በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት—በአውሮፓ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ

የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት—በአውሮፓ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ

የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት—በአውሮፓ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ

“በርካታ የአውሮፓ መሪዎች ልክ እንደ ዛሬው በአንድ ላይ የሚሰበሰቡት ከስንት አንዴ እንደሆነ የታወቀ ነው።” በጥቅምት 1998 በተደረገ ስብሰባ ላይ ይህን የተናገሩት የጀርመን ፌደራል ሪፑብሊክ ፕሬዚዳንት የነበሩት ሮማን ሄርሶክ ሲሆኑ ከተሰብሳቢዎቹ መካከል አራት ነገሥታት፣ አራት ንግሥቶች፣ ሁለት ልዑላን፣ አንድ መስፍንና በርካታ ፕሬዚዳንቶች ይገኙበት ነበር። በአውሮፓ ምክር ቤት የተዘጋጀው ይህ ስብሰባ በዘመናዊቷ ጀርመን የ50 ዓመት ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። የስብሰባው ዓላማ ምን ነበር?

ጥቅምት 1998 የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት 350ኛ ዓመት ክብረ በዓል ነበር። ብዙውን ጊዜ የሰላም ስምምነቶች የታሪክን አቅጣጫ የሚቀይሩ አበይት ክንውኖች ሲሆኑ የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት ደግሞ በዚህ ረገድ በዓይነቱ ልዩ ነበር። በ1648 የዚህ ስምምነት መፈረም የሠላሳው ዓመት ጦርነት እንዲያበቃ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ሉዓላዊ መንግሥታትን የያዘች ዘመናዊ አውሮፓ መወለዷን ያበሰረ ነበር።

ለዘመናት ጸንቶ የቆየው ሥርዓት ተናጋ

በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና የቅድስት ሮማ ሥርወ መንግሥት ከፍተኛ ሥልጣን ነበራቸው። የሮማ ሥርወ መንግሥት የተለያየ ስፋት ያላቸውን በመቶዎች የሚቆጠሩ ራስ ገዝ አስተዳደሮች ያቀፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኦስትሪያ፣ በቼክ ሪፑብሊክ፣ በምሥራቃዊ ፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በስዊዘርላንድ፣ በቤልጂየም፣ በሉክዘምበርግ፣ በኔዘርላንድና በተወሰኑ የኢጣሊያ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ቦታዎችን ያጠቃልል ነበር። የሥርወ መንግሥቱ ግዛት አብዛኛው ክፍል በጀርመን ክልል ውስጥ ይገኝ ስለነበር ከጊዜ በኋላ የጀርመን ሕዝብ ቅድስት የሮማ ግዛት ተብሎ ይጠራ ጀመር። እያንዳንዱ ራስ ገዝ አስተዳደር የራሱ መስፍን ነበረው። ንጉሠ ነገሥቱ ራሱ የሮማ ካቶሊክ ተከታይና የኦስትሪያ ሃብስበርግ ቤተሰብ አባል ነበር። በመሆኑም ዋናውን ሥልጣን የያዙት ሊቀ ጳጳሱና የሮማ ሥርወ መንግሥት ስለነበሩ አውሮፓ በሮማ ካቶሊኮች እጅ ውስጥ ነበረች።

ይሁን እንጂ በ16ኛው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን ይህ ለዘመናት የቆየ ሥርዓት ተናጋ። በመላው አውሮፓ ኅብረተሰቡ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ልቅነት አንገሽግሾት ነበር። እንደ ማርቲን ሉተርና ጆን ካልቪን ያሉት የተሃድሶ አራማጆች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ስለ መመለስ ማስተማር ጀመሩ። ሉተርና ካልቪን ሰፊ የሕዝብ ተቀባይነት ያገኙ ሲሆን እንቅስቃሴያቸውም እያደገ ሄዶ ታዋቂው የተሃድሶ ንቅናቄና የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች ብቅ አሉ። በተሃድሶ ንቅናቄው የተነሳም የሮማ ግዛት ካቶሊክ፣ ሉተራንና ካልቪኒስት ተብሎ በሦስት እምነቶች ተከፈለ።

ካቶሊኮቹ ፕሮቴስታንቶቹን በጥርጣሬ ዓይን ይመለከቷቸው የነበረ ሲሆን ፕሮቴስታንቶቹ ደግሞ የካቶሊክ ተቀናቃኞቻቸውን ይንቋቸው ነበር። ይህ ሁኔታ በ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የፕሮቴስታንት ኅብረትና የካቶሊክ ማኅበር እንዲመሠረቱ አደረገ። ከሥርወ መንግሥቱ መሳፍንት መካከል አንዳንዶቹ የፕሮቴስታንት ኅብረቱን ሌሎቹ ደግሞ የካቶሊኮቹን ማኅበር ተቀላቀሉ። በዚህ ወቅት በአውሮፓ በተለይም በቅድስት ሮማ ሥርወ መንግሥት ግዛት ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ የነበረ ሲሆን በጥርጣሬ ዓይን የሚተያዩት ሁለቱም ወገኖች ወደ ጦርነት ለማምራት በቋፍ ላይ ነበሩ። በመጨረሻም ግጭቱ ሲቀሰቀስ ለቀጣዮቹ 30 ዓመታት የዘለቀ ጦርነት ተጀመረ።

አውሮፓ በጦርነት ታመሰች

የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑት መሳፍንት ተጨማሪ የአምልኮ ነጻነት እንዲሰጣቸው ካቶሊክ በሆነው የሃብስበርግ ሥርወ መንግሥት ላይ ግፊት ለማሳደር ሞከሩ። ካቶሊኮቹ ግን የተጠየቀውን ነጻነት የሰጡት እያንገራገሩ ሲሆን ይባስ ብሎ ከ1617-18 በቦሔሚያ (ቼክ ሪፑብሊክ) የሚገኙ ሁለት የሉተራን ቤተ ክርስቲያኖች በኃይል እንዲዘጉ አደረጉ። ይህ አድራጎት ያስቆጣቸው የፕሮቴስታንት መኳንንት በፕራግ ወደሚገኝ ቤተ መንግሥት ገብተው ሦስት የካቶሊክ ባለ ሥልጣናትን ከፎቅ በመስኮት ወረወሯቸው። በአውሮፓ የጦርነቱን እሳት ያቀጣጠለው ይህ ነበር።

የሁለቱም ተጻራሪ ሃይማኖቶች አባላት የሰላሙ መስፍን የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን ቢሉም አሁን ግን አንዳቸው ሌላውን ለማጥፋት ትግል ገጠሙ። (ኢሳይያስ 9:6) በኋይት ማውንቴይን በተደረገው ውጊያ የካቶሊኩ ማኅበር በፕሮቴስታንቶቹ ላይ ከፍተኛ ውድመት በማድረሱ ኅብረቱ ፈራረሰ። የፕሮቴስታንት መኳንንት በፕራግ የገበያ ሥፍራ ተገደሉ። በመላው የቦሔሚያ ግዛት ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ፕሮቴስታንቶች ንብረት በሙሉ ተወረሰና ለካቶሊኮቹ ተከፋፈለ። 1648—ክሬክ ኡንት ፍሬደን ኢን ኢሮፓ (1648—ጦርነትና ሰላም በአውሮፓ) የተባለው መጽሐፍ ይህን ድርጊት “በመካከለኛው አውሮፓ ከተፈጸሙት የንብረት ውርሶች በሙሉ ተወዳዳሪ የሌለው” በማለት ገልጾታል።

በቦሔሚያ በሃይማኖታዊ አለመቻቻል የተፈጠረው ግጭት እየተባባሰ ሄደና ዓለም አቀፋዊ የበላይነት ለማግኘት ወደሚደረግ ትግል ተሸጋገረ። በቀጣዮቹ 30 ዓመታት ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ኔዘርላንድ፣ ስፔይንና ስዊድንም ወደ ጦርነቱ ገቡ። ስግብግብነትና የሥልጣን ጥማት ያሰከራቸው ካቶሊክና ፕሮቴስታንት መሪዎች የፖለቲካ የበላይነትና የንግድ ጥቅም ለማግኘት ይሽቀዳደሙ ጀመር። የሠላሳው ዓመት ጦርነት በተለያዩ ደረጃዎች የተከፋፈለ ሲሆን እያንዳንዱ ደረጃ በጊዜው ንጉሠ ነገሥቱን ይፋለም በነበረው ወገን ስም ተሰይሟል። በርካታ የማመሣከሪያ ጽሑፎች አራት ደረጃዎችን የሚጠቅሱ ሲሆን እነርሱም የቦሔሚያ እና የፓላታይን ጦርነት፣ የዳኒሽ ሎወር ሳክሶኒ ጦርነት፣ የስዊድን ጦርነትና የፍራንኮ ስዊድን ጦርነት ናቸው። አብዛኛው ጦርነት የተደረገው በቅድስት ሮማ ግዛት ውስጥ ነበር።

በዘመኑ እንደ ሽጉጥ፣ ነፍጥ፣ አዳፍኔና መድፍ ያሉ የጦር መሣሪያዎች የነበሩ ሲሆን ስዊድን ዋነኛዋ መሣሪያ አቅራቢ ነበረች። ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ቀንደኛ የጦርነቱ አራጋቢዎች ነበሩ። ወታደሮች ወደ ውጊያ ሲሄዱ “ሳንታ ማሪያ” (ቅድስት ማርያም) ወይም “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” እያሉ ይጮሁ ነበር። እንዲሁም በጀርመን ግዛቶች ውስጥ ሲያልፉ መንደሮችን ይዘርፉና ተቃዋሚዎቻቸውንና ሰላማዊ ሰዎችን እንደ እንስሳት ያንገላቱ ነበር። በዚህም የተነሳ ጦርነቱ ቀስ በቀስ አረመኔያዊነት ይንጸባረቅበት ጀመር። ሁኔታው “አንዱ መንግሥት በሌላው መንግሥት ላይ ሰይፍ አያነሳም፤ ከእንግዲህም የጦርነት ትምህርት አይማሩም” ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ ነበር።—ሚክያስ 4:3

አንድ የጀርመን ትውልድ ያደገው ከጦርነት ሌላ ምንም ሳያውቅ ሲሆን ሕዝቡም ጦርነት ስለሰለቸው ሰላምን መናፈቅ ጀመረ። መሪዎቹ እርስ በርስ የሚጻረር የፓለቲካ ፍላጎት ባይኖራቸው ኖሮ ገና ድሮ ሰላም መስፈን በቻለ ነበር። እየዋለ እያደር ጦርነቱ ሃይማኖታዊ ገጽታውን እያጣና ፖለቲካዊ ይዘት እየተላበሰ ሄደ። የሚያስገርመው ለዚህ ለውጥ አስተዋጽኦ ያደረገው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሰው ነው።

ካርዲናል ሪሸሎው ክንዱን አሳየ

ከ1624 እስከ 1642 ድረስ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው አርማን ዣን ዱ ፕሌሴ በሰፊው የሚታወቀው ካርዲናል ደ ሪሸሎው በሚለው የማዕረግ ስሙ ነው። ሪሸሎው ፈረንሳይን በአውሮፓ ኃያል አገር የማድረግ ሕልም ነበረው። ይህንን ሕልሙን እውን ለማድረግም እንደ እርሱ ካቶሊክ የነበሩትን የሃብስበርግ ንጉሣዊ ቤተሰብን ሥልጣን ለማዳከም ይጥር ነበር። ይህ ጥረቱ የተሳካለት እንዴት ነበር? ከሃብስበርግ ቤተሰብ ጋር ይዋጉ የነበሩትን የጀርመን፣ የዴንማርክ፣ የኔዘርላንድና የስዊድን ሠራዊቶች በገንዘብ በመደገፍ ነው።

በ1635 ሪሸሎው ለመጀመሪያ ጊዜ የፈረንሳይ ወታደሮችን ወደ ጦር ግንባር ላከ። ቪቫት ፓክስ—ኤስ ላበ ደ ፍሬደ! (ሰላም ለዘላለም ይኑር!) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የሠላሳው ዓመት ጦርነት [ወደ መጨረሻ አካባቢ] በሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ጦርነት መሆኑ አብቅቶ ነበር። . . . ጦርነቱ በአውሮፓ የፖለቲካ የበላይነት ለመቀዳጀት የሚደረግ ትግል ሆነ።” በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል በተፈጠረው ሃይማኖታዊ ግጭት የተጀመረው ይህ ጦርነት ውሎ አድሮ ካቶሊኮች ከፕሮቴስታንቶች ጎን ቆመው ከሌሎች ካቶሊኮች ጋር የሚዋጉበት ጦርነት ወደመሆን ተሸጋገረ። ቀድሞውኑ በ1630ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተዳክሞ የነበረው የካቶሊክ ማኅበር በ1635 ሙሉ በሙሉ ፈረሰ።

በዌስትፋሊያ የተካሄደው የሰላም ድርድር

አውሮፓ በዝርፊያ፣ በነፍስ ግድያ፣ በአስገድዶ መድፈርና በቸነፈር ሳቢያ እንዳልነበረች ሆና ነበር። ጦርነቱ አሸናፊ የሌለው ጦርነት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ ሲሄድ ኅብረተሰቡ ሰላም የሚወርድበትን ጊዜ ይበልጥ መናፈቅ ጀመረ። ቪቫት ፓክስ—ኤስ ላበ ደ ፍሬደ! የተባለው መጽሐፍ “በ1630ዎቹ መገባደጃ አካባቢ በሥልጣን ላይ የነበሩት መሳፍንት ወታደራዊ ኃይል ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ እንደማያስችላቸው ተገንዝበው ነበር” ብሏል። ሆኖም ሰላም የሁሉም ጥያቄ ከሆነ ሊገኝ የሚችለው እንዴት ነው?

የሮማው ግዛት ንጉሠ ነገሥት የነበረው ፈርዲናንድ ሦስተኛ፣ የፈረንሳዩ ንጉሥ ሉዊስ 16ኛ እና የስዊድኗ ንግሥት ክርስቲና በጦርነቱ እጃቸው ያለበት አገሮች በሙሉ ተሰብስበው እርቀ ሰላም ለማውረድ የሚወያዩበት ስብሰባ መደረግ እንዳለበት ተስማሙ። ድርድሩ በጀርመን የዌስትፋሊያ ግዛት ውስጥ በሚገኙት የኦዝነብሩክና የሙንስተር ከተሞች እንዲካሄድ ተወሰነ። እነዚህ ከተሞች የተመረጡት ለስዊድንና ለፈረንሳይ ዋና ከተሞች አማካይ ቦታ ላይ ይገኙ ስለነበር ነው። ከዚያም ከ1643 ጀምሮ ወደ 150 የሚጠጉ የድርድሩ ልዑካን በርካታ አማካሪዎችን አስከትለው ወደ ሁለቱ ከተሞች መጉረፍ የጀመሩ ሲሆን የካቶሊኮቹ ተደራዳሪዎች በሙንስተር ፕሮቴስታንቶቹ ደግሞ በኦዝነብሩክ ተቀመጡ።

በመጀመሪያ እንደ ማዕረግ፣ ደረጃ፣ አቀማመጥና የድርድር ሥርዓት ያሉ ጉዳዮችን ጨምሮ ስብሰባው የሚካሄድበት ጠቅላላ ደንብ ተዘጋጀ። ከዚያም የመፍትሔ ሐሳቦች ከአንዱ ወገን ወደሌላው በአደራዳሪዎች አማካኝነት እየተላለፉ የሰላም ውይይቱ እንዲጀመር ተደረገ። በመጨረሻም ጦርነቱ እንደቀጠለ ለአምስት ዓመታት ከተደራደሩ በኋላ ስምምነት ላይ ተደረሰ። የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት የተፈረመው በተለያዩ ሰነዶች ላይ ነበር። አንደኛው ስምምነት በንጉሠ ነገሥት ፈርዲናንድ ሦስተኛና በስዊድን መካከል የተፈረመ ሲሆን ሌላው ደግሞ በንጉሠ ነገሥቱና በፈረንሳይ መካከል የተፈረመው ነው።

የስምምነቱ ወሬ ሲሰማ ሕዝቡ ደስታውን መግለጽ ጀመረ። በበርካታ ከተሞች ውስጥ ሰማዩ በርችት አሸበረቀ። የቤተ ክርስቲያን ደወሎች አስተጋቡ፣ መድፎች ተተኮሱ፣ ሰዎችም በጎዳናዎች ላይ ወጥተው ዘመሩ። አውሮፓ ዘላቂ ሰላም መጠበቅ ትችል ይሆን?

ዘላቂ ሰላም ማምጣት ይቻል ይሆን?

የዌስትፋሊያ የሰላም ስምምነት በሉዓላዊነት ጽንሰ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነበር። በሌላ አባባል የሰላም ስምምነቱን የፈረሙት ወገኖች በሙሉ አንዳቸው የሌላውን ድንበር ለማክበርና በውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ላለመግባት ተስማምተዋል። ይህም ሉዓላዊ መንግሥታትን ያቀፈች ዘመናዊ አውሮፓ እንድትፈጠር አድርጓል። ከእነዚህ መንግሥታት መካከል ግን አንዳንዶቹ ከስምምነቱ ያገኙት ጥቅም ከሌሎች ላቅ ያለ ነበር።

ፈረንሳይ ኃያል አገር መሆኗን ስታረጋግጥ ኔዘርላንድና ስዊዘርላንድ ደግሞ ነጻነታቸውን ተቀዳጁ። በአብዛኛው በጦርነቱ ለወደሙት የጀርመን ግዛቶች ግን ስምምነቱ ብዙም አልጠቀማቸውም። በተወሰነ መጠንም ቢሆን የጀርመን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በሌሎች አገሮች ነበር። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል፦ “የጀርመን መሳፍንት በስምምነቱ ጥቅም ማግኘታቸውም ሆነ አለማግኘታቸው የተመካው እንደ ፈረንሳይ፣ ስዊድንና ኦስትሪያ ባሉት ኃያላን አገሮች ፍላጎት ላይ ነበር።” የጀርመን ግዛቶች ኅብረት ፈጥረው አንድ መንግሥት በመመሥረት ፈንታ እንደቀድሞው እንደተበታተኑ ቀጠሉ። ከዚህም በላይ የተወሰነው የጀርመን ክፍልና እንደ ራይን፣ ኤልበና ኦደር ያሉት የጀርመን ትላልቅ ወንዞች ከሚፈስሱባቸው አካባቢዎች ውስጥ የተወሰኑት ለባዕድ አገሮች ተሰጡ።

ለካቶሊክ፣ ለሉተራንና ለካልቪኒስት ሃይማኖቶች እኩል እውቅና ተሰጣቸው። በዚህ የተደሰተው ግን ሁሉም አልነበረም። ሊቃነ ጳጳሳት ኢኖሰንት አሥረኛ ስምምነቱን ተቀባይነት የለውም በማለት አጥብቆ ተቃውሞታል። የሆነ ሆኖ ይህ ሃይማኖታዊ ክፍፍል በቀጣዮቹ ሦስት ክፍለ ዘመናት ሳይለወጥ ጸንቶ ቀጥሏል። በግለሰብ ደረጃ ሃይማኖታዊ ነጻነት ባይገኝም ቢያንስ አንድ እርምጃ መራመድ ተችሏል።

የሰላም ስምምነቱ ለሠላሳ ዓመት ለዘለቀው ጦርነትና በሕዝቡ መካከል ለተፈጠረው የጠላትነት ስሜት መቋጫ አበጅቶለታል። በአውሮፓ በሃይማኖት ሳቢያ መጠነ ሰፊ ጦርነት ሲደረግ ይህ የመጨረሻው ነበር። ሆኖም መንስኤው ከሃይማኖት ወደ ፖለቲካና ንግድ ተሸጋገረ እንጂ ጦርነት ሙሉ በሙሉ አልቀረም። እንዲህ ሲባል ግን ሃይማኖት በአውሮፓ ግጭቶች ውስጥ ያለውን ቦታ አጥቷል ማለት አይደለም። በአንደኛውና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች ወቅት የጀርመን ወታደሮች “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት ዘለበት ያለው ቀበቶ ይታጠቁ ነበር። በእነዚህ አሰቃቂ ጦርነቶች ወቅት ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ጎን ለጎን ሆነው በተቃራኒው ወገን ካሉ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ጋር ተፋልመዋል።

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የዌስትፋሊያው የሰላም ስምምነት ዘላቂ ሰላም አላመጣም። ይሁን እንጂ ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች በቅርቡ እንዲህ ዓይነቱን ሰላም ያገኛሉ። ይሖዋ አምላክ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ መሲሐዊ መንግሥት በኩል ለሰው ልጆች ዘላቂ ሰላም ያመጣላቸዋል። በዚህ መንግሥት አገዛዝ ሥር የሚኖረው አንድ እውነተኛ ሃይማኖት መከፋፈልን ሳይሆን አንድነትን ያመጣል። ማንም በሃይማኖታዊም ሆነ በሌሎች ምክንያቶች በሚነሱ ጦርነቶች አይካፈልም። የአምላክ መንግሥት አገዛዝ በመላው ምድር ላይ በሚሰፍንበትና ‘ለሰላሙም ብዛት ፍጻሜ በማይኖርበት’ ጊዜ ምንኛ እፎይታ ይሆናል!—ኢሳይያስ 9:6, 7

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች መካከል በተፈጠረው ግጭት የተጀመረው ይህ ጦርነት ውሎ አድሮ ካቶሊኮች ከፕሮቴስታንቶች ጎን ቆመው ከሌሎች ካቶሊኮች ጋር የሚዋጉበት ጦርነት ወደመሆን ተሸጋገረ

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ወታደሮች ወደ ውጊያ ሲሄዱ “ሳንታ ማሪያ” (ቅድስት ማርያም) ወይም “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” እያሉ ይጮሁ ነበር

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

From the book Spamers Illustrierte Weltgeschichte VI

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርዲናል ሪሸሎው

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሃይማኖታዊ መሪዎች በትግል ላይ፦ From the book Wider die Pfaffenherrschaft; map: The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሉተር፣ በካልቪንና በሊቀ ጳጳሱ መካከል የነበረውን ትግል የሚያሳይ የ16ኛው ክፍለ ዘመን ስዕል