን?

አብያተ ክርስቲያናት ከመበታተን ይድኑ ይሆን?

አብያተ ክርስቲያናት ከመበታተን ይድኑ ይሆን?

“በብሪታንያ የሚኖሩ ሰዎች በአምላክ ቢያምኑም የክርስቶስ ተከታዮች መሆን ግን አይፈልጉም።” ይህን የተናገሩት ስቴፈን ቲርዎምዌ የተባሉ ከ20 ዓመት በፊት በኡጋንዳ አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ላይ ከተፈጸመው ከባድ ስደት በሕይወት የተረፉ ቄስ ናቸው። ስቴፈን ቲርዎምዌ በአሁኑ ወቅት በሊድስ፣ እንግሊዝ በሚገኝ በአንድ የወንዶች ክበብ ውስጥ የቢንጎ ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ለአሥር ደቂቃ ይሰብካሉ።

ከአትላንቲክ ባሻገር በምትገኘው በአሜሪካ ደግሞ በቅርቡ የተደራጀችው የአንግሊካን ሚስዮን ቤተ ክርስቲያን ተመሳሳይ መንፈሳዊ ቀውስ አጋጥሟታል። የቤተ ክርስቲያኒቱ የዌብ ገጽ እንዲህ ይላል:- “በአሁኑ ወቅት በዓለማችን ላይ ከሚገኙት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሕዝቦች መካከል የየትኛውም ቤተ ክርስቲያን አባል ባልሆኑ ወይም ለመንፈሳዊ ነገሮች ደንታ በሌላቸው ሰዎች ብዛት ከፍተኛውን ቁጥር የያዘችው ዩናይትድ ስቴትስ ነች። አገራችን ሚስዮናውያን በእጅጉ የሚያስፈልጓት ሆናለች።” ይህ አዲስ የተቋቋመ ሚስዮን በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ያደረገው ጥረት ስላልተሳካለት በፊት ይከተለው የነበረውን ልማድ በመተው በእስያና በአፍሪካ የሚገኙ ሃይማኖታዊ መሪዎች “ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሚስዮናውያንን እንዲልኩ” ማድረግ ጀምሯል።

ይሁን እንጂ ከአፍሪካ፣ ከእስያና ከደቡብ አሜሪካ የመጡ ሚስዮናውያን በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ለሚኖሩ ክርስቲያን ነን ለሚሉ ሰዎች መስበክ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

ማን ማንን ነው የሚያድነው?

ከአራት መቶ ለሚበልጡ ዓመታት በርካታ ቀናተኛ የአውሮፓ ሚስዮናውያን የቅኝ ገዢዎችን ኮቴ ተከትለው ወደ አፍሪካ፣ እስያ፣ የፓስፊክ ደሴቶችና ደቡብ አሜሪካ ሲጎርፉ ነበር። ዓላማቸው በእነዚህ አሕጉራት ለሚኖሩት አረማውያን ለሚሏቸው ሰዎች ሃይማኖታቸውን ለመስበክ ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በክርስትና ትምህርቶች ላይ እንደተመሠረቱ የሚነገርላቸው የአሜሪካ ግዛቶችም ሚስዮናውያን መላክ የጀመሩ ሲሆን ውሎ አድሮም በዓለም ዙሪያ የራሳቸውን ወንጌላዊ ሚስዮኖች በማቋቋም በአውሮፓ ከሚገኙ መሰሎቻቸው ልቀው ተገኙ። አሁን ግን ሁኔታው የተገላቢጦሽ ሆኖ ሚስዮናውያኑ የሚጎርፉበት አቅጣጫ ተቀይሯል።

ከምዕራቡ ዓለም ውጪ ባለው ክርስትና ላይ ጥናት የሚያደርግ የአንድ ማዕከል መሥራችና ዳይሬክተር የሆኑት አንድሪው ዎልስ ‘[የክርስትና] ማዕከል ተብሎ ይታሰብ የነበረው አካባቢ ተለውጧል’ በማለት ተናግረዋል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ክርስቲያን ነን ከሚሉት ሰዎች መካከል 80 በመቶ የሚሆኑት የሚገኙት በአውሮፓ ወይም በሰሜን አሜሪካ ነበር። በዛሬው ጊዜ ግን 60 በመቶ የሚሆኑት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች የሚኖሩት በአፍሪካ፣ በእስያና በላቲን አሜሪካ ነው። በቅርቡ የተሰጠ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲህ ይላል:- “በአውሮፓ የሚገኙ የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ከፊሊፒንስና ከሕንድ በመጡ ቀሳውስት መጠቀም አስፈልጓቸዋል። በአሜሪካ በሚገኙ የካቶሊክ ደብሮች ውስጥ ከሚያገለግሉት ስድስት ቀሳውስት መካከል አንዱ ከሌላ አገር የመጣ ነው።” በአብዛኛው የጋና ተወላጅ የሆኑት በኔዘርላንድ የሚያገለግሉ አፍሪካዊ ወንጌላውያን ራሳቸውን የሚቆጥሩት “ዓለማዊ በሆነ አሕጉር ውስጥ እንደሚያገለግሉ ሚስዮናውያን” አድርገው ነው። ከብራዚል የመጡ ወንጌላውያን ደግሞ በእንግሊዝ የተለያዩ ክፍሎች ክርስትናን የማስፋፋት ዘመቻ እያካሄዱ ነው። አንድ ጸሐፊ “ሚስዮናውያን የሚጎርፉበት አቅጣጫ ተቀይሯል” በማለት ተናግረዋል።

እያጠላ የመጣው አደጋ

መንፈሳዊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋባቸው የመጡት የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አሕጉራት ሚስዮናውያን ሳያስፈልጓቸው አይቀርም። አንድ መጽሔት “በስኮትላንድ አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን የሚሳለሙ ሰዎች ቁጥር ከ10 በመቶ ያነሰ ነው” ይላል። በፈረንሳይና በጀርመን ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም ዝቅ ያለ ነው። ሌላ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከተው በአንድ ጥናት መሠረት “አዘውትረው ቤተ ክርስቲያን እንደሚሄዱ የተናገሩት 40 በመቶ የሚያህሉ አሜሪካውያንና 20 በመቶ የሚሆኑ ካናዳውያን ብቻ ናቸው።” በአንጻሩ ግን ፊሊፒንስ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ሰዎች ቁጥር ወደ 70 በመቶ የሚጠጋ ሲሆን በማደግ ላይ በሚገኙ ሌሎች አገሮችም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ከዚህ ይበልጥ ጎልቶ የሚታየው ደግሞ በሰሜናዊ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙት የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች ይልቅ በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚገኙት ጥንታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚከተሉ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስና በአውሮፓ የሚኖሩ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች አስተያየት ሲጠየቁ በቀሳውስት ሥልጣን ላይ እምነት እያጡ መምጣታቸውን የሚናገሩ ከመሆናቸውም በላይ ምዕመናን የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸውና የሴቶች እኩልነት እንዲረጋገጥ ይፈልጋሉ። በሌላ በኩል ግን በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ የሚኖሩ ካቶሊኮች ቤተ ክርስቲያኒቱ እነዚህን ጉዳዮች በሚመለከት ያላትን ጥንታዊ ሥርዓት አጥብቀው ይከተላሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላት ተሰሚነት ከሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ወደ ደቡብ ንፍቀ ክበብ እየዞረ በሄደ መጠን ወደፊት ልዩነት እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሁኔታዎች ይበልጥ እየታዩ በመምጣት ላይ ናቸው። ፊሊፕ ጄንከንዝ የተባሉ አንድ የታሪክና የሃይማኖት ምሑር የወደፊቱን ጊዜ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል:- “ከአንድ ወይም ከሁለት አሥርተ ዓመታት በኋላ በሁለቱም ንፍቀ ክበባት የሚኖሩ ክርስቲያኖች አንዱ ሌላውን እውነተኛ ወይም ትክክለኛ ክርስቲያን አድርጎ መመልከቱ የሚያበቃለት ጉዳይ የሚሆን ይመስላል።”

ከዚህ አዝማሚያ አንጻር አንድሪው ዎልስ “በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በደቡብና በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በአውሮፓ የሚኖሩ ክርስቲያኖች አንድ እምነት ኖሯቸው በአንድ ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር ሊኖሩ የሚችሉት እንዴት ነው?” የሚል አንገብጋቢ ጥያቄ ይነሳል ብለዋል። አንተስ ምን ትላለህ? በዚህ በተከፋፈለ ዓለም ውስጥ አብያተ ክርስቲያናት ከመበታተን ይድኑ ይሆን? ለእውነተኛ ክርስቲያናዊ አንድነት መሠረቱ ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ አንድ ክርስቲያናዊ ቡድን በዓለም ዙሪያ በፍጥነት እየተስፋፋ እንዳለ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ያቀርባል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህ የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን አሁን የሙዚቃ ትርዒት የሚቀርብበት ምግብ ቤት ሆኗል

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

AP Photo/Nancy Palmieri