በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

የይሖዋ ቃል ሕያው ነው

የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች

‘ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ’ በባርነት ተገዝቶ የነበረ ሕዝብ ነፃነቱን እንዴት እንደተጎናጸፈ የሚገልጽ እውነተኛ ታሪክ ይዟል። (ዘፀአት 1:13) ስለ አንድ ብሔር መወለድ የሚያወሳ ስሜት ቀስቃሽ ዘገባም ይገኝበታል። ትኩረት ከሚስቡት ገጽታዎቹ መካከል አስገራሚ የሆኑ ተዓምራት፣ በውስጡ የሰፈረው ፍጹም ሕግ እንዲሁም የመገናኛው ድንኳን ግንባታ አንዳንዶቹ ናቸው። የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች እነዚህ ናቸው።

ዕብራዊው ነቢይ ሙሴ የጻፈው የዘፀአት መጽሐፍ፣ ዮሴፍ ከሞተበት ከ1657 ከክርስቶስ ልደት በፊት አንስቶ የመገናኛው ድንኳን ተሠርቶ እስከተጠናቀቀበት እስከ 1512 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባሉት 145 ዓመታት እስራኤላውያን ያሳለፉትን ሕይወት ይተርካል። ይሁን እንጂ ዘፀአት የታሪክ መጽሐፍ ብቻ አይደለም። አምላክ ለሰው ልጆች የላከው መልእክት ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው። በመሆኑም ‘ሕያውና የሚሠራ ነው።’ (ዕብራውያን 4:12) ከዚህ አንጻር የዘፀአት መጽሐፍ ለእኛ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።

“እግዚአብሔርም የጩኸታቸውን ሲቃ ሰማ”

(ዘፀአት 1:1 እስከ 4:31)

በግብፅ የሚኖሩት የያዕቆብ ዝርያዎች ቁጥራቸው በጣም በመጨመሩ ንጉሡ በባርነት እንዲገዙ የሚያዝዝ ሕግ አወጣ። ፈርዖን ይህም አልበቃ ብሎት እስራኤላዊ የሆኑ ወንድ ሕፃናት በሙሉ እንዲገደሉ አወጀ። ከዚህ መዓት የተረፈ ለፈርዖን ሴት ልጅ በማደጎ የተሰጠ ሙሴ የተባለ የሦስት ወር ሕፃን ነበር። ሙሴ በንጉሣዊ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድግም 40 ዓመት ሲሆነው ለወገኖቹ በመቆርቆር አንድን ግብፃዊ ገደለ። (የሐዋርያት ሥራ 7:23, 24) ሕይወቱን ለማትረፍ መሸሽ ግድ ስለሆነበት ወደ ምድያም ኮበለለ። በዚያም ትዳር መሠረተና እረኛ ሆኖ ይኖር ጀመር። አንድ ቀን ተዓምራዊ በሆነ መንገድ በእሳት በተያያዘ ቁጥቋጦ አጠገብ ይሖዋ ለሙሴ ተገለጠለትና ወደ ግብፅ ተመልሶ እስራኤላውያንን ከባርነት ነጻ እንዲያወጣ ተልእኮ ሰጠው። ወንድሙ አሮን ቃል አቀባዩ እንዲሆን ተመረጠ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

3:1—ዮቶር ካህን የተባለው ከምን አንጻር ነው? በዕብራውያን አባቶች ዘመን አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ ካህን ሆኖ ያገለግል ነበር። ዮቶር የምድያማውያን ነገድ መንፈሳዊ መሪ ነበር። ምድያማውያን ኬጡራ ከተባለችው ሚስቱ የተወለዱ የአብርሃም ዝርያዎች በመሆናቸው ስለ ይሖዋ አምልኮ ሳያውቁ አይቀሩም።—ዘፍጥረት 25:1, 2

4:11ይሖዋ ሰውን ‘ደንቆሮ፣ ዲዳ እንዲሁም ዕውር ያደርጋል’ ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ሰዎችን ዓይነ ስውር እንዲሁም ዲዳ ያደረገባቸው ጊዜያት ቢኖሩም እንደዚህ ላሉት እክሎች በሙሉ ተጠያቂው እርሱ አይደለም። (ዘፍጥረት 19:11፤ ሉቃስ 1:20-22, 62-64) የእነዚህ ችግሮች መንስኤ የወረስነው ኃጢአት ነው። (ኢዮብ 14:4፤ ሮሜ 5:12) ሆኖም አምላክ ይህ ሁኔታ እንዲኖር በመፍቀዱ ሰውን ዲዳ፣ ደንቆሮ እንዲሁም ዕውር ‘እንደሚያደርግ’ ሊናገር ይችላል።

4:16ሙሴ ለአሮን “እንደ አምላኩ” የሆነለት እንዴት ነው? ሙሴ የአምላክ ወኪል ነበር። በመሆኑም ሙሴ፣ እርሱን ወክሎ ለሚናገረው ለአሮን “እንደ አምላኩ” ሆኖለታል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

1:7, 14 ይሖዋ ሕዝቡ በግብፅ ጭቆና ሲደርስባቸው ረድቷቸዋል። በተመሳሳይም በዚህ ዘመን ያሉ ምሥክሮቹ ከባድ ስደት በሚያጋጥማቸው ጊዜም ጭምር ይደርስላቸዋል።

1:17-21 ይሖዋ “በመልካም” ያስበናል።—ነህምያ 13:31 የ1954 ትርጉም

3:7-10 ይሖዋ የሕዝቡን ጩኸት ይሰማል።

3:14 ይሖዋ ምንጊዜም ዓላማዎቹን ይፈጽማል። በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩትን ተስፋዎች እውን እንደሚያደርጋቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

4:10, 13 ሙሴ መለኮታዊ ድጋፍ እንደማይለየው ቢነገረውም ጥሩ የመናገር ችሎታ እንደሌለው ስለተሰማው ፈርዖንን ለማነጋገር ሌላ ሰው እንዲልክ አምላክን ለምኗል። ያም ሆኖ ይሖዋ በሙሴ የተጠቀመ ሲሆን ተልእኮውን ለመወጣት የሚያስችለውን ጥበብና ማበረታቻም ሠጥቶታል። እኛም ብቃት እንደሌለን ከማሰብ ይልቅ በይሖዋ በመመካት እንድንሰብክና እንድናስተምር የተሰጠንን ተልእኮ በታማኝነት እንወጣ።—ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20

ይሖዋ በተዓምራዊ መንገድ ሕዝቡን ነፃ አወጣ

(ዘፀአት 5:1 እስከ 15:21)

ሙሴና አሮን ፈርዖን ፊት ቀርበው እስራኤላውያን በምድረ በዳ ለይሖዋ በዓል ለማድረግ እንዲፈቅድላቸው ጠየቁት። የግብፁ ንጉሥ ይህንን ለማድረግ አሻፈረኝ አለ። ይሖዋ በሙሴ በመጠቀም ኃይለኛ የሆኑ መቅሰፍቶችን እያከታተለ አወረደበት። ፈርዖን እስራኤላውያንን የለቀቀው በአሥረኛው መቅሰፍት ከተመታ በኋላ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ሠራዊቱን አስከትሎ እስራኤላውያንን ማሳደዱን ተያያዘው። ሆኖም ይሖዋ ቀይ ባሕርን ከፍሎ እንዲያመልጡ በማድረግ ሕዝቡን አዳናቸው። ያሳድዷቸው የነበሩት ግብፃውያን ባሕሩ ተከደነባቸውና ሰመጡ።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

6:3—የአምላክ ስም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅና ለያዕቆብ አልተገለጠላቸውም ሊባል የሚችለው እንዴት ነው? እነዚህ የእምነት አባቶች በመለኮታዊው ስም ይጠቀሙ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይሖዋ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም እነዚህን ተስፋዎች በመፈጸም ረገድ ይሖዋን አላወቁትም ወይም ቃል የገባቸውን ነገሮች ሲፈጽም አልተመለከቱትም።—ዘፍጥረት 12:1, 2፤ 15:7, 13-16፤ 26:24፤ 28:10-15

7:1—ሙሴ “ለፈርዖን እንደ አምላክ” የሆነው እንዴት ነው? ሙሴ በፈርዖን ላይ መለኮታዊ ኃይልና ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር። በመሆኑም ይህንን ንጉሥ የሚፈራበት ምንም ምክንያት አልነበረውም።

7:22—የግብፅ አስማተኞች ወደ ደም ያልተለወጠ ውኃ ማግኘት የቻሉት ከየት ነው? በግብፅ ምድር ያለው ውኃ በመቅሰፍቱ ከመመታቱ በፊት ከናይል ወንዝ የተቀዳ ሊሆን ይችላል። በናይል ወንዝ ዙሪያ የሚገኘውን እርጥበት ያለው አፈር በመቆፈርም ወደ ደም ያልተቀየረ ውኃ ማግኘት ሳይችሉ አልቀሩም።—ዘፀአት 7:24

8:26, 27—ሙሴ የእስራኤላውያን መሥዋዕት “በግብፃውያን ዘንድ አስጸያፊ” እንደሚሆን የተናገረው ለምንድን ነው? ግብፅ ውስጥ በርካታ እንስሳት ይመለኩ ነበር። በመሆኑም ሙሴ፣ እንስሳትን መሥዋዕት እንደሚያደርጉ መግለጹ ለይሖዋ ለመሠዋት እንዲሄዱ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝና አሳማኝ እንዲሆን ያደርገዋል።

12:29—እንደ በኩር ልጅ የተቆጠሩት እነማን ነበሩ? የበኩር ልጆች ሆነው የተቆጠሩት ወንዶች ብቻ ነበሩ። (ዘኍልቍ 3:40-51) ፈርዖን ራሱ የበኩር ልጅ ቢሆንም የራሱ ቤተሰብ ስለነበረው አልተገደለም። አሥረኛው መቅሰፍት የገደለው የቤተሰብ ራስ ያልሆኑ የበኩር ልጆችን ነበር።

12:40—እስራኤላውያን በግብፅ የኖሩት ለምን ያህል ጊዜ ነበር? እዚህ ላይ የተገለጸው 430 ዓመት የእስራኤል ልጆች “በግብፅና በከነዓን” ያሳለፏቸውን ዓመታት ያጠቃልላል። (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) አብርሃም በ1943 ከክርስቶስ ልደት በፊት ኤፍራጥስን ተሻግሮ ወደ ከነዓን ሲሄድ ሰባ አምስት ዓመቱ ነበር። (ዘፍጥረት 12:4) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ያዕቆብ በ130 ዓመቱ ወደ ግብፅ እስከገባበት ጊዜ ድረስ 215 ዓመታት አልፈዋል። (ዘፍጥረት 21:5፤ 25:26፤ 47:9) ይህም እስራኤላውያን ከዚያ በኋላ በግብፅ ለ215 ዓመታት ኖረዋል ማለት ነው።

15:8—የቀይ ባሕር ውኃ “ረጋ” ሲባል በረዶ ሆነ ማለት ነው? “ረጋ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል መሰብሰብ ወይም መጋገር የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። በኢዮብ 10:10 ላይ ይህ አገላለጽ ከረጋ ወተት ጋር በተያያዘ ተሠርቶበታል። በመሆኑም ውኃው ረጋ ስለተባለ በረዶ ሆኗል ማለት አይቻልም። በዘፀአት 14:21 ላይ የተገለጸው “ብርቱ የምሥራቅ ነፋስ” ውኃው በረዶ እንዲሆን የሚያደርግ ቅዝቃዜ ቢኖረው ኖሮ አየሩ በጣም ስለመቀዝቀዙ ይገለፅ ነበር። ውኃውን አግዶ የያዘው በዓይን የሚታይ ነገር ስላልነበረ የረጋ ወይም የተጋገረ ይመስል ነበር።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

7:14 እስከ 12:30 አሥሩ መቅሰፍቶች እንዲሁ በአጋጣሚ የተከሰቱ ነገሮች አልነበሩም። መቅሰፍቶቹ እንደሚደርሱ አስቀድሞ የተነገረ ሲሆን ይህም በትክክል ተፈጽሟል። ፈጣሪ እነዚህን መቅሰፍቶች በማምጣት ውኃ፣ ፀሐይ፣ ነፍሳት፣ እንስሳትና ሰዎች በቁጥጥሩ ሥር እንደሆኑ በግልጽ አሳይቷል! ከዚህም በላይ እነዚህ መቅሰፍቶች አምላክ አገልጋዮቹ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በጠላቶቹ ላይ ብቻ ጥፋት ማምጣት እንደሚችል አመልክተዋል።

11:2፤ 12:36 ይሖዋ ሕዝቡን ባርኳል። በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው እስራኤላውያን ግብፅ ውስጥ ላከናወኑት ሥራ የድካማቸውን ዋጋ እንዲያገኙ አድርጓል። ወደ ግብፅ ሲገቡ ነፃ ሕዝብ እንጂ በባርነት የሚገዙ የጦር ምርኮኞች አልነበሩም።

14:30 በመጪው “ታላቅ መከራ” ወቅት ይሖዋ አምላኪዎቹን እንደሚያድን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማቴዎስ 24:20-22፤ ራእይ 7:9, 14

ይሖዋ በመለኮታዊ ሕግ የሚመራ ብሔር አቋቋመ

(ዘፀአት 15:22 እስከ 40:38)

እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ በወጡ በሦስተኛው ወር በሲና ተራራ ግርጌ ሠፈሩ። በዚያም አሥርቱን ትእዛዛትና ሌሎች ሕጎችን ተቀበሉ እንዲሁም ከይሖዋ ጋር ቃል ኪዳን ተጋቡ፤ በተጨማሪም በመለኮታዊ ሕግ የሚመራ ብሔር ተቋቋመ። ሙሴ እውነተኛውን አምልኮ እንዲሁም የይሖዋን የመገናኛ ድንኳን (ተንቀሳቃሽ ቤተ መቅደስ) ግንባታ በተመለከተ መመሪያ ለመቀበል በተራራው ላይ ለ40 ቀናት ቆየ። በዚህ መሃል እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ ሠርተው ማምለክ ጀመሩ። ሙሴ ከተራራው ሲወርድ በተመለከተው ነገር በጣም ከመበሳጨቱ የተነሳ አምላክ የሰጠውን ሁለት የድንጋይ ጽላቶች ወርውሮ ሰባበራቸው። ጥፋተኞቹ ተገቢው ቅጣት ከተሰጣቸው በኋላ ሙሴ እንደገና ወደ ተራራው ወጣና ሌሎች ጽላቶች ተቀበለ። ሙሴ ከተራራው ሲወርድ የመገናኛው ድንኳን ግንባታ ተጀመረ። እስራኤላውያን ነፃ በወጡ በዓመታቸው የዚህ ግሩም ድንኳንና የቁሳቁሶቹ ሥራ ተጠናቀቀና ድንኳኑ ተተከለ፤ ይሖዋም ድንኳኑን በክብሩ ሞላው።

ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦

20:5—ይሖዋ ‘በአባቶች ኀጢአት የተነሣ’ ቀጣዮቹን ትውልዶች ‘የሚቀጣው’ እንዴት ነው? ኃላፊነት መቀበል የሚችልበት ዕድሜ ላይ የደረሰ ማንኛውም ግለሰብ ፍርድ የሚሰጠው ራሱ በፈጸመው ነገር ወይም በዝንባሌው መሠረት ነው። ሆኖም እስራኤላውያን ወደ ጣዖት አምልኮ ዘወር ባሉ ጊዜ ይህ አድራጎታቸው ያስከተለውን መዘዝ ቀጣዮቹ ትውልዶችም ቀምሰዋል። ብሔሩ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቸልተኛ በመሆኑ ታማኞቹ እስራኤላውያንም ጭምር ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀው መኖር አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።

23:19፤ 34:26—ጠቦቱን በእናቱ ወተት እንዳይቀቅሉ የተሰጠው ሕግ ምን ትምህርት ይዟል? ጠቦትን (የፍየል ወይም የበግ ግልገል) በእናቱ ወተት መቀቀል ዝናብ ለማስገኘት ታስቦ የሚደረግ የአረማዊ አምልኮ ልማድ እንደሆነ ይነገራል። ከዚህም በላይ የእናት ወተት ለግልገሏ ምግብ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ በመሆኑ ጠቦቱን በወተቷ መቀቀል የጭካኔ ድርጊት ነው። ይህ ሕግ የአምላክ ሕዝቦች ርኅሩኅ መሆን እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል።

23:20-23—እዚህ ላይ የተገለጸው መልአክ ማን ነው? የይሖዋ ስም “በርሱ ላይ” የሆነውስ እንዴት ነው? ይህ መልአክ ኢየሱስ (ሰብዓዊ አካል ከመልበሱ በፊት በነበረው ሕልውና) ሳይሆን አይቀርም። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲጓዙ በመምራት አገልግሏል። (1 ቆሮንቶስ 10:1-4) ኢየሱስ የአባቱን ስም በማስከበርና በማስቀደስ ረገድ ዋነኛውን ሚና ስለሚጫወት የይሖዋ ስም “በርሱ ላይ” ነው ሊባል ችሏል።

32:1-8, 25-35—አሮን የወርቁን ጥጃ በመሥራቱ ያልተቀጣው ለምንድን ነው? አሮን በጣዖት አምልኮው ሙሉ በሙሉ አልተስማማም። በኋላም ከሌዋውያን ወገኖቹ ጋር ሆኖ ከአምላክ ጎን በመቆም ሙሴን በተቃወሙት እስራኤላውያን ላይ እርምጃ ሳይወስድ አልቀረም። ጥፋተኞቹ ከተገደሉ በኋላ ሙሴ በአምላክ ላይ ታላቅ ኃጢአት እንደሠሩ ለሕዝቡ ነግሯቸዋል፤ ይህም ከአሮን በተጨማሪ የይሖዋን ምሕረት ያገኙ እስራኤላውያን እንደነበሩ ያሳያል።

33:11, 20—አምላክ ከሙሴ ጋር “ፊት ለፊት” ይነጋገር የነበረው እንዴት ነው? ይህ አገላለጽ አፍ ለአፍ መነጋገርን የሚያመለክት ነው። ሙሴ ከአምላክ ወኪል ጋር ይነጋገር የነበረ ከመሆኑም በላይ በእርሱ በኩል ከይሖዋ የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሏል። ሆኖም ‘ማንም አምላክን አይቶ መኖር ስለማይችል’ ሙሴ ይሖዋን አልተመለከተውም። እንዲያውም ይሖዋ ሙሴን በቀጥታ አላነጋገረውም። ገላትያ 3:19 ሕጉ “የመጣው በመላእክት በኩል፣ በአንድ መካከለኛ እጅ” እንደሆነ ይናገራል።

ምን ትምህርት እናገኛለን?

15:25፤ 16:12 ይሖዋ ሕዝቡን ይንከባከባል።

18:21 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲያገለግሉ የሚመረጡት ወንዶችም ብቃት ያላቸው፣ አምላክን የሚፈሩ፣ ታማኞችና ከራስ ወዳድነት የራቁ ሊሆኑ ይገባል።

20:1 እስከ 23:33 ይሖዋ ከሁሉ የላቀ ሕግ አውጪ ነው። እስራኤላውያን ሕግጋቱን ሲታዘዙ በተደራጀ መልክና በደስታ ሊያመልኩት ችለዋል። ይሖዋ ዛሬም በመለኮታዊ ሕግ የሚመራ ድርጅት አለው። ከዚህ ድርጅት ጋር መተባበር ደስታና ደኅንነት ያስገኝልናል።

ከዘፀአት መጽሐፍ የምናገኘው ጥቅም

የዘፀአት መጽሐፍ ስለ ይሖዋ ምን ያስተምረናል? ለሕዝቦቹ ፍቅራዊ እንክብካቤ የሚያደርግና ዓላማዎቹን የሚፈጽም አምላክ እንዲሁም ተወዳዳሪ የሌለው ነጻ አውጪ እንደሆነ ይገልጻል። ሕዝቦቹን በድርጅት መልክ በማሰባሰብ በመለኮታዊ ሕግ የሚያስተዳድር አምላክ መሆኑን ያሳያል።

ለቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ በምትዘጋጅበት ጊዜ ከዘፀአት መጽሐፍ በምትማረው ነገር በጥልቅ እንደምትነካ ጥርጥር የለውም። “ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉት ሐሳቦች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በጥልቀት ለመረዳት ያስችሉሃል። “ምን ትምህርት እናገኛለን?” በሚለው ርዕስ ሥር ያሉት ነጥቦች ከሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ምን ጥቅም ማግኘት እንደምትችል ይጠቁሙሃል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ፣ ትሑት የነበረው ሙሴ እስራኤላውያንን ከባርነት ነጻ እንዲያወጣ ልኮታል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አሥሩ መቅሠፍቶች ፈጣሪ በውኃ፣ በፀሐይ፣ በነፍሳት፣ በእንስሳትና በሰዎች ላይ ያለውን ሥልጣን አሳይተዋል

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በሙሴ በመጠቀም እስራኤላውያንን በመለኮታዊ ሕግ የሚመራ ብሔር አድርጎ አደራጅቷቸዋል