በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን”

“የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን”

“የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን”

“በሁኔታዎች ሁሉ የረጋህ ሁን፤ . . . የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን።”—2 ጢሞቴዎስ 4:5

1. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የሰጣቸው ተልዕኮ ምንድን ነው?

 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ስምና ዓላማ በመላው ምድር እየታወጀ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ኢየሱስ “ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው” ሲል የሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ስለሚጥሩ ነው።—ማቴዎስ 28:19, 20

2. የበላይ ተመልካች የነበረው ጢሞቴዎስ ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቶታል? ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች አገልግሎታቸውን መፈጸም የሚችሉበት አንዱ መንገድስ ምንድን ነው?

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ተልእኮ በቁም ነገር ተመልክተውታል። ለምሳሌ ያህል ሐዋርያው ጳውሎስ የበላይ ተመልካች የነበረውን ጢሞቴዎስን “የወንጌል ሰባኪን ተግባር አከናውን፤ አገልግሎትህን ፈጽም” ሲል አሳስቦታል። (2 ጢሞቴዎስ 4:5) በዛሬው ጊዜ አንድ የበላይ ተመልካች የአምላክን መንግሥት በቅንዓት በማወጅና በመስክ አገልግሎት አዘውትሮ በመካፈል አገልግሎቱን ይፈጽማል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካች በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆኖ የማገልገልና ሌሎችን የማሰልጠን ግሩም መብት አለው። ጳውሎስ ምሥራቹን የማወጅ ግዴታውን በሚገባ ከመወጣቱም በላይ ሌሎችን ለዚህ ሥራ አሠልጥኗል።—የሐዋርያት ሥራ 20:20፤ 1 ቆሮንቶስ 9:16, 17

የጥንቶቹ ቀናተኛ ወንጌላውያን

3, 4. ፊልጶስ በወንጌላዊነቱ ምን ተሞክሮዎች አጋጥመውታል?

3 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ቀናተኛ ወንጌላውያን ነበሩ። ወንጌላዊውን ፊልጶስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ፊልጶስ በኢየሩሳሌም ለነበሩ ግሪክኛ ተናጋሪና ዕብራይስጥ ተናጋሪ ክርስቲያን መበለቶች በየዕለቱ ያለ አድልዎ ምግብ እንዲያድሉ ከተመረጡት ‘በመንፈስ ቅዱስና በጥበብ የተሞሉ ለመሆናቸው ከተመሰከረላቸው ሰባት ሰዎች’ መካከል አንዱ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 6:1-6) ይህ ሥራ ሲያቆምና ከሐዋርያት በቀር ሁሉም ክርስቲያኖች በስደት ምክንያት ወደተለያየ ቦታ ሲበተኑ ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ሄደ። በዚያም ምሥራቹን ከመስበኩም በላይ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ርኩሳን መናፍስትን አውጥቷል፤ እንዲሁም አንካሶችንና ሽባዎችን ፈውሷል። ብዙዎቹ የሰማርያ ነዋሪዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት ተቀብለው ተጠመቁ። በኢየሩሳሌም ያሉት ሐዋርያት ይህን ሲሰሙ የተጠመቁት አዳዲስ አማኞች መንፈስ ቅዱስን ይቀበሉ ዘንድ እንዲረዷቸው ሐዋርያው ጴጥሮስንና ዮሐንስን ወደ ሰማርያ ላኳቸው።—የሐዋርያት ሥራ 8:4-17

4 ከዚያም የአምላክ መንፈስ ፊልጶስን ወደ ጋዛ በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዘ ከነበረው ከኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጋር እንዲገናኝ አደረገው። “የኢትዮጰያ ንግሥት የህንደኬ ባለሟል” የነበረው ይህ ሰው ፊልጶስ የኢሳይያስን ትንቢት በሚገባ ካብራራለት በኋላ በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ተጠመቀ። (የሐዋርያት ሥራ 8:26-38) ከዚያም ፊልጶስ በሚያልፍባቸው “ከተሞች ሁሉ ወንጌልን” እየሰበከ ወደ አዛጦንና ወደ ቂሳርያ ሄደ። (የሐዋርያት ሥራ 8:39, 40) ፊልጶስ የወንጌላዊነትን ሥራ በማከናወን ረገድ ግሩም ምሳሌ ነው!

5. የፊልጶስ አራት ሴቶች ልጆች ምን በማከናወን ይታወቁ ነበር?

5 ይህ ከሆነ ከ20 ዓመት በኋላም ፊልጶስ በቂሳርያ በትጋት ይሰብክ ነበር። ጳውሎስና ሉቃስ ቤቱ ባረፉበት ወቅት “ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።” (የሐዋርያት ሥራ 21:8-10) እነዚህ ልጆች በመንፈሳዊ በጥሩ ሁኔታ ተኮትኩተው በማደጋቸው ለአገልግሎት ከፍተኛ ቅንዓት የነበራቸው ከመሆናቸውም በላይ ትንቢት የመናገር መብት እስከማግኘት ደርሰዋል። በዛሬው ጊዜ ወላጆች ለአገልግሎት ያላቸው ቅንዓት በልጆቻቸው ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ የሚኖረው ሲሆን ወንጌላዊነትን የዕድሜ ልክ ሥራቸው አድርገው እንዲይዙት ሊያነሳሳቸው ይችላል።

በዘመናችን ያሉ ቀናተኛ ወንጌላውያን

6. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ወንጌላውያን በስብከት ሥራቸው ምን ውጤት አግኝተዋል?

6 ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዘመናችንና ስለ መጨረሻው ቀን በተናገረው ታላቅ ትንቢት ‘አስቀድሞ ወንጌል ለሕዝብ ሁሉ መሰበክ አለበት’ ሲል ገልጿል። (ማርቆስ 13:10) መጨረሻው የሚመጣው ምሥራቹ “በዓለም ሁሉ” ከተሰበከ በኋላ ነው። (ማቴዎስ 24:14) ጳውሎስና ሌሎች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ወንጌላውያን ምሥራቹን በመስበካቸው ብዙ ሰዎች አማኞች ከመሆናቸውም በላይ በመላው የሮም ግዛት በተለያየ ቦታ አዳዲስ ጉባኤዎች ይመሠረቱ ነበር። በእነዚህ ጉባኤዎች እንዲያገለግሉ የተሾሙ ሽማግሌዎች ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ጋር ሆነው በዚህ የወንጌላዊነት ሥራ በመካፈል የስብከቱ ሥራ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርገዋል። በዘመናችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች በወንጌላዊነቱ ሥራ በመካፈላቸው እድገት እንደተገኘ ሁሉ በዚያ ዘመንም የይሖዋ ቃል እያደገና እየተስፋፋ ሄዶ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 19:20) አንተስ በዛሬው ጊዜ ይሖዋን በደስታ ከሚያወድሱት ሕዝቦቹ ጎን ተሰልፈሃል?

7. የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች በዛሬው ጊዜ ምን በማከናወን ላይ ናቸው?

7 ዛሬ ያሉ ብዙዎቹ የመንግሥቱ አስፋፊዎች በወንጌላዊነቱ ሥራ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማስፋት ጥረት እያደረጉ ነው። በሺዎች የሚቆጠሩ በሚስዮናዊነት በማገልገል ላይ ሲሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ የዘወትርና ረዳት አቅኚዎች በመሆን ሙሉ ጊዜያቸውን ለወንጌላዊነቱ ሥራ በማዋል ላይ ናቸው። ቀናተኛ የአምላክ መንግሥት ሰባኪዎች ሆነው የሚያገለግሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች የሚያስመሰግን ሥራ እያከናወኑ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዘው የወንጌላዊነቱን ሥራ በማከናወን የተትረፈረፈ በረከት በማግኘት ላይ ናቸው።—ሶፎንያስ 3:9

8. በግንባር ላይ ምልክት ከማድረግ ጋር የሚመሳሰል ምን ሥራ በመከናወን ላይ ነው? ይህን ሥራ እያከናወኑ ያሉትስ እነማን ናቸው?

8 አምላክ በመንፈስ የተቀቡት የኢየሱስ ተከታዮች በመላው ዓለም ምሥራቹን እንዲሰብኩ ኃላፊነት የሰጣቸው ሲሆን ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” በዚህ የወንጌላዊነት ሥራ ከጎናቸው ተሰልፈዋል። (ዮሐንስ 10:16) ይህ ሕይወት አድን ሥራ በሚያዝኑና በሚተክዙ ሰዎች ግንባር ላይ ምልክት ከማድረግ ጋር እንደሚመሳሰል ትንቢታዊ በሆነ መንገድ ተገልጿል። በቅርቡ ክፉዎች ይጠፋሉ። እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን ሕይወት አድን የሆነውን እውነት ለምድር ነዋሪዎች ማድረስ ምንኛ ታላቅ መብት ነው!—ሕዝቅኤል 9:4-6, 11

9. አዲሶችን በአገልግሎት መርዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

9 በወንጌላዊነቱ ሥራ በመካፈል ልምድ ያለን አስፋፊዎች በጉባኤ ውስጥ ያሉ አዲሶችን መርዳት እንደምንችል የታወቀ ነው። አልፎ አልፎ አብረውን እንዲያገለግሉ ልንጋብዛቸው እንችላለን። የጉባኤ ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መንፈሳዊነት ለመገንባት የተቻላቸውን ጥረት ያደርጋሉ። ትሑት የሆኑ የበላይ ተመልካቾች መልካም ጥረት፣ ሌሎችም ቀናተኛና ፍሬያማ ወንጌላውያን እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል።—2 ጴጥሮስ 1:5-8

ከቤት ወደ ቤት መመስከር

10. ክርስቶስም ሆነ የጥንት ተከታዮቹ በአገልግሎት ምን ምሳሌ ትተዋል?

10 ኢየሱስ ክርስቶስ ባከናወነው የወንጌላዊነት ሥራ ለተከታዮቹ ግሩም ምሳሌ ትቶላቸዋል። የአምላክ ቃል ክርስቶስ ከሐዋርያቱ ጋር ስላከናወነው አገልግሎት ሲገልጽ “የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ በየከተማውና በየመንደሩ አለፈ። ዐሥራ ሁለቱም ከእርሱ ጋር ነበሩ” ይላል። (ሉቃስ 8:1) ስለ ራሳቸው ስለ ሐዋርያትስ ምን ለማለት ይቻላል? በ33 በጰንጠቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው በኋላ “በየዕለቱም፣ በቤተ መቅደስም ሆነ በየቤቱ፣ ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ከማስተማርና ከመስበክ ከቶ ወደ ኋላ አላሉም ነበር።”—የሐዋርያት ሥራ 5:42

11. በሐዋርያት ሥራ 20:20, 21 ላይ በተገለጸው መሠረት ጳውሎስ ያከናወነው ምንድን ነው?

11 ጳውሎስ ቀናተኛ ወንጌላዊ ስለነበረ በኤፌሶን ለሚገኙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች “በአደባባይም ሆነ ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር፣ እናንተን ከማስተማርና ይጠቅማችኋል ብዬ ያሰብሁትን ከመስበክ ወደ ኋላ አላልሁም” በማለት ሊናገር ችሏል። ጳውሎስ ‘ከቤት ወደ ቤት በመዘዋወር ያስተምር’ ነበር ሲባል ይሖዋን ያመልኩ ለነበሩ የእምነት ባልንጀሮቹ እረኝነት ያደርግ ነበር ማለት ነው? አይደለም፤ ምክንያቱም “በንስሓ ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱና በጌታችን በኢየሱስ እንዲያምኑ፣ ለአይሁድም ለግሪክ ሰዎችም አጥብቄ መስክሬላቸዋልሁ” በማለት አክሎ ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 20:20, 21) ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑትን ክርስቲያኖች ‘በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ስለ መመለስና በጌታችን በኢየሱስ ስለ ማመን’ እንደ አዲስ ማስተማር እንደማያስፈልግ የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ አማኝ ያልሆኑትን ሰዎች ስለ ንስሐና ስለ እምነት በሚያስተምርበት ጊዜ በኤፌሶን ያሉትን ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እንዲያገለግሉ አሠልጥኗቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ በማድረግ ኢየሱስ ስብከቱን ለማከናወን የተጠቀመበትን ዘዴ ኮርጆአል።

12, 13. በፊልጵስዩስ 1:7 መሠረት የይሖዋ ሕዝቦች የመስበክ መብታቸውን ለማስከበር ምን አድርገዋል?

12 ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገል ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንዳንድ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ልንነግራቸው ቤታቸው ስንሄድ ይበሳጫሉ። እርግጥ ነው፣ እኛ ሰዎችን ማበሳጨት አንፈልግም። ሆኖም ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገልን መጽሐፍ ቅዱስ የሚደግፈው ከመሆኑም በላይ ለአምላክና ለሰዎች ያለን ፍቅር በዚህ የአገልግሎት መስክ እንድንሳተፍ ግድ ይለናል። (ማርቆስ 12:28-31) ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ የመስበክ መብታችንን በሕግ ለማስከበርና ‘መከላከያ ለማቅረብ’ የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች ቆመን ተሟግተናል። (ፊልጵስዩስ 1:7 የ1980 ትርጉም) ይህ ፍርድ ቤት በሁሉም ጊዜያት ለማለት ይቻላል ለእኛ ፈርዶልናል። የሚከተለው ብያኔ ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው፦

13 “ሃይማኖታዊ ትራክቶችን ማሰራጨት የማተሚያ መሣሪያዎች ከተፈለሰፉበት ዘመን ጀምሮ ወንጌልን ለማስፋፋት እንደ ዋነኛ ዘዴ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ባለፉት በርካታ ዓመታት የተለያዩ ሃይማኖቶች ይህን ዘዴ ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ይህን በስፋት የሚጠቀሙበት ሲሆን ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን የሚያሰራጩ አባሎቻቸው ተከታዮችን ለማፍራት በየቤቱ እየሄዱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ወንጌልን ያዳርሳሉ። . . . ይህ ዓይነቱ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ በመጀመሪያው [የዩናይትድ ስቴትስ ሕገ መንግሥታዊ] ማሻሻያ በአብያተ ክርስቲያናት ከሚከናወነው አምልኮና ከመስበኪያ ሰገነት ከሚቀርብ ስብከት የማይተናነስ እውቅና ተሰጥቶታል።”—ከሳሽ መርዶክና ተከሳሽ ፔንስልቬንያ 1943

መስበካችንን የምንቀጥለው ለምንድን ነው?

14. አገልግሎታችን ውሎ አድሮ ምን ውጤት ሊያስገኝ ይችላል?

14 ከቤት ወደ ቤት እየሄድን የምንሰብክበት ብዙ ምክንያት አለን። ሰዎችን ባነጋገርን ቁጥር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በልባቸው ውስጥ ለመትከል እንጥራለን። ከዚያም ተመልሰን በማነጋገር የተከልነውን እናጠጣለን። እንደዚህ ማድረጋችን ውሎ አድሮ ጥሩ ውጤት ያስገኛል። ስለሆነም ጳውሎስ “እኔ ተከልሁ፤ አጵሎስ ውሃ አጠጣ፤ ያሳደገው ግን እግዚአብሔር ነው” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 3:6) እንግዲያው ‘ይሖዋ እንደሚያሳድገው’ በመተማመን ‘መትከላችንንና ማጠጣታችንን’ እንቀጥል።

15, 16. ሰዎችን በተደጋጋሚ ቤታቸው እየሄድን የምናነጋግራቸው ለምንድን ነው?

15 የሰዎች ሕይወት በአደጋ ላይ ስለሚገኝ በወንጌላዊነቱ ሥራ እንካፈላለን። በመስበክ የራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን ሰዎች ሕይወት እናድናለን። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) የአንድ ሰው ሕይወት አደጋ ላይ እንደወደቀ ብናውቅ እርሱን ለመርዳት ባለ በሌለ ኃይላችን አንጥርምን? እንዲህ እንደምናደርግ የታወቀ ነው! በተመሳሳይም የሰዎችን ሕይወት ለማዳን ስንል ያለማሰለስ ቤታቸው እየሄድን እናነጋግራቸዋለን። ሰዎች ያሉበት ሁኔታ በየጊዜው ይለዋወጣል። በአንድ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ጊዜ የለኝም ብሎ የነበረ ሰው በሌላ ጊዜ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ድጋሚ በምንሄድበት ጊዜ ቀደም ሲል ያላገኘነውን ሌላ የቤተሰቡን አባል ልናገኝና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ልናወያየው እንችላለን።

16 የሰዎች ሁኔታ ብቻ ሳይሆን አመለካከታቸውም ሊለወጥ ይችላል። ለምሳሌ አንድ ግለሰብ የሚወደውን ሰው በሞት ማጣቱ ያስከተለበት መሪር ሐዘን ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን መልእክት ለመስማት ጆሮውን እንዲሰጥ ሊገፋፋው ይችላል። ይህን ሰው ልናጽናናው እንዲሁም ለመንፈሳዊ ፍላጎቱ ትኩረት እንዲሰጥና ይህን ፍላጎቱን እንዴት ማርካት እንደሚችል እንዲገነዘብ ልንረዳው እንችላለን።—ማቴዎስ 5:3, 4

17. እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው?

17 ከቤት ወደ ቤት በመሄድ እንድንመሰክርም ሆነ በሌላ ክርስቲያናዊ የአገልግሎት ዘርፍ እንድንካፈል የሚገፋፋን ዋነኛ ምክንያት የይሖዋ ስም እንዲታወቅ ያለን ልባዊ ፍላጎት ነው። (ዘፀአት 9:16፤ መዝሙር 83:18) የወንጌላዊነት ሥራችን እውነትንና ጽድቅን የሚወዱ ሰዎች ይሖዋን እንዲያወድሱ የሚረዳ መሆኑ እንዴት የሚያስደስት ነው! መዝሙራዊው “ወጣት ወንዶችና ደናግል፣ አረጋውያንና ልጆች ያመስግኑት። ስሙ ብቻውን ከፍ ያለ ነውና፣ ክብሩም ከምድርና ከሰማይ በላይ ነውና፣ እነዚህ ሁሉ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ” ሲል ዘምሯል።—መዝሙር 148:12, 13

ወንጌላዊነት በግል የሚያስገኝልን ጥቅም

18. በወንጌላዊነቱ ሥራ በመካፈላችን ምን ጥቅም እናገኛለን?

18 የወንጌላዊነት ሥራ በግለሰብ ደረጃ የተለያዩ ጥቅሞች ያስገኝልናል። ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት እየሄድን መስበካችን ትሕትናን እንድናዳብር ይረዳናል። በተለይ ደግሞ ሰዎች ሲያመናጭቁን ይህን ባሕርይ ማሳየት ይኖርብናል። በወንጌላዊነት ሥራችን ውጤታማ ለመሆን ‘አንዳንዶችን ያድን ዘንድ ከሁሉም ጋር ሁሉን ነገር እንደሆነው’ እንደ ጳውሎስ መሆን አለብን። (1 ቆሮንቶስ 9:19-23) በአገልግሎት የምናገኘው ተሞክሮ ብልሃተኞች እንድንሆን ይረዳናል። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመንና የምንናገራቸውን ቃላት በጥንቃቄ በመምረጥ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን፦ “ለእያንዳንዱ ሰው እንዴት መልስ መስጠት እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ በጨው እንደተቀመመ ሁልጊዜ በጸጋ የተሞላ ይሁን።”—ቆላስይስ 4:6

19. መንፈስ ቅዱስ ወንጌላውያንን የሚረዳው እንዴት ነው?

19 በወንጌላዊነቱ ሥራ መካፈላችን በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንድንታመንም ይገፋፋናል። (ዘካርያስ 4:6) በመንፈስ ቅዱስ ከታመንን ደግሞ በአገልግሎታችን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ የሆኑትን ‘ፍቅርን፣ ደስታን፣ ሰላምን፣ ትዕግሥትን፣ ቸርነትን፣ በጎነትን፣ እምነትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን’ እናፈራለን። (ገላትያ 5:22, 23) ምሥራቹን ስንሰብክ የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተላችን ፍቅር እንድናሳይ፣ ደስተኞች፣ ሰላማውያን፣ ታጋሾችና ደጎች እንድንሆን፣ ቸርነትንና እምነትን እንድናሳይ እንዲሁም ራሳችንን እንድንገዛ ስለሚረዳን ከሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት በእጅጉ ሊጠቅመን ይችላል።

20, 21. በወንጌላዊነቱ ሥራ ራሳችንን ማስጠመዳችን የሚያስገኛቸው አንዳንድ በረከቶችና ጥቅሞች ምንድን ናቸው?

20 በተጨማሪም ወንጌላውያን መሆናችን ለሌሎች እንድናዝንና እንድንራራ ያደርገናል። ሰዎች እንደ በሽታ፣ ሥራ አጥነትና የቤተሰብ ችግር ያሉ በዕለታዊ ሕይወታቸው የሚያጋጥሟቸውን ሁኔታዎች ሲያዋዩን ከራሳችን ያመነጨነውን ምክር ከመለገስ ይልቅ የሚያበረታቱና የሚያጽናኑ ጥቅሶችን እናነብላቸዋለን። የጽድቅ ዝንባሌ ያላቸው በመንፈሳዊ የታወሩ ሰዎች ሁኔታ ያሳስበናል። (2 ቆሮንቶስ 4:4) ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁ’ ሰዎችን በመንፈሳዊ መርዳት መቻል ምንኛ ታላቅ በረከት ነው!—የሐዋርያት ሥራ 13:48

21 በወንጌላዊነቱ ሥራ ዘወትር መካፈላችን አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል። (ሉቃስ 11:34) ይህ በእርግጥም ጠቃሚ ነው፤ አለበለዚያ ይህ ዓለም በሚያቀርባቸው ቁሳዊ ነገሮች ተታልለን ልንወሰድ እንችላለን። ሐዋርያው ዮሐንስ ለክርስቲያኖች የሚከተለውን ጥብቅ ምክር ሰጥቷል፦ “ዓለምን ወይም በዓለም ያለውን ማናቸውንም ነገር አትውደዱ፤ ማንም ዓለምን ቢወድ፣ የአብ ፍቅር በእርሱ ዘንድ የለም፤ ምክንያቱም በዓለም ያለው ሁሉ፦ የሥጋ ምኞት፣ የዐይን አምሮትና የኑሮ ትምክሕት ከዓለም እንጂ ከአብ የሚመጣ አይደለም። ዓለምና ምኞቱ ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚፈጽም ግን ለዘላለም ይኖራል።” (1 ዮሐንስ 2:15-17) የጌታ ሥራ የበዛልን በመሆን በወንጌላዊነቱ ሥራ ራሳችንን ማስጠመዳችን ዓለምን ከመውደድ እንድንቆጠብ ይረዳናል።—1 ቆሮንቶስ 15:58

በሰማይ ሀብት አከማቹ

22, 23. (ሀ) ክርስቲያን ወንጌላውያን የሚያከማቹት ሀብት ምንድን ነው? (ለ) የሚቀጥለው ርዕስ ስለ ምን ነገር ያብራራል?

22 ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት መስበክ ዘላቂ ጥቅሞች አሉት። ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ በመናገር ይህን አመልክቷል፦ “ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በሚችልበት በዚህ ምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ። ነገር ግን ብል ሊበላው፣ ዝገት ሊያበላሸው፣ ሌባም ቈፍሮ ሊሰርቀው በማይችልበት በዚያ በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ፤ ሀብትህ ባለበት ልብህም በዚያው ይሆናልና።”—ማቴዎስ 6:19-21

23 የሉዓላዊው ጌታ የይሖዋ ምሥክሮች መሆንና እሱን ማገልገል ታላቅ መብት እንደሆነ በመገንዘብ በሰማይ ሀብት ማከማቸታችንን እንቀጥል። (ኢሳይያስ 43:10-12) በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አንዲት እህት በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፉት ረጅም ዘመን የሚሰማቸውን እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “የተለያዩ ድክመቶች ቢኖሩብኝም ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት እሱን እንዳገለግለው መብት ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ። አባታዊ ፍቅሩ ለዘላለም እንዳይለየኝ ከልብ እጸልያለሁ።” እኛም አምላክን የማገልገል ተልእኳችንን ለመፈጸም በምንጥርበት ጊዜ እንዲህ እንደሚሰማን የታወቀ ነው። ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና እንደ ውድ ሀብት አድርገን የምንመለከተው ከሆነ የወንጌላዊነት ሥራችንን በተሟላ መልክ እንፈጽማለን። የሚቀጥለው ርዕስ አገልግሎታችንን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም የምንችልባቸውን መንገዶች ያብራራልናል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የወንጌላዊነትን ሥራ መፈጸም ያለብን ለምንድን ነው?

• በጥንት ዘመንም ሆነ በዘመናችን ያሉ ወንጌላውያን ስላከናወኑት ሥራ ምን ለማለት ይቻላል?

• ከቤት ወደ ቤት እየሄድን የምንሰብከው ለምንድን ነው?

• የወንጌላዊነትን ሥራ በማከናወን በግልህ ልትጠቀም የምትችለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ፊልጶስና ሴቶች ልጆቹ ሁሉ ዛሬም ደስተኛ ወንጌላውያን አሉ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ምሥራቹን ለሌሎች በማካፈል በግል የምታገኘው ጥቅም ምንድን ነው?