አዎንታዊ አመለካከት አዳብሩ
አዎንታዊ አመለካከት አዳብሩ
ቦታው መካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን ወቅቱ የበጋ ወራት ነበር። ገና በማለዳ ፍንትው ብላ የወጣችው ፀሐይ ለአካባቢው ድምቀት ሰጥታዋለች። በዚህ ደስ የሚል ጠዋት አንድ አባት የ22 ዓመት ዕድሜ ያለው የመጀመሪያ ልጁ ሌሊቱን የመኪና አደጋ አጋጥሞት ሕይወቱ እንዳለፈ የሚገልጽ አስደንጋጭ መርዶ ደረሰው።
በዚህ አባት ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ይሰማህ ነበር? በመካከለኛው ምሥራቅ የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ በጣም ስለሚቀራረቡ የልጁ ወላጆች በጣም ነበር ያዘኑት። የደረሰባቸው ድንገተኛ ሐዘን በእጅጉ እንዲመረሩ ቢያደርጋቸው አይፈረድባቸውም። ሆኖም ስለ አደጋው ከሰሙበት ዕለት ጀምሮ ለሁኔታው የነበራቸው አመለካከት የአካባቢውን ነዋሪዎች ያስገረመ ነበር። ሐዘኑ ጠልቆ ቢሰማቸውም ይሖዋ በቀጠረው ጊዜ ልጃቸውን ከሞት ሊያስነሳው እንደሚችል ሙሉ ትምክህት ነበራቸው። አምላክ ቃል የገባውን ‘ሞት የማይኖርበት’ አዲስ ሥርዓት በተስፋ ይጠባበቁ ነበር። (ራእይ 21:4) ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ እንኳን ይህን ቤተሰብ የሚያውቁ ሰዎች ወላጆቹ ያሳዩትን ብሩህ አመለካከትና ምሳሌ የሚሆን እምነት ያነሳሉ።
አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ሲባል ምን ማለት ነው? አዎንታዊ አመለካከት ያለው ሰው ሁኔታዎች የቱንም ያህል ቢለዋወጡ ሚዛኑን አይስትም። በጣም ፈታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ጊዜም እንኳን አፍራሽ በሆኑ አመለካከቶች ላይ በማተኮር አይመረርም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት እስቲ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ሰውን መፍራት ፈተና ሲሆንብን
በ1512 ከክርስቶስ ልደት በፊት የእስራኤል ብሔር በፋራን ምድረ በዳ ሰፍሮ በነበረበት ወቅት ሙሴ የተስፋይቱን ምድር እንዲሰልሉ 12 ሰላዮች ላከ። (ዘኍልቍ 13:17-20) ሁሉም ሰላዮች የነገድ አለቆች ሲሆኑ ተሰሚነት ያላቸውና ጥሩ ምሳሌ መሆን የሚጠበቅባቸው ሰዎች ነበሩ። (ዘኍልቍ 13:1, 2) ሆኖም የተከሰተው ሁኔታ በጣም የሚያሳፍር ነበር! ምድሪቱን ለአርባ ቀናት ሰልለው ሲመለሱ አሥሩ ሰላዮች የሚያሸብር ሪፖርት በማቅረባቸው ሕዝቡ በይሖዋ አመራር ላይ ያመፁ ከመሆኑም በላይ ወደ ግብፅ ለመመለስ ፈለጉ። ሰላዮቹ “በዚያም የሚኖሩት ሰዎች ግን ኀያላን” ስለሆኑ “ልናሸንፋቸው አንችልም” በማለት ተናገሩ።—ዘኍልቍ 13:28, 31
እንዴት ያለ አፍራሽ አመለካከት ነው! በአንጻሩ ግን ኢያሱና ካሌብ የተባሉት ሁለት ሰላዮች “ዞረን ያየናትና የሰለልናት ምድር እጅግ ሲበዛ መልካም ናት። እግዚአብሔር በእኛ ደስ ከተሰኘብን ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደዚያች ምድር መርቶ ያገባናል፤ ለእኛም ይሰጠናል” በማለት አዎንታዊ አመለካከት እንዳላቸው አሳይተዋል። (ዘኍልቍ 14:7, 8፤ 13:30) ኢያሱና ካሌብም ሆኑ አሥሩ ሰላዮች ምድሪቱን ሲሰልሉ የተመለከቱት ነገር ተመሳሳይ ቢሆንም የነበራቸው አመለካከት ግን ፍፁም የተለያየ ነበር። የአሥሩ ሰላዮች አፍራሽ አመለካከት በመላው ብሔር ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ ሕዝቡ ማጉረምረም ጀመረ። ይህም ከ20 ዓመት በላይ የሆኑት ሁሉ በምድረ በዳ እንዲያልቁ ምክንያት ሆኗል። ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት የታደሉት በይሖዋ ላይ የተማመኑት ኢያሱና ካሌብ ብቻ ነበሩ። (ዘኍልቍ 14:22-30) የእነርሱ ምሳሌ በዚህ ዘመን ስደት ሲያጋጥመን ወይም ተቃውሞ እያየለ ሲሄድ አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝና ታማኝ ሆነን እንድንቀጥል ሊያበረታታን ይገባል።
ለበርካታ ዓመታት በዕገዳ ሥር በነበረ አገር ውስጥ የሚያገለግል አንድ ልዩ አቅኚ ታሰረና ከባድ እንግልት ደረሰበት። ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል:- “ፖሊሶቹ ቅጣቱን እያከበዱብኝ በሄዱ መጠን ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንደቀረብኩ ተሰማኝ። መዝሙር እዘምር የነበረ ከመሆኑም በላይ በቃሌ በማውቃቸው ጥቅሶች ላይ አሰላስል ነበር። ይሖዋ ይህ ሁኔታ እንዲያጋጥመኝ ቢፈቅድም በማንኛውም ጊዜ ነፃ ሊያወጣኝ እንደሚችል አውቅ ነበር። እነዚህ ነገሮች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረኝ ረድተውኛል። እኔም እንደ ሐዋርያት ሁሉን ቻይ ለሆነው ለይሖዋ ስም ስል በመደብደቤ ደስተኛ ነበርኩ። ይሖዋ ብርታት እንዲሰጠኝ ያለማቋረጥ እጸልይ የነበረ ሲሆን እርሱም በድብደባው ወቅት ከመጀመሪያው ምት በስተቀር ምንም እንዳይሰማኝ በማድረግ ረድቶኛል። ያገኘሁትን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሜ ለሌሎች እስረኞች እሰብክ ነበር።”
ይህ ወንድም ከእስር ከተፈታ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “ሕይወታችንን ለይሖዋ ስለወሰንንና ለእርሱ ታማኝ ሆነን ለመኖር ቃል ስለገባን ምንም ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥመን እርሱን ማገልገላችንን መቀጠል ይኖርብናል። ይሖዋ ልናመልከውና በሙሉ ልብ ልናገለግለው የሚገባን አምላክ ነው።”
እኛም ወደፊት ተመሳሳይ ተቃውሞ ሊያጋጥመን ይችላል። ስለሆነም ልክ እንደዚህ ወንድም በሰው ፍርሃት ላለመሸነፍ ቁርጥ አቋም ሊኖረን ይገባል። አዎንታዊ አመለካከት ካዳበርን እንደ ኢያሱና ካሌብ ብዙ በረከቶችና ሽልማቶችን እናገኛለን።
የአገልግሎት መብት ስናጣ
አሥራ ሁለቱን ሰላዮች የላከው የእስራኤል ብሔር መሪ የነበረው ሙሴ ነው። ሕዝቡን ከግብፅ ያወጣቸው እርሱ ሲሆን ዘኍልቍ 20:2-13) ታዲያ ሙሴ ምን ተሰማው? ከጊዜ በኋላ ባቀናበረው መዝሙር ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እኔ የእግዚአብሔርን ስም ዐውጃለሁ፤ . . . እርሱ ዐለት፣ ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ ትክክል ነው፤ የማይሳሳት ታማኝ አምላክ፣ ቀጥተኛና ጻድቅ አምላክም እርሱ ነው።” (ዘዳግም 32:3, 4) ሙሴ ትልቅ የአገልግሎት መብት ቢያጣም አዎንታዊ አመለካከት ነበረው።
ወደ ተስፋይቱ ምድር እየመራ ሊያስገባቸው ይፈልግ እንደነበረም አያጠራጥርም። ሆኖም በአንድ ወቅት በብስጭት በተናገረው ቃል ለይሖዋ ክብር ሳይሰጥ በመቅረቱ ይህን መብት አጣ። (እኛም ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥመን ይህን የሙሴ ተሞክሮ ማስታወሳችን ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የአንድ ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ለአገልግሎት መብቱ የሚያስፈልጉት አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ስለሚጎድሉት ከኃላፊነቱ እንዲወርድ ሊወስን ይችላል። ወንድም ግን ከኃላፊነት ሊወርድ እንደማይገባው ተሰምቶት ሊበሳጭና አላስፈላጊ ረብሻ ሊፈጥር ይችላል። አፍራሽ አመለካከት በመያዝ ማጉረምረምና የሌሎችን ስህተት መለቃቀም ሊጀምር አልፎ ተርፎም ሐሜት ሊነዛ ይችላል። ውሎ አድሮም በስብሰባ ላይ መገኘቱንና በስብከቱ ሥራ መካፈሉን ሊያቆም ይችላል። እንዴት ያለ መጥፎ አካሄድ ነው! ከዚህ ይልቅ አዎንታዊ አመለካከት ቢይዝና ከኃላፊነት መውረዱን የተሻለ የይሖዋ አገልጋይ ለመሆን እንደሚረዳው ተግሣጽ ወይም ማሰልጠኛ አድርጎ ቢመለከተው ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር። ይህንን አጋጣሚ ይሖዋን በበለጠ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ብቃት እንደገና ለማሟላት የአምላክን ቃል ለማጥናትና ለማሰላሰል ሊጠቀምበት ይችላል። እንደዚህ ያደረጉ ብዙዎች ከጊዜ በኋላ የላቁ የአገልግሎት መብቶችን በማግኘት ተባርከዋል።—ዕብራውያን 12:11
ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ
ሕይወት ቅር እንድንሰኝ እና አፍራሽ አመለካከት እንድንይዝ በሚያደርጉ ያልተጠበቁ ገጠመኞች የተሞላ ነው። አንድ ነገር እንደጠበቅኸው ሳይሆን ሲቀር ምን ይሰማሃል? አንዳንድ ጥቃቅን ጉዳዮች እንኳን ትልቅ ቦታ ከሰጠናቸው ተስፋ ሊያስቆርጡን ይችላሉ። ይሁን እንጂ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ያጋጠመህን ያልተጠበቀ ሁኔታ በተሻለ መንገድ ለመቋቋም እንደሚረዳህ አትዘንጋ።
በዚህ ረገድ ሩት ጥሩ ምሳሌ ትሆነናለች። ገና በወጣትነቷ መበለት የሆነችው ሩት በእስራኤል የረሃቡ ጊዜ ሲያልፍ ከምራቷ ከኑኃሚን ጋር ወደዚያ ሄደች። መሠረታዊ ፍላጎቶቿን እንኳ የሚያሟላ ባል ባይኖራትም ብሩህ አመለካከት ነበራት። ለእርሷና ለምራቷ የሚሆን ምግብ ለማግኘት ከአጫጆች ኋላ እየተከተለች ለመቃረም ፈቃደኛ ነበረች። ሥራው አድካሚ መሆኑ ተስፋ አላስቆረጣትም። ባሏን ማጣቷንና ከወዳጅ ዘመዶቿ ርቃ የምትኖር መሆኗን በማብሰልሰል አፍራሽ አስተሳሰብ አላዳበረችም። ታሪኩ እንደሚያሳየው ለተከተለችው የሕይወት ጎዳና ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኳታል።—ሩት 4:13-17
አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ለአንዳንዶች ቀላል አይደለም። በምንኖርበት አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ የኑሮ ሁኔታዎች ሲያስጨንቁን በተለይም እረፍት የሚነሱ ችግሮች ሲያጋጥሙን ደስታችንን ልናጣ እንችላለን። ሆኖም በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ አዎንታዊ አስተሳሰብ መያዝ ይቻላል። ብዙዎች በከባድ ፈተናዎች ውስጥ ቢሆኑም ብሩህ አመለካከት አዳብረዋል። እኛስ እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
አፍራሽ የሆኑ ሐሳቦችን በአእምሮህ ይዘህ አትብሰልሰል። በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር እንኳን ብሩህ አመለካከት እንዲኖረን የሚያደርጉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሐዋርያት በተደጋጋሚ ስደት ቢደርስባቸውና ለእስራት ቢዳረጉም ይሖዋን ማወደስ መቻላቸው ያስደስታቸው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 13:50-52፤ 14:19-22፤ 16:22-25) ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎች የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በፈተና ወቅት ምን እንዳደረጉ በማሰላሰል ለእኛ የሚጠቅሙ ትምህርቶችን ማግኘት እንችላለን። በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ደስተኞች የነበሩትና አዎንታዊ አመለካከት ሊኖራቸው የቻለው ለምን ነበር? በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህትና እምነት ስለነበራቸው ነው። እንዲሁም ከሞት ሊያስነሳቸውና ሽልማት ሊሰጣቸው እንደሚችል ይተማመኑ ነበር። (ራእይ 2:10) በተመሳሳይም ጽድቅ በሰፈነበት የይሖዋ አዲስ ሥርዓት ውስጥ ለመኖር ያለህ ተስፋ እውን ሆኖ እንዲታይህ አድርግ።—ከዕብራውያን 12:2 ጋር አወዳድር።
በተጨማሪም አፍራሽ አስተሳሰብ ወደ ልባችን ገብቶ ሥር እንዳይሰድ አዘውትረን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ወደ ይሖዋ ይበልጥ መቅረባችንና እርዳታ እንዲሰጠን መጸለያችን በጣም ጠቃሚ ነው! (መዝሙር 62:8) ሽማግሌዎች እንዲረዱንም መጠየቅ እንችላለን። እንዲሁም የትሕትናና የታዛዥነት መንፈስ ማዳበር አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 119:69, 70) ጠቃሚና ሊደረስባቸው የሚችሉ ግቦች አውጡ። እነዚህ ምክሮች አዎንታዊ አመለካከት እንድንይዝና ‘ልባችንንና አሳባችንን የሚጠብቀውን የአምላክ ሰላም’ እንድናገኝ ይረዱናል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
እርግጥ ነው፣ አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ ትጋት የታከለበት ጥረት በማድረግና ጠንካራ እምነት በመያዝ ይህን አመለካከት ማዳበር ይቻላል። እንግዲያው ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ሁላችንም አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ማድረጋችን ምንም ኪሳራ አያስከትልብንም፤ እንዲያውም አሁንም ሆነ ወደፊት ብዙ አስደሳች በረከቶችን ያስገኝልናል።