በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ግርማዊነትህ ከተራሮች ይልቃል’

‘ግርማዊነትህ ከተራሮች ይልቃል’

ዕጹብ ድንቅ የሆኑት የይሖዋ ፍጥረታት

‘ግርማዊነትህ ከተራሮች ይልቃል’

በፉጂ ተራራ አናት ላይ ሆኖ ጎሕ ሲቀድ መመልከት ፈጽሞ የማይረሳ ትዝታ ይፈጥራል። በአድማሱ ላይ ፍም መስላ የምትወጣው ፀሐይ በበረዶና ግራጫ መልክ ባለው የእሳተ ገሞራ አለት በተሸፈነው የተራራው አናት ላይ ብርሃኗን ትፈነጥቃለች። ቀኑ እየጠባ ሲሄድ የተራራው ጥላ ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኙት ኮረብታዎችና ሸለቆዎች ላይ ያጠላል።

“ወደር የለሽ” የሚል ትርጉም ባላቸው ፊደላት ይጻፍ እንደነበረው እንደ ፉጂ ያሉ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ተራራዎችን ስንመለከት መደመማችን አይቀርም። እንዲያውም ግዝፈታቸውን ስናይ ኢምንት እንደሆንን ሊሰማን ይችላል። ተራሮች ግርማ ሞገስ የተላበሱ ከመሆናቸው የተነሳ ብዙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ በጉምና በደመና የሚሸፈኑት የተራራ ጫፎች የአማልክት መቀመጫ እንደሆኑ ያምኑ ነበር።

በተራሮች ውበት ሊወደስ የሚገባው ጥበበኛ የሆነው ፈጣሪያቸው ይሖዋ ብቻ ነው። ‘ተራሮችን የሠራው’ እርሱ ነው። (አሞጽ 4:13) አንድ አራተኛ የሚሆነው የምድራችን ክፍል ተራራማ ሲሆን አምላክ ፕላኔታችንን በፈጠረበት ወቅት በዘመናት ሂደት ውብ የሆኑ የተራራ ጫፎችና ሰንሰለቶች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ ተፈጥሯዊ ኃይሎችን አዘጋጅቷል። (መዝሙር 95:4) ለምሳሌ ያህል፣ የሂማልያ እና የአንዲስ የተራራ ሰንሰለቶች የተፈጠሩት በመሬት ውስጠኛ ክፍል በተከሰተ ኃይለኛ ግፊትና የምድራችን የላይኛው ክፍል ሲንቀሳቀስ በሚፈጠር እጥፋት እንደሆነ ይታመናል።

እኛ የሰው ልጆች ተራሮች ለምንና እንዴት እንደተፈጠሩ ሙሉ በሙሉ አናውቅም። በመሆኑም ይሖዋ “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ የት ነበርህ? . . . መሠረቶችዋ ምን ላይ ተተከሉ?” በማለት ለጻድቁ ኢዮብ ያቀረበለትን ጥያቄዎች ለመመለስ አንችልም።—ኢዮብ 38:4-6

ይሁን እንጂ ህልውናችን የተመካው በተራሮች ላይ መሆኑን እናውቃለን። በዓለማችን የሚገኙት ትላልቅ ወንዞች በሙሉ ውኃ የሚያገኙት ከተራሮች በመሆኑና በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ከተራሮች ላይ በሚፈልቅ ውኃ የሚጠቀሙ በመሆናቸው ተራሮች የተፈጥሮ የውኃ ማጠራቀሚያ ተብለው ይጠራሉ። (መዝሙር 104:13) ኒው ሳይንቲስት መጽሔት እንደሚለው “በዓለማችን ለምግብነት ከሚያገለግሉት 20 ዋና ዋና ተክሎች መካከል 6ቱ የተገኙት ከተራሮች ነው።” አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ውስጥ የምድራችን ሥነ ምሕዳር ሲስተካከል ‘በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፈረፋል፣ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዛል።’—መዝሙር 72:16፤ 2 ጴጥሮስ 3:13

ብዙዎች ስለ ተራራ ሲነሳ ወደ አእምሯቸው የሚመጣው በአውሮፓ የሚገኘው የአልፕስ የተራራ ሰንሰለት ነው። በስዕሉ ላይ የሚታየውን የቺቬታ ተራራ ጨምሮ የአልፕስ የተራራ ጫፎች ስለ ፈጣሪ መኖር ግሩም ምሥክርነት ይሰጣሉ። (መዝሙር 98:8) ‘ተራሮችን በብርታቱ ለመሠረተው’ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣሉ።—መዝሙር 65:6 a

በእውነትም የአልፕስ ተራሮች በግግር በረዶ ከተሸፈነው ጫፍና ተረተር፣ ብናኝ በረዶ ከተከመረበት ሸንተረር፣ ከሸለቆውና ከሐይቁ እንዲሁም ከተንጣለለው መስክ ጋር ሲታዩ በአድናቆት ያስደምማሉ። ንጉሥ ዳዊት “በተራሮችም ላይ ሣር ያበቅላል” በማለት ስለ ይሖዋ ተናግሯል።—መዝሙር 147:8

በስዕሉ ላይ እንዳለው በቻይና፣ ጉዋሊን የሚገኝ ኮረብታ ያሉ ከፍተኛ ቦታዎች ከአልፕስ ተራራ ጋር ለመወዳደር አይበቁም ይሆናል፤ ሆኖም የራሳቸው የሆነ ልዩ ውበት አላቸው። በሊ ወንዝ አጠገብ በረድፍ በረድፍ የተደረደሩት በኖራ የተሸፈኑ ሹል ኮረብታዎች ውበታቸው ጎብኚዎችን ያፈዝዛል። ጉም በለበሱት በእነዚህ ኮረብታዎች መካከል ኮለል እያለ የሚወርደውን ንጹሕ ውኃ የተመለከተ ሰው “ምንጮችን በሸለቆ ውስጥ እንዲሄዱ አደረግህ፤ በተራሮችም መካከል ይፈሳሉ” የሚሉትን የመዝሙራዊውን ቃላት ያስታውሳል።—መዝሙር 104:10

ተራሮች ፈጣሪ ለሰው ልጆች ደህንነትና ደስታ ሲል በፈጠራቸው ነገሮች ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደሚይዙ ስለምናውቅ በውበታቸው መደመማችን ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ የቱንም ያህል የሚያስደንቁ ቢሆኑም ከይሖዋ ግርማ ጋር ሊወዳደሩ አይችሉም። የእርሱ ‘ግርማዊነት ከተራሮች ይልቃል።’—መዝሙር 76:4

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የ2004 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ መጋቢትና ሚያዝያ ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከዓለማችን ሕዝብ ውስጥ አሥር በመቶ የሚሆነው የሚኖረው በተራራማ ቦታዎች ነው። ይሁን እንጂ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለሰዎች ሁሉ ለሚያውጁት የይሖዋ ምሥክሮች ይህ የማይወጡት እንቅፋት አይደለም። እነዚህ ክርስቲያን ወንጌላውያን በከፍተኛ ቦታዎች ላይ በሚገኙ ክልሎች ምሥራቹን በትጋት ይሰብካሉ። አዎን፣ “በተራሮች ላይ የቆሙ፤ የምሥራች ይዘው የሚመጡ እግሮች፣ ሰላምን የሚናገሩ፣ መልካም ዜና የሚያበስሩ፣ ድነትን የሚያውጁ . . . እንዴት ያማሩ ናቸው።”—ኢሳይያስ 52:7

መዝሙራዊው “ረጃጅሙ ተራራ የዋልያ መኖሪያ [ነው]” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 104:18) በቀንዱ ውበት እንደሚታወቀው እንደ ኑቢያን አይቤክስ ያሉ የተራራ ፍየሎች በተራራ ላይ ከሚኖሩት እንስሳት ሁሉ ይልቅ የማያዳልጥ ሰኮና አላቸው። ቀጭን ከመሆናቸው የተነሳ ለማለፍ አስቸጋሪ በሆኑ የገደል ጫፎች ላይ ለመራመድ አይፈሩም። ዋልያ በቀላሉ ሊደረስባቸው በማይችሉ ቦታዎች ለመኖር ተፈጥሮ የለገሰችው ችሎታ አለው። ይህ ችሎታው በከፊል ከሰኮናው አሠራር ጋር የተያያዘ ነው። የሰኮናው ስንጥቅ እንደ ዋልያው ክብደት ሊሰፋ የሚችል ስለሆነ በጣም ቀጭን በሆኑ የገደል ጫፎች ላይ ሲራመድም ሆነ ሲቆም መሬቱን ቆንጥጦ መያዝ ይችላል። በእርግጥም ዋልያ ድንቅ የፈጠራ ችሎታ የተንጸባረቀበት እንስሳ ነው!

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የፉጂ ተራራ ሆንሹ፣ ጃፓን