በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በጥንቷ እስራኤል ሌዋውያን ርስት ካልነበራቸው በኤርምያስ 32:7 ላይ እንደተገለጸው ሌዋዊው አናምኤል ለአጎቱ ልጅ ለኤርምያስ እንዴት እርሻውን ሊሸጥለት ይችላል?

ይሖዋ ሌዋውያንን በሚመለከት አሮንን “ከምድራቸው የምትካፈለው ርስት፤ ከእነርሱም የምታገኘው ድርሻ የለህም” ብሎት ነበር። (ዘኍልቍ 18:20) ይሁን እንጂ ሌዋውያን በመላው የተስፋይቱ ምድር ውስጥ ተሰበጣጥረው በሚገኙ ቦታዎች 48 ከተሞችና የግጦሽ መሬት ተሰጥቷቸው ነበር። ኤርምያስ የተወለደው “ለካህናቱ ለአሮን ዝርያዎች” ከተሰጡት ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በዓናቶት ነበር።—ኢያሱ 21:13-19፤ ዘኍልቍ 35:1-8፤ 1 ዜና መዋዕል 6:54, 60

በዘሌዋውያን 25:32-34 ላይ ሌዋውያን በባለቤትነት የያዙትን ንብረት ‘የመቤዠትን መብት’ በሚመለከት ይሖዋ የሰጠውን ግልጽ መመሪያ እናገኛለን። ሁሉም ሌዋውያን ቤተሰቦች በውርስ ያገኙትን ንብረት በባለቤትነት የመያዝ፣ እንደፈለጉት የመጠቀም ብሎም ለሌላ የማዛወር መብት እንደነበራቸው ግልጽ ነው። ይህ ደግሞ ንብረትን መሸጥንና መቤዠትንም እንደሚጨምር ምንም ጥርጥር የለውም። a ሌዋውያን ርስታቸውን በባለቤትነት የሚይዙበትና የሚጠቀሙበት መንገድ ከሌሎች እስራኤላውያን ነገዶች እምብዛም የተለየ አልነበረም።

ምናልባትም እንዲህ ያለው የሌዋውያን ንብረት ከአንዱ ወደ ሌላው ይተላለፍ የነበረው በውርስ መልክ ሳይሆን አይቀርም። ‘የመቤዠትን መብት’ በሚመለከት ግን ሽያጭም ሆነ ግዥ የሚከናወነው በሌዋውያን መካከል ብቻ ነበር። “በከተሞቻቸው ዙሪያ ያለው የግጦሽ መሬት . . . ለዘላለም ቋሚ ንብረታቸው” ስለሆነ መሸጥ ወይም መቤዠት የሚቻለው በከተማ ውስጥ የሚገኙ ንብረቶችን ብቻ ሳይሆን አይቀርም።—ዘሌዋውያን 25:32, 34

ስለዚህ ከሁኔታው እንደምንረዳው ኤርምያስ ከአናምኤል መሬቱን መግዛት የቻለው ቦታው በከተማው ክልል ውስጥ ይገኝ ስለነበር መሆን አለበት። ይሖዋ ራሱ ‘መሬቱ’ የአናምኤል መሆኑንና ኤርምያስ “የመቤዠት መብት” እንደነበረው ገልጿል። (ኤርምያስ 32:6, 7) ይሖዋ አናምኤል መሬቱን ለኤርምያስ እንዲሸጥለት ያደረገው እስራኤላውያን ለተወሰኑ ዓመታት በባቢሎን በግዞት ከኖሩ በኋላ ወደ ምድራቸው ተመልሰው ርስታቸውን እንደገና እንደሚያገኙ የገባላቸውን ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ጠንከር አድርጎ ለመግለጽ ነው።—ኤርምያስ 32:13-15

አናምኤል በዓናቶት የነበረውን መሬት ያለአግባብ እንደያዘው የሚጠቁም ማስረጃ የለም። በተጨማሪም አናምኤል መሬቱን እንዲገዛው ኤርምያስን ሲጠይቅ የይሖዋን ሕግ እንደጣሰ እንዲሁም ኤርምያስ መሬቱን ሲገዛ የመቤዠት መብቱን ያለአግባብ እንደተጠቀመ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አናገኝም።—ኤርምያስ 32:8-15

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሌዋዊው በርናባስ መሬቱን ሸጦ ገንዘቡን በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ችግረኛ ክርስቲያኖችን ለመርዳት እንዲውል ሰጥቶ ነበር። መሬቱ ይገኝ የነበረው በጳለስጢና ወይም በቆጵሮስ ሊሆን ይችላል። አሊያም በርናባስ ኢየሩሳሌም አካባቢ ለመቃብር የገዛው መሬት ሊሆን ይችላል።—የሐዋርያት ሥራ 4:34-37