ሕይወትህን የሚነካ በዓል
ሕይወትህን የሚነካ በዓል
ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ሳለ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ አንድ በዓል አቋቁሞ ነበር። እንዲያውም ተከታዮቹ እንዲያከብሩት ያዘዘው ሃይማኖታዊ በዓል ይህ ብቻ ነበር። በዓሉ የጌታ እራት በመባል ይታወቃል።
ይህ በዓል ከመከበሩ በፊት የተከናወኑትን ነገሮች በታዛቢነት ለመመልከት አጋጣሚ አግኝተህ ነበር እንበል። ኢየሱስና ሐዋርያቱ የአይሁድን የማለፍ በዓል ለማክበር ኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ፎቅ ላይ ባለ ክፍል ውስጥ ተሰብስበዋል። ለማለፍ በዓል የተዘጋጀውን የተጠበሰ የበግ ሥጋ፣ መራራ ቅጠል፣ ያልቦካ ቂጣና የወይን ጠጅ በልተውና ጠጥተው ጨርሰዋል። ከሃዲው ሐዋርያ የአስቆሮቱ ይሁዳ ተሰናብቶ የወጣ ሲሆን ጌታውን አሳልፎ የሚሰጥበት ጊዜ ደርሷል። (ማቴዎስ 26:17-25፤ ዮሐንስ 13:21, 26-30) በቦታው ኢየሱስና ታማኝ ሐዋርያቱ ብቻ የቀሩ ሲሆን ከእነርሱ አንዱ ማቴዎስ ነበር።
የዓይን ምሥክር የነበረው ማቴዎስ እንደዘገበው ኢየሱስ የጌታ እራትን ያቋቋመው እንደሚከተለው ነበር:- “ኢየሱስ እንጀራን አንስቶ ባረከ፤ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ በመስጠት፣ ‘እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ሥጋዬ ነው’ አላቸው። ከዚያም ጽዋውን አንሥቶ አመሰገነ፤ ለደቀ መዛሙርቱም በመስጠት እንዲህ አላቸው፤ ‘ሁላችሁም ከዚህ ጠጡ፤ ስለ ብዙዎች የኀጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ይህ ነው።’”—ማቴዎስ 26:26-28
ኢየሱስ የጌታ እራትን ያቋቋመው ለምን ነበር? በበዓሉ ላይ ያልቦካ ቂጣ እና ቀይ የወይን ጠጅ የተጠቀመውስ ለምንድን ነው? ሁሉም የክርስቶስ ተከታዮች ከቂጣውና ከወይኑ ይካፈሉ ነበር? ይህ በዓል መከበር የሚኖርበት በየስንት ጊዜው ነው? ለአንተስ ምን ትርጉም አለው?