በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ናዖድ የአስገባሪውን ቀንበር ሰበረ

ናዖድ የአስገባሪውን ቀንበር ሰበረ

ናዖድ የአስገባሪውን ቀንበር ሰበረ

ታሪኩ ከ3,000 ዓመታት ገደማ በፊት የተፈጸመ ድፍረትና ዘዴኛነት የተንጸባረቀበት እውነተኛ ክንውን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ዘገባ እንዲህ በማለት ይጀምራል:- “እስራኤላውያን እንደገና በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ ይህን በማድረጋቸውም እግዚአብሔር የሞዓብ ንጉሥ ዔግሎን በእስራኤል ላይ እንዲበረታባቸው አደረገ። እርሱም አሞናውያንንና አማሌቃውያንን ካስተባበረ በኋላ እስራኤልን ወግቶ የዘንባባ ዛፎች ከተማ የሆነችውን ኢያሪኮን ያዙ። እስራኤላውያንም ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን ዐሥራ ስምንት ዓመት ተገ[ዙለ]ት።”—መሳፍንት 3:12-14

የሞዓባውያን ምድር የሚገኘው ከዮርዳኖስ ወንዝና ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ ነው። ይሁንና ሞዓባውያን ወንዙን ተሻግረው “የዘንባባ ከተማ” የተባለችውን ኢያሪኮንና አካባቢዋን በመቆጣጠር እስራኤላውያንን በባርነት ይገዙ ጀመር። (ዘዳግም 34:3) እጅግ “ወፍራም” የነበረው የሞዓብ ንጉሥ ዔግሎን ለሁለት አሥርተ ዓመታት ያህል እስራኤላውያንን ከፍተኛ ግብር አስከፈላቸው። (መሳፍንት 3:17) ሆኖም ከእስራኤላውያን ይመጣለት የነበረው ግብር ይህ አምባገነን ገዢ የሚወገድበት ሁኔታ እንዲመቻች አድርጓል።

ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እስራኤላውያን እንደ ገና ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ግራኙን ናዖድን ነጻ እንዲያወጣቸው አስነሣው። እስራኤላውያን ናዖድን ግብር አስይዘው ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎን ላኩት።” (መሳፍንት 3:15) ይሖዋ ግብሩን ለማቅረብ ናዖድ እንዲመረጥ ሁኔታዎችን አመቻችቶ መሆን አለበት። ከዚህ በፊት ይህን ተግባር አከናውኖ ስለመሆኑ ምንም የተገለጸ ነገር የለም። ይሁን እንጂ ናዖድ ከንጉሡ ጋር ለመገናኘት የታሰበበት ዝግጅት ማድረጉና የተጠቀመባቸው ዘዴዎች ስለ ዔግሎን ቤተ መንግሥትም ሆነ እዚያ ምን ሊያጋጥመው እንደሚችል የተወሰነ ግንዛቤ እንደነበረው ያሳያል። ናዖድ ያወጣውን እቅድ ዳር ለማድረስ ግራኝ መሆኑም በጣም ጠቅሞታል።

ናዖድ—ጀግና ነው ወይስ የአካል ጉዳተኛ?

‘ግራኝ’ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ቀጥተኛ ትርጉም ‘ቀኝ እጁ የማይሠራ፣ ሽባ የሆነ ወይም የታሰረ’ ማለት ነው። ታዲያ ይህ አባባል ናዖድ ምናልባት ቀኝ እጁ ችግር ያለበት የአካል ጉዳተኛ መሆኑን ያመለክታል? መጽሐፍ ቅዱስ ከብንያም ነገድ ስለሆኑ “ሰባት መቶ ምርጥ” ግራኝ ሰዎች ምን እንደሚል ተመልከት። መሳፍንት 20:16 “እያንዳንዳቸው ድንጋይ ወንጭፈው ጠጉር እንኳ የማይስቱ . . . ነበሩ” ይላል። እነዚህ ሰዎች የተመረጡት የላቀ ችሎታ ያላቸው ተዋጊዎች በመሆናቸው ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን እንደሚሉት ‘ግራኝ’ የሚለው ቃል በግራውም የቀኙን ያህል መሥራት የሚችልን ሰው ያመለክታል።

በብንያም ነገድ ውስጥ በግራ እጃቸው በደንብ መሥራት የሚችሉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። አንደኛ ዜና መዋዕል 12:1, 2 ስለ ብንያማውያን ሲገልጽ “በጦርነቱ ላይ ከረዱት ተዋጊዎች መካከል ነበሩ። ሰዎቹ ቀስተኞች ሲሆኑ፣ በቀኝም ሆነ በግራ እጃቸው ፍላጻ መወርወርና ድንጋይ መወንጨፍ የሚችሉ ነበሩ” ይላል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዳለው ልጆች ይህን ችሎታ እንዲያዳብሩ “ቀኝ እጃቸው ታስሮ በግራ እጃቸው አቀላጥፈው መሥራት እንዲችሉ ሥልጠና ይሰጣቸው ነበር። ‘ቀኝ እጁ የታሰረ’ የሚለው አባባል የመጣው ከዚህ ነው።” የእስራኤል ጠላቶች ሥልጠና የሚሰጣቸው በቀኝ እጃቸው መሣሪያ ከሚይዙ ወታደሮች ጋር ለመፋለም ስለሆነ በግራ እጁ የሚዋጋ ወታደር ድንገት ሲያጋጥማቸው ያገኙት ሥልጠና በሙሉ መና ይቀራል።

ለንጉሡ ‘በምስጢር የሚነገር ጉዳይ’

ናዖድ በመጀመሪያ ደረጃ በልብሱ ውስጥ ሊደብቀው የሚችል በሁለቱም በኩል ስለታም የሆነ አጠር ያለ ‘ሰይፍ አዘጋጀ።’ ፍተሻ ሊኖር እንደሚችል ሳይጠብቅ አልቀረም። በቀኝ እጃቸው የሚዋጉ ሰዎች ሰይፋቸውን በፍጥነት መምዘዝ እንዲችሉ የሚታጠቁት በግራ በኩል ነበር። ናዖድ ግራኝ በመሆኑ ሰይፉን “በልብሱ ውስጥ በቀኝ ጭኑ” በኩል የደበቀው ሲሆን የንጉሡ ጠባቂዎች በዚያ በኩል ይፈትሻሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። በመሆኑም ምንም ዓይነት ችግር ሳያጋጥመው “ግብሩን . . . ለሞዓብ ንጉሥ ለዔግሎን አቀረበ።”—መሳፍንት 3:16, 17

ናዖድ ወደ ዔግሎን ቤተ መንግሥት እንደገባ ምን ነገሮች እንደተከናወኑ በዝርዝር አልተገለጸም። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሠፍሮ የምናገኘው “ናዖድም ግብሩን ካቀረበ በኋላ፣ ግብር ተሸክመው የመጡት ሰዎች ተመልሰው እንዲሄዱ አደረገ” የሚል አጭር መግለጫ ብቻ ነው። (መሳፍንት 3:18) ናዖድ ግብሩን ካቀረበና ዕቃውን ተሸክመው የመጡትን ሰዎች ከዔግሎን ቤተ መንግሥት ራቅ ወዳለ አካባቢ ወስዶ ካሰናበታቸው በኋላ ተመልሶ መጣ። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? እነዚህን ሰዎች ይዟቸው የመጣው ጥበቃ እንዲያደርጉለት ነው? ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲገባ ማሟላት ያለበት ግዴታ ስለሆነ ነው? ወይስ ግብሩን ተሸክመው እንዲያደርሱለት ብቻ ብሎ ነው? ደግሞስ እቅዱን ተግባራዊ ከማድረጉ በፊት ለደኅንነታቸው በማሰብ ከአካባቢው ርቀው እንዲሄዱ ፈልጎ ይሆን? ናዖድ ሰዎቹን ያሰናበተበት ምክንያት የትኛውም ቢሆን ብቻውን ወደ ቤተ መንግሥቱ በድፍረት ተመልሷል።

“[ናዖድ] ጌልጌላ አጠገብ ድንጋዮች ተጠርበው ከሚወጡበት አካባቢ ሲደርስ ወደ ኋላ በመመለስ ወደ ንጉሡ ሄዶ፣ ‘ንጉሥ ሆይ፤ በምስጢር የምነግርህ ነገር አለኝ’ አለው።” ዔግሎን ፊት እንደገና ሊቀርብ የቻለው እንዴት እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ጠባቂዎቹ ጥርጣሬ ሊያድርባቸው አይገባም ነበር? አንድ እስራኤላዊ ብቻውን በንጉሣቸው ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት የለም ብለው አስበው ይሆን? ናዖድ ብቻውን መመለሱ የአገሩን ሰዎች ከድቷል የሚል ግምት አሳድሮ ይሆን? ያም ሆነ ይህ ናዖድ ንጉሡን ለብቻው ማነጋገር ፈልጓል፤ አጋጣሚውም ተፈቅዶለታል።—መሳፍንት 3:19

በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው ዘገባ በመቀጠል እንዲህ ይላል:- “ንጉሡ ሰገነት ላይ ባለው ነፋሻ ዕልፍኝ ውስጥ ብቻውን ተቀምጦ ሳለ ናዖድ ቀረብ ብሎ፣ ‘ከእግዚአብሔር ዘንድ ለአንተ ያመጣሁት መልእክት አለኝ’ አለው።” ናዖድ ከአምላክ ያመጣው በቃል የሚነገር መልእክት እንዳለ መግለጹ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በያዘው ሰይፍ ሊወጋው መዘጋጀቱን መናገሩ ነበር። ንጉሡ ከአምላኩ ከካሞሽ የመጣለት መልእክት ያለ መስሎት ሳይሆን አይቀርም “ከዙፋኑ ተነሣ።” ናዖድ ከመቅፅበት ሰይፉን መዝዞ የዔግሎን ሆድ ላይ ሻጠው። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሰይፉ በስለቱና በእጀታው መካከል መግቻ አልነበረውም። በመሆኑም “እጀታው ሳይቀር ሰይፉ እንዳለ ሆዱ ውስጥ ገባ፤ ስለቱም በጀርባው ወጣ፤ ሞራም ስለቱን ሸፈነው፤ . . . አንጀቱ[ም] ተዘረገፈ።”—መሳፍንት 3:20-22

ያለምንም ችግር አመለጠ

ናዖድ ሰይፉን ከሆዱ ለማውጣት ጊዜ ሳያባክን “በዕልፍኙ መግቢያ ወጣ፤ የዕልፍኙንም በር በንጉሡ ላይ ዘግቶ ቈለፈው። ናዖድ ከሄደ በኋላ፣ የንጉሡ አገልጋዮች ሲመጡ፣ የዕልፍኙ በር ተቈልፎ አገኙት፤ እነርሱም ‘በውስጠኛው ክፍል እየተጸዳዳ ይሆናል’ አሉ።”—መሳፍንት 3:23, 24

ናዖድ የወጣበት ‘የዕልፍኝ መግቢያ’ የተባለው ምን ያመለክታል? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “[የዕብራይስጡን ቃል] ትክክለኛ ትርጉም ማወቅ አይቻልም፣” ሆኖም “‘በረንዳ’ ወይም ‘ኮሪደር’ እንደሆነ ይገመታል” በማለት ይገልጻል። ናዖድ በሩን ከውስጥ በኩል ቆልፎ በሌላ መንገድ ወጥቶ ይሆን? ወይስ የበሩን ቁልፍ ከሞተው ንጉሥ ላይ ወስዶ ከውጭ በኩል ቆልፎት ይሆን? ከዚያም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ በማስመሰል በጠባቂዎቹ ፊት ተረጋግቶ አልፎ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ ናዖድ የተጠቀመበት ዘዴ የትኛውም ቢሆን የዔግሎን አገልጋዮች በሩን ተቆልፎ ሲያገኙት ወዲያውኑ የጠረጠሩት ነገር አልነበረም። ንጉሡ “እየተጸዳዳ ይሆናል” ብለው አሰቡ።

የንጉሡ አገልጋዮች በሩ እስኪከፈት እየተጠባበቁ ባለበት ሰዓት ናዖድ አመለጠ። ከዚያም የአገሩን ሰዎች ጠርቶ “ጠላታችሁን ሞዓብን እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ስለ ሰጣችሁ ተከተሉኝ” አላቸው። የዮርዳኖስን ወንዝ መሻገር የሚቻልባቸውን ቁልፍ ቦታዎች በመያዝ መሪያቸውን ያጡት ሞዓባውያን ወደ አገራቸው ሸሽተው እንዳይሄዱ መንገዱን ዘጉባቸው። ከዚህም የተነሳ “በዚያን ጊዜ ብርቱና ኀይለኛ የሆኑ ዐሥር ሺህ ሞዓባውያንን ገደሉ፤ አንድም ሰው አላመለጠም። በዚያን ቀን ሞዓብ በእስራኤል ድል ሆነች፤ ምድሪቱም ለሰማንያ ዓመት ሰላም አገኘች።”—መሳፍንት 3:25-30

ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት

በይሖዋ ፊት ክፉ ድርጊት መፈጸም አስከፊ መዘዝ እንደሚያስከትል በናዖድ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ትምህርት እናገኛለን። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ በሠሩት ጥፋት ተጸጽተው ወደ እርሱ የሚመለሱ ሰዎችን ይረዳቸዋል።

ናዖድ እቅዱ ሊሰምርለት የቻለው የረቀቀ ጥበብ በመጠቀሙ ወይም ደግሞ የጠላት ወገን ድክመት በማሳየቱ አይደለም። የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን ማግኘቱ በሰዎች ላይ የተመካ አይደለም። ናዖድ ስኬት እንዲያገኝ ያስቻለው ዋናው ነገር መለኮታዊ ድጋፍ ማግኘቱ ነው። ምንም ነገር ሊያግደው ከማይችለው ይሖዋ ሕዝቡን ነጻ ለማውጣት ካለው ፈቃድ ጋር የሚስማማ እርምጃ መውሰዱ የእርሱን ድጋፍ እንዲያገኝ አስችሎታል። ናዖድን ያስነሳው አምላክ ከመሆኑም በላይ ‘መሳፍንትን ለሕዝቦቹ ባስነሣላቸው ቁጥር ከመስፍኑ ጋር ይሆን’ ነበር።—መሳፍንት 2:18፤ 3:15