በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዘፀአት 4:24-26 በተገለጸው ሁኔታ ላይ የተፈጸመው ነገር ምንድን ነው? ሊገደል የነበረውስ ማን ነው?

ሙሴ ሚስቱን ሲፓራን እንዲሁም ጌርሳምና አልዓዛር የተባሉ ወንዶች ልጆቹን ይዞ ወደ ግብፅ እያመራ በነበረበት ወቅት የሚከተለው ሁኔታ ተከሰተ:- “እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ ባደረበት ስፍራ እግዚአብሔር ተገናኘው፣ ሊገድለውም ፈለገ። ሲፓራም ሚስቱ ባልጩት ወሰደች፣ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፣ ወደ እግሩም ጣለችው:- አንተ ለእኔ የደም ሙሽራ ነህ አለች። ከእርሱም ፈቀቅ አለ። የዚያን ጊዜ:- ስለ ግርዛቱ አንተ የደም ሙሽራ ነህ አለች።” (ዘፀአት 4:20, 24-26 የ1954 ትርጉም) የጥቅሱ ሐሳብ ለመረዳት የሚያስቸግርና ትርጉሙን በእርግጠኝነት መናገር የማይቻል ቢሆንም ቅዱሳን ጽሑፎች ጥቅሱን በመጠኑ ግልጽ ያደርጉልናል።

ዘገባው ሊገደል የነበረው ማን እንደሆነ በግልጽ አይናገርም። ይሁንና ሙሴ እስራኤላውያንን ከግብፅ እንዲያወጣ መለኮታዊ ተልእኮ የተሰጠው በመሆኑ ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው እርሱ አይደለም ብለን መደምደማችን ምክንያታዊ ነው። (ዘፀአት 3:10) ይህን ተልእኮ ለመወጣት በጉዞ ላይ እያለ የአምላክ መልአክ እርሱን ለመግደል ይቃጣል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። በመሆኑም ሊገደል የነበረው ከልጆቹ መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል። ግርዘትን በተመለከተ ቀደም ሲል ለአብርሃም የተሰጠው ሕግ እንዲህ ይላል:- “የሥጋ ሸለፈቱን ያልተገረዘ ማንኛውም ወንድ ኪዳኔን በማፍረሱ ከወገኖቹ ይወገድ።” (ዘፍጥረት 17:14) ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሙሴ ልጁን የመግረዝ ኃላፊነቱን ሳይወጣ ቀርቷል። በዚህም ምክንያት የይሖዋ መልአክ ልጁን ሊገድለው ነበር።

ሲፓራ ልጅዋን ከሞት ለማዳን በወሰደችው እርምጃ ሸለፈቱን የጣለችው የማን እግር ላይ ነበር? ያልተገረዘውን ልጅ የመግደል ሥልጣን የተሰጠው መልአኩ ነበር። በመሆኑም ሲፓራ ሕጉን ማክበሯን ለማሳየት ሸለፈቱን የመልአኩ እግር ላይ ጥላው መሆን አለበት።

ሲፓራ “አንተ የደም ሙሽራ ነህ” በማለት የተናገረችው ሐሳብ ያልተለመደ አባባል ነው። ይህ አባባሏ ምን ያመለክታል? ሲፖራ የግርዘት ቃል ኪዳን የሚጠይቀውን ግዴታ ማሟላቷ ይሖዋ ያቋቋመውን ቃል ኪዳን እንደተቀበለች ያሳያል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጋር በገባው በሕጉ ቃል ኪዳን አማካኝነት በመካከላቸው በተመሠረተው ዝምድና እርሱ እንደ ባል እነርሱ ደግሞ እንደ ሚስት ተደርገው ተቆጥረዋል። (ኤርምያስ 31:32) በመሆኑም ሲፓራ ይሖዋ (እርሱን ወክሎ የመጣው መልአክ) “የደም ሙሽራ” እንደሆነ ስትናገር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዞ ለሚመጣው ግዴታ ተገዢ መሆኗን መግለጿ ሊሆን ይችላል። ከግርዘት ቃል ኪዳኑ ጋር በተያያዘ ይሖዋ አምላክ የባልነት ቦታውን ሲይዝ እርሷ ደግሞ የሚስትነት ቦታውን የተቀበለች ያህል ነው። ያም ሆነ ይህ አምላክ ያወጣውን ሕግ ለማክበር ፈጣን እርምጃ በመውሰዷ የልጅዋ ሕይወት ከሞት ሊተርፍ ችሏል።